ከአዲስ አበባ በ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ደብረ ማርቆስ ከተማ በየዓመቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራን፣ የሙያ ማኅበራትና ሌሎችም እንግዶችን ታስተናግዳለች፡፡ አካባቢው በተለይም በሥነ ጽሑፍ ዝና ላተረፉ ባለሙያዎች በመፍለቂያነቱም ይጠቀሳል፡፡ ከቀደምቱ ሐዲስ ዓለማየሁና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ከዚህ ዘመን ጌትነት እንየውና በዕውቀቱ ሥዩምን ማንሳት ይቻላል፡፡
ከጸሐፍቱ በአንዱ ሐዲስ ዓለማየሁ የተሰየመ የባህል ማዕከል በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተገነባውም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎች ላይ ጥናት ለማካሄድ ነው፡፡ በማዕከሉ ከኪነ ጥበብ ጐን ለጐን በቋንቋና ባህል ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች በየዓመቱ መቅረብ ከጀመሩ አራት ዓመት ሆኗል፡፡
የዘንድሮው ጉባኤ ‹‹ኪነ ጥበብ ለማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ሳምንት የተካሄደ ሲሆን፣ ወደ 10 የሚጠጉ የጥናት ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡ ከጥናቶቹ መካከል አካባቢው ያፈራቸውን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጀግኖች ሕይወት የዳሰሱ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ውስጥ በሐዲስ ሥራዎች ላይ ሥነ ጽሑፋዊ ሒስ ተሰጥቷል፡፡ ይህ ዓመት የ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› 50ኛ ዓመት እንደመሆኑ በመጽሐፉ ዙሪያ የተሠሩ የጥናት ወረቀቶች ለጉባኤው ተመርጠዋል፡፡
ከጥናቶቹ አንዱ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር በ50 ዓመት ጉዞ ውስጥ ያበረከተው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ›› የተሰኘ ሲሆን፣ በዶ/ር ታዬ አሰፋ ቀርቧል፡፡ ከመጽሐፉ በፊትና በኋላ ከተጻፉ መጻሕፍት በተለየ ለሥነ ጽሑፍ ያበረከታቸው አስተዋጽኦዎች በጥናቱ ተዳሰዋል፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፉ ያሉት ገጸ ባህሪያት በተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍል መገኘታቸው የመጽሐፉን ተደራሽነት አስፍቶታል፡፡ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በሥራና አመለካከት የተለያዩ ሰዎችን ከመድረስ በተጨማሪ፣ በሰው ልጆች ሕይወት የሚከሰቱ እንደ ሐዘን፣ ደስታ፣ ፍቅርና ጥላቻ ያሉ ስሜቶችን ያንፀባርቃል፡፡ ስለመጽሐፉ ዘመን አይሽሬነት የተናገሩት አጥኚው፣ ‹‹የመጽሐፉ ፖለቲካዊ ሒስ ዘውዳዊ ሥርዓትን በመቃወም የርዕዮተ ዓለም መርህን ያፈለቀ ነው፤›› በማለት ነው የገለጹት፡፡
መጽሐፉ ስለእኩልነት፣ ሥልጣን የሕዝብ ስለመሆኑና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ያነሳል፡፡ ባህላዊ ሥርዓቶችና ማኅበረሰቡን በተመለከተ የሚሰነዘሩት ትችቶች የለውጥ መነሻ እንደሆኑም ጥናቱ ያመለክታል፡፡ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰውም፣ የሰብለ ወንጌል አባት ፊታውራሪ መሸሻ ለልጃቸው ‹‹ለጋብቻ የሚመጥን ዘር›› ማፈላለጋቸውን ነው፡፡ ሰው ሁሉ እኩል ሆኖ ሳለ በብሔር ሀብትና ሌሎችም መሥፈርቶች ያላግባብ መመዘንን ይተቻል፡፡
በመጽሐፉ የተጠቀሱት ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ጊዜ የማያልፍባቸው መሆናቸው ያለው ሥነ ጽሑፋዊ ፋይዳ በአጥኚው ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ ኅብረተሰቡን ለለውጥ በማነሳሳት ረገድ ስለነበረው ሚና አስተያየት የሰጡ የጉባኤው ታዳሚዎችም ነበሩ፡፡ ሐዲስ የወቅቱን ሥርዓት በመተቸት፣ ማኅበረሰቡን ለለውጥ እንዳነሳሱና የተሻለ የተባለ ሥርዓት እንዲሰፍን ማመላከታቸው ተነስቷል፡፡
ስለመጽሐፉ ይዘት ከተደረጉ ውይይቶች በተጨማሪ፣ በውስጡ ያሉት ገጸ ባህሪያትና ሁነቶች በሥዕል ታይተዋል፡፡ ወጋየሁ ንጋቱ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብርን›› በመተረክ ሕይወት እንደ ዘራበት ይነገራል፡፡ ትረካው የታጀበው ደግሞ በባለ ዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ሙዚቃ ነው፡፡ የባህል ጥናት ተቋሙ ይህንን ከግምት በማስገባትም የባለዋሽንቱን የሕይወት ታሪክ የያዘ ዘጋቢ ፊልም አሠርቶ በጉባኤው ላይ አስመርቋል፡፡ በቦታው የተገኙት ዮሐንስም ብዙዎችን በትውስታ ወደ መጽሐፉ የሚወስደው የዋሽንት ዜማቸውን አሰምተዋል፡፡
ከአካባቢው ተወላጆች መካከል ከሐዲስ በመቀጠል የተወሳው የአርበኛው በላይ ዘለቀ ታሪክ ነው፡፡ ዶ/ር ሰለጠነ ሥዩም ስለበላይ የሕይወት ታሪክና ጀግንነት የሚያትት ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የጣልያን ሠራዊት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት አርበኛ ከመሆኑ በፊት ሸፍቶ ጫካ ገብቶ ነበር፡፡ ጦርነቱ ሲመጣ ግን አርበኝነትን ተቀላቀለ፡፡ የጎጃም አካባቢ አርበኞችን በማዘጋጀትና ሠራዊቱ ድል እንዳይነሳ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አጥኚው ትኩረታቸውን ያደረጉት ጦርነቱ ከተፈጸመ በኋላ፣ በላይ የሚገባውን ያህል እውቅናና ሥልጣን ያልተሰጠው ስለመሆኑ ነው፡፡
የጉባኤው ተሳታፊ የነበሩ የበላይ ቤተሰቦችና ከተለያዩ የሙያ ማኅበራት የተውጣጡ አስተያየት ሰጪዎችም የአጥኚውን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ ለአገሪቱ ካበረከቱት አስተዋጽኦ በተቃራኒው እስከ መታሰርና የሞት ፍርድ ድረስ ያደረሳቸው ሁኔታ መፈጠሩ አሳዛኝ መሆኑን የተናገሩ ነበሩ፡፡ የአሁኑ ትውልድ ስለበላይ ተጋድሎ ጥልቅ መረጃ እንዲኖረው ታሪኩን የሚያስረዱ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች መኖር እንዳለባቸው ያመለከቱ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ፡፡
የጉባኤው ሌላው የትኩረት አቅጣጫ የአካባቢው ባህላዊ እሴቶች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ናቸው፡፡ ጥናትና ምርምር ተደርጎባቸው በጉባኤው ከቀረቡ ባህላዊ እሴቶች መካከል በጎጃም አካባቢ ካሉ ባህላዊ ጭፈራዎች ልዩ የሆነው ‹‹ሌፎ ሌፎ›› ይጠቀሳል፡፡ ስለአጨፋፈሩ ጥናት ያቀረቡት አቶ ጥላሁን ፀጋዬ ናቸው፡፡
ሴቶችና ወንዶች በተለያየ ረድፍ በመሆን፣ እንዲሁም ክብ በመሥራት የሚጨፈር ሲሆን፣ በብዛት በበዓላትና በአጨዳ ወቅት ይዘወተራል፡፡ አጥኚው ስለአጨፋፈሩ ከመግለጽ ባሻገር፣ አሁን ‹‹ሌፎ ሌፎ›› የመደብዘዝ አደጋ እንዳንዣበበበት ገልጸዋል፡፡ ውዝዋዜው በድምፅና በምሥል ተቀርጾ ቢቀመጥ፣ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ቢካሄድበትና በፌስቲቫሎች እየቀረበ ቢተዋወቅ ከመጥፋት የሚድንበት አጋጣሚ እንደሚሰፋም አጥኚው አመላክተዋል፡፡ የመፍትሔ ሐሳባቸው በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎችም ባህላዊ እሴቶች እንደሚሠራ የተናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ነበሩ፡፡
በሌላ በኩል ቋንቋ ላይ ያተኮሩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ በአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ችግር ላይ ጥናት የሠሩት ዶ/ር ዓለማየሁ ተመስገን ናቸው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ንግግር ሲያደርጉ ሌሎች የውጭ ቋንቋዎችን መቀላቀል፣ የሆሄያትን ቅርጽ አለመለየት፣ ሐሳብን በግልጽ አለማስፈር፣ የቃላትን ፍቺ ባለማወቅ ቃላትን ከዐውድ ውጪ ማስገባትና ሌሎችም ችግሮች እንደሚስተዋሉ አጥኚው አመላክተዋል፡፡ ጥናታቸውን የሠሩት በደብረ ማርቆስ አካባቢ ወጣቶች ላይ ቢሆንም፣ ችግሩ በሌሎች አካባቢዎችም ይስተዋላል፡፡
አጥኚው እንደ መፍትሔ ሐሳብ ያስቀመጡት ለአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የተሻለ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ነው፡፡ እንደ መነሻ በወሰዱት የአማርኛ ቋንቋ፣ ቋንቋው የአፍ መፍቻቸው የሆኑ ሰዎች ቋንቋውን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ስለሚያምኑ ለአማርኛ ትምህርት ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡ ‹‹አማርኛ የአፍ መፍቻዬ ነውና አውቀዋለሁ ብሎ ለትምህርቱ ትኩረት መንፈግ ተገቢ አይደለም፡፡ የቋንቋውን ትክክለኛ አጠቃቀም ማወቅና መተግበርም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ የትምህርት ተቋማትና ማኅበረሰቡም ኃላፊነት እንዳለበት ያመለከቱ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡
ከሰኔ 27 – 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጉባኤ ተጨማሪ ጥናቶችም ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስለቅኔ ታሪካዊ አመጣጥና ኪነ ጥበብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስላለው ፋይዳ የቀረቡት ጥናቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ማዕከሉ ባለፉት አራት ዓመታት ስላካሄዳቸው ጉባኤዎችና አጠቃላይ እንቅስቃሴው ጥናት የሠሩት ዶ/ር መርሻ አለኸኝ እንደተናገሩት፣ በማዕከሉ አሁንም ተጠንቶ ያላለቀው የጎጃም ማኅበረሰብ ባህላዊ እሴቶች መጠናት አለባቸው፡፡ በይበልጥ ደግሞ የመጥፋት አደጋ ያንዣበበባቸው እሴቶችን በመጠበቅና ለትውልዱ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለበት አክለዋል፡፡ ‹‹ማዕከሉ ምሁራንን አሰባስቦ በሥልታዊ መንገድ ሊንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ጥናትና ምርምር ያልተደረገባቸው የአካባቢው ባህልና ታሪክ መጠናት አለባቸው፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በኪነ ጥበብ፣ ባህል፣ ቋንቋና ተያያዥ ዘርፎች የሚሠሩ ጥናቶችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ሰንደው ለሕዝቡና ለመንግሥት ተቋማት እንደሚቀርቡ ለሪፖርተር የገለጹት ደግሞ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አንዳርጌ ናቸው፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከሚካሄዱ ጥናቶች በተጨማሪ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ካሉ ተመራማሪዎች ጋር በመጣመር መሥራታቸው ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው እምነታቸው ነው፡፡