ገረመው ደንቦባ፣ የሜልቦርንና ሮም ኦሊምፒክ ብስክሌተኛ
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መስክ አይረሴ ታሪኮችን እንድትቀዳጅ ያስቻሏት ስሟን አድምቀው የከተቡ ባለድሎች አፍርታለች፣ እያፈራችም ነው፡፡ ከአትሌቲክሱ ባሻገር በብስክሌት የሜልቦርን ኦሊምፒክን ቀዳሚ ተሳታፊነቷ እንድትዘክር ባለውለታ የሆኗት አራት ብስክሌተኞች ገረመው ደንቦባ፣ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐዬ ባሕታና መንግሥቱ ንጉሤ ይጠቀሳሉ፡፡ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ተብሎ በሚወሰደው ዳኮታ አውሮፕላን 72 ሰዓታትን ሳያቋርጡ በአየር ላይ በመጓዝ በአውስትራሊያው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ውድድር ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ለውጤት ባይበቁም በቡድን በተደረገውና ገረመው ደንቦባ፣ መስፍን ተስፋዬና ፀሐዬ ባሕታ በተፎካከሩበት እሽቅድድም ኢትዮጵያ በ99 ነጥብ የዘጠነኛ ደረጃን ማግኘቷ፣ በግል በተደረገው የ187.73 ኪ.ሜ እሽቅድድም ገረመው 25ኛ (5 ሰዓት 26፡58)፣ መስፍን 36ኛ (5፡34፡25)፣ ፀሓዬ 38ኛ (5፡34፡37) ሆነው ሲያጠናቅቁ መንግሥቱ ንጉሤ ግን አቋርጦ ወጥቷል፡፡
የቀድሞው ብስክሌተኛ የጉዞው አድካሚነት ብቻውን ከተሳትፎ ውጪ ሊያደርግ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ቢሆኑም፣ ለመጀመርያ ጊዜ በሜልቦርን ኦሊምፒክ መሳተፋቸው ትልቅ ነገር መሆኑን ያወሳሉ፡፡
ስለ ሜልቦርን ኦሊምፒክ ስድስት አሠርታትን ወደ ኋላ በምናባቸው ተጉዘው የወቅቱን ሁኔታ የሚያስታውሱት የቀድሞው ብስክሌተኛ ገረመው፣ የወቅቱ ብቃታቸው የአገር ውስጥ ውድድሮችን ያለተቀናቃኝ አሸናፊ ያደርጋቸው ስለነበር አገራቸውን በመወከል የሜልቦርን ኦሊምፒክን ጨምሮ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ፍላጎቱ ያድርባቸዋል፡፡ ሆኖም ያንን የሚያሳኩበት ቀዳዳ ለመኖሩ እርግጠኛ ባይሆኑም ያገኙትን አጋጣሚ ለመጠቀም ግን ለራሳቸው ቃል መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በአንድ አጋጣሚ ከአዲስ አበባ፣ ዱከምና ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ልምምድ ላይ ሳሉ ንጉሡ ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ሲያመሩ ይገጣጠማሉ፡፡ በራሳቸው የእጅ ጽሑፍ የተዘጋጀውን ደብዳቤ ከፍ አድርገው በመያዝና በማሳየት ንጉሡን መንገድ ላይ አስቁመው የሰጡበት አጋጣሚ መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡
በጊዜው ንጉሠ ነገሥታቱ እጅ የደረሰው የቀድሞ ብስክሌተኛ ደብዳቤ፣ ይሆናል አይሆንም የሚለው ከሁለት ቀናት በኋላ በንጉሡ እልፍኝ አስከልካይ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጄኔራል መኮንን ፈለቀ አማካይነት ቤተ መንግሥት እንዲገቡ ተደርገው ንጉሡም ‹‹አቅሙ ካለህ ይሁን›› ብለው የፈቀዱላቸው ስለመሆኑም አይዘነጉም፡፡ እንደ አቶ ገረመው ምንም እንኳ በጊዜው ስፖርቱን በሚመለከት ግንዛቤ ኖሮ ድጋፍና ክትትሉ ባይኖርም፣ ነገር ግን የንጉሡ ይሁንታ ለእሳቸው የነበረው ትርጉም ብዙ ነው፡፡
በአውስትራሊያ ሜልቦርን በ1949 ዓ.ም. የሚካሄደው ኦሊምፒክ ተቃርቧል፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ለዝግጅት የተመረጡት ሰባት አባላት ቤት ያፈራውን ብቻ በመመገብ ልምምድ ከማድረግ የቦዘኑበት ጊዜ ለቀድሞው ብስክሌተኛ ትዝ አይላቸውም፡፡ መወዳደሪያ ብስክሌቶቻቸው ሁሉም በጊዜው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በቻለበት ጊዜ ያመጣቸው በመሆኑ ችግር እንዳልገጠማቸው የሚያወሱት ገረመው፣ የዝግጅት ጊዜው አብቅቶ አውስትራሊያ ሜልቦርን ለመግባት የፈጀባቸው 72 ሰዓታት ከሁሉም በላይ የማይዘነጉት አሰልችውና መጥፎው መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ በሮም ኦሊምፒክ በብስክሌት የተሳተፉት ገረመው፣ ከአልአዛር ክፍሉ፣ ተሰማ አሞሳና መንግሥቱ ንጉሤ ጋር በመሆን በቡድን በተደረገው የ100 ኪ.ሜ ግልቢያ በ2 ሰዓት 38 ደቂቃ 34.08 ሰከንድ 28ኛ ደረጃን ተቀዳጅተዋል፡፡ በግል በተደረገው የ175.38 ኪ.ሜ ውድድር ግን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለመፈጸም አልታደሉም፡፡
በተወዳዳሪነት ዘመናቸው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ እሳቸው የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ቡድን ያስመዘገበው የዘጠነኛነት ውጤት ትልቁ ነው፡፡ እስካሁን የተሻለ ውጤት ለመመዝገብ ያልተቻለው ተተኪ ጠፍቶ ሳይሆን በስፖርቱ ያለውን አቅም ለመጠቀም ፍላጎት ማጣት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ብስክሌተኛው በተወዳዳሪነት ዘመናቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለተተኪዎቻቸው ለማስተላለፍ ያልቻሉበት ምክንያት ለምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ሲናገሩ፣ ‹‹ዕውቀትና አቅም የለህም እንዳልባል አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የስፖርቱ አስተዳዳሪ በነበሩበት በ1965 ዓ.ም. በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የብስክሌቱን ብሔራዊ ቡድን በዋና አሠልጣኝነት እንድመራ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ በብስክሌት ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩበት የኤርትራ ክፍለ ሀገር ወጣቶች ነበሩ፡፡ ለብሔራዊ ቡድን ቅድሚያ ተመራጭ የሆኑትም ሁሉም ከኤርትራ የተገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ በውድድር ተሳትፎዎቻችንም በሰዓትም ሆነ በጎዳና አሸናፊው የኢትዮጵያ ቡድን ሆነ፡፡ ይሁንና ውድድሩን አጠናቀን ወደ አገር ቤት ስንመለስ የጠበቅነው ሽልማትና አክብሮት ቀርቶ ሊጠቀስ የሚችል የአቀባበል ሥነ ሥርዓት እንኳ አልተደረገልንም፡፡ በዚህም ልጆቹ ቅሬታ አሰሙ፡፡ የእኔም የአሠልጣኝነት ዘመን በዚያው እንዲያበቃ ምክንያት ሆኖ ቀረ፤›› በማለት ትውስታቸውን ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በብስክሌት ከሜልቦርን እስከ ሞስኮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በባርሴሎና ከተካፈለች በኋላ ተካፋይነቷ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ ፅጋቡ ገብረማርያምን በመሰሉ ወጣት ተተኪዎች ስፖርቱ እሳቸውና ሌሎቹ በጀመሩት መንገድ ለመቀጠል ሲታትሩ መመልከታቸው ‹‹የቅብብሎሹ ጊዜ ቢዘገይም በሕይወት ኖሬ ስላየሁት ደስ ብሎኛል፤›› በማለት ለብቸኛው የሪዮ ኦሊምፒክ ተወዳዳሪ ፅጋቡ ገብረማርያም መልካሙን በመመኘት ስሜታቸውን ገልጸውታል፡፡ በወጣቱ የተጀመረው የኦሊምፒክ ተሳትፎም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመማፀን አደራውንም ለአትሌት ፅጋቡ አስተላልፈው ትውስታቸውን አጠናቀዋል፡፡
የአንጋፋውን ብስክሌተኛ አደራ የተቀበለው የሪዮ ኦሊምፒክ የአገሪቱ ብቸኛ ተወካይ ፅጋቡ ገብረማርያም የሪዮ 2016 ተሳትፈው በውጤት መታጀብ ይችል ዘንድ ዝግጅቱን በኢትዮጵያና በጣሊያን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ አትሌቱ ለእሱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ስፖርተኞች ትልቅ ህልም ተደርጎ የሚወሰደውን የኦሊምፒክ ተሳትፎን ማሳካቱ ያስደሰተው ስለመሆኑም አክሏል፡፡
‹‹ውጤት ሁለተኛው ህልሜ ነው›› በማለት ወቅታዊ ብቃቱንና ዝግጅቱን አስመልክቶ ገለጻ ያደረገው ፅጋቡ፣ በአሁኑ ወቅት በመቐለና ማይጨው አካባቢ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ አትሌቱ ከሆነ ወጣ ገባና ሞቃታማ የሆነውን ማይጨው የመረጠበት ምክንያት በአውሮፓውያኑ ዘንድ ከኦሊምፒክ ያልተናነሰ ቦታ የሚሰጠው ‹‹ቱር ደ ፍራንስ›› ውድድር ላይ የመሳተፍ እቅድ ስላለው ነው፡፡ ዓመታዊው ቱር ደ ፍራንስ የ21 ቀን ውድድር መሆኑን የሚናገረው ፅጋቡ ከሦስት ሳምንት በኋላ የማይጨው ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ጣሊያን የሚያመራ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በዓመታዊው ውድድር የቱር ደ ፍራንስ ዓለም ላይ በብቃታቸው የሚመረጡ 22 ክለቦች በነጠላ ሳይሆን በቡድን የሚፎካከሩበት ነው፡፡ እንደ አትሌቱ ከሆነ በዚህ ውድድር ላይ ሲሳተፉ የመጀመሪያው ነው፡፡ አትሌቱ ስለውድድሩ ሲናገር ቱር ደ ፍራንስ ለእሱ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ውድድሩ ምንም እንኳ ምርጥ ክለቦች በነጠላ ሳይሆን በቡድን የሚሳተፉበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ በኩል ግን ክለቡ ለዚህ ውድደር ከሚመርጣቸው አትሌቶች አንዱ ሆኖ ለመቅረብ ደግሞ የግል ጥረትና ጥንካሬ ትልቁን ቦታ ይወስዳል፡፡ በዚህ ሻምፒዮና ላይ በቡድን የሚያስመዘግበው ውጤት ለኦሊምፒክ ተሳትፎው ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ተናግሯል፡፡