Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክመንግሥት የሚያጭበረብርና የተጭበረበረ ነጋዴ መለየት አለበት

መንግሥት የሚያጭበረብርና የተጭበረበረ ነጋዴ መለየት አለበት

ቀን:

በተካ መሓሪ ሓጐስ

  የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ሐሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች መንግሥት ሊሰበስበው በሚገባ የግብር ገቢና በሕጋዊ የንግድ ማኅበረሰብ ሥራዎች ላይ እንዲሁም በንግድ ሥርዓቱ በአጠቃላይ እያደረሱት ስላለው ጉዳት በተወሰነ መልኩ በማንሳት የመፍትሔ ሐሳብ ጠቁሞ ለማለፍ ነው፡፡

    “A VAT invoice……” as Birds (1993) puts it, is a check written on the government.” (Emphasis mine)

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹መግለጫው አሳሳች ነው የሚባለው የፍሬ ጉዳይ ነው››

በአገራችን በ1983 ዓ.ም. የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሥርዓት ከዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ መቀየሩ ይታወቃል፡፡ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለውጡን መሠረት በማድረግ ደግሞ በግብርና ታሪፍ ፖሊሲና ሕግ ላይ ዘርፈ ብዙ ለውጦች አምጥቷል፡፡ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በተካሄደው የታክስ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም መሠረትም የአገሪቱን የግብር ሥርዓት የሚያዘምኑ አስፈላጊ ሕጎችና አሠራሮች እየተተገበሩ አገሪቱ የምትሰበስበው የግብርና ቀረጥ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ለውጦች ውስጥ ለሕጋዊ የንግድ ሥርዓት መጐልበትና የግብር ሕግ ተገዥነት ለማሳደግ ግብይቶች በደረሰኝ አማካኝነት እንዲከናወኑ ያስቻለ አሠራር አንዱ ነው፡፡ ይህ አሠራር በግብር ከፋዩና በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት መካከል በመተማመን፣ በመቀራረብና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ግብይቶች በደረሰኝ አማካኝነት እንዲከናወኑ ማድረጉ ለሁለቱም ወገን በጣም ጥሩ የሚባል አሠራር ቢሆንም፣ አንዳንድ በሕገወጥ መንገድ የመበልፀግ ፍላጐት ያላቸው ሰዎች ለሚፈጽሙአቸው ግብይቶች ሐሰተኛ ደረሰኞች ቆርጠው በመስጠት መንግሥት መሰብሰብ ይገባው የነበረ ታክስ ለራሳቸው በመውሰድ በመንግሥት ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት በተጨማሪ የሕጋዊ ነጋዴውን ገንዘቡ እየመዘበሩ ለኪሳራና ለተለያዩ እንግልቶች እንዲጋለጥ ያደርጋሉ፡፡ በአጠቃላይ በገዥና ሻጭ መካከል መተማመን ላይ የተመሠረተ ግብይት እንዳይኖር በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንኑ ሕገወጥ ድርጊት መንግሥትና ነጋዴው ማኅበረሰብ በጋራ ታግለው አፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት ተፅዕኖው ዘርፈ ብዙና የከፋ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሕገወጥነት ለመከላከል የሚያስችል የሕግና የአሠራር ሥርዓት በማስፈን በሕገወጥ ድርጊቱ የሚሳተፋ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያደርግ የእርምት ዕርምጃ በመውሰድ፣ ሕጋዊ ነጋዴው ላይ ሊደረስ የሚችል ኪሳራና እንግልት መቀነስ ብሎም ማስወገድ አለበት፡፡ ይህንኑ ማድረግ ካልተቻለ ግን በአገሪቱ ሕገወጥነት እያየለ በሕጋዊ መንገድ የሚነግድ ነጋዴ ማኅበረሰብ ከንግድ ሥርዓቱ እየወጣ መንግሥት መሰብሰብ የሚገባው የግብርና ቀረጥ መጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡም ቢሆን የንግድ ሥርዓቱ ሕጋዊ እንዲሆን ለማድረግ የራሱን ድርሻ ካልተወጣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ቀዳሚ ተጐጂ ራሱ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አለበት፡፡

   በአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ያሉ ሕገወጥ ደረሰኞች ዓይነታቸው ብዙ ስለሆነ፣ ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ በሐሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች አማካኝነት እየተፈጠሩ ያሉ ሕገወጥ ድርጊቶችና ያመጡት ተፅዕኖ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ሐሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች ደግሞ ተፅዕኖአቸው በተጨማሪ እሴት ታክሱ ብቻ ሳይሆን በገቢ ግብር ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተፅዕኖ ያላቸው በመሆኑ፣ እግረ መንገዴን በሁለቱን የግብር ዓይነቶች ስለሚያመጣው ጉዳት በተወሰነ መልኩ አነሳለሁ፡፡

በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በሌላ ሁኔታ ካልተወሰነ በቀር ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት የተመዘገበና ታክስ የሚከፈልበት ግብይት የሚያከናወን ሰው ዕቃዎቹን ወይም አገልግሎቶቹን ለሚያቀርብለት ሰው ደረሰኝ ወዲያውኑ መስጠት እንዳለበት በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 22(1) ላይና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 609/ 2001 አንቀጽ 2/10/ ላይ ተደንግጓል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ምን ዓይነት ይዘት ሊኖረው  እንደሚገባም  በአዋጅ ቁጥር 285/94፤ አዋጅ ቁጥር 609/2001 እና መመርያ ቁጥር 28/2001 በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ በውስጡ ለዕቃዎች ወይም ለአገልግሎቶች ግብይት የተከፈለ የግዥ ዋጋ ከመያዙም በላይ ለአንዱ ነጋዴ እንደ ግብዓት ታክስ ለሌላው ደግሞ እንደ ውጤት ታክስ የሚያወራርድበት የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን ስለሚያዝ፣ ይህ ደረሰኝ  ሐሰተኛ ከሆነ  ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግሥት ፈሰስ እንዳይደረግ ብሎም በንግድ ትርፍ ግብር አሰላል ጊዜ ያልወጣ ወጪ አላግባብ እንዲያዝ ወይም ደግሞ በአግባቡ የወጣ የንግድ ዕቃ የመግዣ ዋጋ ወጪ በጥርጣሬ እንዲታይ ያደርጋል፡፡

ሐሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ በቅድሚያ ከሕጉ አንፃር ማየቱ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 609/2001 አንቀጽ 2(13)  ላይ ‹‹ሐሰተኛ ደረሰኝ ማለት በባለሥልጣኑ ሳይፈቀድ የታተመ ወይም በኮምፒውተር የተዘጋጀ ደረሰኝ ወይም የግዥውን ወይም የሽያጩን ሒሳብ ለማሳነስ ወይም ለመጨመር በማሰብ ወይም በቸልተኝነት በሰነዱ ላይ አኃዝ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ደረሰኝ በማሳተም ወይም በማባዛት ወይም ሁሉንም ቅጂዎች እንደ በራሪ በመጠቀም ወይም የሚፈቀደው የታክስ ተቀናሽ ወይም ተመላሽ ሒሳብ እንዲጨምር ወይም የማይገባውን ተመላሽ ለማግኘት ወይም ሌላ ማናቸውም የማጭበርበር ተግባር ለመፈጸም የተዘጋጀ ሰነድ ነው፤›› የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህ ደረሰኞች በጥቅሉ ሲታዩ በይዘት ደረጃ ሙሉ በሙሉ ሕገወጥ የሆኑና በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የማይታወቁ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተፈቅደው የታተሙ ወይም ከማሽን የወጡ ነገር ግን ግብይት በአግባቡ ሳይከናወን ሕጋዊ ደረሰኞቹ ብቻ እየተሸጡ እየተፈጠረ ያለው ጉዳትም በቀላሉ የሚታይ እይደለም፡፡ በእነዚህ ሁለት ዓይነት ደረሰኞች በተፈጠረ ግብይት በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤትና በግብር ከፋዮች ዘንድ ብዙ ክርክር እያስነሳ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ደረሰኞች በሁለት ዓይነት ነጋዴዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እነዚህም በሕገወጥ መንገድ የመበልፀግ ፍላጐት ያላቸው አንዳንድ ነጋዴዎች ያላወጡት የንግድ ሥራ ወጪ እንደ ወጪ አድርጐ በማስያዝ የሚከፍሉት የንግድ ትርፍ ለመደበቅ ብሎም ያልከፈሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ በግብዓት ታክስ ለማወራረድ የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሕጋዊ መንገድ የንግድ ሥራቸውን የሚያከናውኑ ነጋዴዎች የደረሰኞቹ ሕገወጥነት ሳያውቁ ለግብይቱ የመግዣ ዋጋና የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፍለውበት በመጨረሻ የንግድ ዕቃው ወይም አገልግሎቱ ለመግዛት ያወጡት ወጪ እንደ ሽያጭ ወጪ (Cost of sales) እንዲያዝላቸውና በእነዚህ ግብይቶች የከፈሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ የግብዓት ታክስ ለማወራረድ ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ሰነዶቹ በቅንነት የሚያቀርቡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተቀላቀሉ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜ በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የሚፈጥረው ተፅዕኖና የሥራ ጫና ቀላል ባይሆንም፣ የሚሰጡ ውሳኔዎች አጥፊውንና ንፁህ በአግባቡ በመለየት መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ በግብርና ንግድ ሥርዓቱ የሚያመጣው ጉዳት ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ለጉዳዮቹ ተገቢውን ክትትልና ምርመራ በማድረግ አጭበርባሪና የተጭበረበረ ነጋዴ በአግባቡ ሳይለይ ሁሉንም በጋራ ተጠያቂ የሚያደርግ አስተዋይነት ያልተሞላበት አሠራር ካለ ግን፣ ሕጋዊ ነጋዴው ከደረሰበት ኪሳራ በተጨማሪ ላላስፈላጊ እንግልትና እስር እንዲዳረግና ከገበያው እንዲወጣ ወይም ተስፋ ቆርጦ ሙሉ በሙሉ በሕገወጥ ንግድ እንዲሰማራ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሕጋዊ ነጋዴው ቁጥር እንዲያንስ ብሎም ዜጐች በንግድ ሥራ ላይ እንዳይሰማሩ የፍርኃት ድባብ እንዲፈጥርባቸው በማድረግ ከዘርፉ አገሪቱ ማግኘት ያለባት ገቢ እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡

በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሐሰተኛ ተብለው በሚፈረጅ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች አማካኝነት ለተፈጸሙ ግብይቶች በገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ አወሳሰን ላይ በተቋሙ ደረጃ የተዘበራረቀ አሠራር ይታይበታል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሕገወጥ ናቸው ከሚባሉ ደረሰኞች ጋር በተያያዘ እነዚህ ደረሰኞች ለተቋሙ ባቀረቡ ነጋዴዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 በመተላለፍ ያልተገባ ተመላሽ በመጠየቅ የሚፈጸም የግብር ስወራ ወንጀል መፈጸምና የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 50 በመተላለፍ አሳሳች ወይም የሐሰት መግለጫ ማቅረብ፤ አንቀጽ 50 (ሐ) በመተላለፍ ሐሰተኛ ደረሰኝ መጠቀም ወንጀል ክስ እንዲሁም የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 በመተላለፍ የገቢ ግብር መሰወር ወንጀል ፈጽመዋል የሚሉ ክሶች ሲቀርብባቸው ይታያል፡፡ በሌላ በኩል በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ  ፈቃድ መሠረት ለተጨማሪ እሴት ሰብሳቢነት ተመዝግበው ደረሰኝ ካሳተሙ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ወስደው በንግድ ሥርዓቱ ከገቡ በኋላ ለብዙ ጊዜያት የተጨማሪ እሴት ታክስ አሳውቀው የማይከፍሉ አንዳንድ ነጋዴዎች  በሚኖሩበት ጊዜ ከነዚህ ነጋዴዎች ግብይት ፈጽመው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ይዘው የከፈሉት የግብዓት ታክስ ለማወራረድ ጥያቄ በሚያቀርቡበት ጊዜ ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ላልተፈጸመ ዓብይት ተመላሽ ታክስ አልከፍልም የሚል ምላሽ በመስጠት ከዚህ አልፎም ያልተገባ ተመላሽ ጠይቃችኋል በማለት የወንጀል ክስ የሚያቀርቡበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ከሁለተኛው ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሌላ መልኩ አንዳንድ ነጋዴዎች በሕጋዊ መንገድ ያሳተሙት ወይም ከማሽን የወጣ ደረሰኝ በመሸጥ በሕገወጥ ድርጊት ላይ መሳተፋቸው የሚያሳይ ማስረጃ በማሰባሰብ ግብይት ሳይፈጽሙ ደረሰኙ ብቻ በመግዛት የማይገባ ተመላሽ በሚጠይቁ ግለሰቦች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የመሰወርና ሐሰተኛ መግለጫ የማቅረብ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በማለት የሚያቀርባቸው ክሶች አሉ፡፡ በሁለቱም ዓይነት ደረሰኞች (ሙሉ በመሉ ሕገወጥ በሆኑ ደረሰኞችና ግብይት ሳይፈጸምባቸው ደረሰኞቹ በመግዛት ብቻ የተመላሽ ጥያቄ የሚቀርብባቸው) ላይ በሕገወጥ መንገድ የሚሳተፋ ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የሚደረግ ምርመራና ክስ ይበል ሊባል ካልሆነ ሊቀርብ የሚችል መቀሳ አይኖርም፡፡ ነገር ግን  በሐሰተኛ ደረሰኞቹ አማካኝነት ተታለው ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰን ውሳኔ በጥንቃቄ የሚታይ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሐሰተኛ ደረሰኞች አማካኝነት በመንግሥት ገቢና በሕጋዊ ነጋዴው ሊፈጠር የሚችለው ተፅዕኖ በአግባቡ ታይቶ የደረሰኞቹ ዓይነት ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ ሊቀመጥ ይገባል፡፡

  1. ሙሉ በሙሉ ሕገወጥ በሆኑ ደረሰኞች ለሚፈጸሙ ግብይቶች ሊኖር የሚችለው መፍትሔ

ሙሉ በሙሉ ሕገወጥ ከሆኑ ደረሰኞች ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያለው የውሳኔ አሰጣጥ ሁኔታ ሲታይ ደረሰኞቹ ሕገወጥ ስለሆኑ ግብይቱ ያልተደረገ ነው የሚል አቋም በመያዝ እነዚህ ደረሰኞች እንደ በቂ ማስረጃ በመውሰድ ደረሰኙን ይዞ በተገኘ ግለሰብ ላይ እንጂ ከዚህ አልፎ ምንጫቸውና የተገኙበት መንገድ ያለማረጋገጥ፤ ዕቃው በገዥ እጅ አለ ወይስ የለም ከተሸጠስ ለማን ተሸጠ መቼና በምን ያህል ዋጋ የሚለው ፍሬ ነገር ያለማጣራት ሁኔታ፤ ደረሰኙ ሕገወጥ ቢሆንም ግብይቱ በትክክል መከናወን አለመከናወኑን አለማረጋገጥ፤ ሕገወጥ ደረሰኞቹ ሊያዘጋጁ የሚችሉና ለሽያጭ ሊያቀርቡ የሚችሉ ሰዎች ዒላማ ያደረገ የወንጀል ምርመራ ሥራ አለማከናወን፤ በአጠቃላይ በገዥው በኩል ሊቀርቡ የሚችሉ የማስተባበያ ማስረጃዎችና ምክንያቶች በሚገባ የማይጣራበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህንኑ ለችግሩ  መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረግ ጥረት አናሳነት የሚያሳይና ሥር ነቀል ለውጥ የማያመጣ ከመሆኑም በላይ የተጭበረበረ ነጋዴ አለጥፋቱ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በሐሰተኛ ደረሰኞች አማካኝነት የተፈጸሙ ግብይቶች በአግባቡ የተከናወኑ መሆናቸው ከተረጋገጠ  ለገዥው ሐሰተኛ ደረሰኞቹ ከማንና እንዴት ሊሰጠው እንደቻለ ከገዥው ጋር በመተባበር ምንጫቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የእነዚህ ሕገወጥ ደረሰኞች ምንጭ የማፈላለግ ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን በገዥዎች በኩል የሚፈጸሙ አንዳንድ ስህተቶችም አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በተለይ ደግሞ በመርካቶ ላይ ያለው ንግድ አየር በአየር የሚፈጸም ገዥና ሻጭ በዓይን ሳይተያዩ በመሀል ባሉ ደላሎች አማካኝነት የዕቃ ርክክብ የሚደረግበት ሁኔታ ለግብይቱ የሚሰጡ ደረሰኞች ከየት ተሰጡ የሚለው ጉዳይ ለማረጋገጥ ሁኔታው አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ገዥና ሻጭ ዓይን ለዓይን ሳይተያዩ መሀል ባሉ ደላሎችና በስልክ ንግግር ብቻ ግብይት የሚከናወንበት ሒደት ለግብይቱ ሻጭ ከሚባሉ ሰዎች የሚላኩ ደረሰኞች በመጨረሻ ሕገወጥ ሆነው ሲገኙ ገዥዎች የሻጩ አድራሻ እንዲያሳዩ ሲጠየቁ የሚቸገሩበት ሁኔታ እንደሚኖር አስቀድሞ የሚገመት ነው፡፡ በአገሪቱ ያለ የንግድ ሥርዓት ሙሉ በመሉ ሕጋዊነት የተላበሰ ስላልሆነ አንዳንድ የዕቃ አቅርቦት የሚፈጽሙ ሰዎች የዕቃ መጋዘናቸው በሕጋዊ መንገድና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገዙ ዕቃዎች ተቀላቅሎ የሚቀመጥበት ሁኔታ ስለሚኖር የዕቃ መጋዘናቸው ገዥዎች እንዲያዩባቸው አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ነው በተለይ በመርካቶ ገበያ ላይ የአየር በአየር የዕቃ ሽያጨ በስልክና በደላሎች አማካኝነት እንዲፈጸም ምክንያት እየሆነ ያለው፡፡ በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት በኩል ያለው ዘመናዊነት ያልተላበሰ አሠራርም በነጋዴዎች የሚቀርቡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች ለግብዓት ታክስ ማወራረጃ ሲቀበላቸው ከቆየ በኋላ ከሦስትና ከአራት ዓመታት በኋላ ግብይት የፈጸመላችሁ ሻጭ ካላመጣችሁ እናንተ ሕገወጥ ሥራውን ሠርታችሁታል በማለት ሕጋዊ የሆኑ ነጋዴዎች ስህተታቸው በጊዜው አውቀው አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ያጠፋ ሕገወጥ ድርጊት ፈጻሚ ግለሰቦች በጊዜው እንዳይፈለጉ በማድረግ ተቋሙም ለጥፋት አስተዋጽኦ የሚያደርግበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በአገር ደረጃ ሲታይም  ነጋዴው ማኅበረሰብ ትክክለኛና ሐሰተኛ የሚባሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች በቀላሉ የሚለዩበት የአሠራር ሥርዓት ባለመዘርጋቱና ሕገወጥ የሚባሉ ደረሰኞች በየማተሚያ ቤቱ የሚታተሙበት ሰፊ ዕድል ያለ ከመሆኑ አንፃር ግብር ከፋዩን በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ የደረሰኞቹን ሕገወጥነት ብቻ በማየት የሚሰጥ ውሳኔ ትክክለኛና ፍትኃዊ የሆነ ውጤት ላይ አያደርስም፡፡ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳይሰጥ በኮምፒውተር በተዘጋጀ ወይም በሚታተም ደረሰኝ ተጠቅመሀል በማለት አንድን ግብር ከፋይ ተጠያቂ ለማድረግ ሕገወጥ ደረሰኝ ሲጠቀም የነበረው የሒሳብ ክፍል ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 ሥር ከተጠቀሱ ወንጀል ሊያቋቁሙ ከሚችሉ ሦስት ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልቶ መገኘት (ሕጋዊ ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች) አንፃርም መታየት አለበት፡፡ በትክክል መንገድ ግብይቱን ፈጽሞ የተሰጠው ደረሰኝ ደግሞ ትክክለኛ መስሎት የተቀበለ ገዥ ለራሱ የተታለለ መሆኑን ከሚያሳይ በቀር በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፈሀል ተብሎ ሕገወጥ ደረሰኝ በመጠቀም ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ አያስችልም፡፡ በዚሁ ዓይነት ግብይቶች የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ ስለማቅረብ የሚደነግገው የተጨማሪ እሴት ታክስ ወንጀል ድንጋጌ ደግሞ ግብር ከፋዩ ለታክስ ባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ ያቀረበ እንደሆነ ወይም ሊያቀርብ ከሚገባው መግለጫ ውስጥ መግለጫውን አሳሳች ሊያደርግ በሚችል አኳኋን መካተት የሚገባቸውን ነጥቦች ያስቀረ እንደሆነ የወንጀል ክስ የሚመሠረትበት መሆኑ ያሳያል፡፡ የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ ወይም መግለጫ አቀረበ የሚባለው ምን ዓይነት ድርጊት በፈጸመ አጥፊ ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን በሚፈለገው መልኩ ድንጋጌው ግልጽ ስላልሆነ ከወንጀል ሕግ የአተረጓጎም መርሆች አንፃር ተተርጉሞ የድንጋጌው ይዘት መታወቅ አለበት፡፡ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ለመተረጎም ከሚንጠቀምባቸው ስልቶች ውስጥ የሕጉ የማብራሪያ ሰነድ መጠቀም አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕጉ በሚያብራራው ሰነድ የአዋጁ አንቀጽ 50 ማብራሪያ  ላይ ‹‹መግለጫው አሳሳች ነው የሚባለው  የፍሬ ጉዳይ ነው›› በማለት ተቀምጧል፡፡ ከዚሁ ማብራሪያ ይዘት አንፃር ድንጋጌውን በመተላለፍ አንድ ግብር ከፋይ የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ ወይም መግለጫ አቀርቧል ብሎ በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ሐሰተኛ ደረሰኝ መኖሩ ብቻ ሳይሆን በዚሁ ምክንያት የተፈጠረ የፍሬ ጉዳይ መፋለስ ስለመኖሩ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሐሰተኛ ደረሰኝ ለተፈጸመ ግብይት የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ አቀረበ ለማለት የግብይት ደረሰኙ ሐሰተኛ መሆኑን ሳይሆን ግብይቱ በትክክል ያልተከናወነ ስለመሆኑ ማሳየት እንጂ ግብይቱ ተፈጽሞ እያለ ደረሰኝ ሐሰተኛ በመሆኑ ብቻ በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ተጠያቂነት ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ግዥውን ስለመከናወን አለመከናወኑ ደግሞ በገዥው ለግዥ የወጣ የገንዘብ እንቅስቃሴ /Cash flow/ መኖር አለመኖሩ፣ ገዥው ዕቃዎቹን ሲረከብ ዕቃዎቹ የተመዘገቡበት ሕጋዊ ሰነዶች መኖር አለመኖራቸው፣ የገዥውን የዕቃ ቆጠራ ግኝት የሚያሳይ መዝገብ ማየት እንዲሁም ከተቻለ ቴክኒካል ኦዲት /Technical audit/ በማድረግ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ግብር ከፋዩ ግዥ ሲፈጽም በዚሁ ግብይት የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ የግዥ ዋጋ በመክፈል ዕቃውን ከገዛ በኋላ የተሰጠው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሕጋዊ መስሎት የግብዓት ታክስ ለማወራረድ ቢያቀርበውም ሆነ ብሎ ግብር ለመሰወር የፈጸመው ድርጊት እስካልሆነ ድረስ ያልተገባ ተመላሽ ወስደሀል ወይም ጠይቀሀል በማለት ሊመጣ የሚችል የወንጀል ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ ነገር ግን ግብር ከፋዩ በእነዚህ ሐሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኞች በፈጸመው ግብይት ላይ የተከፈለ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግሥት ፈሰስ ያልተደረገ በሕገወጦች የተወሰደ ስለሆነ መንግሥት ደግሞ ላልወሰደው (ላልተቀበለው) የተጨማሪ እሴት ታክስ በግብዓት ታክስ ማወራረድ አለብህ ለማለት ስለማይቻል በዚሁ ዓይነት ሕገወጥ ደረሰኝ የተከፈለ የተጨማሪ እሴት ታክስ ኪሳራውን የተጭበረበረው ነጋዴ በራሱ መቻል አለበት፡፡ ከቻለም ያታለለውን ሰው ፈልጐ እንዲመልስለት ማድረግ ይችላል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነት ግን ከወንጀል ሕጉ መርህ ጋር ስለማይሄድና ገዥው በሌሎች ሰዎች ተታሎ የማጭበርበር ድርጊቱ ሰለባ በመሆኑ ከኪሳራው በተጨማሪ አለአግባብ በወንጀል ተጠያቂ መሆን የለበትም፡፡ የንግድ ትርፍ በተመለከተ ደግሞ ግብር ከፋዩ ግዥውን በአግባቡ አከናውኖት ከሻጩ የተሰጠው ደረሰኝ ግን ሐሰተኛ መሆኑን ማረጋገጥ ከተቻለ ለዕቃው መግዣ የከፈለው ዋጋ በመጨረሻ የንግድ ትርፍ ግብሩ በሚወራረድበት ጊዜ እንደ ሽያጭ ወጪ /Cost of sales/ ሊያዝለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም አንድ ነጋዴ ዕቃ ሳይገዛ ሊሸጥ ስለማይችል ሽያጩን ተቀብሎ የግዥ ዋጋ መጣል ከሒሳብ አሠራር መርህም ሆኖ ከነባራዊ እውነታ የማያስኬድ አሠራር በመሆኑ፡፡ ግዥውን የሚጣል ከሆነ ግን ሽያጩንም መቀበል አይችልም በሽያጩም የንግድ ትርፍ ግብር ማስላት ተገቢነት አይኖረውም፡፡

2. በባለሥልጣኑ ፈቃድ ታትመው የሚሰጡ /ከማሽን የሚወጡ ደረሰኞች ጋር በተያያዘ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ከተሰጡት ሥልጣኖች  ውስጥ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት የተመዘገቡ ሰዎች የሚጠቀሙበት የደረሰኝ ዓይነትና ብዛት ቀድሞ አውቆት በሰጠው ፈቃድ ልክ ብቻ እንዲያሳትሙ መቆጣጠር ከማሽን የወጣ ደረሰኝ የሚጠቀሙ ከሆነ ደግሞ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ከሰጠው አቅራቢ ብቻ በአግባቡ ግዥ ተፈጽሞ የማሽኑ ዓይነትና በዚሁ ማሽን የሚጠቀማቸው ሥርዓት የማረጋገጥ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ የሚያሳትሙ ሕትመት ቤቶችም የሚያሳትሙት ደረሰኝ ቀድሞ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ በተሰጠበት ዓይነትና መጠን በቻ መሆን እንዳለበት  በደንብ ቁጥር 78/1995 በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በተግባር ላይ የደረሰኝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ አንዳንድ ነጋዴዎች በባለሥልጣኑ ፈቃድ መሠረት ያሳተሙት ወይም ከማሽን የሚወጡ ደረሰኝ ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኙ የመሸጥ ድርጊት ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከፈጸሙት ግብይት ላይ የሰበሰቡት የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግሥት ሳይከፍሉት ይዘውት የሚጠፉበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ዕውቅና የታተሙ ወይም ከማሽን የሚወጡ ደረሰኞች አማካኝነት የሚፈጠሩ ጥፋቶች ለመለየት በዋናነት በሻጩ የተሸጠ ዕቃ አለመኖሩን ገዥው ደግሞ ዕቃውን ያልገዛው መሆኑን መሠረት ያደረገ ክትትልና ምርመራ በማከናወን ግብይት በአግባቡ ሳይፈጸም እንደ ተፈጸመ ተደርጐ የተፈጸመ የግብዓት ታክስ የማወራረድ ደርጊት ካለ፣ አጥፊው ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰወርና አሳሳች ወይም የሐሰት መግለጫ የማቅረብ ወንጀል ፈጽሟል የሚል የወንጀል ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን  በእንደዚህ ዓይነት ደረሰኞች ጋር በተያያዘ  በሚጣሩ ጉዳዮች ላይ በኢንቨስትጌሽን ኦዲት ክፍል፤ በወንጀል ምርመራና በዓቃቤ ሕግ ውሳኔ ላይ የተዘበራረቀ አሠራር ይታይበታል፡፡

በሕጋዊ መንገድ በታተሙ ደረሰኞች ወይም ከማሽን የሚወጡ ደረሰኞች አማካኝነት የተፈጸሙ ግብይቶች ትክክለኛ አለመሆናቸው እየታወቀ በባለሥልጣኑ የኢንቨስትመንት ኦዲት ክፍል ደረሰኞቹ በባለሥልጣኑ ፈቃድ የታተሙ መሆናቸው፤ ገዥና ሻጭ ማንነትና የግብይት ዋጋ በደረሰኞቹ ላይ ስለሚገለጽ ደረሰኞቹ ብቻ መሠረት በማድረግ ግብርና ታክስ የመወሰን ሁኔታ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ደረሰኞች ይዘው በመምጣት የግብዓት ታክስ ተመላሽ የሚጠይቁ ግብር ከፋዮች የሚያቀርቡት ጥያቄ  በመከልከል እርስ በራሱ የሚጋጭ ውሳኔ ሲሰጥ ይታያል፡፡ በወንጀል ምርመራ ክፍሉና በዓቃቤ ሕግ በኩል የሚታዩ ውሳኔዎችና አካሄዶችም በተመሳሳይ መልኩ እርስ በራሱ የሚጋጭና ወጥነት የጎደለው አቋም ይታያል፡፡ በእነዚህ ዓይነት ደረሰኞች አማካኝነት በሚደርስ ጉዳት አጥፊውን ለመቅጣት የሚፈለግ ከሆነ ጉዳዩ መታየት ያለበት ግብይት አለመፈጸሙና ባልተፈጸመ ግብይት ደግሞ አለአግባብ የግብዓት ታክስ ተመላሽ ጥያቄ በማቅረብ የታክስ ስወራና ሐሰተኛ ወይም የተሳሳተ መግለጫ የማቅረብ የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸሙ ሊያሳይ የሚችል የኢንቨስትጌሽን ኦዲትና የወንጀል ምርመራ ሥራ በአግባቡ ተጣርቶ መቅረብ አለበት፡፡ ለግብይቱ የተሰጠው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ በሕጋዊ መንገድ የታተመ ወይም ከማሽን የወጣ ደረሰኝ በመሆኑ ብቻ ለግብይቱ ሕጋዊነት እንደ በቂ ማስረጃ ተደርጐ መወሰድም የለበትም፡፡ በሌላ በኩል በእንደዚህ ዓይነት ደረሰኞች ገዥው ግብይቱ በአግባቡ ያከናወነው መሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ ካለ ሻጩ በመጥፋቱ ብቻ በሕጋዊ መንገድ ግብይቱ የፈጸመ ነጋዴ የሚያቀርበው የግብዓት ታክስ ተመላሽ ጥያቄ ውድቅ መደረግ የለበትም፡፡ ምክንያቱም የተጨማሪ አሴት ታክስ ደረሰኞቹ ለገዥ የሰጠው በሕጋዊ መንገድ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በኩል ደግሞ የተጨማሪ እሴት ታክስ መንግሥትን ወክሎ ሽያጭ ከሚያከናውንላቸው ሰዎች እንዲሰበስብ  የመንግሥት ውክልና የወሰደ ሰው ለመንግሥት የገባው የውክልና ሥልጣን በአግባቡ ካልተወጣ ኃላፊነቱ ወካይና ተወካይ ሊወጡት ይገባል እንጂ በዚሁ መሀል በሕጋዊ መንገድ ግብይት አከናውኖ የተጨማሪ እሴት ታክስ በከፈለ ሕጋዊ ነጋዴ ላይ መውደቅ የለበትም፡፡ ወካይ የተባለ አንድ ሰው ተወካይ ለሚባል ሌላ ሰው ውክልና ሲሰጥ ዝም ብሎ በዘፈቀደ ከመሬት ተነሥቶ የሚሰጠው ሥልጣን መሆን የለበትም፡፡ አንድ ሥራ እንዲሠራልህ የምትወክለው ሰው ውክልናው በአግባቡ ለመወጣት ይችላል ብለህ በአቅሙና በምግባሩ የምትተማመንበት ሰው መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበሰብ ውክልና የሚሰጠው ነጋዴ በግብር ሰብሳብው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በኩል ውክልና ከመሰጠቱ በፊት መረጋገጥ ያለባቸው ሁኔታዎች መኖር አለባቸው፡፡ በተለያዩ አገሮች ያለው ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት የመመዝገብ አካሄድ ሲታይ ነፃ ከተደረጉት ውጪ የዕቃ ማቅረብ ወይም የአገልግሎት መስጠት ሥራ የሚያከናውን ሰው ሁሉ ለቫት ሰብሳቢት የመመዝገብ ሁኔታ አይታይም፡፡ ምክንያቱም ገደብ የሌለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት ምዝገባ ካለ በትክክል የንግድ ሥራ የማያከናውን ሰው የታክስ ተመላሽ ለማግኘት ብቻ ለቫት ሰብሳቢነት ሊመዘገብ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ለቫት ሰብሳቢነት የተመዘገበ ነጋዴ በበዛ ቁጥር በታክስ አስተዳደሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመጣ ስለሚችል ብርቱ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ በግዴታ ለቫት ሰብሳቢነት ለመመዝገብ ነጋዴው ቢያንስ ዓመታዊ ግብይቱ ብር 500.000 እና ከዚያ  በላይ እንዲሆን በፍላጐት የሚደረግ ደግሞ ጥብቅ የሆነ መሥፈርት ማሟላት እንዳለበት በተጨማሪ እሴት ታክስ የተለያዩ ሕጎች ላይ በግልጽ የተደነገገው፡፡ ስለዚህ በሕጋዊ መንገድ በታተመ ደረሰኝ ወይም ከማሽን በሚወጣ ደረሰኝ በትክክለኛ መንገድ ግብይት ፈጽሞ የተጨማሪ እሴት ታክስ የከፈለ ሕጋዊ ነጋዴ በመጨረሻ የሚያቀርበው የግብዓት ታክስ የማወራረድ ጥያቄ  የግብዓት ታክሱ የሰበሰበው ነጋዴ ስለጠፋ ወይም ለግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ስለማያሳውቅ የሚሉ መሰል ምክንያቶች በማቅረብ የሚዳረጉ ክልከላዎች ሕጋዊም ሆነ ፍትኃዊ አይደሉም፡፡ ሕጋዊ ነጋዴው ያለው ግዴታ በአግባቡ ግብይት ፈጽሞ በዚሁ ግብይት የከፈለው የግብዓት ታክስ በትክክለኛ ሰነድ የማወራረድ እንጂ ሽያጩ ያከናወነለት ነጋዴ የሰበሰበው የግብዓት ታክስ ለመንግሥት መክፈል አለመክፈሉ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት የለውም፡፡ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት የተመዘገበ ነጋዴ ላይ በሕጉ ላይ የተቀመጡ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መሥራት የግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት መወጣት ያለበት ግዴታ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ቫት እንዲሰበሰብ ውክልና የተሰጠው ነጋዴ በውክልናው መሠረት የሰበሰበው ቫት ለመንግሥት ካልከፈለ ተጠያቂው እሱ ራሱ እንጂ ከዚሁ ነጋዴ በሕጋዊ መንገድ ግዥ በፈጸመ ሌላ ነጋዴ ላይ መወደቅ የለበትም፡፡ በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት ተወካይ ከሆነው ነጋዴ ትክክለኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ የተቀበለ ነጋዴ በዚሁ ደረሰኝ ላይ የከፈለው የግብዓት ታክስ መንግሥትን አስገድዶ የማወራረድ ሕጋዊ መብት ያለው መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም በጽሑፋ መግቢያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የገለጽኩት የአንድ ምሁር አባባል በሕጋዊ መንገድ የተሰጠ የቫት ደረሰኝ በመንግሥት ላይ የተጻፈ ቼክ ነው ብሎ እንደተረጎመው የቫት ደረሰኙ በትክክለኛ መንገድ ተቀብሎ የግብዓት ታክስ ለማወራረድ ጥያቄ በሚያቀርብ ነጋዴ ላይ ደግሞ ጥያቄው በአግባቡ ሊመለስለት እንደሚገባ መታወቅ አለበት፡፡ እዚሁ ላይ ሌላ ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አንዳንድ  ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት ተመዝግበው የነበሩ ነጋዴዎች የንግድ ሥራቸው ሲያቆሙ በሕጋዊ መንገድ ያሳተሙት ደረሰኝ ወድያውኑ እንዲመልሱ አለመደረጉ የንግድ ሥራቸው ካቆሙ በኋላ በሕጋዊ መንገድ ያሳተሙት ደረሰኝ እየሸጡ በመንግሥት ገቢና በሕጋዊ ነጋዴው ላይ ጉዳት የሚያደርሱት ሁኔታ ስላለ በግብር ሰበሳቢው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ያለው የአሠራር ክፍተት መታረም ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...