Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎችና ግለሰቦች ተከላከሉ ተባሉ

በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎችና ግለሰቦች ተከላከሉ ተባሉ

ቀን:

መንግሥት በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሊገነባቸው ካሰባቸው አሥር የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ በሆነው ኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ፣ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሦስት ኃላፊዎችና አራት ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

የተከሰሱበትን ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው፣ በኮርፖሬሽኑ የአገዳ ተክልና የፋብሪካ ግንባታ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አበበ ተስፋዬ (ኢንጂነር)፣ የዕቅድና የፕሮጀክት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ከበደ (በሌሉበት)፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁ ሲሆኑ፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ፣ ለ፣ ሐ አንቀጽ 33 እና 411(1)ሀ፣ ሐ እና (3) ሥር የተደነገገውን መተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በምስክሮቹና በሰነድ ማስረጃዎች በማስረዳቱ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 142(1) መሠረት እንዲከላከሉ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ብይን ሰጥቷል፡፡

በድለላ ተሳትፈዋል የተባሉት ግለሰቦች ደግሞ ወ/ሮ ሳሌም ከበደ፣ አቶ ፀጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ፍሬው ብርሃነና ዩአን ጃሊን (ስቲቨን) ሲሆኑ፣ አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 9(1ሀ እና ሐ)ን በመተላለፍ በልዩ የሙስና ወንጀል ተሳታፊ በመሆን፣ አዋጅ ቁጥር 686 (2002 አንቀጽ 30(1) እና 60(10) የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ድንጋጌን መተላለፋቸውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29(1) ሀ እና ለ፣ 2(1)ን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና መቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ድንጋጌ መተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ማስረዳት በመቻሉ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡  

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሠረተው ክስ፣ የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት አምስት የቻይና ኩባንያዎች ፍላጎት ያሳያሉ ይላል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ በወቅቱ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር በጽሑፍ በሰጡት መመርያ፣ ፍላጎት ካሳዩት አምስት የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ ቢያንስ ከሁለት እስከ ሦስት ከሚሆኑት ጋር የቴክኒክና የፋይናንስ ድርድር ተደርጎ ከተመረጡ ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ የበታች የሥራ ኃላፊዎች በተሰጣቸው መመርያ መሠረት ከቻይና ላይት ኢንዱስትሪያል ኮርፖሬሽን ፎር ፎሬይን ኢኮኖሚክ ኤንድ ቴክኒካል ኮኦፕሬሽንና ከቻይና ናሽናል ሔቪ ማሽነሪ ኮርፖሬሽን ጋር ውል ለመፈራረም ጥሪ ማቅረባቸውንም፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ነገር ግን በክሱ ደላላ በመሆን በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉት ወ/ሮ ሳሌም ከበደ፣ አቶ ፀጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ፍሬው ብርሃነ ‹‹ጃንዚ ጃንግሊያን ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ (ጄጄአይኢሲ)›› የተባለ የቻይና ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ዩአን ጃሊን (ስቲቨን) ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ ኮርፖሬሽኑ አውጥቶት በነበረው ጨረታ የተወዳደረና የተመረጠ በማስመሰል ውል እንዲፈጽም ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ የፋይናንስ ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ ጥሪ ተደርጎላቸው የነበሩት ከላይ የተጠቀሱትን ኩባንያዎች ወደ ጎን በመተው፣ ከጄጄአይኢሲ ጋር የ647,058,000 ዶላር ወይም 12,119,913,986 ብር የኦሞ ኩራዝና ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት ውል መፈራረማቸውንም አክሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ቀደም ብሎ ተይዞ የነበረው በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የነበረ ሲሆን፣ ወደ ኮርፖሬሽኑ ከተመለሰ በኋላ፣ ደላላ የተባሉት ተከሳሾች፣ በሜቴክና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያሉ ኃላፊዎችን በማግባባትና ፕሮጀክቱ ለተጠቀሰው ኩባንያ እንዲሰጥና ውሉ እንዲፈረም ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ይኼንንም በማድረጋቸው ኮርፖሬሽኑ በጨረታው ተሳትፈው ጥሪ ያደረገላቸው ኩባንያዎች እንዳይቀርቡ በማድረግ፣ መንግሥት ከቻይና መንግሥት ባንክ (ኤግዚም ባንክ) የሚያገኘውን ብድር ቀስ ብሎ መክፈል የሚችልበትን ዕድል እንዲያጣ ማድረጋቸውን አክሏል፡፡ ውል የፈጸመው ኩባንያ ብድሩን ከቻይና ኢንዱስትሪና ኮሜርሻል ባንክ እንዲገኝ በማድረጉ፣ በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና ደላሎቹ ከተገኘው 550 ሚሊዮን ዶላር ወይም 10,301,940,000 ብር ላይ 2.75 በመቶ ኮሚሽን ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የሚያጠናክሩለት የሰነድ ማስረጃዎችንና የሰው ምስክሮችን ማሰማቱን ፍርድ ቤቱ የሰጠው ብይን ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያሰማቸው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች፣ የስኳር ፋብሪካውን ለመገንባት የተፈጸመው የጨረታ የግዥ ሒደት የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመርያና ዋና ዳይሬክተሩ የሰጡትን መመርያ ያልተከተለ መሆኑን፣ የኮርፖሬሽኑ ሦስት ምክትል ዳይሬክተሮች (ከላይ የተጠቀሱት) የግዥና የዋና ዳይሬክተሩን መመርያ ተከትለው ሥራውን ባለመምራታቸው፣ መንግሥት ከዋጋና ከጥራት አንፃር ማግኘት የሚችለውን ጥቅም ሳያገኝ መቅረቱን መገንዘብ እንደቻለ አብራርቷል፡፡ ሌሎቹ ተከሳሾች (ደላላዎች የተባሉት) ከኮርፖሬሽኑና ከዋና ዳይሬክተሩ መመርያ ውጪ ያለ ውድድር ኩባንያው ፕሮጀክቱን እንዲያገኝ በሙሉ ሐሳባቸውና ፍላጎታቸው በመሳተፍና ሕገወጥ ውል እንዲፈጸም በማድረግ፣ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ኮሚሽን ከመንግሥት ገንዘብ ላይ ማግኘታቸውን ምስክሮችና ሰነዶች እንደሚያሳዩም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ በእያንዳንዱ ተከሳሽ ላይ ምስክሮችና ሰነዶች ያረጋገጡትን ድርጊት በሚመለከት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት፣ ሦስቱ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዳይሬክተሮች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) ሀ እና ሐ፣ 33 እና 411 (1) እና (3)ን በመተላለፍ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት፣ እንዲሁም አራቱ ተከሳሾች ደግሞ አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 9(1ሀ) (ሐ)ን በመተላለፍ በልዩ የሙስና ወንጀል ተሳታፊ በመሆናቸው፣ ሁሉም ተከሳሾች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 142(1) መሠረት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ከታኅሳስ 11 እስከ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...