Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ያለው ሽኩቻ ከባድ ስለሆነ ብቁና ተሰሚነት ያለው አመራር መምረጥ ችግር ሆኗል››

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ያለው ሽኩቻ ከባድ ስለሆነ ብቁና ተሰሚነት ያለው አመራር መምረጥ ችግር ሆኗል››

አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ፣ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

የንግድ ምክር ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 341/95 እንደ አዲስ እንዲደራጁ ከተደረገ ወዲህ ከተቋቋሙት የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መካከል አንዱ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በአባልነት ካቀፋቸው 18 አባላት አንዱ ነው፡፡ ከ40 ሺሕ በላይ አባላትን ያቀፉ 42 የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በመያዝ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረሥላሴ እንደሚገልጹት፣ ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱን ለማጠንከር የክልል ንግድ ምክር ቤቶች መጠንከር አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ እየሠራንም ነው ይላሉ፡፡ በቅርቡ በሚካሄደው የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ፣ በክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አቋምና ወቅታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ዳዊት ታዬ ፕሬዚዳንቱን አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴን አነጋግሯል፡፡  

ሪፖርተር፡- የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አሁን ያለበት የሥራ እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል? እንደ አንድ ንግድ ምክር ቤት ምን እየሠራን ነው ትላላችሁ?

አቶ አሰፋ፡- የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በ42 ወረዳዎችና አንድ የክልል የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡ ከ40 ሺሕ በላይ አባላት አለን፡፡ በእርግጥ በአባልነት ዙሪያ ብዙ መሥራት እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ካሉን ወረዳዎች በጣም ጥቂት ከሚሆኑት ውጭ ሌላውን አደራጅተናል፡፡ በግል ዘርፉና በመንግሥት መካከል የሚደረገውን የምክክር መድረክ ከክልል እስከ ከተማ ድረስ ያለማቋረጥ እንዲካሄድ እያደረግን ነው፡፡ ይህ አንዱ ጥንካሬያችን ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ተጠናክሮ ተአማኒ የሚሆንበትንና የንግድ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ያስችለናል ያልነውን አሠራር ዘርግተን እየሠራን ነው፡፡ በጥቅል ሲታይ አሁን ንግድ ምክር ቤታችን በጥሩ አቋም ላይ ነው ብለን እናምናለን፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ ለምሳሌ በክልላችን ያሉ ማኑፋክቸረሮችን በመጐብኘት፣ ያለባቸውን ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለመግባት የሚፈልገውንም ብድር የሚያገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት እየጣርን ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ለዚህ እገዛ እንዲያደርጉ የውይይት መድረክ እያዘጋጀን እናናግራለን፡፡ ከዚህ በኋላም ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመግባት ሐሳብ ያላቸውን የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት እያሰባሰብን በአክሲዮን ተደራጅተው እንዲሠሩ ለማድረግ አቅደናል፡፡

ትልላቅ የገበያ ማዕከሎችን ለመገንባት ወደ 20 ማኅበራት ተደራጅተዋል፡፡ እነዚህ ማኅበራት ወደ 120 ሚሊዮን ብር አሰባስበዋል፡፡ በሚሰበሰበው ገንዘብም ትላልቅ ሞሎች እንዲገነቡ እየጣርን ነው፡፡ መንግሥት መሬት እያዘጋጀ ነው፡፡ ሌላው ጠንካራ የምንለው ሥራችን በየሁለት ወሩ ከተሞች የምክክር መድረክ ያደርጋሉ፡፡ በየስድስት ወር ርዕሰ መስተዳድሩ ወይም ምክትላቸው የሚመሩት የውይይት መድረክ ይካሄዳል፡፡ በክልል ደረጃ እንደ ሞዴል የሚታይ ነው፡፡ ውጤትም አግኝተንበታል፡፡ በየዓመቱም በየወር ‹‹የቻምበር ዴይ›› ብለን የምናከብረው ቀን አለ፡፡ በዚህ በዓል አባል ያልሆኑ እንዲሆኑ የምንጠቀምበትም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቶች ዋነኛ ዓላማ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል ድምፁን ማሰማት ነው፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ ለሚያጋጥሙት ችግሮች መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር እንዴት እያገለገልን ነው ትላላችሁ?

አቶ አሰፋ፡- እንዳልከው ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ኅብረተሰቡን ከማገልገል ውጭ ሌላ ዓላማ የለውም፡፡ ንግድ ምክር ቤታችን መሠረታዊ ይዘቱ በአዋጅ ቁጥር 341/95 ከተቋቋመ ወዲህም ሆነ በፊት ይህንን መሠረት አድርጐ የሚሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ንግድ ምክር ቤቱ የተጠበቀውን ያህል ለንግድ ኅብረተሰቡ እያገለገለ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህ ባሻገር የተመለከተ እንደሆነ የንግድ ኅብረተሰቡን ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡  

ለምሳሌ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲሳካ ወደ ማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ እንዲገባ ነጋዴው ግንዛቤ እንዲኖረው ኮንፈረንሶችንና መድረኮችን እያዘጋጀን እናወያያለን፡፡ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ለምሳሌ በክልላችን ወደ ሁመራ አካባቢ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ የተመረጠ ቦታ ነው፡፡ መቀሌ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ትላልቅ ኢንቨስተሮች እየገቡ ናቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም እየተስፋፉ ናቸው፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ላይ የንግዱ ኅብረተሰብ ከተራ ንግድ ወጥቶ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዲገባ እየጣርን ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን የንግዱ ኅብረተሰብ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዲገባና ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ስኬት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እየጣርን ነው፡፡ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግና የወጪ ንግዱን ማሳደግ መቻል አለብን፡፡ አባሎቻችንም ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የችርቻሮ ንግድ ብቻ እየተሠራ አገር አይለውጥምና የወጪ ንግዱ ላይ እንዲገባም አንዳንድ ጥረቶችን እናደርጋለን፡፡

በክልላችን ተጨባጭ ሁኔታም አሁን ባቡር እየገባ ነው፡፡ ለውጭ ባለሀብቶች ተመራጭ እየሆነች ነው፡፡ ደረቅ ወደብ አለ፡፡ እንደ ወርቅ ያለ ትልቅ ሀብትም አለ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የንግድ ኅብረተሰቡ አገር ሊለወጥ ወደሚችል ኢንቨስትመንት እንዲገባ መደረግ አለበት፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ መደራጀት የግድ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህም ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤታችን ለማጠናከር ከተፈለገ መጀመሪያ እንዲህ ያለውን ሥራ በክልል ደረጃ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በክልላችን ንቁና የተደራጀ የንግድ ኅብረተሰብ መፍጠር አለብን ብለን የተነሳነውም ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱን ማጠናከር ይቻላል የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ንግድ ምክር ቤቱ የተጠበቀውን ያህል እያገለገለ አይደለም ብለውኝ ነበር፤ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡- ዋናው የንግድ ምክር ቤቶች የአደረጃጀት ችግር ነው፡፡ አደረጃጀቱ በጣም በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከተለያዩ ንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች የአደረጃጀት ችግር አለ የሚለው ምክንያት በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል፡፡ በዚህ ዙሪያ አለ የሚባለው የአደረጃጀት ችግር ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡- የንግድ ምክር ቤቶችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር በ341/95 መሠረት ያለው አደረጃጀት ወጥ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የዘርፍ ማኅበራት ለብቻው ይደራጃል፡፡ እንደገና ደግሞ በክልል፣ በከተማና በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የዘርፍ ማኅበራት አወቃቀር የተለያየ ነው፡፡ የንግዱ ኅብረሰሰብ የሚደራጅበት ሒደት የተበታተነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስታየው አደረጃጀቱ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ትገነዘባለህ፡፡ መስተካከል እንዳለበትም እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ችግር አለበት ከተባለ ይህ አደረጃጀት እንዲስተካከልና ጠንካራ የንግድ ምክር ቤት እንዲፈጠር በእናንተ በኩል የተደረገ ጥረት አለ?

አቶ አሰፋእስካሁን ድረስ ብዙ ጊዜ ያለውን ችግር የሚያሳይ አስተያየት እንሰጣለን፡፡ አዋጁ ያለበት ክፍተት ይሄ ነው፤ መሆን ያለበት ደግሞ እንዲህ ነበር የሚልም መፍትሔዎችን አቅርበናል፡፡ ከዚህ ውጭ የማደራጀት ሥልጣን የመንግሥት ነው፡፡ ሆኖም የአደረጃጀት ችግር አለ ተብሎ ወደኋላ የምትሄድበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እየታገልክ በሒደት የምታስተካክለው እንጂ የአደረጃጀት ችግር አለበት ብለህ አትቆምም፡፡ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የሚባሉ ንግድ ምክር ቤቶች የሚጠቀሙበትን ዓይነት አደረጃጀት እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ እኛም የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖር ነው የምንታገለው፡፡ ስለዚህ በእኛ ረገድ አላሠራ ያሉት ችግሮች የት አካባቢ ያለው ነው? መፍትሔያቸውስ ምንድን ነው? በሚል መፍትሔ በመጠቆም ከመንግሥት ጋር በምናደርጋቸው የምክክር መድረኮች ላይ ጭምር ሐሳባችንን እናቀርባለን፡፡ በአደረጃጀት ዙሪያ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ እየጣርን ነው፡፡ ትግላችንም ይቀጥላል፡፡   

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ የንግድ ምክር ቤቶች ከመንግሥትጋር በመሆን የንግድ ኅብረተሰቡ የንግድ ምክር ቤቶች አባል እንደሆኑ ይሠራል ይባላል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸው መንገድ አባላትን ያፈራሉ፤ እናንተስ?

አቶ አሰፋ፡- መደራጀት ለራስ ነው፡፡ ከማንም የምታገኘው አይደለም፡፡ መንግሥት ደግሞ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ተደራጅተው ቢመጡ ይጠቅመኛል ከሚል ይደግፋል፡፡ ይህ የታወቀ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች መደጋገፍ አለ፡፡ ልማታዊ ባለሀብት እንዲሆንና ነጋዴው የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖረው ጥረት ያደርጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ዋናው የመደራጀት ኃላፊነቱ ያለው ነጋዴው ላይ ነው፡፡ ከማንም የምትጠብቀው አይደለም፡፡ ጉዳዩ ተደራጅተህ ስለማኅበርህ በምታርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች የሚወሰን ነው፡፡ መንግሥት ድጋፍ መስጠት እንጂ እጁን አስገብቶ በዚህ ግባ በዚያ ውጣ የሚልበት ሁኔታ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ምክር ቤቶች አንዱ ችግር በቂ አባላትን ያለመያዝ ነው፡፡ በእናንተ ክልል የማደራጀት ሥራ ምን ያህል ተሳክቶልናል ትላላችሁ?

አቶ አሰፋ፡- በእኛ እምነት የማደራጀቱ ወይም አባላት ቁጥር በማሳደጉ ረገድ 100 በመቶ ተሳክቶልናል ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም አባል የሆነውም ንግድ ምክር ቤቱን ማኅበሬ ነው ብሎ ተቀብሎታል ወይ? ብለህ ስትጠይቅ፣ ብዙ የሚቀር ነገር አለ፡፡ እኛም ለንግዱ ኅብረተሰብ የሚፈለገውን ያህል አገልግለናል ብለን አናምንም፡፡ አባል መሆን የሚገባው የንግዱ ኅብረተሰብ በሚፈለገው ደረጃ በአባልነት አልታቀፈም፡፡ ገና በሒደት ላይ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ አባል ያልሆነው አምኖ አባል እስኪሆን ድረስ እኛም በቂ የሆነ አገልግሎት እስከምንሰጥ ድረስ ክፍተት አለ፡፡ አንድ ሚሊዮን ነጋዴ ያለበት ቦታ 300 ሺሕ ብቻ አባል ቢሆን በቂ አይደለም፤ ሒደቱ ገና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከክልል ንግድና ምክር ቤቶችም ሆነ ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጋር ያላችሁ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?

አቶ አሰፋ፡- አሁን እንደ አቋም የያዝነው መጀመሪያ የክልላችንን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ብቁ እናድርግ ነው፡፡ ከክልላችን ሌላ በወረዳና በከተማ የተደራጁትን ማጠንከርና ብቁ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር የምንገናኝበት ሁኔታ ሲታይ ግን ለእኔ ይህንን ያህል አጥጋቢ አይደለም፡፡ 

ሪፖርተር፡- አጥጋቢ አይደለም የተባለበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡- አንደኛ ለምርጫና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ነው የምትገናኘው፡፡ በምርጫ ወቅት ስትገናኝ ደግሞ ንትርኩ መዓት ነው፡፡ ለዚያች ምርጫ በቡድን በቡድን ተደራጅቶ መጥቶ መነታረክና መጨቃጨቁን ስታይ ነገሩን ፋይዳ ቢስ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ በዓመት ስትገናኝ ለንትርክ መገናኘት የለብህም፤ እኛ እንደ ክልል የያዝነው አቋም ክልላችን ውክልና ይኑረውም አይኑረውም ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው የክልላችንን ንግድ ምክር ቤት ማጠናከሩ ላይ ነው፡፡ የክልላችን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መጠንከር ደግሞ ለአገር አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ጥንካሬ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነትም አለን፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ምርጫ በደረሰ ቁጥር የሚደረግ ንትርክ ለእኛ ጠቃሚ ስላልሆነ ራሳችንን ማጠንከር ላይ አቋም ይዘን እየሠራን ነው፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                  ሪፖርተር፡- በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የንግድ ምክር ቤቶች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ የበርካታ አገሮች ልምድም የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ በኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ግን ብዙ ጊዜ ስማቸው የሚነሳው ከንትርክ ጋር እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በምርጫ ወቅት ይህ ይታያል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው? እንዴትስ መቀረፍ አለበት?

አቶ አሰፋ፡- እንደ ክልላችን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ኅብረተሰቡን ከማገልገል ውጭ አጀንዳ የለም፡፡ ይኼ የታወቀ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታየው ጉዳይ ከእኛ የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ምርጫ በመጣ ቁጥር ሽኩቻዎችን ታያለህ፡፡ በዚህ ረገድ የእኛ የተሻልን ነን ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንኳን በማይገባህ መልኩ ሽኩቻዎች ይታያሉ፡፡ የአገር አቀፉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ሲመጣ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሆን ያለው ሽኩቻ ከባድ ነው፡፡ ይህ አካሄድ መልካም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሽኩቻና ፍጥጫ የንግድ ምክር ቤቶች መገለጫ እንዳይሆን ለማድረግ ለምን ጥረት አይደረግም፡፡ ተደጋግሞ ሲነገር እንደነበረውም ሽኩቻው ተደጋግሞ መታየቱ ወደ ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ አመራር እንዳይመጣ አድርጓል ይባላል፡፡ ከዚህ አንፃር እናንተም የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ አባል ናችሁና ይህ ችግር እንዲቀረፍ ምን አድርጋችኋል? ምንስ ታስቧል?

አቶ አሰፋ፡- ብሔራዊ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ 18 አባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ ሁሉም አባል በንግድ ምክር ቤቶች በእኩል አቋም ላይ ያሉ አይደሉም፡፡ 18ቱም መጠንከር አለባቸው፡፡ የሁለት ሦስት ንግድ ምክር ቤቶች መጠንከር ብቻ ፋይዳ የለውም፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱን ለማጠንከር 18ምንቱን አባል ንግድ ምክር ቤቶች ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ አገር አቀፉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከ18ቱ አባል ምክር ቤቶች ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ አይደለም፡፡ ክፍተት አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ የሚካሄደው ምርጫ በሽኩቻ የታጀበ ስለሚሆን ወደ አመራር የሚመጣው በቡድንተኝነት ስለሆነ ምርጫ በምታካሂድበት ጊዜ በዚህ መንገድ ከተውጣጡት ዕጩዎች ነው የምትመርጠው፡፡ ይህ ደግሞ ጠንካራ አመራር እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ አማራጭ የምታገኝበት ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ ለምሳሌ እንደ አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ብትወስድ ከእኛ የተሻለ አባላትን ማፍራት የሚችል፣ ከእኛ የተሻለ አቀም ያለው ነው ብለህ ታስባለህ፡፡

ከዚህም ይምጣ ከዚያ ተወክሎ የሚመጣው በመቧደን በመሆኑ የጠነከረ ሰው የምታገኝበት አይደለም፡፡ የግል ዘርፉን ለማገልገል ተሰሚነት ያለውና ብቁ የሆነ አመራር የምታገኝበት ዕድል የለም፡፡ ትልቁ ችግርም ይሄ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ተሰሚ ሰዎች ወደ አመራር መምጣት አይፈልጉም፡፡  

ሪፖርተር፡- ተሰሚ ናቸው የተባሉ አባላት ወደ አመራር የማይመጡበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡- የሽኩቻ ቦታ ስለሆነ ነዋ! የሽኩቻ ቦታ መምጣት አይፈልጉም፡፡ የተረጋጋ ነገር ይፈልጋሉ፡፡ ሰላማዊ የሆነ የምርጫ ሥርዓት የማይካሄድ በመሆኑ እንዴት ሊመጡ ይችላሉ? ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ያለው ሽኩቻ ከባድ ስለሆነ ብቁና ተሰሚነት ያለው አመራር መምረጥ ችግር ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ 18ቱ አባል ንግድ ምክር ቤቶች ትልቅ የቤት ሥራ አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለትና ሦስት ወር በኋላ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን የሚመሩ አመራሮችን ለመምረጥ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ከዚህ ምርጫ ምን ይጠብቃሉ?

አቶ አሰፋ፡- እኛ የምንፈልገው የተሻለ ምርጫ እንዲካሄድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን ባለው አካሄድ መኬድ ከተፈለገ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ አንዳንዴ እንደ ምንም የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ይይዙና ከዚያ በኋላ ሌላውን ይረሳሉ፡፡ ስለዚህ የተሻለ ነገር ከተፈለገ የክልል ንግድ ምክር ቤቶች የተሻለና ቻምበሩን በትጋት የሚያገለግል ሰው ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ ለግል ዘርፉ ሊያገለግል የሚችል፤ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ ሊደመጥ የሚችል ጠንካራ ሰው መምጣት አለበት፡፡ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት ፍላጐት ያለውም መሆን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የዕቅዱ ስኬት የንግድ ኅብረተሰቡን የሚጠቅም በመሆኑ፣ ይህም መታሰብ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ እስካሁን በወጣንበት መንገድ የምንሄድ ከሆነ አዳስ ነገር ሊፈጠር አይችልም፡፡   

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ በንግድ ምክር ቤት አመራር ላይ ያሉ ሰዎች በተደጋጋሚ ወደ ኃላፊነት መምጣት እንደ ችግር ይታይል፡፡ አዲስ ፊት አለመታየቱ ለምን? የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ አዲስ ሰዎች ወደ አመራር እንዲመጡ ምን መደረግ አለበት? ችግሩስ ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡- ትልቁ ችግር እኮ ይህ ነው፡፡ አሁን አንዳንዶቹን ስታይ ከታች እስከ ላይ ባለ አመራር ቦታ ላይ በተደጋጋሚ የመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ አዲስ የማፍራት ፍላጐት አታይበትም፡፡ ለውጥ ከተፈለገ እስካሁን የነበረው ሒደት መቆም አለበት፡፡ የፀዳ አሠራር መኖር አለበት፡፡

ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቃኝ የማለት ልምድ ሊኖር ይገባል፡፡ ወደ አመራር ለመምጣት ከዚህም ከዚያ ቡድን አደራጅቶ ከመምጣት እስቲ አገር አቀፉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ የተሻለ ሰው እንዲያገኝ እኛ በቃን ማለት አለባቸው፡፡ መወሰን አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አመራር ለመምጣት ያለውን ፍላጐት ለማሟላት አንዳንዶች የአባላቶቻቸውን ቁጥር አሳድገው ድምፅ ለማግኘት ሲጥሩ ይታያል ይባላል?

አቶ አሰፋ፡- ይህንን በሁለት መንገድ እመለከተዋለሁ፡፡ አንዱ ነገር የክልል መንግሥታት የየክልሎችን የንግድ ማኅበረሰብ ለማገልገል መደራጀት አለበት ብለው አምነው የሚሄዱትንና ይህንንም ለማድረግ መንግሥትና ንግድ ምክር ቤቶች አብረው መሥራታቸውን አደንቃለሁ፡፡ አሁን እኮ ያለው ካለው ነጋዴ 30 በመቶ የማይሞላው ነው የተደራጀው፡፡ ስለዚህ የአባላት ቁጥርን ለማሳደግ ተቀናጅቶ የማደራጀቱን ሥራ መሥራታቸው ጥሩ ነው፡፡

ሁሉም ክልል በተመሳሳይ መንገድ ተሠርቶ ሁሉም የንግድ ኅብረተሰብ በአባልነት ቢታቀፉ ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሌላ ዓላማ ካለው የሚደገፍ አይደለም፡፡ ከዚህ ውጭ የሌላ የአባልነት ቁጥር ይዘህ የምትመጣ ከሆነ ንግድ ምክር ቤቱን ማሳደግ ሳይሆን መግደል ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ የሌለውን አባል አለኝ ብሎ የሚመጣ ከሆነ ንግድ ምክር ቤቱን መግደል ይሆናል፡፡ ነገር በትክክለኛው መንገድ ሁሉንም የንግድ ኅብረተሰብ አባል አድርጐ ከመጣ ይህ ክፋት የለበትም፤ ምክንያቱም ሁሉም አባል ከሆነ ነው የተሻለ ሰው የምታገኘው፡፡ በዚህ መልኩ ከሆነ እኔ ችግር የለብኝም፡፡  

ሪፖርተር፡- ሌላው የንግድ ምክር ቤቶች ችግር ትላልቅ የሚባሉ ኩባንያዎችና የንግድ ምክር ቤቶች አባል አለመሆን ነው፡፡ በእናንተስ ክልል ትላልቅ ኩባንያዎች አባሎቻችሁ ናቸው?

አቶ አሰፋ፡- በክልላችን ያሉ ትላልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች በሙሉ አባሎቻችን ናቸው፡፡ ንግድ ምክር ቤታችንንም የሚያጠናክሩት እነሱ ናቸው፡፡ መቀሌ ብትሄድ ለንግድ ምክር ቤቱ ድጋፍ እያደረጉ ያሉት ትልልቅ የሚባሉት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ወደ ንግድ ምክር ቤቱ መጥቶ ለማገልገል ቁርጠኝነት፣ ጊዜና ፍላጐትን ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ በቅርቡ ለሚያካሂደው ምርጫ ከክልላችሁ የሚወከልና ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ አመራርነት የምታስመርጡት ይኖራል? ለምሳሌ ለፕሬዚዳንት?

አቶ አሰፋ፡- እስካሁን እኛ ስለክልላችን ንግድ ምክር ቤት ጥንካሬ ነው የምናስበው፡፡ የክልላችንን የንግድ ኅብረተሰብና ንግድ ምክር ቤታችንን ካጠናከርን በኋላ ነው ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ የምናስበው፡፡ አሁን ግን ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ሊመራ የሚችለው ከየትም ይምጣ ብቃት ያለው ይሁን የሚል አቋም አለን፡፡

ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ የምታስብ ከሆነ አመራሩ ከየትም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡንና አገርን የሚያገለግል እንዲሆን ፍላጐታችን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ ያለው የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ አመራር ጠንካራ ነው ደካማ?

አቶ አሰፋ፡- እስካሁን ድረስ ጠንካራ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አልፈጠርንም የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያት አለዎት?

አቶ አሰፋ፡- አዎ፡፡ አንዱ ሽኩቻ የሚታይበት መሆኑ ጠንካራ አመራሮችን መያዝ ያለመቻሉ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ አቅም የሚመጥን አመራር ለማምጣት ያለመቻሉ ድክመት ነው፡፡ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ይህ መቀጠል ግን የለበትም፡፡ እንደኔ እንደኔ ብቃት ያላቸውን አመራሮች ለማምጣት ሁሉም ክልሎች የየራሳቸውን ጠንካራ ቻምበር በመፍጠር ብሔራዊ ንገድ ምክር ቤቱም እንዲጠነክር መሥራት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ እያደገች ቢዝነሱም እየሰፋ ስለመጣ ይህንን የሚመጥን አመራር መገኘት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ለውጥ አይመጣም፡፡ ስለዚህ በቀጣይም ምርጫ የክልል ንግድ ምክር ቤቶች በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያለው አመራር መሰየም አለብን ብለው መምጣት አለባቸው፡፡ የክልሌን ሰው አስመርጣለሁ ማለት ሳይሆን ለአገርና ለንግድ ምክር ቤቱ ጠቃሚ አመራር ያስፈልጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች