Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ማደል ሥራ ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የሺ ኦይል ሰባተኛው አገር በቀል ኩባንያ ሆኗል

በኢትዮጵያ ነዳጅ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ አገር በቀል የነዳጅ ማደያ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ሌሎች ኩባንያዎች ጥያቄ ያቀረቡ ስለመሆኑ ተጠቆመ፡፡

ከ40 ዓመታት በላይ በውጭ ኩባንያዎች በስፋት ተይዞ በነበረው የነዳጅ ችርቻሮ ንግድ ለአገር ኩባንያዎችም ክፍት ከሆነ ወዲህ፣ በቅርቡ የሺ የተባለ የነዳጅ ድርጅት ገበያውን በመቀላቀሉ ቁጥራቸውን ወደ ሰባት ማሳደግ አስችሏል፡፡

የሺ ኦይል ዘርፉን የተቀላቀለው ከአዲስ አበባ ውጭ በከፈታቸው አራት የነዳጅ ማደያዎች መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የሺ ኦይል ከገነባቸው የነዳጅ ማደያዎች ሌላ በሱሉልታ የራሱን የነዳጅ ማከማቻ በማስገንባት ወደ ሥራ እንደገባም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኩባንያው ባለቤት ቀደም ብለው የሺ ቶታል በሚል መጠሪያ የቶታል ወኪል በመሆን ሲሠሩ የቆዩ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የአገር ውስጥና የውጭ የነዳጅ ድርጅቶች በድምሩ ያላቸው ማደያዎች ከ660 በላይ ነው፡፡ ይህ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር ግን ከአገሪቱ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት አንፃር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው ተጨማሪ ማደያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ክፍተት በማየትም ነዳጅ ማደያዎችን ለመክፈት መንግሥት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ተግባራዊ ሳይሆን በእንጥልጥል ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት ነዳጅ ማደያዎችን የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ሲያሳውቅ፣ ይህ ሥራ ለግል ዘርፉ መተው ይገባዋል በሚል ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ መንግሥት የነዳጅ ማደያዎችን ለመገንባት ያለውን ውጥን ካሳወቀ ከሁለት ዓመታት በላይ በመቆጠሩና በተጨባጭ የተሠራ ሥራ ያለመኖሩ ግን በዘርፉ ለመሰማራት ያለውን ዕቅድ የሰረዘ አስመስሎታል፡፡

ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘውም መረጃ ዕቅዱ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ወደ ተግባራዊ ሥራ ያለመሸጋገሩን የሚያመለክት ነው፡፡

 እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች ከኢትዮጵያ ያነሰ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት ያላቸው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ካላት የነዳጅ ማደያዎች በእጥፍ የሚበልጡ ማደያዎች ያላቸው ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ከአንዳንድ የነዳጅ ድርጅቶች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ፣ ማደያዎችን የማስፋፋት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ቢሆንም ለማደያዎቹ መገንቢያ የሚሆን ቦታ እጦት አግዷቸዋል፡፡ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ለማደያ መገንቢያ ቦታ ማግኘት እንዳልተቻለ ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያ የነዳጅ ችርቻሮ ሥራ ላይ በብቸኝነት ሲሠሩ የነበሩት ሼል፣ ሞቢልና አጅፕ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ አሁን በዘርፉ በሥራ ላይ የሚገኙት የውጭ ኩባንያዎች የፈረንሣዩ ቶታል ኢትዮጵያ፣ የሊቢያው ኦይል ሊቢያ፣ የኬንያው ኮብል ኦይልና የሱዳን ኩባንያዎች የሆኑት ዋዲና ናይል ኦይሎች ናቸው፡፡

ዘርፉ ለአገር ውስጥ ከተፈቀደ በኋላ በመጀመርያ ወደ ገበያ የገባው ኖክ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ የተባበሩት፣ ዳሎል፣ ታፍ፣ ተባረክ፣ ኦልዌይስና የሺ ኦይል የተባሉ አገር በቀል ኩባንያዎች ተቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ እንደምንጮች ገለጻ አሁን በሥራ ላይ ከሚገኙት የነዳጅ ማደያዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች ወደ አራት የሚሆኑ አገር በቀል ኩባንያዎች የነዳጅ ማደል ሥራ ላይ ለመሰማራት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች