Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሙስና ወንጀል በተከሰሱት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊ ላይ ብይን ተሰጠ

በሙስና ወንጀል በተከሰሱት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊ ላይ ብይን ተሰጠ

ቀን:

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የሺፒንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ዓለሙ አምባዬ (ቺፍ ኢንጂነር)፣ ተጠርጥረው በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሹ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881 (2007 አንቀጽ 9(3) በመተላለፍ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቁሞ ክስ ቢያቀርብም፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የአዋጁን ድንጋጌ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 113(2) መሠረት በመቀየር፣ በተመሳሳይ አዋጅ በአንቀጽ 13(1) ሐ እና (2) ሊከላከሉ እንደሚገባ ብይን ሰጥቷል፡፡

ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ክስ የተመሠረተባቸው ድርጅቱ ሊገዛ ካሰባቸው ኮንቴይነሮች ጋር በተያያዘ 65,594,160 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል መሆኑን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ በማቅረቡ ነው፡፡ ድርጅቱ ለኮንቴይነሮች ኪራይ በወር 400,000 ዶላር የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ ‹‹ኮንቴይነር ይገዛ›› የሚል ጥያቄ ተከሳሹ ከሚመሩት ዘርፍ መቅረቡን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ የአዋጭነት ጥናት ሲጠና አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ፣ ጥናቱ በቦርድ ፀድቆ በ2007 ዓ.ም. 1,800 ባለ 20 ጫማና 780 ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነር ለመግዛት 199,237,000 ብር በጀት ተይዞ እንደነበርም አክሏል፡፡ በተያዘው በጀት ግዥ ለመፈጸም ጨረታ ወጥቶ ‹‹ጄኔራል ኤክስፐርት›› የሚባል ድርጅት ማሸነፉንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ግዥው ሳይፈጸም በመቅረቱ በ2008 ዓ.ም. ከአሸናፊው ድርጅት የግዥ ሒደቱን ተከትሎ እንዲገዛ ማድረግ ሲገባቸው፣ ተከሳሹ ግን ግዥው እንዲሰረዝ፣ በወቅቱ የድርጀቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለነበሩት አቶ አህመድ ቱሳ ሐሳብ በማቅረብ ሳይገዛ መቅረቱን ክሱ ያብራራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመሆኑም ግዥው ከተሰረዘበት የግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ 2,580 ኮንቴይነሮችን በመከራየት፣ ድርጅቱ ክስ እስከቀረበበት ታኅሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ 65,594,160 ብር ወጪ ማድረጉን ጠቁሟል፡፡ ኮንቴይነሮቹ ተገዝተው ቢሆን ኖሮ ወጪ የተደረገው ገንዘብ በመንግሥት ካዝና ሊቀር ይችል እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሞ፣ ተከሳሹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ባቀረበው ክስ ላይ አብራርቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተከሳሹን ከሌሎች ተከሳሾች ጋር አንድ ላይ የከሰሳቸው ቢሆንም፣ ክሳቸው ተለይቶ እንዲቀርብ በጠበቃቸው አማካይነት ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ ዓቃቤ ሕግ የተቃውመ ቢሆንም፣ ተቃውሞው ውድቅ ተደርጎ ክሳቸው ተነጥሎ ለብቻቸው ሒደቱ ቀጥሏል፡፡

ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ስምንት በድርጅቱ የተለያዩ ኃላፊነት ላይ የሚሠሩ ግለሰቦችንና አንድ የሙያ ምስክር፣ በድምሩ ዘጠኝ ምስክሮችን አሰምቷል፡፡ የሰነድ ማስረጃዎችንም ማቅረቡን ብይኑ ያብራራል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንፃር መመርመሩንም ብይኑ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ ‹‹ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ተረጋግጦባቸዋል? ወይስ አልተረጋገጠባቸውም? ሊከላከሉ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩንም ጠቁሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያሰማቸውን ምስክሮች ቃል ሲመረምር፣ እንደ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዱ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኮንቴይነር አዋጭነት ጥናት ተከሳሽ ባሉበት ተፈጽሞና በቦርድ ፀድቆ እያለ አዲስ ጥናት እንዲደረግ መጠየቃቸውና 90 ሚሊዮን ብር በጀት እያለ አዲስ በጀት እንዲያዝ ማለታቸው፣ ያለባቸውን የሥራ ኃላፊነት ካለመወጣታቸው ባለፈ፣ የመንግሥትን ጥቅም ማሳጣታቸውን አስረድቷል፡፡ ከተቋሙ የግዥ መመርያ አኳያም ቢታይ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ፍርድ ቤቱም ማረጋገጡን አክሏል፡፡

በመሆኑም ጉዳቱ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳስረዳው፣ የጨረታው ሒደት ከተሰረዘበት ቀን ጀምሮ ሊሰላ የማይገባው ቢሆንም፣ ተከሳሽ ኃላፊነታቸውን ቢወጡና የግዥ ሒደቱን ተከትሎ በአግባቡ ቢመሩት፣ ሊያስቀር የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ እንደነበር አስረድቷል፡፡

ነገር ግን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ለኮንቴይነሮች ኪራይ የወጣው የውጭ ምንዛሪ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑና የወንጀሉም ዓላማ ከባድ በመሆኑ፣ ተከሳሹ የተመሠረተባቸውን የሙስና ወንጀል፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 113(2) ተቀይሮ፣ በአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13(1ሐ) እና (2) ‹‹የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት›› በሚለው እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ የመከላካያ ምስክሮችን ለመስማት ለኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...