Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ባለቤት የሆኑ የቱርክ ኩባንያዎች በጥጥ እርሻ ልማት እየገቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ የቱርክ ኩባንያዎች፣ ኢንቨስትመንታቸውን በማስፋት በጥጥ ልማት ዘርፍ እየገቡ ነው፡፡ በጥጥ ልማት ከተሰማሩ የቱርክ ኩባንያዎች መካከል ቶረን አግሮ ኢንዱስትሪ፣ የተረከበውን ሰፊ መሬት ሙሉ ለሙሉ በማልማት ብቸኛው ኩባንያ ሆኗል፡፡

ቶረን አግሮ ኢንዱስትሪ እ.ኤ.አ. መስከረም 2011 ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ በጋምቤላ ክልል ስድስት ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቧል፡፡ ቶረን መሬቱን በጋምቤላ ክልል አኙዋ ዞን ጎግ ወረዳ የተረከበ ሲሆን፣ በዚህ መሬት ላይ በዋናነት ጥጥ፣ በተያያዥነት ደግሞ አኩሪ አተር የማልማት ዕቅድ ነድፏል፡፡

ቶረን ለዚህ መሬት በአንድ ሔክታር 158 ብር የሚከፈል ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለዚህ ይዞታ 23.7 ሚሊዮን ብር በመክፈል ለ25 ዓመታት የሊዝ ዘመን ለመጠቀም ውል ገብቷል፡፡

ኩባንያው ይህንን መሬት በውሉ መሠረት ማልማቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ዘነበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሥሪያ ቤታቸው ባካሄደው ግምገማ ቶረን አግሮ ኢንዱስትሪ የተሰጠውን መሬት ሙሉ በሙሉ አልምቷል፡፡

ኩባንያው ያመረተውን ምርት ለአገሩ ኩባንያና በኢትዮጵያ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለሆነው አይካ አዲስ ለማቅረብ እንደተስማማ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት የተመቸ የአየር ፀባይ ቢኖትም የጥጥ አቅርቦት ግን በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቶረን አግሮ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ጥጥ ያቀርብለታል ተብሎ የሚጠበቀው አይካ አዲስ የራሱን እርሻ ማልማት ጀምሯል፡፡

አይካ አዲስ አገር በቀል ኩባንያ ከሆነው ኦሞቫሊ ግብርና ልማት ኩባንያ ጋር በጋራ ባቋቋመው አይኮም ግብርና ልማት ኩባንያ አማካይነት፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን 10 ሺሕ ሔክታር መሬት ጥጥ ለማልማት ተረክቧል፡፡

አይኮም እ.ኤ.አ. መጋቢት 2014 መሬቱን የተረከበ ሲሆን፣ በአንድ ሔክታር 158 ብር ሒሳብ ለ25 ዓመታት የሊዝ ዘመን ለመጠቀም ውል ገብቷል፡፡

ወደ ጥጥ ልማት የገባው ሌላኛው የቱርክ ኩባንያ ኤልሴ አዲስ ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ነው፡፡ ኤልሴ በአዳማ ከተማ 46 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ገንብቷል፡፡

ኩባንያው ለፋብሪካው ጥሬ ዕቃ የሚሆን ጥጥ ለማምረት በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ 10 ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቦ ወደ ሥራ እየገባ መሆኑ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዙ፣ በአማራ፣ በደቡብና በአፋር ክልሎች ለጥጥ ልማት አመቺ መሬት ቢኖርም፣ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ለመጣው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በቂ ጥጥ ማቅረብ ባለመቻሉ እጥረት እየተፈጠረ ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የሚፈለጉትን ጥጥ በአገር ውስጥ ማቅረብ ባለመቻሉ ከውጭ አገር እየተገዛ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ፋብሪካ የከፈቱ ኩባንያዎች ራሳቸው ወደ ጥጥ ማምረት እየገቡ ሲሆን፣ የቱርክ ኩባንያዎቹ ለዚህ ማሳያ እንደሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

በጥጥ ብቻ ሳይሆን ሰፋፊ እርሻ ከወሰዱ ኩባንያዎች መካከል የቱርክ ኩባንያዎች  በመልካም የሥራ አፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች