የዓለም ጤና ድርጅት አካል የሆነው ዓለም አቀፉ የካንሰር ምርምር ማዕከል ቡና ለካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል በሚል ሲያቀርብ የነበረውን ሥጋት፣ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አጣጣለው፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የጥናት ኤጀንሲው እ.ኤ.አ. ከ1991 ጀምሮ ቡናን ከብላደር ካንሰር ጋር አያይዞት የነበረ ቢሆንም፣ ከድርጅቱ የተውጣጡ ኤክስፐርቶች ባደረጉት ምርምር ቡና ካንሰር እንደሚያስከትል በቂ መረጃ አለማግኘታቸውን አሳውቀዋል፡፡
ሆኖም በጣም ትኩስ መጠጦችን መጠቀም ምናልባት ለችግሩ ሊያጋልጥ ይችላል ሲሉ ደምድመዋል፡፡ ከመጠን በላይ ትኩስ የሆነ ሻይ መጠጣትን አስመልክቶ ልምድ ባላቸው ኢራን፣ ቻይናና ደቡብ አሜሪካ የተደረጉ ጥናቶች፣ ተጠቃሚዎቹ ለካንሰር ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክተዋልም ተብሏል፡፡
ቡናን በተመለከተ ግን ከዚህ ቀደም ብላደር ካንሰር ሊያስከትል ይችላል በሚል መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን ሥጋት ማረጋገጥ እንዳልተቻለ፣ ሲጋራ ማጨስና የተቀነባበረ ሥጋ መመገብም ለብላደር ካንሰር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ አሳውቀዋል፡፡ ቡና ላይ የተደረገው ምርምር ግን ለካንሰር ያጋልጣል ወይም አያጋልጥም ከሚለው መደምሚያ ላይ እንዳላደረሰ ድርጅቱ አሳውቋል፣ የነበረውን ሥጋትም አጣጥሎታል፡፡