ኢትዮጵያና ሱዳን በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን ለመለዋወጥ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. ያደረጉት ስምምነት ለፓርላማ ቀረበ፡፡
ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላምንና መረጋጋትን ለማስፈን እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመወጋት ጠቃሚ እንደሚሆን የስምምነቱ አባሪ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገሮች በብሔራዊ ሕጎቻቸው ከአንድ ዓመት ጀምሮ ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ክስ የቀረበበት ወይም የተቀጣ ግለሰብን ለጠያቂው አገር አሳልፎ ለመስጠት ግዴታ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ የታክስ፣ የጉምሩክና የውጭ ምንዛሪን የተመለከቱ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠረ ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጥ በሚጠየቅበት ጊዜ ጥያቄው በቀረበበት ወገን ሕግ መሠረት መሰል የግብር ወይም የቀረጥ ግዴታ አለመኖሩ የቀረበውን አሳልፎ የመሰጠት ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ እንደማይቻል በስምምነቱ ተገልጿል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ አራት መሠረት አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ የሚችልባቸውን ሁኔታዎችም ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት ጥያቄ በቀረበለት አገር የወንጀል ድርጊቱ ፖለቲካዊ ይዘት አለው ተብሎ ሲታመን፣ ጥያቄው የቀረበው ግለሰቡን በዘሩ፣ በሃይማኖት፣ በዜግነቱ፣ በፆታው፣ በፖለቲካዊ አመለካከቱ ወይም በመሰል ምክንያቶች ለመክሰስ መሆኑን በሚመለከት በቂ መረጃ ሲኖር እንዲሁም የሚፈለገው ሰው ያለመከሰስ መብት ሲኖረውና ቅጣቱ ወይም ክሱ በይርጋ የታገደ እንደሆነ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው ውድቅ ሊደረግ ይችላል፡፡
ጥያቄውን የሚያቀርበው አገር የግለሰቡን ማንነት በተሟላ ሁኔታ የሚገልጹ ማስረጃዎች፣ በፍርድ ቤት የወጣ የእስር ማዘዣ ዋናውንና ኮፒውን፣ የወንጀለኛነት ውሳኔ የመሳሰሉትን ማስረጃዎች ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 8 መሠረት አስቸኳይ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ጠያቂው ወገን አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት በወንጀል የሚፈለገው ግለሰብ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ሥር እንዲውል ሊጠየቅ ይችላል፡፡
የስምምነቱ ማፅደቂያ ረቂቅ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርጧል፡፡