ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 ሰዓት አካባቢ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን በጎንጅ ቆላ ወረዳ አዲስ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ለጥናት መረጃ ያሰባስቡ የነበሩ ሁለት ተመራማሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ ተቀጥቅጠው ተገደሉ፡፡
በግድያው አቶ ወሰን ታፈረ የተባሉ የኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ኢንስቲትዩት ባልደረባ፣ ተመራማሪና የመጨረሻ ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ተማሪ፣ እንዲሁም በቅርቡ ከአውሮፓ ዶክትሬታቸውን ይዘው የተመለሱት የዋናው አጥኝው ጓደኛ የሆኑት ማንደፍሮ አቤ የተባሉ ግለሰብ ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ሁለቱ ሟች ተመራማሪዎች ረፋዱ ላይ ለጥናታቸው መረጃ ለማሰባሰብ ወደ ትምህርት ቤቱ መጓዛቸውንና ለሰዓታት መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ወሰን ጥናቱን ለማከናወን ወደ ትውልድ ቦታቸው ምዕራብ ጎጃም ዞን ያቀኑት፣ በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡
አቶ ወሰን ባደጉበት አካባቢ በተለይ በሕፃናት ላይ በተለያዩ ምክንያት የሚከሰቱ የሆድ ሕመሞችን መስንዔ ለማጥናት መሄዳቸውን፣ የአቶ ወሰን የሥራ ባልደረባ አቶ ማሞ ካሰኝ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ይኼንንም ዓላማ በማንገብ ወደ ትውልድ ቦታቻው የተጓዙት አቶ ወሰን፣ አስፈላጊውን ፈቃድና ሕጋዊ ማስረጃዎች ይዘው ወደ ቦታው መንቀሳቀሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከምዕራብ ጎጃም ዞንና ከወረዳው ፈቃድ አግኝተው ነው ጥናቱን የጀመሩት፡፡ ‹‹እኛ ማስረጃውን ዓይተን ሕጋዊነታቸውን አረጋግጠን የትብብር ደብዳቤ ጽፈናል፤›› ሲሉ የወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቹ አበባው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ለወረዳው አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም በጥናቱ ለተካተቱት ትምህርት ቤቶች የትብብር ደብዳቤ መጻፋቸውን አቶ አቹ አክለዋል፡፡
በተጨማሪም በጥናቱ እገዛ እንዲያደርጉላቸው በወረዳው የሚሠሩ የላቦራቶሪ ባለሙያ አቶ ኃይለየሱስ ሙሉ የተባሉ ግለሰብ አብረው መላካቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት አቶ ወሰን፣ አቶ ማንደፍሮና አቶ ኃይለየሱስ አንድ ላይ በመሆን ወደ ትምህርት ቤቱ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በመሄድ፣ ከተማሪዎች ላይ የምራቅና የዓይነ ምድር ናሙና መውሰዳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ለተፈጸመው ግድያ መንስዔ ሆኗል የተባለው የተወሰኑ የከተማው ግለሰቦች ልጆቻችንን ‹ፀጉረ ልውጦች› የማይታወቅ ነገር እየከተቧቸው ነው የሚል ያልተጨበጠ ወሬ በማሠራጨታቸው ነው ተብሏል፡፡
ይህ ወሬም የከተማውን ነዋሪዎች ለጥቃት እንዳነሳሳቸው፣ የዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ቁጥራቸው በዛ ያሉ ሰዎች ጥናት ላይ የነበሩትን ሦስቱንም ግለሰቦች ከትምህርት ቤቱ በማውጣት በድንጋይና በዱላ የታገዘ ጥቃት መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡
ተመራማሪዎቹ ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸውን ለማቃጠል ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ የክልሉ ልዩ ፖሊስ ደርሶ ማስቆሙ ተጠቁሟል፡፡
በጥቃቱ የምዕራብ ጎጃም ዞን ተወላጅ የሆኑት ሁለቱም ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ አቶ ኃይለየሱስ ግን ከባድ የሆነ ጉዳት ጭንቅላታቸው ላይ ደርሶባቸው በአሁኑ ጊዜ ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጥቃቱ የሞቱት ሁለቱ ተመራማሪዎች በዞኑ ውስጥ ማለትም አቶ ወሰን በአዴት ከተማ፣ እንዲሁም አቶ ማንደፍሮ በዱር ቤቴ ከተማ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመድ በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
ሁለቱ ተመራማሪዎች በተገደሉ ዕለት አቶ ኤልያስ አብዲና ወ/ሮ ፀደይ ቸኮል የተባሉ የአካባቢው ተወላጆች፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ለቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ለማድረግ የሄዱ ሁለት ግለሰቦችም ጥቃት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሁለት ግለሰቦች በአካባቢው በመሠራት ላይ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ለማድረግ የግንባታ ቁሳቁስ ጭነው ሲሄዱ፣ ከተመራማሪዎቹ ጋር አብረው የሚሠሩ ናቸው ተብለው ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ከወረዳው ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
በዚህም ምክንያት ግለሰቦቹ ይዘውት ነበረው መኪና ሲቃጠል ለዕርዳታ የወሰዱት የግንባታ ቁሳቁስ መውደሙ ታውቋል፡፡
ይኼንን መሰል የደቦ ፍርድና ጥቃት በአማራ ክልል በተደጋጋሚ እየታየ ሲሆን፣ ከወራት በፊት በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 13 የክልሉን የኤችአይቪ ሥርጭት ለማጥናት የሄዱ ባለሙያዎች ጥቃት ደርሶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ በተገደሉበት ወረዳ በቅርቡ ለእናቶች የጤና ድጋፍ የሚያደርጉ የባለሙያዎች ቡድን ጥቃት ተፈጽሞበት ሁለት ሾፌሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡
የአሁኑ ጥቃት ለመፈጸም ምክንያቱ ከዚህ ቀደም በተፈጸሙ ጥቃቶች ማንም ተጠያቂ ባለመደረጉ ነው ሲሉ አቶ አቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከአሁኑ ጥቃት ጋር በተያያዘ 30 ያህል ሰዎች ተጠርጥረው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በወረዳው ውስጥ ያሉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተንቀሳቅሰው መሥራት አልቻሉም ሲሉ ኃላፊው አክለዋል፡፡
‹‹ስለጉዳዩ ሰምተናል፣ በቀጣይ የሕዝብ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡ ጥቃት እየተፈጸመ ያለው በተሳሳተ መረጃ በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያው እየፈጠረ ባለው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፤›› ሲሉ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አበባው ገበያው (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተጠቀሰው ዞን በቡሬ ከተማ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውስጥ አንድ ግለሰብን ‹ፀጉረ ልውጥ ነህ›፣ ቤተ ክርስቲያኑን ለማቃጠል ሞክረሃል ተብሎ በድንጋይ ተደብድቦ መገደሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡