የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ የቋንቋ፣ የባህልና የታሪክ ነፀብራቅ ቢሆኑም፣ በግልጽ በአደባባይ ይህ አኩሪ አገራዊ ማንነት የበለጠ ጎልቶ እንዳይወጣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ተፅዕኖዎች እየተደረጉባቸው እንደሚገኝና ይህም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ይህንን አሳሳቢ ያለውን ሁኔታ የገለጸው ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹አስተዳደራዊና የማንነት ጥያቄዎች በሚያነሱ ዜጎች ላይ በየትኛውም መንገድ የሚወሰድ የኃይል ዕርምጃ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው›› በሚል ርዕስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ በቁመናው ልክ መብቱን የሚያስከብርለት፣ የልማት ተጠቃሚነቱን የዴሞክራሲና የነፃነት ባለቤትነቱን በተግባር የሚያረጋግጥለት አካል ሊኖረው ይገባል፤›› በማለት፣ የአዲስ አበባን ሕዝብ ጥያቄዎች በሚገባ የሚመልስ አስተዳደር መኖር እንዳለበት ጠይቋል፡፡
‹‹ባለፉት ሳምንታት የተለያየ ፍላጎት ባላቸው ሰዎችና ድርጅቶች የአዲስ አበባ ነዋሪ የአገሩ ባለቤት ሳይሆን ተፈቅዶለት በይሁንታ እንደሚኖር በተደጋጋሚ መገለጹ፣ ከዚህ መንፈስ ባልራቀ ሁኔታ የከተማዋ ነዋሪ መብቴ ተነፍጓል ማለቱን ተከትሎ በፖሊስ የተወሰደው ዕርምጃ ፍፁም ሥርዓት የጣሰ፣ ያለፈውን መንገድ በብዙ መልኩ እንድናስታውስና ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ኩነት ሆኖ አልፏል፤›› ሲል ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በራያ፣ በቆቦ፣ በኮረም፣ በዓላማጣና በወልቃይት አካባቢዎች ዜጎች ለሚያነሱት ጥያቄ የፌዴራል መንግሥት፣ እንዲሁም የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠታቸው የንፁኃን ዜጎች ሞት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች በኃይል ምላሽ ለመስጠት የሚደረገው የትኛውም አካሄድ ከሕገወጥነቱ ባሻገር በምንም ዓይነት ሁኔታ መፍትሔ የሚያመጣ ባለመሆኑ፣ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ ያለውን ድርጊት እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ለሕግ ተገዥ ባልሆኑ ግለሰቦች የተነሳ ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ ለከፋ የውኃ ችግር መጋለጧን በመጥቀስ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲያበጅ አሳስቧል፡፡