Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ኢትዮጵያዊነትን ከሰላም ጋር አንድ ለማድረግ መሥራት አለብን›› ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

‹‹ኢትዮጵያዊነትን ከሰላም ጋር አንድ ለማድረግ መሥራት አለብን›› ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ቀን:

ወ/ሮ ዘውዲቱ ምኒልክን ንግሥተ ነገሥታት፣ ራስ ተፈሪ መኮንን ደግሞ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ በማድረግ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ዙፋን ካረካከበው ታሪካዊ ክስተት ወዲህ፣ ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሹመዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት አራተኛዋ ፕሬዚዳንት በመሆን ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት የገቡት ታዋቂዋ ዲፕሎማት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አገሬንና ሕዝቦቿን ለማገልገል በመመረጤ ታላቅ ክብር ይሰማኛል፤›› ብለዋል፡፡ በዲፕሎማሲው ዓለም ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች የወከሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የቀድሞ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በምክትል ዋና ጸሐፊነት ደረጃ የተመድ የናይሮቢ ዋና መሥሪያ ቤት ኃላፊ ተደርገው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ በፓርላማ ንግግራቸው ለሰላም ልዩ ትኩረት የሰጡት ፕሬዚዳንቷ፣ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) አገራቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ ባለውለታ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ያስመሠግናቸዋል ብለዋል፡፡ ‹‹እሳቸው ኃላፊነትን በመልቀቅ ያሳዩት አርዓያነት እስከ ወረዳ ድረስ ተግባራዊ መሆን ያለበት ልማድ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ የተጀመረውን ለውጥ በኃላፊነት ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ታላቅ አገርን የመገንባት ህልምን ዕውን ለማድረግ፣ ከሰላም ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ መንገድ የለም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነትን ከሰላም ጋር አንድ ለማድረግ መሥራት አለብን፤›› በማለትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡     

‹‹ከያዝነው ሥልጣንና ኃላፊነት በፊትም ሆነ በኋላ ሕይወት ይቀጥላል›› ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የዛሬ አምስት ዓመት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ፓርላማው በሙሉ ድምፅ ነበር የደገፋቸው፡፡ ከእሳቸው በፊት የነበሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሁለት የፕሬዚዳንትነት ዘመን (አሥራ ሁለት ዓመታት) ጨርሰው ሥልጣናቸውን ያስረከቡ ሲሆን፣ በእሳቸው ምትክ የመጡት ፕሬዚዳንት ሙላቱም ሁለት የፕሬዚዳንትነት ዘመን ሳያጠናቅቁ ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ ብሎ የጠበቁ ቢኖሩ እንኳን እጅግ ጥቂት ቢሆኑ ነው፡፡ ይህም ፕሬዚዳንቱ ያለው ሥልጣን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ስላልሆነና ቦታውም ሽሚያ ስለማይኖርበት፣ እሳቸው ሁለት የፕሬዚዳንትነት ዘመን እንዳያገለግሉ የሚገታቸው ጉዳይ እምብዛም እንደሚሆን በሚኖር እሳቤ ነው፡፡

- Advertisement -

ይሁንና ፕሬዚዳንቱ ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአምስት ዓመታት በፊት ቀርበው ቃለ መሃላ የፈጸሙበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፣ ‹‹ሥልጣኔን በፈቃዴ ልለቅ ነው›› ሲሉ፣ በዋዜማው ከተሰማ ጭምጭምታ ውጪ ማን ለቦታው እንደታጨ በይፋ አልተነገረም ነበር፡፡

በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ ከተሾሙ ጀምሮ ባሉት አምስት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት አፈ ጉባዔዎች፣ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትርና አንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተፈራርቀዋል፡፡ ፓርላማውም ውስጣዊ ገጽታው በብዙ ተቀይሯል፡፡

ለወትሮው በዚህ ፓርላማ ፊት ለፊት በዓመት አንዴ ብቻ የሕዝብ ተወካዮችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ንግግር ለማድረግና የዓመቱን የሥራ ዘመን መከፈት ከማብሰር ውጪ የማይገኙት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህኛው ፓርላማ አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሁለቴ ተገኝተዋል፡፡ የመጀመርያው መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ የምክር ቤቶቹን የጋራ መክፈቻ ንግግር ለማድረግ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሥልጣናቸውን የለቀቁበትና የመጨረሻ የስንብት ንግግራቸውን ያሰሙበት ክስተት ነበር፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት በዚህ ንግግራቸው የዛሬ አምስት ዓመት በፕሬዚዳንትነት ሲሾሙ ፓርላማው በሙሉ ድምፅ የመረጣቸው መሆኑን በማስታወስና ለዚህም በማመሥገን፣ ‹‹እነዚህ አምስት ዓመታት በሕይወት ጉዞዬ ከተጓዝኳቸው መንገዶች ሁሉ ትልቁን ቦታ የሚይዙና ለዚህም የሚሰማኝ ክብር በዓይነቱ ልዩ  ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንትነታቸው የመጀመርያ ዓመታት በሰላም የተጠናቀቁ ቢሆንም፣ ‹‹የተጣለብኝን ኃላፊነት በታማኝነት እንደፈጸምኩ ይሰማኛል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ ቀሪዎቹን ሦስት ዓመታት ‹‹አገራችን ትልቅ አደጋ ላይ የወደቀችበትና ብሔራዊ ደኅንነታችን አደጋ የተጋረጠበት ጊዜ፤›› ነው ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከስድስት ወራት በፊት የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ከቶ ልንረሳው አይገባም፡፡ ያንን ማስታወስ ከተሳነን ምን ያህል ርቀት እንደመጣን መገንዘብ ስለሚያዳግተን፤›› ብዙው፣ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ ጊዜ ላይ ሆና አድኑኝ እያለች ስትጣራ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ይሁንና አሁን ‹‹የፀደይ ወራት ላይ ደርሰናል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የዛሬ ሰባት ወር እነዚህ ለውጦች ይመጣሉ ብሎ የጠበቀ ይቅርና ያለመ ጥቂት ነው ሲሉም ምን ያህል የጭንቅ ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ስለዚህም ‹‹በከባድ ዋጋ የተገኙ ስኬቶቻችንን ለማስቀጠልና ከፍ ወዳለ ጥግ ለመውጣት መትጋት አለብን፤›› ሲሉ አሳስበው፣ በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካና ልዩነት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ትርክት አገሪቱን ወደ አደጋ የሚወስዳት ሊሆን እንደሚችል፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው ይገባል ሲሉም አስምረውበታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም መንግሥታዊ ውሳኔዎችን በብሔር መነጽር ብቻ መመልከት ‹‹የምንመኛትን ኢትዮጵያ ምኞት ብቻ ሆና እንድትቀር ያደርጋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ምክር የታከለበትን ንግግራቸውን በዚህ ከቋጩ በኋላ፣ አዲስ የሚመረጡትን ዕጩ ፕሬዚዳንት በሚመለከት ለመወያየት ፓርላማው በዝግ እንዲሰበሰብ ተደርጎ፣ ከደቂቃዎች በኋላ በታዋቂዋ ዲፕሎማት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዕጩነት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ ፕሬዚዳንቷ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

የ63 ዓመቱ ፕሬዚዳንትም ሥልጣነ መንበራቸውን ለ68 ዓመቷ ዲፕሎማትና ዓለም አቀፍ ልምዶችን ላካበቱት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ አስረክበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷና ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ወደ አዳራሹ ሲገቡ የፓርላማው አባላት በጭብጨባ ሲቀበሏቸው በእንግድነት የታደሙ ዲፕሎማቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሁነቱን ለመዘገብ የታደሙ ጋዜጠኞች በጉጉት ከወንበራቸው ተነስተው ሲመለከቷቸው ተስተውለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷን ቃለ መሃላ ያስፈጸሙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለመጀመርያ ጊዜ ፕሬዚዳንት ቃለ መሃላ ያስፈጸሙ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቷም የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን በታሪክ መዝገብ ተጽፈዋል፡፡ በአፍሪካም የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍና ከማላዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ ቀጥሎ ሦስተኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ብቸኛዋ ፕሬዚዳንትም ሆነዋል፡፡

በእርጋታና በሞገስ ወደ አዳራሹ ገብተው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ፣ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የሥልጣን ርክክብ አድርገው እጃቸውን በደረታቸው አድርገው ከፓርላማው ፊት በመቆም የአገር እናትነትን የተላበሰ በግርማ ሞገስ በተሞላ ዕይታ ፎቶዎች ተነስተዋል፡፡

በመቀጠልም የብዞዎችን ቀልብ የሳበና በፓርላማው ተደጋጋሚ ጭብጨባዎች የተደረገለት የ18 ደቂቃዎች ንግግር አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ከእሳቸው በፊት የነበሩትን ፕሬዚዳንት ሙላቱን በማመሥገን፣ ‹‹ከዚህ የምንማረው በብዙ የአፍሪካ አገሮች ከተለመደው ውጪ በአገራችን በገዛ ፈቃድ ሥልጣን በመልቀቅ ለለውጥና ተስፋ መስጠት መጀመሩን ነው፡፡ ይህም ባደጉትና ዴሞክራሲ በዳበረባቸው አገሮች እንደተለመደው ከያዝነው ሥልጣንና ኃላፊነት በፊትም ሆነ በኋላ ሕይወት የሚቀጥል መሆኑን መረዳታችንን ያሳያል፤›› በማለት፣ በሁሉም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተመሳሳይ ድርጊቶች እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሥልጣን ዘመን ጉዞ እጅግ ውስብስብና በርካታ ፈተናዎች ያሉበት እንደሚሆን እንደሚጠብቁ ያስታወቁት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹የተጀመረው ለውጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርባትን አገር ዕውን እንደሚያደርግም እተማመናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለራሳችንም ሆነ ለትውልድ የሚያኮራ አገር መፍጠር ይኖርብናል፤›› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመጀመርያ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን ከ20 የአገሪቱ የካቢኔ አባላት ግማሹ ሴት ሆነው በተመረጡ በሳምንቱ የተሾሙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ባደረጉት ንግግር በዋናነት ሰላምና ሴቶች ላይ ያጠነጠኑ መልዕክቶችን በአጽንኦት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ታላቅ አገር የመገንባት ህልማችንን ዕውን ለማድረግ ከሰላም ውጪ አቋራጭም አማራጭም የለንም፡፡ ስለዚህም ሁላችንም ሰላማችንን አጥብቀን እንድንጠብቅ ከሁሉ በላይ ሰላም ሲታወክ በምትሰቃየዋ የእናት ስም አጥብቄ እጠይቃችኋለሁ፤›› ሲሉም ጥሪ አድርገዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነትን ከሰላም ጋር አንድና ህያው ለማድረግ በጋራ እንሥራ፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ ‹‹በኃላፊነት ቆይታዬ ዋነኛ ትኩረቴ ሰላም በማስፈን ላይ እንድንረባረብ ማድረግ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ሥልጣን የያዙም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ መስረፅ ዜጎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹም ሆነ ሰላማቸውን ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ በሁሉም መስክ ሰላም እንዲሰፍን ከቀበሌ እስከ ዓለም ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ የእሳቸው እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ለብዙዎች ብርታት እንደሚሆን፣ በተለይም ሴቶች ከተማሩና ከጠነከሩ ያሰቡበት ቦታ ለመድረስ የሚያግዳቸው ነገር እንደማይኖር ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሴቶች ከወንዶች እንደማያንሱ በተለያየ መስክ ኑሯችሁን ለማሸነፍ ሌት ተቀን የምትተጉ ልፋታችሁ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ከትግላችሁ ወደ ኋላ እንዳትሉ፤›› ሲሉ  ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹ሴቶች የቤተሰብም የአገርም ምሰሶ ናቸው፡፡ ሴት አገር ነች፣ አገርን ደግሞ ሴቱም ወንዱም ሊንከባከበው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የሴቶችን ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት የማይቀበል ትውልድ መገንባት እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ‹‹ስለ ዜት አብዝቼ የተናገርኩ ከመሰላችሁ ገና ምኑ ተነክቶ?›› ሲሉ አዳራሹን በፈገግታ ሞልተውታል፡፡

‹‹ደስታችን ሙሉ የሚሆነውና ሳላማዊ ዕድገታችን የሚረጋገጠው ሴቶችም ወንዶችም እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው፤›› ሲሉ አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹የሁላችንንም የግልና የጋራ ጥረት ፈጣሪ ይባርክልን፤›› ብለዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሥልጣን ምንም እንኳን የተገደበ ቢሆንም፣ የበርካታ ግለሰቦችንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቷ ባላቸው የሥራ ልምድና በትምህርት ደረጃቸው በርካቶች እውነትም ለቦታው ይመጥናሉ እንዲሉ ያስባለ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በአዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፣ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ተከታትለው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ፈረንሣይ አገር ከሚገኘው ሞንትፔለ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ሲያገኙ የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሣይኛና አማርኛ ቋቋዎችን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያን በመወከል በሴኔጋል፣ በኬፕ ቨርዲ፣ በጊኒ ቢሳኦ፣ በጋምቢያና በጊኒ በአምባሳደርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና የኢጋድ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በተጨማሪም በፈረንሣይ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ በቱኒዝያና በሞሮኮም የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቀናጀ የሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ልዩ ረዳትና በአፍሪካ ኅብረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሠርተዋል፡፡

በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እ.ኤ.አ. በ2011 በወቅቱ በተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ሙን ተሹመው ማገልገላቸውን የሕይወት ገጻቸው ያሳያል፡፡ በዚህ ወቅት ኃላፊነታቸው የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ ደረጃ ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያን ወክለው በቆዩባቸው ጊዜያት የአክሱም ሐውልት ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ አገሩ እንዲመለስ ያደረጉት አስተዋፅኦ ጎልቶ ይነገራል፡፡

የፕሬዚዳንቷ መመረጥ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንና ድርጅቶችን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጀምሮ አፍሪካ ኅብረት፣ የኢጋድና የተለያዩ አገሮች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ይኼንን አስመክልተው እንኳን ደስ አለዎት ያሉት የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ታሪካዊ ጊዜ ነው፤›› ብለው ‹‹በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳሉ በርካታ ፍሬያማ ውይይቶችን ያደረግን ሲሆን፣ ጠንካራ የሥራ ግንኙነትንም ልንመሠርት ችለናል፡፡ ለሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅም ሲባል ይኼንን ግንኙነት ለማጠናከር አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማሃመት በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ የፆታ እኩልነትን ያረጋገጠ ካቢኔ መዋቀሩን ተከትሎ የመጣ ሹመት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ሴቶችን በማጎልበትና ውጤታማ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ወደ ማድረግ እየተስፈነጠረች መሆኗን የሚያሳይ መሠረት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ትኩረታቸውም ሰላምን መስበክና የሴቶችን መብት በሚመለከት መሥራት እንደሚሆን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...