የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካለአግባብ መሬት በያዙና፣ በተሰጣቸው ጊዜ ግንባታ ባላካሄዱ ባለሀብቶች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ፡፡
የኦሮሚያ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቃሲም ፊጤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሕገወጥ መንገድ መሬት በያዙ፣ ከተፈቀደላቸው መሬት ውጭ አስፋፍተው በያዙ፣ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ግንባታ ባላካሄዱ ባለሀብቶች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡
እስካሁን 300 ሔክታር መሬት ከባለሀብቶቹ መነጠቁንና የተነጠቀውም መሬት ወደ መሬት ባንክ እየገባ መሆኑን አቶ ቃሲም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከኦሮሚያ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ በተጨማሪ፣ የኦሮሚያ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሕገወጥ መንገድ መሬት ይዘዋል ያላቸውን እንዲሁም፣ ከቀረጥ ነፃ የተሰጣቸውን መብት ላልተገባ ተግባር አውለዋል ያላቸውን ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑም ታውቋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ዙርያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ዕርምጃው የቀጠለ ሲሆን፣ በሸኖ፣ በሰበታና በሌሎችም የልዩ ዞኑ ከተሞች ከይዞታ ጋር በተያያዘ ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ቃሲም እንደገለጹት፣ ከተነጠቁ ቦታዎች ውስጥ የሚበዛው በልዩ ዞኑ የሚገኝ ነው፡፡ የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በእነዚህ አካባቢዎች በርካታ ባለሀብቶችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን ሪፖርተር ከስፍራው የደረሰው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተለይ በሆቴል፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በእንስሳት ማደለብ፣ በመኖርያ ቤት ግንባታ፣ የተሰማሩ 44 ባለሀብቶች በሸኖ ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በሸኖ ከተማ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሬት ያገኙት የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የሊዝ ጨረታ በመወዳደር ነው፡፡ መሬት ያገኙት በሕጋዊ መንገድ ሆኖ እያለ፣ እየታደኑ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸው አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከቀረጥ ነፃ በተሰጠ መብት ከውጭ አገር ብረት ያስመጣም፣ ያላስመጣም ባለሀብት አንድ ላይ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ተቃውመዋል፡፡
እነዚህ ባለሀብቶች እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት ቅሬታቸውን እየተቀበለ ባለመሆኑና ሰሚ በማጣታቸውም ለችግር እየተዳረጉ ነው፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ በአጠቃላይ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጡ በመግለጽ ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡