Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክፓርላማውን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ ሕግጋትና ተግባራት

ፓርላማውን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ ሕግጋትና ተግባራት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ክፍል ሦስት

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚያወጣቸው ሕግጋት ከሚይዛቸው ቴክኒካዊ ጉዳዮች አኳያ ከፓርላማ አባላት ምን እንደሚጠበቅ የተወሰኑ ነጥቦችን በአስረጂ እያስደገፉ ማቅረብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛው የሥልጣን አካል የሚያርፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 (3) ላይ ተገልጿል፡፡

ይህንን ሥልጣኑን ተግባራዊ ከሚያደርግባቸው ዘዴዎች ዋነኛው ሕግ አውጥቶ እንዲተገበር በማድረግ ነው፡፡ የሚያወጣቸው ሕግጋት በነጋሪት ጋዜጣ መታተም እንዳለባቸው እንዲሁም አዋጆች (Proclamations) እንደሆኑም ይታወቃል፡፡ የፓርላማ አባላት ሕግ እንዲፀድቅ ድጋፋቸውን ለመስጠት አለበለዚያም ለመቃወም አስቀድመው አጥንተው አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕግ ማርቀቅ በራሱ የተለየ ችሎታ ይጠይቃል፡፡ ሕግ የሚወጣለትን ነገር ይዘቱን ከማወቅ ባለፈም የሕግ አረቃቀቅ ዕውቀት እንዲኖር ይጠበቃል፡፡ የፓርላማ አባላት ሕግ የማርቀቅ ዕውቀትና ችሎታ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ረቂቅ ሕግ መያዝ ያለበትን ዋና ዋና ነጥቦች እንዲሁም የሕግ ድንጋጌዎች መሠረታዊ ባህሪያትን ማወቅ ከፓርላማ አባላት የሚጠበቅ ግዴታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

ረቂቅን መገምገም

ረቂቅ ሕግ በተለያዩ ባለሙያዎች ዕገዛ በመርህ ደረጃ በተለያዩ ተቋማት አማካይነት ሊቀርብ ይችላል፡፡ በፓርላማውም ቋሚ ኮሚቴዎች ወይም አባላት አማካይነት ሊቀርብ ይችላል፡፡ በማንም ይረቀቅ በማንም፣ በረቂቅ ሕጉ ውስጥ ደንብ የሚሠራላቸው ጉዳዮች ማርቀቁ ሲጀመርም ሆነ ሲፀድቅም ከብዙ መለኪያዎች አንፃር አስቀድሞ እየተመዘነ መሆን አለበት፡፡ ለመመዘኛነት የሚያገለግሉትም ማኅበራዊ መዋቅሮች (ጾታ፣ ብሔርና ሃይማኖት)፣ ሰብዓዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከብሔራዊ ኢኮኖሚና ከሌሎች መለኪያዎች አንፃር እየታየ መገምገም አለበት፡፡ እነዚህ ለአርቃቂም ለአፅዳቂም በመለኪያነት ያገለግላሉ፡፡  ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ እናንሳ፡፡ የመጀመርያው ስለቆዳ ግብይት የወጣውን አዋጅ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን እየለዩ ስለሚሰጡ ማበረታቻዎች ነው፡፡ በየተራ እንመልከታቸው፡፡

የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይትን ሥርዓት ለማስያዝ ሲባል አዋጅ ቁጥር 814/2006 ወጥቷል፡፡ ለማሳካት ካሰባቸው ግቦች መካከል አንዱ በቆዳ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለውን የተንዛዛ የግብይት ሥርዓት ማስቀረት ይገኝበታል፡፡ ይህንን ለማሳካት በመፍትሔነት የቀረበው ደግሞ በቆዳና ሌጦ ላይ እሴት ሳይጨምሩ መሸጥን ማስቀረት ነው፡፡ ስለሆነም ከእንስሳት ቆዳና ሌጦ ያገኘው ከመጀመርያው ባለቤት በመቀጠል ቆዳና ሌጦው ላይ ማሻሻያ ሳያደርጉ ከቆዳና ሌጦ ፋብሪካ ወይም መሰል ድርጅቶች መካከል ላይ ያሉ ደላሎችን በሕግ ቀሪ ተደርጓል፡፡ እሴት ሳይጨምር ሲሸጥ የተገኘም የወንጀል ኃላፊነትም እንዲኖርበት ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቆዳና ሌጦ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደላሎች ጠፉ፡፡ ግብይቱ በግለሰብ አምራች፣ አቅራቢና ባለፋብሪካ መካከል እንዲሆን ሕግ ወጣ፡፡ ይህ የድለላ ተግባር እንደ ሁኔታው የውጭ ገበያ ማፈላለግንም ይጨምር ስለነበር ገበያ አፈላላጊ ደላሎች ሲቀሩ የቆዳ ዋጋ ረከሰ፡፡ ለቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪው በርካሽ ጥሬ ዕቃ ስለሚያገኝ ካመረተው ላይ (ባገኘው ገበያ መጠን) የተሻለ ትርፍ ያገኛል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማሳደገም ይረዳል፡፡ ይሁን እንጂ የቆዳና ሌጦ ዋጋ መርከስ ደግሞ በተለይ ገበሬውን እንደሚጎዳው ግልጽ ነው፡፡ ከአምስትና ስድስት ዓመታት በፊት 70 ወይም 80 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው የበግ ቆዳ 20 ብር ገደማ ዝቅ አለ፡፡ የፓርላማ አባላት እንዲህ ዓይነቱን ሕግ ከማፅደቃቸው በፊት የገበሬው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ፣ እንዲሁም በደላላ አማካይነት ይገኝ የነበረውን ገበያ የማፈላለግ ሥራ በምን ዓይነት አሠራር ሊተካ እንደሚችል ቀድመው ማጤን ነበረባቸው ማለት ነው፡፡ አብዛኛው የፓርላማ አባል በገጠር የሚኖረውን ሕዝብ ከወከለ ውግንናው ለወከለው ሕዝብ መሆንም ይጠበቅበታል፡፡ በአዋጁ አማካይነት የተፈጠረውን የጥሬ ቆዳና ሌጦ ዋጋ መቀነስን ግንኙነት የተለያዩ ጥናቶችን መመልከት ይቻላል፡፡

ወደ ሁለተኛው ምሳሌ እንለፍ፡፡ የተለያዩ የንግድና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎችን ለማበረታታት ሲባል የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን መንግሥት አቅርቧል፡፡ ለተወሰኑ ዓመታት የግብር ዕፎይታ መስጠት፣ ግብዓቶችን ከግብር ነፃ ከውጭ ማስገባት የተዘወተሩት ናቸው፡፡ አንዳንድ ዘርፎች ላይ ማበረታቻ እንዲኖር በከፍተኛ ሁኔታ ግፊት የሚያደርጉ ባለሀብቶች መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ለባለኮኮብ ሆቴሎች ግንባታ ከውጭ የሚገባ ብረትን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ መንግሥት በሕግ ይፈቅዳል፡፡ ይህንን የሆቴል ኢንዱስትሪ ማበረታቻ እንደሽፋን በመውሰድ የተወሰኑ ሰዎች በተለያዩ ከተሞች የሆቴል ንግድ ፈቃድ አውጥተው በርካታ ብረት ወደ አገር በማስገባት የብረት ንግዱን እንደተቆጣጠሩት ይታወቃል፡፡ ከአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ ወደ ክልሎች የሚወስዱትን መንገድ ይዞ የሚጓዝ ሰው ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዘ መሠረታቸው ብቻ ተሠርቶ ለዓመታት ቁመው እንደተወጠኑ በጅምር የቀሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕንፃዎች ያስተውላል፡፡ ለምን ተጀምረው ለምን ግንባታቸው እንዳልቀጠለ ለሚጠይቅ ሰው መልሱን ይህ የሆነው ሆቴል ለመገንባት ፈቃድ ወስደው ከቀረጥ ነፃ ብረትና ሌሎች ቁሳቁሶችን አስገብተው ለመሸጥ ሲሉ እንጂ የእውነት ሆቴል ለመገንባት አቅደው እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ ይህን የሚያደርጉት የብረት ነጋዴዎች እንጂ የሆቴል አገልግሎት ሰጪዎች አለመሆናቸውን ለማወቅ የብዙዎቹ ጅምር ሕንፃ ባለቤቶችን ማንነት ማወቅ መልሱ ግልጽ ይሆናል፡፡

በእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ለማሳየት የተፈለገው እያንዳንዱ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ጥቅምና ጉዳቱን በአግባቡ መመዘን እንደሚገባ፣ እንዲሁም ሕጉ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ እንዳይውል ለመከላከል የሚረዱ አሠራሮችን አብሮ ማሰብና የሕጉ አካል ማድረግ ያስፈልጋል ለማለት ነው፡፡ ቀድሞ መገመት ያልተቻለውንምና በሒደት ችግር ሲከተለው ደግሞ እየተከታተሉ ማስተካከል የፓርላማው ዓይነተኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ሕግ የሚያፀድቁት የፓርላማ አባላት ስለሆኑ እነሱም የቀረበላቸውን ረቂቅ ሕግ ከላይ በተጠቀሱት መሥፈርቶች ከገመገሙ በኋላ ነው መደገፍም ሆነ መቃወም ያለባቸው፡፡ እንደሚታወቀው ረቂቅ ሕግ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲላክ አጭር ማብራሪያም አብሮ ይላካል፡፡ ረቂቁን ያቀረበው አካል አብሮ የሚልከው ነው፡፡ አባላቱ ይህንን ማብራሪያ እንዳለ ሳይበሉ የራሳቸውን ጥናት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምንም እንኳን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለእያንዳንዱ የፓርላማ አባል አማካሪና ተመራማሪ ባይቀጥርላቸውም የቻሉትን ያህል መጣር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር እንዲኖርም ፓርላማው መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ረቂቅ ሕግን በአጭርና በተቻኮለ ጊዜ ሳያፀድቁ ማጤን ከሕግ አውጭ የሚጠበቅ ነው፡፡ በችኮላ በርካታ ሕግጋትን በማውጣት ረገድ የክልል ምክር ቤቶቻችን ወደር የላቸውም፡፡ በአንድ ዓመት ሦስት ወይም አራት ጊዜ ይሰበሰባሉ፡፡ ሁለት ወይ ሦስት ቀናት ይሰበሰቡና የቀረበላቸውን አዋጅ አፅድቀው ይበተናሉ፡፡ ሰከን ብሎ ረቂቅ ሕግን መመርመር አልተለመደም፡፡ የክልል ምክር ቤቶች ቋሚ አለመሆናቸው ለዚህ ችግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የምክር ቤት አባላትን ከማብዛት ቁጥራቸውን አነስ አድርጎ ቋሚ ማድረግ በአማራጭነት ሊታይ ይችላል፡፡ እንግዲህ የረቂቁን አንድምታ ለመረዳት ረቂቁን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያልተረዱትን ነገር አንድምታው ምን እንደሆነማ እንዴት መረዳት ይቻላል? የፓርላማችን ነገር የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ መጠነኛ ማሻሻያ በቋሚ ኮሚቴ አማካይነት ማድረግ፣ አልፎ አልፎ (እንደ ሊዝ አዋጁ) ሕገ መንግሥታዊነቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመክርበት ከማለት በስተቀር ከማፅደቅ ወደ ኋላ አይልም፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመት በአዋጅ ያቋቋማቸውን አስፈጻሚ አካላት መሥሪያ ቤቶችን ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲፈርሱ (እንዲታጠፉና ከእንደገና እንዲዋቀሩ) ረቂቅ አዋጅ ሲቀርብለት ከማፅደቁ አስቀድሞ ፓርላማው መቋቋማቸው ያመጣውን ጥቅም ያስከተለውን ጉዳት በመመርመር እንደ አዲስ ሲዋቀርም የሚኖረውን ጥቅምና ጉዳት በጥልቀት መዝኖ መሆን ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች፣ ዙሪያ መለስ አንድምታዎቹን በመገንዘብ እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለቀረቡ (ስለፈለጉት) ብቻ መቀበል ከሆነ የተቋቋመበትን ግብ መርሳት ነው፡፡ በመሆኑም ፓርላማው ከድርጅትነት ወደ ተቋምነት ለመሸጋገር መትጋት አለበት፡፡ የፓርላማ ጥንተ ተፈጥሮ ለመያዝ የሚያግዙ አሠራሮችን ማስፈን ይጠበቅበታል፡፡

የሕግ ማርቀቅ ጥበብነቱ ሌላው ተግዳሮት

ሕግ ማርቀቅ የራሱ የሆነ የተለየ ዕውቀትና ችሎታ እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሳይንስ ባህሪ አለው፡፡ ይሁን እንጂ በሳይንስነት ብቻ ሳይገደብ የጥበብነት ፀባይም አለው፡፡ እንደውም ሕግን ማርቀቅ ከሳይንሳዊነቱ ይልቅ የጥበብነት ፀባዩ ያመዝናል፡፡ አሥር ተቀራራቢ የሕግ ማርቀቅ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎችን ስለአንድ ጉዳይ ረቂቅ ሕግ እንዲያቀርቡ ቢደረግ አንድ ዓይነት ረቂቅ የማዘጋጀት ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው፡፡ በይዘት ብዙ ባይራራቁ እንኳን በአቀራረብና በአዘገጃጀት የመለያየቱ ነገር እሙን ነው፡፡ ስለሆነም የአርቃቂው ተፅዕኖ ስለሚጎላ ሳይንስነቱ አንሶ ጥበብነቱ አመዝኖ እናገኘዋለን፡፡ ከሳይንስነቱ ጥበብነቱ ከበዛ ሕግ አውጪን ፈታኝ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ጥበብነቱ ይዞት የሚመጣው መለያየትንም ከግንዛቤ ማስገባት ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ለፓርላማ አባላት ተጨማሪ ተግዳሮት ይሆናል፡፡ ፈጠራ ያስፈልገዋል፡፡ ጥበብነቱ፣ ፖሊሲን በአግባቡ ተገንዝቦና ተረድቶ ለፖሊሲው የሚስማማ ሕግ ማውጣት የራስን ፈጠራ ይጠይቃል፡፡ አርቃቂ ፖሊሲ አውጭ ሳይሆን ለፖሊሲው ሕጋዊ ማዕቀፍ አስቀማጭ/ሠሪ ነው፡፡ ከይዘት አንፃር ሲታይም ሌላ ፈተና አለው፡፡ በዚያ ላይ ሁሉም አዋጅ ይለያያል፡፡ ተመሳሳይ አዋጅ አይወጣም፡፡ ከተመሳሰለ ማውጣት አያስፈልግምና፡፡

በሕግ ማርቀቅ ባለሙያዎች ዘንድ የሚታወቁ ሁለት የረቂቅ ሕግ አዘገጃጀት ደንቦች አሉ፡፡ የመጀመርያው የምትለውን (ሕግ እንዲሆን የምትፈልገውን ነገር መወሰን) ነገር መወሰንና ያንኑ (ውሳኔውን ማስቀመጥ) ማለት ናቸው፡፡ እነዚህ ደንቦች መንግሥት የመረጠውን ፖሊሲ እንዲሁም አርቃቂው ሕግ ያበጀለትን ጉዳይ ብሎም አፅዳቂው የሚስማማበትንም የሚገልጹ ናቸው፡፡ አርቃቂው በማብራሪያው የጻፈውና ድንጋጌ የሆነው በትክክል መመሳሰላቸውን ይፈተሽባቸዋል፡፡

የሕግ ቋንቋ ጉዳይ ተጨማሪ ፈተና

ይህም ሆኖ በጥቅል ሲታይ አዲስ የሚወጣ ሕግ ግልጽ፣ ቀላል፣ እርስ በርስ የሚጣጣምና ወጥ እንዲሁም በቀላሉ ሊረዱት እንዲቻል ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡ ፈተናው፣ ሕግ የራሱ ቃላት ስላሉት፣ እንዲሁም አንዳንድ ቃላት ደግሞ ከፍ ያለ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ነው፡፡ የሕግ ቋንቋ ውስብስብነቱ ስለሚበዛ ዓላማውን ሲስት ይስተዋላል፡፡ የሕግ ዓላማ መብትንና ግዴታን በመለየት ለሚመለከተው ሰው ማሳወቅ ነው፡፡ ሰውም በቀላሉ መብትና ግዴታውን እንዲለይ በግልጽና ቀላል አገላለጽ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም የሕግ ቃላት በተቻለ መጠን መደበኛና የዘወትር እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ አስፈላጊ ሲሆን፣ ብቻ ቴክኒካዊ ቃልን መጠቀም የሚመከረው፡፡ ስለቆዳና ሌጦ ሕግ ሲወጣ ከቆዳና ሌጦ ጋር የተያያዙ ቴክኒካዊ ቃላት መጠቀም ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ይረዳል፡፡

የግልጽነት መጓደል ወጥ አለመሆን መደነጋገርን ያስከትላል፡፡ ለአብነት የንብረት ሕግ “የአላባ ጥቅም” (usufruct) በአንድ መጽሐፍ ላይ በተደነገገው የውርስ ሕግ ላይ ይህንኑ ጽንሰ ሐሳብ “የሪም መብት” ይለዋል፡፡ በንብረት ሕግ ላይ “ሁከት ይወገድልኝ” (action for possession) የሚለውን ተንቀሳቃሽ ንብረትን ማስያዣ (pledge) ስለማድረግ ላይ ተመሳሳይ ጽንሰ ሐሳብን “የእጅ ክስ” ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነት አደናጋሪ አገላለጽን ማስቀረት የሕግ አርቃቂም አፅዳቂም ግዴታ ነው፡፡  ከላይ እንደገለጽነው አንዳንድ ቃላት ደግሞ ልዩ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “ቃል ይገላል፣ ቃል ያድናል” እንደሚባለው ሁሉ ቃል መብት ያስገኛል፤ መብት ያሳጣል፡፡ ግዴታ ይጥላል፤ ከግዴታ ነፃ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑትና ወይም ናቸው፡፡ እና በሚሆንበት ጊዜ የተያያዙት ነገሮችን ሁለቱንም ሲያመለክት ወይም ደግሞ ከሁለት አንዱ አማራጭ ያቀርባል፡፡ ከቃላት አጠቃቀም ባለፈም የዓረፍተ ነገር አወቃቀርና ርዝመትም ለሕግ አዉጪ አስፈላጊ መርሆናች ናቸው፡፡ ሰዋ ሰዋዊ አወቃቀሩ የተስተካከለና የቋንቋ ሕግጋትን ያከበረ እንዲሁም አጭር ዓረፍተ ነገር የተገለጸ መሆኑ በቀላሉ ለመረዳት ያግዛል፡፡ አንድንድ ድንጋጌዎች 70 እና 80 ቃላትን የያዘ አንድ ዓረፍተ ነገር ማግኘት ብዙም አይከብድም፡፡ ለምሳሌ ያህል የተጨማሪ ዕሴት ታክስ አዋጁን ገለጥ ላደረገ ሰው እውነት መሆኑን በቀላሉ ይረዳል፡፡

የሐሳብ አወቃቀርንም በሚመለከት ተያያዥና ጭብጣቸው ተመሳሳይ የሆኑ ሐሳቦችን በአንድ ክፍል፣ አንቀጽ ወዘተ. ማድረግ፡፡ ይህ ለአንባቢው በተሻለ ሁኔታ ግልጽ እዲሆን እንዲረዳውም ያደርጋል፡፡ ሙሉ አዋጅን በማንበብ ጊዜ ላለማባከን ሲባል ርዕስ እንዲኖረው ማድረግ፤ ማውጫ ማዘጋጀት በበርካታ አገሮች የሕግ አወጣጥ ደንብ ላይ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ በኢትዮጵያ በመጽሐፍ መልክ ከታተሙት ሕግጋት ውጭ አዋጅ ላይ ማውጫ ማስቀመጥ እምብዛም አልተለመደም፡፡ ከመቶ ገጽ በላይ ያለው አዋጅ ማውጫ ሲኖረው አይስተዋልም፡፡ ሌላው፣ ሕግ መብት የሚሰጥ፣ ግዴታ የሚጥል ስለሆነ ተነባቢነት እንዲሆን ማድረግ ከሕግ አውጭም ከአርቃቂውም የሚጠበቅ ግዴታ ኃላፊነት ነው፡፡ ተነቦ የሚገባ፣ ሊረዱት የማያዳግት መሆን አለበት፡፡ የመርህና የበስተቀር አጻጻፍንም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡

ለማጠቃለል ያህል አዋጅ የራሱ መዋቅር አለው፡፡ ርዕስ፣ ማውጫ፣ ትርጓሜና ጥቅል መርሆች ቀጥሎ መብትና ግዴታ የሚጥሉ አንቀጾች፣ የሥነ ሥርዓት ጉዳዮች (አስተዳደራዊውን ጨምሮ)፣ የቅጣት፣ አስፈጻሚ ተቋም፣ የተሻሩ፣ የመሸጋገሪያ፣ ተፈጻሚነቱ የሚጀምረበት ቀን ወዘተ. መያዝ አለበት፡፡ ይህ አጽመ ቅርፁ ነው፡፡ በዚህ ቅርፅ የሚወጣውን ሕግ የታሰበለትን ዓላማ ማሳካቱን መከታተል ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሕግን አውጥተው አይጥሉትም፡፡ ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጉታል እንጂ፡፡ ስለሚያወጡት (ስላወጡት) ሕግ ማወቅ ይገባል፡፡ አህያ የተጫነችውን አታውቅም መሆን የለበትም፡፡ ሳያውቁት መደገፍ፣ ወይም መቃወምም እንደራሴነትን አለመወጣት ነው፡፡ የሚወጣውም ሕግ ለሕዝብ መድረስ አለበት፡፡ መታተም አለበት፡፡ በርካታ አገሮች አዋጆች (ደንብና መመርያ ወዘተ.) የሚታተምበት ወረቀት፣ የአስተታተሙ ዓይነት፣ የሚታተምበትን የቀለም ዓይነት ምን መምሰል እንዳለበት ሕግ አላቸው፡፡ መጀመርያ ላይ እንደ አዲስ የሚወጣ ሕግንና ዋናውን ሳይሻርና ሳይለወጥ ነገር ግን ማሻሻያ በሚኖርበት ጊዜ  የማሻሻያ ኅትመት፣ ወረቀት፣ ቀለም፣ የራስጌና የግርጌ ሁኔታው እንዲለይ ያደርጋሉ፡፡ ከማሻሻያው በኋላ የሚታተም የቀድሞው ሕግ ማሻሻያውንም እንዲጨምር ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ አሁን ላይ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ሲታተም በዚህ ሕግ ላይ ተደረጉትን ማሻሻያዎች በአባሪነት ጨምሮ ሊታተም ይገባል እንደማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፓርላማም በተፈጠረበት አማናዊ ዓላማ ያሳካ ዘንድ ማስተካከል ካለበት ጉዳዮች የተወሰኑት በሦስት ክፍል አመላክተናል፡፡ ፓርላማውን ተቋማዊ አሠራር እንዲኖረው የሚረዱ ነጥቦች ተጠቋቁመዋል፡፡ ከተገለጸው ያልተነካው እንደሚበዛ በማመን ፓርላማውን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ በርካታ ጉዳዮች ለመኖራቸው በሦስት ክፍል በተከታታይ የቀረቡት ዋቢ ናቸው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...