Monday, September 25, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሔ ይፈለግለት!

የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ ከምንም ጊዜ በላይ ሰላማዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ ላለፉት 16 ዓመታት ሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም እንደሌለ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ላይ ከዚያም አልፎ በአካባቢው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው፡፡ በእነዚህ 16 ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜ የሁለቱ አገሮች የጦር ሠራዊቶች ግጭቶች ውስጥ ገብተዋል፡፡

በቅርቡም ሰኔ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. እሁድ ጠዋት ላይ አዲስ የሆነ ግጭት ተከስቷል፡፡ አሁንም እንደተለመደው ጣት መጠቋቆም እንጂ በሰው ሕይወትም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰው በግልጽ አይታወቅም፡፡ ይህ አካሄድ ለሁለቱም አገሮች እንደማይበጅ የቀደሙ ታሪኮች ያሳያሉ፡፡ ከዚያም ትምህርት በመውሰድ ወደ መፍትሔ መሄድ ብቸኛ አማራጭ ነው ብለን እናምናለን፡፡

በቅርቡ ኤርትራ 25ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ማክበሯ ይታወሳል፡፡ ኤርትራ በዓሉን በምታከብርበት ወቅት ያለችበት ሁኔታ የጨለመ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአስመራ ያለው መንግሥት ጭካኔውና አምባገነንነቱ በየጊዜው እየባሰ በመሄዱ ምክንያት፣ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ዜጐች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከአገሪቱ እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ በዓለማችን በጦርነት እየታመሱ ከሚገኙት እንደ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታንና ኢራቅ ካሉ አገሮች ባልተናነሰ የኤርትራ ዜጐች ወደ አውሮፓና የተለያዩ የዓለም አገሮች እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ተደርጐ የሚጠቀሰው በአስመራ ያለው መንግሥት በዜጐች ላይ የሚያደርሰው መጠነ ሰፊ ጭቆና ነው፡፡ ይህም ኤርትራን የአፍሪካዋ ሰሜን ኮሪያ አስብሏታል፡፡

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ተደጋጋሚ የሆኑ ማዕቀቦችን ጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት በሕዝባቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸሙ ነው ያለው የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ኮሚሽን፣ ባለሥልጣናቱ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው ብሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኤርትራ ላይ ተደጋጋሚ የሆኑ ትችቶችን ማቅረቡ ቢታወስም፣ ይኼኛው ሪፖርት ግን ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ጠንከር ያለ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም የኤርትራ ዜጐች ግን በአስመራው መንግሥት የሚደርስባቸውን ግፍ ከመቅመስ የሚያስጥላቸው አልተገኘም፡፡

የኤርትራ መንግሥት ችግር ግን በአገሪቱ ዜጐች ብቻ ላይ ያነጣጠረ አይደለም፡፡ የአስመራው መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገሮችን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ ቆርጦ የተነሳ ነው፡፡ በተለያዩ ሪፖርቶች ላይ እንደተጠቀሰው በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብ የተባለውን ፅንፈኛ ቡድን የመደገፍና የማስታጠቅ ሥራ ይሠራል፡፡ በዚህም ተግባሩ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙ አገሮች ላይም ይህንኑ እኩይ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የኤርትራ መንግሥት በዓለም አቀፉ ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል፡፡ ሆኖም ግን አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደሚባለው፣ የአስመራው መንግሥት ከዚህ ያልተገባ ተግባሩ ሊታቀብ አልቻለም፡፡

በተቃራኒው ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት ሰላምና መረጋጋት ይታይባታል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህም ዕድገት እንደ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባሉ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተመስክሯል፡፡ ይህን ስንል ግን አገሪቷ ከችግር የፀዳች ናት ማለታችን አይደለም፡፡ አሁንም አገሪቷ ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከሙስና መላቀቅ አልቻለችም፡፡ እነዚህም ችግሮች አገሪቷ ከዚህም በበለጠ ፍጥነት ኢኮኖሚዋ እንዳያድግ እንደ ማነቆ ሆነዋል፡፡

እንደሚታወሰው አገሪቷ ከአሥር ዓመታት በፊት ዘላቂ የሆነ ዕድገት ማስመዝገብ አቅቷት የነበረው፣ በውስጥና በውጭ በነበሩ ችግሮች ነው፡፡ ከዚህም በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነው፡፡ በዚሁ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሁለቱም አገር ዜጐች ተቀጥፈዋል፡፡ ከዚሁ ባለፈ ይህ ጦርነት የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚ ክፉኛ አድቅቆት ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሰላምና መረጋጋት በኤርትራም መኖር አለበት እንላለን፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ መፍትሔ ሲበጅለት ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ የሁለቱ መንግሥታት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ችግራቸውን መፍታት አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ወንድማማችነት ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ዜጐች በባህልና በቋንቋ የተሳሰሩ ከመሆናቸው በላይ፣ ለበርካታ ዘመናት እንደ አንድ ሕዝብ የኖሩ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያቀል እንጂ የሚያወሳስብ አይደለም፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሁለቱ አገሮች መንግሥታት፣ ጐረቤት አገሮች እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድ ላይ በመሆን ለዚህ ችግር ያለው ብቸኛ መፍትሔ ሰላም መሆኑን አምነው በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት አለባቸው እንላለን፡፡ ይህ መፍትሔ ለሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ሰላም፣ መረጋጋትና ብልፅግና እንደሚያመጣ እርግጥ ነው፡፡

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ሁለቱ አገሮች በየጊዜው እየተተናኮሱ በሚፈጠረው ግጭት፣ በአገሮቹና በአካባቢው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህም ባለፈ እንደዚህ ዓይነት ግጭት ወደ ከፋ ጦርነት ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህም ደግሞ በአካባቢው ዋነኛ ችግር የሆነውን ሽብርተኝነት በማፋፋም፣ አካባቢውን ለከፋ ቀውስ ይዳርገዋል፡፡ በዚህ ደግሞ ዋነኛ ተጐጂ ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማንሰራራት የጀመረውን ኢኮኖሚ ክፉኛ ይጐዳዋል፡፡ እንደተባለውም የሁለቱ አገሮች ሕዝብ ወንድማማቾች መሆናቸው እየታወቀ ወደ ጦርነት መግባታቸው አሳዛኝ ይሆናል፡፡ ከጦርነትም የትኛውም አገር ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ስለሆነም ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት መሣሪያ መማዘዝን እንደ አማራጭ ከማየት ተቆጥበው፣ ለችግሩ ብቸኛ መፍትሔ የሆነውን ሰላም ማስቀደም አለባቸው፡፡       

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...