ዓመታዊው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ‹‹የ2009 ቶታል ታላቁ ሩጫ›› ምዝገባ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ በአገሪቱ ለታላላቅ አትሌቶች መገኛ ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ ዘንድ በጉጉት ከሚጠበቀው ዝንጅቶች ቀዳሚ እየሆነ የመጣው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚያደርገውን 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር፣ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. 42,000 ተሳታፊዎችን ያሳትፋል፡፡
የምዝገባውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ዝግጅት ክፍሉ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ በ15 ቀናት መጠናቀቅ የነበረበት ምዝገባ በአሥር ቀን ውስጥ አብቅቷል፡፡ ለዚህም ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር አዲስ በተከተለው የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ የምዝገባ አገልግሎት መከተል መቻሉ እንደሆነም አስረድቷል፡፡
በመንገድ ጥበት ምክንያት ‹‹የ2009 ቶታል ታላቁ ሩጫ›› ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን በአረንጓዴና በቀይ ደረጃ (ዌብ) አጀማመርን እንዲከተል የተገደደ መሆኑን የገለጸው ዝግጅት ክፍሉ፣ አሠራሩም ዓለም ላይ የተለመደ ስለመሆኑ ጭምር ተናግሯል፡፡ በዚህ የአጀማመር ሥርዓት መሠረት አሥር ኪሎ ሜትሩን ከአንድ ሰዓት ባነስ ጊዜ ማጠናቀቅ የሚችሉ ተሳታፊዎች እስከ 6,000 የሚደርስ ቦታ የተያዘላቸው መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ሆኖም ከተሳታፊዎች ከተጠቀሰው ኮታ በላይ ጥያቄ ቢቀርብም አሠራሩ የመጀመሪያ በመሆኑ ብቻ ማስተናገድ እንዳልተቻለ ጭምር ተናግሯል፡፡
እንደ ዝግጅት ክፍሉ፣ የ2009 ቶታል ታላቁ ሩጫ የተሳታፊዎች ቁጥር 42,000 ሲሆን ‹‹ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ›› በሚል ዓላማ በየዓመቱ ለሚዘጋጀው ተሳታፊዎች 2,000 ቦታ መኖሩንም ገልጿል፡፡