እነሆ መንገድ፣ ከቦሌ ድልድይ ወደ ሳሪስ አቦ ልንጓዝ ነው። የተሳፈርንባት ሐይገር አውቶብስ ጨቅ ብላለች። ‹‹ጠጋ ጠጋ እያላችሁ›› ይላል ስግብግቡ ልጅ እግር ወያላ። ‹‹የት ነው የምንጠጋው? እንጣበቅልህ ከዚህ በላይ?›› ይለዋል አንድ ጎልማሳ ቁልቁል እያየው። ‹‹ድራፍቷን ቀነስ ብታደርጋት እኮ የያዘው ቦታ (ቦርጩን ማለቱ ነው) ለሦስት ሰው በበቃ ነበር፤›› ብሎ ወያላው ይመልስለታል። ‹‹ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ጃንቦዎቻችንን መቁጠር ጀመራችሁ? ይህቺን ይወዳል የአርበኛው ልጅ?›› ጎልማሳው ቀረርቶ ሳያምረው አልቀረም። ‹‹ይኼን ቀበል አርጎ አንድ ወጣት ‹‹ምን ዋጋ አለው? በአንዳቸው አርበኛ ስንሆን ባንዳቸው ባንዳ ሆነን እንገኛለን፤›› ቢለው፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር በሚለው ማለፍ ነው፤›› ይለዋል ከአንዲት ለጋ መጫት ተሳፋሪ ጋር እየተላተመ የሚጓዝ ሸበቶ። ‹‹ካልክስ ከእናት ይልቅ የአገር ሆድ ነው ዥንጉርጉር የሆነብን፤›› ይላል ጎልማሳው በጨዋታ ይዞት የነበረው የበላይነት እንዳይወሰድበት ሲቀላቀል። ‹‹እናትና አገር አንድ አይደሉም ታዲያ?›› ስትል መጫቲቱ፣ ‹‹እውነት ነው። ግን እንዲያው አንቺ እናት ሆነሻል አሁን። የልጅ ነገር እንዲት እንደሚያንሰፈስፍ ታውቂዋለሽ። ንገሪን እስኪ አንዱ ጠብቶ እንዳበቃ ለአንደኛው ጡትሽ ቢደርቅብሽ ዝም ትያለሽ?›› ይላታል ምስኪኗ ወላድ ነገሩ ውስጠ ወይራ መሆኑ ሳይገባት ‹‹አንድ ሁለት ቢራ እስክጠጣ ነው ከዚያ አጠባዋለሁ፤›› ብላ አረፈችው። ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው ወተት ሲደርቅ ቢራ መጠጣት ነው መፍትሔው የተባለው?›› ሲል ከወጣቶቹ አንዱ ‹‹በወተት ዋስትና ራሳችንን ከመቻላችን በፊት በቢራ ዋስትና ራሳችንን ከቻልን ወዲህ አይመስልህም?›› ብሎ ለብቻው ከት ብሎ ሳቀ ጎልማሳው። ‹‹ወይ ሐይገር! ሰው ለካ እዚህ ነው የሆድ የሆዱን የሚጫወተው እናንተ?›› ሲል አንዱ ወዲያ ማዶ ‹‹አገር ውስጥ መስሎኝ የተሳፈርነው። የት እንጫወተው እንግዲያ›› እያለ ያም ያም ተረባረበበት። ጉዟችን እንዲህ በደመቀ ሽሙጥና ቆርጦ መቀጠል ተጀመረ።
ገሚሱ ስለ ሰሞንኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሾሚያ ፉክክር ይቀዳል። ገሚሱ ስለ ትላንት ማታ አመሻሹና አዳሩ ገጠመኙን እየጨመረ እየቀነሰ አብሮት ካለው ወዳጅ ጋር ያሽካካል። ጥቂቱ ስለ ሥራ ኑሮ በሹክሹክታ ይነጋገራል። በዚህ መሃል አንዱ ስልኩን ጮክ አርጎ ከፍቶ ወዳጁን የት ነህ ሲለው ይሰማናል። ‹‹አሁን ከቢሮ ሾልኬ ወጥቼ ወደ ምሽግ እየሄድኩ ነው፤›› ይላል ወዲያኛው። ‹‹በቃ ጦርነት ተጀመረ የሚባለው እውን ነው ማለት ነው?›› ይላል ሌላው ወሬ ጠልፎ። ‹‹የምን ጦርነት?›› ይሉታል እንቅልፍ ሸለብ አርጓቸው የነበሩ ወይዘሮ ባነው። ለእሳቸው መልስ ሳይሰጥ የስልኩ ወሬ ቀጠለ። ‹‹አትመጣም ታዲያ?›› ይላል በወዲያ በኩል። ይኼ ‹‹ዛሬ ቻፓ የለም፤ ተጋባዥ ድምፃዊ ነህ ካልከኝ ግን ከች እላለሁ፤›› ይለዋል። ‹‹ዛሬማ ምን የመሰለ ጫት ነው የማስቅምህ። ያ ባለፈው የነገርኩህን ሰውዬ እኮ አዋክቤ አሥር ሺሕ አስወርጄዋለሁ። በቃ አፍጥነው፤›› ሲለው ሰማን። ስልኩ ተዘጋ። ‹‹እኔ እኮ ምሽግ ሲል ለአገር ዳር ድንበር ዋጋ ሊከፍል ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊታችንን የተቀለቀለ መስሎኝ እኮ ነው። ለካ የበርጫውን ጀማ ነው ምሽግ የሚለው፤›› ሲል ጦር ጦር ብሎ ያደረቀን ተሳፋሪ ‹‹ይብላኝ እሱ ፈጣሪ መርጦ መርቆ በአባቶቻቸው የእናት አገር ፍቅር ስሜት አጥምቆ ሲፈጥራቸው ለለያቸው ወቶ አደር ልጆቻችን እንጂማ ዘንድሮ እናንተ እናንተ ታስፈጁን ነበር፤›› ብለው ወይዘሮዋ ስላቅ ጀመሩ። ‹‹ምን አባታችን እናርግ ብለው ነው ይኼው እኛም እኮ ከተማ ለከተማ የቻልነውን ያህል ኪራይ ሰብሳቢውና ቀማኛ ቀማኛውን እያደንን እያስተፋን ነው፤›› ቢላቸው፣ ያ ‘ተጋባዥ ድምፃዊ ነህ’ የተባላው ወጣት ‹‹አይ ይኸው እያየናችሁ አይደለም እንዴ። አገር በሌባና በሙሰኛ እንደ ቆዳ ተወጥራ ዳር ተቀምጣችሁ ስትሰፉ ውላችሁ ስትሰፉ ስታድሩ። የተሰበረ ቅስማችሁን ሳትጠግኑ ምርቃና ሰበራ እያላችሁ አገሩም ዳንኪራ ቤት ብቻ ሆነ፤›› ሲሉ ሁሉም በዝምታ ሰምቶ እንዳልሰማ አንገት ደፋ። ‘ቢደፉን እንጂ የተደፋነው ወደን አይደለም የተተፋነው’ አሉ ነው የተባለው ቆሻሻ ገንዳውን የሞሉ ቆሻሾች በኅብረት ድምፅ? ይብላኝ ለጠራጊው!
ጉዟችን ቀጥሏል። ወይ ዘመን። ‹‹እኔ እኮ የፈጣሪ ምሕረት ብዙ እንደሆነ የማውቀው እዚህ ከተማ ላይ ፀሐይ ለሁሉም እኩል ስትወጣ ነው፤›› ብሎ አንዱ ከኋላችን ጨዋታ ጀመረ። ‹‹ምነው ካልጠፋ ከተማ አዲስ አባ ላይ ራስህን ነቀነክ?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠው። ‹‹አትሰማቸውም የሚያወሩትን እነዚያ ሰዎች። ትላንት ስለበሉት፣ ስለጠጡትና ስለደፉት ውስኪ ብዛት፣ ሕይወትን እንደ ላባ እያዩ እንዲረግጧት ስላደረጓቸው እንስታት ሲያወሩ እየሰማሁ ገርሞኝ እኮ ነው፤›› ከማለቱ ተገራሚው ሌላ ተገራሚ ተተክቶ ‹‹ውስኪ የሚጠጣ ሰው እንዴት ሐይገር ይሳፈራል? የሀብት ጋፓችን ሳይጠብ የቦታው ጠቦ እንዳይሆን?›› ብሎ አስፈገገን። ‹‹እኔ ደግሞ ግርም የሚለኝ በምንበላውና በምንጠጣው ነገር ማስታወቂያ ሳይቀር የተራቆተ ገላ ሳናይ አለማደራችን ነው። ወይ ስምንተኛው ሺሕ?›› ብላ አጉረመረመች ወዲያ ማዶ። ‹‹መረቡ ነዋ ምን ይደረግ። ዘመኑ የመረብ ሆነ፤›› ብላ ሌላ ማድያት ያጠቆራት ጎስቋላ ወጣት ተሳተፈች። ‹‹ደግሞ መረቡ ምን አረገ? ባገለገለ፣ መረጃ ባለዋወጠ፣ ፎቶና ፕሮፋይል ባስበራበረ፣ መረቡ ምን አደረገ?›› ሲላት አንዱ ‹‹ካቆተው መረጃ ይልቅ ዝም ብዬ ስጠረጠር መረቡ አንዳንዴ ጎትቶ የሚጥል ነገርም ሳይኖረው አይቀርም ወንድሜ፤›› አለችው። ‹‹አልገባንም›› ሲላት ተሳፋሪው ‹‹እንዴት ይገባናል ቋንቋችን ተደበላልቆ?›› ብላ ነገሩን ብታድበሰብሰው ‹‹ሆሆ ሰው እኮ ግራ ገብቶታል እናንተ። ስለ መረጃ መረብ አንስታ አሁን ፌዴራሊዝምን ልተች ስትል ትንሽ አይሸመቅቃትም፤›› እየተባባሉ ባልዋለችበት ባላሰበችው ሲያውሏት ሰማን። አቤት ማነካካት ስንወድ እኮ። መረቡ ይሆን እንዴ?
ወያላው በእግራችን ሥር እየተሽሎከሎከ ገንዘቡን ይቀበላል። በተለምዶ ማሞ የሚባለውን አካባቢ እንዳለፍን አንዲት ዝንጥ ያለች ቀዘባ ገባች። የተሳፋሪው ትኩረት፣ ዓይንና ጆሮ ሁሉ ወደዚያች የደም ገንቦ ተጠላለፈ። ‹‹ቆይ ግን እኛ ስንቱ ላይደፈጥጠን ልንችለው ነው? ለምንድነው ሚስት የመፈለጉን ነገር ችላ የምንለው?›› አለው አንዱ ወደ ወዳጁ ዞሮ። ‹‹መጀመሪያ ሥራ እናግኛ! በባዶ እጅ ዝም ተብሎ እንኳን ሚስት ዘንድ እናት ቤት ይገባል?›› ይላል ወዳጁ ቱግ ብሎ። ይኼኔ የቆንጅት ስልክ ጠራ። አነሳችው። ሰላምታ ስትለዋወጥ ሐይገራችን ሁለት ጊዜ ቆማ ተነሳች። ወራጅ ወረደ ተጓዥ ተሳፈረ። ‹‹አሁን የት ነህ?›› አለች ፀጉሯን እያጥመለመለች ደግሞ ትለቀውና አንገቷ ሥር አለንጋ ጣቶቿን እያርመሰመሰች አንገቷን ደግፋው ያቆመችው ስትመስል። ‹‹አሁን ብመጣ መኪና ታስነዳኛለህ?›› ከማለቷ አፍጦ የነበረው ወጣት ጠቅላላ የተከፈተ አፉን ዘግቶ፣ ለሃጩን ጠራርጎ ወደ ኑሮው ተመለሰ። ‹‹እኔ ድሮም ጠርጥሬያለሁ። አንተ ነህ ዝም ብለህ እያት እያት ብለህ ምች ያስመታኸኝ፤›› ሲለው ወዲያ ማዶ በጓደኛው ጉትጎታ ተናዶ ‹‹እኔ ላይ ከምትናደድ ኑሮህ ላይ ተናደድ እሺ። ወይ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅና ይኼን እልክና ንዴት ወደ ገንዘብ ለውጠው። ዘላለም ከእኔና ከመንግሥት ራስ አትወርድም እንዴ አንተ?›› ሲል ተሳፋሪው ሰማና ‹‹ውስጥ ሳይደራጅ በማኅበር ቢደረጁት ምን ዋጋ አለው። ግቡ መኪናና ቤት ላይ የተገታ የማግኘት ህልም ውሎ አድሮ በጥጋብ ስካር ገሎ ከማጋደል ይዘላል እንዴ?›› እያለ ተቀባበለባቸው። መቼ ይሆን ይኼን ነገር የመቀባበል ‘ታለንታችንን’ ህልምና ራዕይ ወደ መወራረስ ቀይረን የምንቀየረው? አልናፈቃችሁም?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹እኔ የምለው ምንድነው በየአቅጣጫው ፋኖ ፋኖው የበዛው? ሰላም አይደለም እንዴ አገሩ?›› ብሎ ጠየቀ። ‹‹አገሩማ ሰላም ነበር። ሰላም ያጡ ሰዎች ሰላም ካላሳጣናችሁ እያሉ ነው እንጂ መቀመጫ የጠፋው፤›› ብላ አንዷ መመለስ። ‹‹ምንድነው መቀመጫ ጠፋ ማለት? ስንቱ ሕይወቱን ሊከፍልላት ዘብ የቆመላትን አገር መቀመጫ ጠፋባት ማለት ምን ማለት ነው? እዚህ ወንበር ስታጡ በአገር ታሳብባላችሁ እንዴ?›› ብሎ ጎልማሳው ነገር ሊጀምር ሲል ‹‹ምነው ገና ምኑንም ሳትሰሙ ዘራፍ ዘራፍ አላችሁሳ?›› ብለው አንድ አዛውንት ገቡበበት። ‹‹ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰማላችሁ አለ መጽሐፉ። ይኼው ከአንድም ሁለት ሦስቴ ሰማነው። ታዲያ እኔ የምለው ምን ችግር አለው ከዚህ በኋላ አንዴ ሮጥ ብለን ሄደን ያን ግፈኛ ጨቋኝ ሰውዬ ወረድ አርገነው ብንመጣ? በዘፈን ብቻ ተለያይተን ቀረን፣ እንዋደድ ነበር ከመባባል ተግባር አይሻልም፤›› ሲል ሁሉንም የተለያየ አስተያየት ይዞ ተነሳ። ‹‹በማን ጉድጓድ ማን ሊቀበር ነው በሰው እንጀራ ጣት የምናወጣው? ከመጡ እናባርራለን። ካልመጡም እሰየው። ዕድሜ ከግብርናው ቀድሞ በቴክኖሎጂ ሽግግር ለላቀው መከላከያችን፤›› ብላ ከጀርባ አንዷ አስተያየቷን ሰነዘረች። በዚህ መሃል ነበር አዛውንቱ የሆነ ነገር ሲሉ ‹‹አይሰማም›› ብሎ ጎልማሳው ትኩረት ውስጥ የከተታቸው። ‹‹እንዲያው ነው አልኩ እንጂ የዚህ ዓለም ኑሮ። በማያልቅ ግጭት በማያልቅ ጦርነት የሰው ልጅ ጥቂት ያርፍና ጥቂት መታመስ። ደግሞ ታጥቦ ደግሞ ጭቃ። እንዲያው መቼ ይሆን የዘላለም ሰላም የዘላለም እፎይታ የሚኖረን ይሆን?›› ሲሉ አቶ መለስ ‘የእኛንና የኤርትራን ጉዳይ ለዘላለም ፈተነዋል’ ያሉትን አስታውሰው ‹‹ፖለቲካ ሳለ የዘላለም ሰላም ተረት ላይ ብቻ ነው፤›› ብሎ ጎልማሳው አንገት አስደፋቸው። ወያላው መጨረሻ ብሎ ሸኝቶናል። መልካም ጉዞ!