Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የዴሞክራሲ ተቋማት ከመንግሥት ጋር ሌባና ፖሊስ ከሚጫወቱ በአጋርነት ቢሠሩ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣሉ››

አቶ ይበቃል ግዛው፣ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

አቶ ይበቃል ግዛው የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (የቀድሞ ፍትሕ ሚኒስቴር) ባለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አጠናቀዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሰብዓዊ መብት ላይ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲና የኔዘርላንዱ አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በጋራ ከሚሰጡት ፕሮግራም ጨርሰዋል፡፡ ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ሥራ ላይ የነበረው የመጀመሪያው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ቀጣይ ክፍል ረቂቅ በቅርቡ ለውይይት ቀርቧል፡፡ ይህ የድርጊት መርሐ ግብር የተያዘው የበጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይሁኝታ አግኝቶ በፓርላማው እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ሰለሞን ጐሹ የድርጊት መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ላይ ሊኖረው ስለሚችሉ አስተዋጽኦና ተዛማጅ ጉዳዮች አቶ ይበቃልን አነጋግሯቸዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያው የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብርና በሁለተኛው መካከል ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው?

አቶ ይበቃል፡- የመጀመሪያው በዓይነቱ ለየት ያለ ነበር፡፡ በተለይ አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከጀመርንበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠሩ የነበሩ የሰብዓዊ መብት የማስከበር ሥራዎችን፣ ያስገኛቸውን ውጤቶች፣ የነበሩ ክፍተቶችን ሁሉ በመቃኘት የተሠራ መርሐ ግብር ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ተዘጋጅቶ ስናስፈጽመው ቆይተናል፡፡ የማስፈጸም ሒደቱም ራሱን የቻለ ጠንካራ ጎንና ክፍተቶች ነበሩት፡፡ ሁለተኛውን የድርጊት መርሐ ግብር ስናዘጋጅ እነዚህን በድጋሜ ፈትሸናል፡፡ እንደ አዲስ አጢነን ልናካታቸው የሚገቡ ነገሮችንም አካተናል፡፡ ሌሎች ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ለሁለተኛው መርሐ ግብር ዋነኛ መነሻው የመጀመሪያው ነው፡፡ ስለዚህ ትልቅ የሽግግር መሣሪያ ሆኖናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ባሉ ጊዜያት ሰብዓዊ መብት በሕግ ማዕቀፍ፣ በተቋማት ግንባታና ባህል ከማድረግ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ለመቀየር የተደረገው ጥረት የሚታይ ቢሆንም፣ በአፈጻጸም ረገድ ግን ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ ቅሬታዎች ከተለያዩ አካላት ይመጣሉ፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩን ስትቀርጹ ያገኛችሁት የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ይዞታ ምን ይመስላል?

አቶ ይበቃል፡- ከ1983 ዓ.ም. በፊት የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰፊና ሥርዓታዊ የሆነ ነበር፡፡ የነበሩት ሥርዓቶችም በምንም መልኩ ሰብዓዊ መብትን የማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማረጋገጥ አጀንዳ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ግን ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና ሰፊ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ ተሠርቷል፡፡ በተለይ በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዋነኛ  መመርያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ በዚህም ሰፊ ለውጦች መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ፍፁማዊ የሆነ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚረጋገጥ ጉዳይ በባህርይው በየትኛውም የዓለም አገር ተከናውኖ የሚጠናቀቅ ተግባር አይደለም፡፡ ሁልጊዜ በሒደት እየተጠናከረ የሚሄድ ነው፡፡ እንኳን እኛ የዛሬ 25 ዓመት ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ለመገንባት መጣር የጀመርን አገሮች ይቅርና፣ ላለፉት ሁለትና ሦስት መቶ ዓመታት ሰብዓዊ መብትን እንደ መርህ ይዘው ይንቀሳቀሱ ነበር የምንላቸው አገሮች እንኳን ዛሬም ድረስ የሰብዓዊ መብት ክፍተቶች አሏቸው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት ለውጥ መጥቷል ወይ? ነው እንጂ ተከብረው አልቀዋል ወይ? ብሎ መጠየቅ አያስኬድም፡፡ በእኛ ግምገማና አብዛኛው ዓለምም የሚስማማበት በእነዚህ ዓመታት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር ሰፊ ርቀት ተሂዷል፡፡ የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር ተጨማሪ ርቀት ወስዶናል፡፡ ሁለተኛውና ቀጣዮቹም የራሳቸውን እሴት መጨመራቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ በየጊዜው እየጠነከረ የሚሄድ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ እንድኖር ነው ማድረግ የሚቻለው፡፡   

ሪፖርተር፡- መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ዕውቅና ተሰጥቷቸውና ጥበቃ የሚያደርጉ ተቋማትም ተቋቁመው ሥራ ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር እነዚህ ተቋማት ተቀናጅተው ሰብዓዊ መብት ጋር ስምሙ የሆነ የመንግሥት አሠራርና ቁርጠኛ የሆኑ ሠራተኞችን ለመፍጠር ያለመ ነበር፡፡ የሦስት ዓመት ልምዳችሁ እነዚህን ነገሮች ለማረጋገጥ ባደረጋችሁት ጥረት የምትጠብቁትን ድጋፍ አገኛችሁ ወይስ ተቃውሞ ገጠማችሁ?

አቶ ይበቃል፡- ተቃውሞ አላየንም፡፡ የቀደመው የድርጊት መርሐ ግብር በሚዘጋጅበትም ሒደት ቢሆን እንደ ተቋም ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት ሰፊ ተሳትፎ አድርገውበታል፡፡ ስለዚህ የባለቤትነት ስሜቱ በመንግሥት ቁርጠኝነት ብቻ ከላይ ተንጠልጥሎ የሚቀር አይደለም፡፡ በሁሉም ፈጻሚ ተቋማት ዘንድ ሰፊ የሆነ የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን የድርጊት መርሐ ግብሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀረጸ እንደመሆኑ በአፈጻጸም ሒደት የሚፈጠሩ በርካታ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የነበሩ ተቋማዊ አደረጃጀቶች ሥራውን ለማራመድ ምን ያህል ብቁ ናቸው? እኛስ እንደማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በድርጊት መርሐ ግብሩ ዙሪያ ምን ያህል ግንዛቤን የማዳበር ሥራ ሠርተናል? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ መንግሥት ለሰብዓዊ መብት መከበር ቁርጠኝነት አለው፡፡ ይህንን ቁርጠኝነት በሁሉም ደረጃዎች የማባዛት ሥራና ግንዛቤ የማዳበር ሥራዎች በሰፊው ይቀጥላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ሁለተኛው የድርጊት መርሐ ግብር ረቂቅ ለባለድርሻ አካላት ውይይት ቀርቧል፡፡ ሰነዱ ስለመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር ባቀረበው ግምገማ የመንግሥት ቁርጠኝነት ይበልጥ መጎልበቱንና በሒደቱም ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች መገኘታቸውን ይዘረዝራል፡፡ ሌሎች በርካታ አካላት በተለይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ይህን ድምዳሜ ይቃወማሉ፡፡ በተለይ ለሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ያለው አያያዝ መንግሥትን ያስተቸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ መንግሥት ያለው ቁርጠኝነት አፋዊ እንጂ በተግባር የተደገፈ ስላልሆነ አፈና ይፈጽማል የሚሉ ሪፖርቶችን ማንበብ የተለመደ ነው፡፡ እነዚህን የተራራቁ ግምገማዎች እንዴት አያችኋቸው?

አቶ ይበቃል፡- ከውጭ የሚቀርቡ ተቃውሞና ጥርጣሬዎችን መነሻ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከውስጥ ካሉ አካላትም ቢሆን የሚነሳው ተቃውሞ መነሻን ምክንያት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አፈጻጸሙን የሚገመግምበትን አግባብ ከዚህ አንፃር ማየት ያስፈልጋል፡፡ አጠቃላይ ምዘናው የሚያሳየው ነገር በጣም ሰፊ መሻሻል የተመዘገበ መሆኑን ነው፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩ ስለተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና መስፈን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሠራ ነው፡፡ ባህል ነው እየገነባን ያለነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማክበር ባህል ሲሆን ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ትልቅ ዋስትና ነው፡፡ ይህን ባህል የመፍጠር ጉዳይ ግን በአንድ ምሽት ተከናውኖ የሚጠናቀቅ ተግባር አይደለም፡፡ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ልክ እንደ ኢኮኖሚያችን ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን ስንመለከተው የዛሬ አሥር ዓመት ከነበርንበት ይልቅ የተሻለ አገራዊ የኢኮኖሚ አቅም ላይ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን ሀብታም አገር ሆናለች? አልሆነችም፡፡ ሰብዓዊ መብትም ልክ እንደ ኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁሉ በጊዜ ሒደትና በተከታታይ ጥረት የሚሻሻል ነው፡፡ መንግሥት ሰብዓዊ መብትን አስከብሬ ጨርሻለሁ አይልም፡፡ መንግሥት ችግሮች ሲኖሩ ይቀበላል፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ ተለፍቶና ተጥሮ የተገኙ ስኬቶች ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ መንግሥትን የሚተቹ አንዳንድ አካላት ደግሞ ፍፁም ፀለምተኝነት የተጠናወታቸውና በአንድ ወይም በሌላ የፖለቲካ አጀንዳ መነሻነት ምንም ዓይነት ጥሩ ሥራ ቢሠራ ዕውቅና የማይሰጡ ናቸው፡፡ መሻሻሎች ቢኖሩም በቂ አለመሆናቸው ሁላችንንም ያግባባል፡፡

ሌላው መንግሥት ለሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ያነሰ ትኩረት ይሰጣል የሚለው በየትኛውም የፖሊሲ ሰነድ ውስጥ አይታይም፡፡ በአተገባበርም ይህ ልዩነት አይታይም፡፡ በተለይ በቅርብ ጊዜ መንግሥት በተያያዘው የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ሰፊ ትኩረት ተሰጥቷቸው በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እርግጥ የሕዝብን እርካታ ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ ርቀት በሚፈለገው መጠን አልሄደም የሚል ግምገማ ከተደረገባቸው አንዱ የፍትሕ ሥርዓቱ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በአብዛኛው የሚያከናውናቸው ሥራዎች ከሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ እዚህ መዋቅር ውስጥ ክፍተት አለ ስንል እንዴ ሌሎቹ የመንግሥት የሥራ ዘርፎች ሁሉ እኩል ትኩረት ተሰጥቶት መንቀሳቀስ ይገባዋል የሚል ዕውቅና በመንግሥት ውስጥ እንዳለ ማየት ይገባል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ያነሰ ትኩረት ይሰጣል የሚለውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ትግበራዎች አያንፀባርቁትም፡፡ እንደ አገር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የምናደርገው ጥረት ሁለንተናዊ ነው፡፡ ሁሉንም መብቶች በእኩል ወስዶ ለማሻሻል ሰፊ ትኩረትና ጥረት እየተደረገ ነው ያለው፡፡     

ሪፖርተር፡- ከዚህ የመንግሥት አቋም በተቃራኒ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዋነኛ መገለጫ የሆኑትን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የመቃወምና ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ፣ አቤቱታ የማቅረብ መብቶች ይዞታዎች ላይ አንፃራዊ ጥናት በማቅረብ ባለፉት አሥር ዓመታት እንዳሽቆለቆሉ የሚሞግቱ አሉ፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ ይበቃል፡- ዕይታችን እንደምንነሳበት የፖለቲካ አቋም ይለያያል፡፡ እስካሁን ድረስ የተመዘገቡት ስኬቶች ሁለንተናዊ ናቸው ብለን እንወስዳለን፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ወይም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቀደም ሲል ከነበረበት ተሻሽሏል ወይስ አልተሻሻለም የሚለውን መመዘኑ በጣም ቀላል ነው፡፡ እናንተም ነፃ ሚዲያ ሆናችሁ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ የምትፈልጉትን አጀንዳ እየሸፈናችሁ፣ የትኛውም የመንግሥት ተቋም ውስጥ ገብቶ የሕዝብን መረጃ የማግኘት መብት ለማሟላት በነፃነት እየተንቀሳቀሳችሁ ነው ብለን እንወስዳለን፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኝነት ከሕግ ተጠያቂነት ነፃ አይደለም፡፡ ዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ አንዳቸው የሌላውን መብት እንዳይጥሱ መቆጣጠር የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ሕግም ቢሆን የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሙያውን ሽፋን በማድረግ ሽብረተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፍ የፕሬስ ነፃነት ነው ብለህ ዝም የምትል ከሆነ ራስህ ሰብዓዊ መብት እየጣስክ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ችግር የሚሆነው ሙያዊ ነፃነታቸው ተጠብቆና አስፈላጊው ምህዳር ተፈጥሮላቸው በነፃነት የሚሠሩ ሰዎች ገደብ ሲደረግባቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይም ይኼው ነው፡፡ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመደራጀት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ፡፡ በመሠረቱ እውነተኛ የሆነ መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት አለ፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ የማድረግ መብት ግን ልቅ ተደርጎ ለሌሎች መብቶች መጣስና ለሌሎች ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቅ፣ የአገር አንድነትን አደጋ ላይ ለመጣል መሣሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ እንዲውል መፍቀድ ተገቢ አይሆንም፡፡ ከተፈቀደ ያው የመብት ጥሰት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሚዛኑን መጠበቅ የግድ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ በተለይ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ላይ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን እነዚህ ተቋማት ባለፉት ሁለት አሥር ዓመታት አደረጃጀታቸው እንጂ ነፃነታቸው ላይ ለውጥ አላሳዩም በሚል ይወቀሳሉ፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች መንግሥትን ሞጋች ለምን አልሆኑም?

አቶ ይበቃል፡- ይኼ ጉዳይ በተለይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ይመለከታል፡፡ ተቋማቱ ምን ያህል ገለልተኛ ናቸው? የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ ወይስ የለም? የሚለውን ለመመለስ አልችልም፡፡ ይህን ተቋማቱ ራሳቸው ቢመልሱት የተሻለ ነው፡፡ ይበልጥም ተዓማኒ ይሆናል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ከመንግሥት ጋር ሌባና ፖሊስ ከሚጫወቱ በአጋርነት ቢሠሩ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ የሁለቱም ዓላማ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መተግበር ነው፡፡ ስለዚህ በትብብር ቢሠሩ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ደግሞ መሠራት አለበት፡፡ ነፃነትና ገለልተኝነት የሚመጣው እዚህ ጋር ነው፡፡ አንድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊያደርግ የሚገባውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እየተወጣ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ማሳያው ቀላል ነው፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩን ስናዘጋጅ እዚህ አገር ምን ዓይነት የሰብዓዊ መብት ክፍተት አለ የሚለውን ስንመለከት በተለይ ከሲቪልና ፖለቲካ መብቶች አንፃር በዋናነት ከወሰድናቸው ግብዓቶች መካከል የምንጠቅሰው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርቶችን ነው፡፡ ክፍተቶችን በደንብ ያሳያሉ፡፡ የፖሊሲ ጣቢያ ሪፖርቶችና የማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርቶች ግልጽ በሆነ መንገድ ዕውቅና የሚሰጠውን ሥራ ይሰጣሉ፡፡ ክፍተት ያለበትንም ክፍተት ብለው መዝግበዋል፡፡ ሪፖርቶቹ ለማንም ክፍት ናቸው፡፡ በማረሚያ ቤቶች ወይም በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ያስመዘገብናቸው መሻሻሎች በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡ በሌላ በኩል ተገቢ በሆነ ጥራት ምግብ የማይቀርብባቸው አካባቢዎች ተጠቅሰዋል፡፡ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ሥነ ምግባር በጎደለው የፖሊስ ወይም የማረሚያ ቤት መኮንን የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ተካቷል፡፡ ነፃነትና ገለልተኝነት በዚህ ነው የሚገለጸው፡፡ ክትትልና ቁጥጥርም መገለጫው ይህ ነው፡፡ ሌላም አገር የሚደረገው ይኸው ነው፡፡ ስለዚህ ጠላትነትና ፍጥጫ አይጠቅምም፡፡    

ሪፖርተር፡- ነገር ግን የነፃነትና ገለልተኝነት ሌሎች መገለጫዎችም አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜያት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይ በኦሮሚያ የተለያዩ ግጭቶች ነበሩ፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ስለመፈጸማቸው የተለያዩ ሪፖርቶች አመልክተዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ገለልተኛ ሪፖርት ወዲያው መቅረብ ነበረበት በማለት ይተቻሉ፡፡ አልፎ አልፎም ከተቋማቱ ሪፖርት ይልቅ የዓቃቤ ሕግ ክሶች ቀድመው ፍርድ ቤት ይደርሳሉ፡፡

አቶ ይበቃል፡- የማጣራት ተግባር ማከናወን ሲገባቸው ካላከናወኑ ችግር በመሆኑ መነጋገር ይገባል፡፡ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ የነበሩ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ጋር ተያይዞ ባለኝ መረጃ ኮሚሽኑ የማጣራት ተግባር ሲያከናውን ነበር፡፡ ሪፖርቱ ዘግይቷል ወይ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ መዘግየት ግን የነፃነትና የገለልተኝነት አለመኖርን አያሳይም፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፖርቱ በዘገየ ቁጥር ለአስፈጻሚ አካሉ ጣልቃ ገብነት የመጋለጥ ዕድሉ ይሰፋል ተብሎ ይገመታል፡፡

አቶ ይበቃል፡- መዘግየቱ እኮ እንደ ጥሩ ነገር አይወሰድም፡፡ አንድ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ የሚያስነሳ ድርጊት ካለ እነዚህ ገለልተኛ ተቋማት ማጣራት አለባቸው፡፡ ሪፖርቱም በወቅቱ መውጣት አለበት፡፡ መዘግየቱ ከምን ጋር የተያያዘ እንደሆነ መልሱን ለኮሚሽኑ እተዋለሁ፡፡ ነገር ግን በርካታ ከግንዛቤ ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ የሎጅስቲክስ ጉዳዮች፣ ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ የድርጊቶቹ ስፋት ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የድርጊት መርሐ ግብሩ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶች መካከል አንኳር የሆኑት በተቀናጀ መልኩ የሚፈጸሙበትን መንገድ ያስቀምጣል፡፡ ፈጻሚ አካላት፣ የሚወሰዱ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎችም ተቀምጠዋል፡፡ ይህ አሠራር ከመጀመሪያው አንፃር ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል?

አቶ ይበቃል፡- አብዛኞቹ ሥራዎች በድርጊት መርሐ ግብሩ እንዲፈጽሙት የሚሰጧቸው የመንግሥት አካላት ተፈጥሯዊ ግዴታዎች ናቸው፡፡ ተቋማቱ ሲቋቋሙ እንዲያስፈጽሟቸው የሚጠበቁ ሥራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች በተሻለ እንዲፈጸሙ ለማድረግ መርሐ ግብሩ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ስለዚህ እጅግ አብዛኛዎቹ ሥራዎች የተወሰነ ርቀት ተጉዘዋል፡፡ በሦስት ዓመት ሥራዎች መሻሻሎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሥራዎች ደግሞ በባህርያቸው መቼም ሠርተህ አትጨርሳቸውም፡፡ ለምሳሌ ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠርና ኅብረተሰቡ ስለ ሰብዓዊ መብት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ዘለዓለማዊ ሥራ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ በቁጥር የሚገለጹ ድርጊቶችም አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ይህን ያህል በመቶ እፈጽማለሁ ብለህ የምታስቀምጣቸው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ይህ ያህል አገልግሎቶችን ተደራሽ እናደርጋለን፣ ጤና ጣቢያ እንገነባለን፣ በሚል ቅኝት የሚቀመጡ ናቸው፡፡ አሁን አዲስ የተቀረጸው የድርጊት መርሐ ግብር በጊዜ እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡ ይኼ በኋላ የቁጥጥርና የግምገማ ሥራ ስንሠራ እያንዳንዱ ተቋም በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ርቀት ሄዶበታል የሚለውን ለማየት ይጠቅመናል፡፡   

ሪፖርተር፡- የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በብዙዎች በጣም የተለጠጠ ነው በሚል ይወቀሳል፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩ ለተቋማቱ የሰጠው ሥራ አቅምንና የሚፈጸም ግብን ያገናዘበ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ይበቃል፡- እንደ አርቃቂ ቡድን ቆጥቦ ማቀድ ያስኬዳለ ብለን አንወስድም፡፡ ለጥጠን ማቀድ አሰብን፡፡ በማደግ ላይ ያለን አገር እንደመሆናችን በየጊዜው ተጨማሪ ኃላፊነቶችን እየወሰድን መሄድ አለብን፡፡ የማስፈጸም አቅማችንም የዚያኑ ያህል በየጊዜው እያደገ መሄድ አለበት፡፡ ነገር ግን ሊፈጸም የማይችል ነገር ማቀድ ደግሞ ችግር ነው፡፡ ዕቅዱ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ የሕግ ማዕቀፎችን፣ የተቋሙን ሪከርድ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርትን ጨምሮ በቂ ጥናት ይደረጋል፡፡ ረቂቁ ከተዘጋጁም በኋላ ከፈጻሚ አካላቱ ጋር ምክክር ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ቀድመው ግብዓት ይሰጣሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- እውነታው ምንም ይሁን በበርካታ አካላት ያለው ዕይታ ግን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ግድ የሌለው ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው የተያዘው ግንዛቤ አላቸው በሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ መንግሥት አሉታዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች አሳምኖ የሰብዓዊ መብት ይዞታን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት አካል ለማድረግ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ይበቃል፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ላይ ሊያዙ የሚችሉ አቋሞች የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥት የሠራውን ሥራም በአግባቡ ሸጧል ብዬ አልወስድም፡፡ የፈረምናቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አፈጻጸም ሪፖርት ልናደርግ ስንሄድ አንዳንድ አካላት ይህን ከሠራችሁ ለምን አልነገራችሁንም በሚል ይገረማሉ፡፡ በሌላ በኩል ምንም ብታደርግ በጎ የሆነ ነገር ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነ ወገን አለ፡፡ እርግጥ ይኼ ወገን በጣም ጥቂት ነው፡፡ የገፅታ ግንባታህ ላይ ግን የራሱን ጥላ የማጥላት አቅም አለው፡፡ የተሠሩ ሥራዎች በአግባቡ እንዲታወቁ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች አሉ፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩም አንድ ታሳቢ አድርጎ የሚነሳው ነገር የተሠሩ ሥራዎች በአግባቡ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለተኛው የድርጊት መርሐ ግብር ሲጠናቀቅ ከአራት ዓመት በኋላ የሰብዓዊ መብት ይዞታ የት ይደርሳል?

አቶ ይበቃል፡- በእርግጠኝነት ረጅም ርቀት ይወስደናል፡፡ በዓለም ላይ ካሉ ሰፊ የድርጊት መርሐ ግብሮች አንዱ ነው፡፡ 23 ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አካተናል፡፡ በጣም በዝርዝር ነው የቀረቡት፡፡ ሰፊ የሆነ ቁርጠኝነት የተወሰደበት ነው፡፡ መንግሥት፣ የልማት አጋሮች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ በትብብር ከተንቀሳቀሰ መፈጸም ይቻላል፡፡ ይህን የምናደርግ ከሆነ ከአራት ዓመት በኋላ አሁን ካለንበት ይበልጥ የተሻለ የሰብዓዊ መብት ይዞታና አያያዝ ላይ እንደርሳለን፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...