Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከአሜሪካው የቦንድ ሽያጭ ጥፋት ምን ተማርን?

ከአሜሪካው የቦንድ ሽያጭ ጥፋት ምን ተማርን?

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም. የመሠረተ ድንጋዩ ሲጣል ታላቁ የሚሊኒየም ግድብ ተባለ፡፡ በዚህ ስያሜው ብዙ አልተጠራበትም፡፡ ግንቦት 2003 አጋማሽ ላይ የወጣው የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሎ ሰየመው፡፡

ይህ ግድብ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ታላቅም ነው፡፡ ትልቅም ታላቅም፣ የሚያደርገው ግን ከአካላዊ ግዝፈቱ፣ ከሚከሰከስበት ገንዘብ፣ ከሚያመነጨው የታቀደ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ይልቅ፣ አንድምታው ነው፡፡ ይህንን ጥቂት አፍታትተን ጠጋ ብለንም እንየው፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ የውኃ ሀብት እያላት ግን ሀብቷን ያላለማች፣ የሰማይ ዝናብ ከመጠበቅ ያልተላቀቀች፣ ውኃ እያላት የሚጠማት፣ ለም መሬት እያላት ረሃብ ያልተለያት አገር መሆኗ ተብሎ ያለቀ ነው፡፡ ረሃብን የማሸነፍ ትግላችን (ማለትም የግብርናና የኢንዱስትሪ ልማታችን) ዞሮ ዞሮ የውኃ ሀብታችንን መሠረት ከማድረግ አያመልጥም፡፡ የኢትዮጵያ የውኃ ልማት ግን ውስብስብና ፈተና ያለበት የበዛበትም ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ አገር ነች፡፡ እንዲያውም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ ይኑረን ብለው ከሚታገሉት አገሮች  አንዷ ነች፡፡ በዓባይ ወንዝ ውኃ ላይ ከሱዳንም ይልቅ የዋና ተጠቃሚነቱን ድርሻ ይዛ ያለችው ግብፅ እስካሁን ካላት ጥቅም በላይ ገና ተጨማሪ የምትፈልግ ዓባይን የራሷ ያህል እንዲያውም የራሷ ብቻ አድርጋ የምታይ አገር ሆና ኖራለች፡፡ ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ ልማት ለህልውና አደጋ ብላ ኢትዮጵያን እንደ ‹‹ጠላት›› ስትወስድ ኖራለች፡፡ የዓባይን ውኃ ጭቅጭቅ ደግሞ ዋናውን ወንዝ ዓባይን ባለመንካት ብቻ የሚላቀቁት አልነበረም፡፡ አይደለምም፡፡ የዓባይ ውኃ ጉዳይ ዓባይን የሚመግቡ በርካታ ገባር ወንዞችንም የሚመለከት ነው፡፡ የየትኞቹም ወንዞችን ውኃ መጠን መብዛትና ማነስ ከትንንሽ የመስኖ ሥራዎች የዝናብ ውኃን ከመሰብሰብ፣ ወደ መሬት ከማስረግና ከመሳሰሉት ተግባራት ጋር ሁሉ ውስብስብ ግንኙነት ያለው ነው፡፡ በዓለም ላይ የታየውና በመታየት ላይ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥረው የዝናብ መዛባት፣ እጥረትና ድርቅ የውኃ ፖለቲካን አባብሶ ኢትዮጵያን ያለ ኃጢያቷ በዳይ ማድረግ ድረስ መሄድ ይችል እንደነበር ሲታሰብ የውኃ ጉዳያችን ውስብስብነት ያስደነግጣል፡፡

ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥያቄ ሰሚ ካጣ ተገቢ ድርሻችን ራሴው በራሴ እወስዳለሁ ማለት የሚያዋጣት አልነበረም፡፡ ግብፅ በመካለኛው ምሥራቅ (ባጠቃላይ የዓረብ) አገሮች ግንኙነት መቆጣጠሪያ የሆነችበት ፖለቲካዊ ስፍራ ብቻውን ኢትዮጵያን የማልሚያ ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝና ሌላም ጫና እንዲጨመርላት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ አሁንም አልቀረም፡፡ የገንዘቡን ችግርና ጫናውን ሁሉ አልፌ እሄዳለሁ ማለት ተችሎ ቢሆን ኖሮ እንኳን፣ አቅም ከመፈተኑ በላይ በኃይል የመጠቃት አደጋው የኖረ ነው፡፡ ይህ ግምት ሳይሆን የዓይነ ቁራኛ፣ ክትትሉና ዛቻው አብሮን የቆየ ነው፡፡ የጎረቤት፣ ጠላትነትን ሲያፈላብን የጎረቤት ባለጋራነትን ከውስጥ ተቃውሞ ጋር ሲያሸራርበን የኖረውና የቆየው ይኸው ልማት የህልውና አደጋ ነው ፖሊሲ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ጀብደኝነት ኢትዮጵያ ባይከጅላትም የተጠቀሱትን አደጋዎች በሩቅ የሚያስቀር ኃይልና ጉልበት ገና አልነበራትም፡፡ የምትገባበት ተቃርኖና ፀብም ከአንድ አገር ጋር ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡

የኢትዮጵያን የውኃ ሀብት የማስክበር አቅም የፈጠረው፣ ስለዚህም የህዳሴውን ግድብ አምጦ የወለደው በአንፃራዊነት ልማትና ሰላሟ እየጠነከረ መሄድ መጀመሩ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ትልቁ ፋይዳም ይኸው ነው፡፡ የታላቅነቱ መገለጫም ዋነኛው ይኸው ነው፡፡

የህዳሴው ግድብ ይህን ያህል ታላቅነት ማስመዝገቡ ግን በቃ ‹‹ዓባይም ሞላልሽ/ያሰብሽው ሆነልሽ›› የሚያሰኝ፣ አደጋ የሌለው የማይቀለበስ አይደለም፡፡ የተፈጠረው የውኃ ሀብት መብትና የማስክበሩ አቅማችንን የሚሸረሽሩ በርካታ ተባያት የሚፈጠሩበት ሜዳና ጉድጓድ አሁንም ገና እንደለማ ነው፡፡

የትኛውም ዓይነት ብሶት፣ የፖለቲካ ፀብና የሕዝብ ቅሬታ እንደወትሮው ወደ ጠመንጃ የሚሄድበት ዕድል ሲሆን ተዘግቶ አለዚያም በጣም ጠብቦ በውይይት፣ በድርድርና በክርክር ወይም በሌላ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ ይፈታል ማለትን ዛሬም ሕጋችንና ወጋችን አላደረግንም፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ አየር ጠርቶ ትግሉ ወግና ማዕረግ ወዳለው ወደሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ‹‹ግብግብ›› አልተለወጠም፡፡ በሰላም ሊፈቱ ያልቻሉ የውስጥ ተቃውሞች ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር ተሸርቧል፡፡ የኢትዮጵያን መጠንከር ከሥጋት የሚቆጥሩት የአገሪቱን ልማት ለህልውና አደጋ ነው የሚሉ ጎረቤቶች ከዚህ ቀደም የኤርትራን ትግል በማዳከሚያነት ሲጠቀሙበት የኖሩት ሰሜናዊ የዓባይ ተጠቃሚዎች ዛሬም በዚህ ውስብስቦሽ ውስጥ ቢያንስ በስውር መሳተፋቸው የሚጠበቅና የኖርንበት ነው፡፡

የውስጥ ችግሮችን ከጎረቤት አገር ጋር ማጠላለፍ፤ አዳዲስ የአካባቢ ቅራኔ ውስጥ መክተት ተቃዋሚን ተንተርሶ የውስጥ ችግሮችን ማባባስ፣ የሃይማኖት ሰላምን ማደፍረስ ሁሉ ለዚህ አገልግሎት ሊውሉ ይችላሉ፡፡

በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይህን ያህል ታላቅ ነው፡፡ የታላቅነቱ መለኪያና መመዘኛ ደግሞ የአዲስ ለውጥና ግንባታ የአስተሳሰብና የአመለካከት እርሾ ሆኖ ባቀጣጠለው ንቃትና የተሃድሶ እንቅስቃሴ ምክንያት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ፊት የመሠረት ድንጋዩን ሲያኖሩ፣ ‹‹የህዳሴ ጉዟችን መሐንዲሶች እኛው፣ ግንበኞችና ሠራተኞች እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ ባጠቃላይ የህዳሴው ጉዟችን ባለቤት እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው፤›› ያሉትም ይህንኑ ታላቅ ግድብ ነው፡፡

ይህን ንግግር በየጊዜውና በያጋጣሚው እንሰማዋለን፡፡ መጋቢት 24 በመጣ ቁጥርም ከነጭብጨባውና እልልታው እንደ አዲስ እንሰማዋለን፡፡ እነሆ እስካሁን ያለፈው መጋቢት 2008ን አምስተኛ መታሰቢያ ጨምሮም ስድስት ጊዜ ሰምተነዋል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ባለቤቶች መሆናችን ማስረጃ ነው ማለት ከፍተኛ ትርጉምና አንድምታ ያለው አባባል ነው፡፡ አንደኛ የህዳሴውን ግድብ ታላቅነት ያልቃል፤ ታላቅነቱን ያደምቃል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአንድን የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታን ወይም ደብተርን ቦታ ያመላክታል፡፡

በመሠረቱ እንዲህ ያለ የአነጋገር ፈሊጥ መጠቀም፣ ለምሳሌ ፍርድ ቤቶች የሰብዓዊ መብቶቻችንና የመሠረታዊ ነፃነቶቻችን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተሮቻችን ናቸው ማለት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ልማድ ግን የታወቀና ሳይታለም የተፈታ የሚሆነው የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ዋጋ ሲታወቅ ነው፡፡ በመንግሥት ለአንድ ሰው የተሰጠ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት ማስረጃው የተሰጠው ሰው የዚሁ ንብረት ባለሀብት እንደሆነ የሚያስቆጥር ሲሆን ነው፡፡ በዚህም ላይ የመንግሥት ኃላፊነት ሲኖር ነው፡፡ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተሩን በማመን አንድ መብት ያገኘ ሰው ለሚደርስበት ጉዳት ኃላፊው መንግሥት ሲሆን ነው፡፡

የአቶ መለስን ውብና ድንቅ ምሳሌያዊ አነጋገርን ግን እንደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ያለ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተርን የሚያውቅና የሚያመክን ኃላፊ የማይሆን መዋቅር ሲያሽሟጥጥበት እናያለን፡፡

አቶ መለስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ባለቤቶች እኛ ኢትዮጵያውያን መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ወይም ደብተራችን ነው ያሉት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ነሐሴ 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው ከአምስት ወራት በፊት መጋቢት 2004 ዓ.ም. ላይ የህዳሴ ግድቡ መሠረት የተጣለበትን የመጀመሪያ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ምክንያት በማድረግ በጽሕፈት ቤታቸው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካይነት ከአገር ውስጥም ከውጭ አገርም የተሰባሰቡ ጥያቄዎችን እየተቀበሉ ይመልሱ ነበሩ፡፡

አቶ መለስ መልስ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከልና ለዚህ አግባብነት በጣም ትልቅ ቦታ ያላቸው ሁለቱም የቦንድን ሽያጭ የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ አቶ መለስ መጀመሪያ ቦንድ መግዛት ግዴታ ነወይ? ግዳጅ ነወይ? ሰው ከአቅሙ በላይ ቦንድ ግዛ ይባላል ወይ? ተብለው ተጠየቁ፡፡ ሁለተኛው የውጭ አገርን የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ በተለይም የቦንድ ሽያጭ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ኤምባሲዎቻችን ምን እየሠሩ እንደሆነ አምባሳደሮቻችን ውጤታማ ሥራ ሠርተው እንደሆነ ተጠይቀው መጋቢት 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ 

ለእያንዳንዱ ጉዳይ የሰጡትን መልስ እንመልከት፡፡ አቶ መለስ የመጀመሪያውን ጥያቄ ሲመልሱ መንደርደሪያ ያደረጉት የህዳሴውን ግድብ ወጪ እኛ እንችላለን ስንል ወጪውን በሙሉ የሚሸፍነው የሕዝብ መዋጮ፣ የቦንድ ሽያጭ ነው ተብሎ አለመነሳቱን፣ የዚህ ድርሻ ሲወጠንም የተወሰነው ከአሥር እስከ 20 በመቶ ያለውን ብቻ መሆኑን ከ80 በመቶና ከዚያ በላይ ያለው ወጪ ከመንግሥት በጀትና ከባንክ በሚገኝ ብድር እንዲሸፈን መወሰኑን ገልጸው ነበር፡፡ ሕዝብ በፋይናንስ ላይ እንዲሳተፍ የተፈለገው አንደኛ ቀጥታ የባለቤትነት መንፈሱና ስሜቱ እንዲዳብር፣ ሁለተኛ የቁጠባ ባህል እንዲጎለብት እንዲሁም አሥርና ሃያ በመቶ ገንዘብ ቀላል ገንዘብ እንዳልሆነ አብራርተው መልስ ሰጥተዋል፡፡

የሚገርም መልስ የሰጡበት የግዳጁ ጉዳይ ነው፡፡ ቦንድ መግዛት ግዴታ ነወይ? ቦንድ አልገዛም ማለትስ ይቻላል ወይ? የአቶ መለስን መልስ እንዳለ እናቅርበው፡፡

‹‹አንድ ሰው ቦንድ ሲገዛ ገንዘብ ነው እየቆጠበ ያለው፡፡ ለመንግሥት ዕርዳታ እየሰጠ አይደለም፡፡ ቦንድ ከገዛ በኋላ የገዛበት ገንዘብ ወይም ካፒታል ብቻ ሳይሆን ከነወለዱ ይከፈለዋል፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ባንክ እንደማስቀመጥ ያህል ነው፡፡ ቁጠባ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ይህ ቁጠባ እዚያው ሳለ ለአገር የሚጠቅም ትልቅ የልማት ሥራ ይሠራል፡፡ የግድብ ሥራ ይሠራል እንጂ ገንዘብ ከአቅሙ በላይ አዋጥቶ እንዲሰጥ የተጠየቀ የለም፡፡

ስለዚህ ከአቅማችን በላይ የሚለው ነገር ከአቅሙ በላይ መቆጠብ የሚፈለግ ሰው የለም፡፡ ከአቅሙም በላይ እንዲቆጥብ የሚጠየቅ ሰው የለም፡፡ ከአቅም በላይ እንዲቆጥቡ የሚያስገድድ ሰው ካለ እሱ የህዳሴ ግድብ አስፈጻሚ ሳይሆን የህዳሴ ግድብ ጠላት ነው፡፡

ገንዘብ አታዋጡ የሚለው ሰው መብቱ ነው፡፡ ማለት ይቻላል፡፡ የህዳሴ ግድቡን መጥላት፣ እንዳይሠራ መፈለግ ወንጀል አይደለም በራሱ፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የመሰለውን አቋም መያዝ ይችላል፡፡ የሚደግፍ ሰው ይኖራል፡፡ በጣም የሚበዛው ሰው ይደግፋል፡፡ በጣም የሚበዛው ሰው ይደግፋል ማለት ይህንን የሚቃወም ወንጀለኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚቃወም ሰው ቢቃወም መብቱ ነው፡፡ መብት የሌለው የመንግሥት ሠራተኛና ሌላውን ዜጋ ማስገደድ ከተጀመረ ነው፡፡ የማስገደድ መብት ያለው ሰው የለም፡፡ እሱ ወንጀል ይሆናል፡፡››

ይህ መጋቢት 2004 ዓ.ም. የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት አንደኛ ዓመት ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተናገሩት የቦንድ መግዛትን፣ በግድቡ የገንዘብ ማሰባሰብ አሠራር ላይ ሐሳብን መግለጽን የሚመለከት ጉዳይ ላይ የሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡ አንዳንዴ አሁን ይኼንን እንኳንስ መልሰው ሊናገሩት ሊሰሙትስ አያስደነግጥም? ያሰኛል፡፡

ይህን የመሰለ የተፍታታ፣ የተብራራና የቦንድ ሽያጭ ጉዳይ የሕጋዊነት ወግ እንኳን ማክበር አቅቶን በጉዳችን ሲያወጣን የሰማነውና ያየነው አሜሪካ ውስጥ የአገሪቱ የገንዘብ ሰነዶችና የግብይት ኮሚሽን ሰኔ 1 ቀን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ኮሚሽኑ የገንዘብ ሰነዶችን ዝውውር የሚቆጣጠር እንዲሁም እነዚህን ሰነዶችን የሚገዙ ኢንቨስተሮችን ከተገቢ ያልሆነ አሠራር የሚጠብቅ ነፃና ከፊል የዳኝነት ተቋም ነው፡፡

ይህ ኮሚሽን በደረሰበት፣ ባረጋገጠውና በጉዳዩ ላይ መልስ ሰጪ ሆኖ የተጠየቀው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ባመነው የፍሬ ነገር ዝርዝር መሠረት፣

  • የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በኮሚሽኑ ያልተመዘገበ፣ ለመመዝገብም የሕግ ፈቃድ ያልተሰጠው የቦንድ ሽያጭ ገበያ አካሂዷል፡፡ በዚህም የአገሪቷን የፋይናንስ ሰነዶች ሕግ ጥሷል፡፡
  • ከ3,100 በላይ የሆኑ የአሜሪካ ነዋሪዎች ከባለ አምስት እስከ ባለ አሥር ሺሕ ዶላር ዋጋ ያላቸው በነፍስ ወከፍ ኢንቨስተር (ቦንድ ግዢ) አንፃር ከ50 ዶላር እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቦንድ ገዝተዋል፡፡ በድምሩ የ5.8 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ገዝተዋል፡፡

ኮሚሽኑ እንዲህ ያለው ተግባር መጀመሪያ ፈቃድ ማግኘትና መመዝገብ የነበረበት መሆኑን፣ እንዲሁም ከመመዝገብና ፈቃድ ከማግኘት ነፃ የሚያደርገው ሕግ አለመኖሩን አረጋግጦ፣ ድርጊቱም ሕገወጥ መሆኑን ወስኖ መልስ ሰጭው (የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል) ድርጊቱን እንዲያቆምና ከዚህ በኋላም ከተግባሩ እንዲከለከል አዞ፣ የሰበሰበውን ገንዘብ 5.8 ሚሊዮን ዶላርና የዚህን የቅድመ ውሳኔ ወለድ በጠቅላላው 6.4 ሚሊዮን ዶላር መልሶ እንዲከፍል ወሰነ፡፡ የዚህ ውሳኔ ኮፒ ለእያንዳንዱ ቦንድ ገዢ እንዲደረሰው አዞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዚህ በተጨማሪ የዚህን ውሳኔ አፈጻጸም የሚከታተለውን አስተዳዳሪ ወጭ፣ የሙያ አገልግሎቶችን ወጪና ኪሳራ፣ የታክስ ግዴታዎችን ሁሉ እንዲወጣ አዟል፡፡

አሜሪካ ሄደን፣ ይህን የመሰለ ‹‹አተርፍ ባይ አጉዳይ›› ውስጥ የገባነው ለምንድነው? ባለማወቅ ነው? በግዴለሽነት ነው? ወይስ አንዳንዶች እንደሚሉት እንደ አገር ቤት ውስጥ ሳይጠየቁ መቅረት እዚያም የሚችል መስሎን ነው?

መጋቢት 2004 ዓ.ም. የታላቁ የህዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት የመጀመሪያው ዓመት ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ከሰጡበት ጉዳዮች መካከል አንዱና ሌላው ይህን የሚመለከት ነበር፡፡

አስቀድመን ጥያቄው እንዴት እንደተነሳ እንይ፡፡ ጥያቄው የተነሳው የውጭ አገር የገንዘብ አሰባሰባችን ሕግን የተከተለ ነወይ? እዚያ ሄደው ደግሞ ጉድ እንዳይሠሩን? እንዳያዋርዱን? ተብሎ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡

ጥያቄው ለአቶ መለስ የቀረበው እንደ አገር ቤቱ የቦንድ ሽያጩ ውጭ አገርም ተፈጽሟል ወይ? በውጭ አገር የግድቡን መሠራት የሚቃወሙትን የሚቋቋም አቻና የበለጠ ሥራ እየተሠራ ነወይ? ተብለው ነው፡፡

አቶ መለስ ግድቡን መቃወም ስህተት መሆኑን ገልጸው ማብራሪያቸውን ቀጠሉ፡፡ የግድቡን ሥራ መቃወም ስህተት ነው ማለት ግን መቃወም ወንጀል ነው ማለት አይደለም፡፡ ማንኛውንም ነገር የመቃወም መብት ዜጋው አለው ማለት ግን ያ አቋም ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህ ግድብ የአንድ ፓርቲና የአንድ መንግሥት ግድብ አይደለም፡፡ የአገር ነው አሉ፡፡

በዚህ ረገድ አቶ መለስ በ2004 ያነሱት ችግር፣ የውጭ አገሩ የገንዘብ ማዋጣት ሥራ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ላይ ውሱንነት የነበረበት መሆኑን ገልጸው፣ የቅድመ ዝግጅቱ ሥራ አንዳንድ አካባቢ በጣም የተወሳሰበ እንደሆነ አስረዱ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ከአሜሪካ ገንዘቡን ለማውጣት የራሱ በጣም የተወሳሰበ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ዝግጅት መሥራት የራሱ ጊዜ የሚጠይቅ ስለነበር ዘግይቶ ነው የተጀመረው፤›› ብለው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የቦንድ ሽያጭም ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ በተሰጠበት መዝገብ ከተጠቀሱት ኢትዮጵያ ካቀረበቻቸው ሰነዶች መካከል አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ማብራሪያ የተባለው ሰነድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 2003 ዓ.ም. ያወጣው መመርያና ማብራሪያ ነው፡፡ እንደተባለው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ‹‹ቅድመ ዝግጅት›› የተደረገበት ጉዳይ እንኳንስ ገንዘቡን ከአሜሪካ ለማውጣት ‹‹የራሱን በጣም የተወሳሰበ ሥራ መሥራት›› የሚጠይቀውን ጉዳይ አሜሪካ ውስጥ ፍቃድ ማስፈለጉን አስፈላጊነቱን ያገናዘበ ዝግጅት አለመኖሩ ለሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ ዳርጎናል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ታላቅነት ከአካላዊ ግዝፈቱና ከሚያመነጨው የኃይል መጠን በላይ ነው ብለናል፡፡ ይህን የመሰለ ከህልውናችን ጋር የተያያዘ ሁሉም የሰላም፣ የልማት፣ የደኅንነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አንድ ላይ የተፈተሉበትና የተገመዱበት ጉዳይ የሕጋዊነትና የሕግ የበላይነት ጉዳይ ሲመጣ እሱን አይመለከተውም አላልንም፡፡ ገንዘብ አላዋጣም ማለት ብቻ ሳይሆን ገንዘብ አታዋጡ ማለት መብት ነው ያልንበት ጉዳይ የህዳሴውን ግድብ መጥላት፣ እንዳይሠራ መፈለግ፣ በራሱ ወንጀል አይደለም፣ መቃወም መብት ነው፡፡ መብት የሌለው ሌላውን ዜጋ በግድ ክፈል ብሎ የሚያስገድድ የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ መፍራትስ ማስገደድ ሲጀመር ነው ብለን የመብትንና የነፃነትን ማዕቀፍ ልክን መልክ ከነውበቱ የገለጽንበት ጉዳይም ከሕግ በታች ነው፡፡ ከሕግ በላይ የሚሆን ሰውም ጉዳይም የለንም፡፡ የህዳሴው ግድብ እንኳን ከሕግ በላይ ይሁን አላልንም፡፡

የኢትዮጵያ ችግር ዋስትና የሚሰጥ ሕግ አለመኖር አይደለም፡፡ መንግሥት፣ ፓርቲዎችና ሹሞች ከሕግ በላይ ሆነው መገኘታቸውና አለመጠየቃቸው ነው፡፡ ዋናው ዋስትናም ያለው ሕግ ማውጣቱ ላይ ብቻ ሳይሆን መንግሥት፣ ፓርቲዎችና ባለሥልጣኖቹ ከሕግ በላይ የማይሆኑበትን የትኛውንም ጉዳይ ከሕግ በላይ የማያደርጉበት ሆነውና አድርገው ሲገኙ ደግሞ የሚጠየቁበትን አሠራር ማልማት ነው፡፡ እንደ አሜሪካ ሕመማችን በሰው ፊት የሚጋለጥበትን ሥርዓት ማደላደል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...