Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሚኒስትሮች ምክር ቤት የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብርን ሊያፀድቅ ነው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብርን ሊያፀድቅ ነው

ቀን:

– ታራሚዎች ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ለብቻቸው እንዲገናኙ ለማድረግ ጥናት ይደረጋል

ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነው ሁለተኛው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር በቀጣዩ ሳምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ምንጮች ገለጹ፡፡

የድርጊት መርሐ ግብሩ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር አብሮ መጽደቅ የነበረበት ቢሆንም፣ ረቂቁ ተጠናቆ ለባለድርሻ አካላት ውይይት ይፋ የሆነው በቅርቡ ነው፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዘጋጀውን የድርጊት መርሐ ግብር ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በማፅደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚልከውና ፓርላማውም ሰኔ 30 ቀን ለዕረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የድርጊት መርሐ ግብሩ ያስፈለገበት ምክንያት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አተገባበር ይበልጥ እየተጠናከረና እያደገ የሚሄድበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሆነ የድርጊት መርሐ ግብሩ መግቢያ ይገልጻል፡፡

ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ በሕይወት የመኖር መብትን ለቀጣይ አምስት ዓመታት ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ ከተቀመጡት የድርጊት መርሐ ግብሮች መካከል አንዱ በፖሊስና ማረሚያ ቤት አባላት የኃይል አጠቃቀምና የተጠያቂነት ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል፡፡ በሕግ ማዕቀፉ ላይም ሁሉም ፖሊስና ማረሚያ ቤት አባላት የሥራ ላይና የቅድመ ሥራ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እንደሚደረግ አስፈጻሚዎቹም ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ሁሉም የፖሊስ ኮሚሽን አባላትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንደሚሆኑ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

የግድያ ወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ ለማድረግ አዋጅ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ፣ ለሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች አማካይ በሆኑ ስፍራዎች የአስክሬን ምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንደሚደራጁ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

የአካል ደኅንነት መብትና የኢሰብዓዊ አያያዝ ክልከላ መብትን ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ በድርጊት መርሐ ግብሩ ዘመን ከታቀዱት መካከል ሁሉም የወንጀል ምርመራ ስፍራዎች አካላዊ ጥቃት ለማድረስ ከሚያስችሉ ቁሳቁሶች የፀዱ እንዲሆኑ እንደሚደረግ፣ በወንጀል ምርመራ ሒደት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለወንጀል ምርመራው ውጤታማነት ከቤተሰብ፣ ከሕግ አማካሪዎቻቸው፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸው፣ ወይም ከማንኛውም ሌላ ሰው ጋር በአካል ወይም በሌላ መንገድ ለተወሰነ ጊዜ እንዳይገናኙ የሚደረግበት አግባብ የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይገልጻል፡፡

የተያዙ በቁጥጥር ሥር የዋሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብትን ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ ከተቀመጡት የድርጊት መርሐ ግብሮች መካከል በወንጀል ምርመራ ሒደት ለምርመራው ውጤታማነትና የሌሎች ተጠርጣሪዎችን መብትና ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር ተጠርጣሪ ለብቻው ተለይቶ የሚታሰርበት አግባብ የሚደነግግ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የቅድመ ፍርድ ጊዜን ለማሳጠር ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የወንጀል ምርመራ የሚጠናቀቅበት ጊዜ የሚወስን ሕግ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግም እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ወጣት ጥፋተኞችን፣ ቅድመ ፍርድ እስረኞችን፣ የአዕምሮ ሕመምተኞችን፣ ፍርደኞችን ለያይቶ ለማቆየት የሚያስችሉ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ይገልጻል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ማረሚያ ቤቶች በሁሉም የሳምንት ቀናት ታራሚዎች በቤተሰቦቻቸው፣ በጓደኞቻቸው፣ በሕግና ሃይማኖት አማካሪዎቻቸው ወዘተ እንዲጎበኙ እንደሚደረግ፣ በማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ለብቻቸው የሚገናኙበት (Conjugal Visit) የአሠራር ሥርዓትን በተመለከተ ጥናት እንደሚደረግ በረቂቅ የድርጊት መርሐ ግብር ሰነዱ ላይ ሰፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...