Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበኢትዮጵያ ቢዝነስ ማከናወን ምን ያህል ቀላል ነው?

በኢትዮጵያ ቢዝነስ ማከናወን ምን ያህል ቀላል ነው?

ቀን:

በሸዋዬ ተስፋዬ

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ ድርሻ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይኼም አገሪቱ በዝቅተኛ ገቢ ደረጃ የምትገኝ በመሆኗ፣ እንዲሁም በቀድሞ ሥርዓት ትከተል በነበረው የዕዝ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ተግባር ላይ በዋለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ አበረታች ዕድገት ቢያሳይም፣ እስካሁን ድረስ የሚጠበቀው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በተለይ ደግሞ የአገር ውስጥ መዋዕለ ንዋይ በአገራችን አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የኢንቨስትመንት ሕግና ማበረታቻዎችን ለማሻሻል ተደጋጋሚ ዕርምጃዎች የወሰደ ቢሆንም፣ በ2009 ዓ.ም. የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 3.26 ቢሊዮን ዶላር ያህል ነበር፡፡ ይኼም ከአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ የሚይዘው ድርሻ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአገራችን ካለው የግል ዘርፍ አቅምና ልምድ ማነስ አኳያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘመናዊ የኮርፖሬት አመራር፣ የቢዝነስ አስተዳደር፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይገመታል፡፡

በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለመድረስ ኢትዮጵያ በያዘችው ራዕይ፣ እንዲሁም ይኼን ለማሳካት በወጠነችው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት ባለፉት ዓመታት ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ቢሆንም፣ ይህ በአመዛኙ በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚመራና የግል ዘርፍ እንቅስቃሴን ለማበረታታት እምብዛም ትኩረት እንዳልሰጠ ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ ለአገራችን ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ፣ ከወዲሁ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችሉ አመቺ ፖሊሲዎችና የአሠራር ደንቦች ሊቀረፁና ሊተገበሩ ያስፈልጋል፡፡

የጽሑፉ ዓላማ በአገራችን የቢዝነስ ሥራን ለማካሄድ የሚያጋጥሙ አዳጋች የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት ሒደቶችን ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር በማሳየት ወደፊት ሊወሰዱ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን መጠቆም ነው፡፡ ይኼም የቢዝነስ ሥራን በማካሄድ በአገር ውስጥ ድርጅቶች ላይ የሚፈጸም የአሠራር ሥርዓትና የቁጥጥር መረጃዎችን በአኃዝ በማጠናቀር፣ 190 አገሮች ያላቸውን የአፈጻጸም ደረጃ በንፅፅር በሚያመለክተው እ.ኤ.አ. በ2018 ዓለም ባንክ ያዘጋጀው ዘገባ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በእዚህ ዘገባ የሚጠናቀር የአገሮች አፈጻጸም ደረጃ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸው የዜና አውታሮች አማካይነት አገሮች በሚያሠራጩት የንግድ ማስታወቂያ በግልጽ የሚጠቀስ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ድንበር ዘለል የንግድ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በልዩ ልዩ መስኮች በኢንቨስትመንት ሊሰማሩ የሚችሉባቸውን አገሮች ለመለየት የሚያገለግል በመሆኑ በእዚህ ረገድ የሚኖረውን ፋይዳ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

- Advertisement -

      የጽሑፉ ይዘት በሦስት ምዕራፎች የተሰናዳ ሲሆን፣ የመጀመርያው በአገራችን የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በአጭሩ ያብራራል፡፡ ከእዚህ በማስከተል በኢትዮጵያ የቢዝነስ ሥራን ለማካሄድ ያለውን የቅለት ደረጃ በአጠቃላይ፣ እንዲሁም ለመስኩ እንቅስቃሴ አስፈላጊ በሆኑ አሥር ዓብይ ፈርጆች ያለውን አፈጻጸም ከዓለምና ከአኅጉራችን አገሮች ጋር በንፅፅር ያቀርባል፡፡ በመጨረሻም በአገራችን ቢዝነስን በቀላል የአሠራር ሥርዓትና ምክንያታዊ ቁጥጥር ለማካሄድ የሚያስችሉና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚያስፈልግ ማሻሻያዎችን ይጠቁማል፡፡

የግል ዘርፍ ዕድገት ተግዳሮቶች

      በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ተግዳሮቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም አነስተኛ መዋዕለ ንዋይ፣ ዝቅተኛ የቢዝነስ ክህሎት፣ የቢዝነስ አስተዳደርና የኮርፖሬት ሥራ አመራር ክህሎት ያለመዳበር፣ በቂ የቢዝነስ ምክርና ድጋፍ አገልግሎት ያለመኖር፣ ዝቅተኛ የንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር፣ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድና የሙስና አሠራር፣ የቴክኒክና የሙያ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረት፣ ፍትሐዊ የንግድ ውድድርና አሠራር ያለመዳበር፣ የተረጋጋ ፖሊሲ የአሠራር መመርያና የቁጥጥር ሥርዓት ያለመስፈን፣ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት ልምድ ያለመዳበር፣ እንዲሁም የንግድና ዘርፍ ማኅበራት እንቅስቃሴ የተጠናከረ ያለመሆን በቅድሚያ ይጠቀሳሉ፡፡

      ከእነዚህ ተግዳሮቶች መሀል የንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎት አቅርቦት በግል ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ፣ ለማሳያ ያህል ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ በእዚህ ረገድ የዓለም ባንክ ባዘጋጀው ዘገባ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2018 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሎጂስቲክስ አገልግሎት አማካይ አፈጻጸም ከዜሮ እስከ አምስት በሆነ መለኪያ 2.40 ሲሆን፣ ይህም ከ167 አገሮች 131ኛ ደረጃ ያስይዛታል፡፡ ከእዚህ በማያያዝ በስድስት የንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዓብይ ዘርፎች ያለው አፈጻጸም ጉምሩክ 2.54 ወይም 79ኛ፣ መሠረተ ልማት 2.13 ወይም 140ኛ፣ ዓለም አቀፍ የመርከብ ጭነት 2.54 ወይም 112ኛ፣ የሎጂስቲክስ ጥራትና ብቃት 2.39 ወይም 119ኛ፣ ጭነትን መለየትና መከታተል 2.24 ወይም 145ኛ፣ እንዲሁም የጭነት በጊዜ መድረስ 2.49 ወይም 158ኛ ደረጃ በመያዝ በዝቅተኛ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ትመደባለች፡፡

      በሌላ በኩል በአገራችን የግል ዘርፍ በዕውን እሴት ከሚጨምር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይልቅ በችርቻሮ ንግድና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች የጎላ እንቅስቃሴ የሚታይ ሲሆን፣ ይህም ለዘርፉ በቂ ማበረታቻ ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ይገመታል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ቢሆን የአገራችን ተወዳዳሪነት ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ የአኅጉራችን አገሮች ጋር በንፅፅር ዝቅተኛ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ከእዚህ አንፃር አብዛኛው የግል ዘርፍ ቢዝነስ እንቅስቃሴ ተወዳዳሪነትን በረዥም ጊዜ ከማሳደግና ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ትስስርን ከማጠናከር ይልቅ፣ በአጭር ጊዜ ትርፍ በሚያስገኙ መስኮች ላይ ትኩረት ማድረግ ዘርፉ ዘላቂ ዕድገት እንዳይኖረው አስችሏል፡፡

      በመንግሥት የልማት ድርጅቶችና በፓርቲዎች ይዞታነት በሚካሄዱ የንግድ ድርጅቶች ተወዳዳሪነትን ከማጠናከር ይልቅ፣ በአድልዎና ድጋፍ (በውጭ ምንዛሪ ፈቃድ፣ የባንክ ብድር፣ የመንግሥት ግዥ ኮንትራት፣ ወዘተ.) እንደሚንቀሳቀሱ ያለው ጥርጣሬ በግል ዘርፍ ዘላቂ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላል የሚገመት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም መንግሥት ከብድርና ከሌሎች ምንጮች የሚያውለው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደሩ፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ በመጨረሻም ባለፉት ዓመታት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የፖለቲካ ያለመረጋጋት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትና የግል ዘርፍ እንቅስቃሴን በማዳከም ተፅዕኖ ማስከተሉ አይካድም፡፡

ቢዝነስን የማካሄድ ቅለት

      የዓለም ባንክ በአገር ውስጥ የቢዝነስ ድርጅቶች ላይ ያለውን ቁጥጥርና የአሠራር ሒደት በቢዝነስ እንቅስቃሴ ዑደት አስፈላጊ በሆኑ አሥር ዓብይ ፈርጆች አኃዛዊ መረጃ በማጠናቀር ይመዝናል፡፡ በእዚህ መልክ ቢዝነስን የማካሄድ አሠራርና የቁጥጥር ሥርዓት ቅለት ደረጃን በ190 አገሮች በንፅፅር ያመለክታል፡፡ ይኼም ከዓመቱ የላቀ አፈጻጸም አንፃር በእያንዳንዱ አገር ያለውን ክፍተት የሚያመለክት ሲሆን፣ ዓላማውም የዓለም አገሮች ብቃት ያለው የቢዝነስ አሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት እንዲቀርፁና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን በየጊዜው ተግባር ላይ እንዲያውሉ ማበረታታት ነው፡፡ ቢዝነስን በማካሄድ ዑደት አስፈላጊ በሆኑ አሥር ፈርጆች የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት ቅለት ደረጃ መለኪያዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡ እነዚህም፣

 1. የቢዝነስ ሥራን መጀመር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ሒደቶች፣ የሚወስድ ጊዜና የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታል መጠን፣
 2. የግንባታ ፈቃድ ማግኘት የማከማቻ መጋዘን ሕንፃ ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ ሒደቶች፣ የሚወስድ ጊዜና ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት የሚጠይቅ ወጪ መጠን፣
 3. የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ማግኘት፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመር አገልግሎት ለማግኘት የሚያስፈልጉ ሒደቶች፣ የሚወስድ ጊዜና የሚጠይቅ ወጪ መጠንና የአቅርቦት አስተማማኝነትና የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ግልጽ መሆን፣
 4. ንብረትን ማስመዝገብ ንብረትን ለማስተላለፍ የሚያስፈልጉ ሒደቶች፣ የሚወስድ ጊዜና የሚጠይቅ ወጪ መጠን እንዲሁም የቦታ አስተዳደር ሥርዓት ጥራት፣
 5. ብድር ማግኘት ተንቀሳቃሽ የብድር ዋስትና መያዣና የብድር መረጃ ሥርዓት፣
 6. አነስተኛ የኢንቨስትመንት ድርሻ ላላቸው ከለላ መኖር አነስተኛ ባለድርሻዎች በድርሻ ልውውጥና በኮርፖሬት አመራር ያላቸው መብቶች፣
 7. የታክስ ክፍያ መፈጸም በንግድ ሥራ ድርጅት ሁሉንም የታክስ መመርያዎችና ድኅረ ማሳወቂያ የአሠራር ሒደቶችን ለማሟላት የሚያስፈልጉ ክፍያዎች፣ የሚወስድ ጊዜና ጠቅላላ የታክስ ምጣኔ፣
 8. የጠረፍ ማዶ ንግድ ማከናወን አንፃራዊ ብልጫ ያላቸው ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚወስድ ጊዜና የሚያስፈልግ ወጪ መጠን፣
 9. የውል ስምምነትን ማስፈጸም የንግድ ክርክር (አቤቱታ) ለመፍታት የሚወስድ ጊዜና የሚያስፈልግ ወጪ እንዲሁም የፍርድ ሒደቶች ጥራት፣
 10.  ለብድርና ዕዳ ያለመክፈል መፍትሔ መኖር የንግድ ብድርና ዕዳ ማስከፈል ውጤት፣ ለእዚህ የሚወስድ ጊዜና የሚያስፈልግ ወጪ እንዲሁም ለብድርና ዕዳ ማስከፈል ያለው የሕግ ማዕቀፍ ጥንካሬ ናቸው፡፡

      እዚህ ላይ ማንኛውንም መደበኛ ቢዝነስ ለማካሄድ በቅድሚያ የሕግ ዕውቅና ማግኘት፣ በመቀጠል ደግሞ ፍትሐዊ የንግድ አሠራር ሥርዓት በመከተል በውድድር እንዲመራ በሁሉም አገሮች ከዚህ በላይ በተዘረዘሩ አሥር ዓብይ ፈርጆችና በሌሎችም ጉዳዮች አግባብነት ያለው የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት መከተል እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማካሄድ ረዥም ጊዜ የሚወስድ የቢሮክራሲ አሠራርና ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል የአስተዳደር ጫና መኖር፣ ዜጎች በመስኩ እንዲሰማሩ የማይጋብዝና የማያደፋፍር ከመሆኑም በላይ ቀልጣፋና ብቃት ያለው ቢዝነስ ለማካሄድ አዳጋች ይሆናል ብሎም በድርጅቶች ትርፋማነትና ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ይህም መስኩ ልዩ ልዩ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት፣ እንዲሁም በታክስ ክፍያ የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ያዳክማል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 የዓለም ባንክ ባዘጋጀው ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለማካሄድ ያለው የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት ቅለት ደረጃ መለኪያ ውጤት 47.77 ሲሆን፣ ይህም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አማካይ 50.43 ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ውጤት ኢትዮጵያን ከ190 የዓለም አገሮች 161ኛ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 48 አገሮች 31ኛ ረድፍ ያሠልፋታል፡፡

በሌላ በኩል ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 48 የአፍሪካ አገሮች መሀል የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ አገሮች በቅደም ተከተል ሞሪሸስ (77.54) ከአኅጉሪቱ 1ኛ ከዓለም 25ኛ፣ ሩዋንዳ (73.40) ከአኅጉሪቱ 2ኛ ከዓለም 41ኛ፣ ኬንያ (65.15) ከአኅጉሪቱ 3ኛ ከዓለም 80ኛ፣ ቦትስዋና (64.90) ከአኅጉሪቱ 4ኛ ከዓለም 81ኛ፣ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ (64.89) ከአኅጉሪቱ 5ኛ ከዓለም 82ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡

ሠንጠረዥ 1 በኢትዮጵያ ቢዝነስን የማካሄድ ቅለት ዓብይ መለኪያዎች (እ.ኤ.አ. 2018)

 

ተ/ቁ

 

ዝርዝር መለኪያዎች

 

ኢትዮጵያ

 

ከሰሃራ በታች አፍሪካ አገሮች አማካይ

ከቀላል ያለ ርቀት

(ከ0 -100)

 

ደረጃ (ከ190 አገሮች

 

ከቀላል ያለ ርቀት

(ከ0 -100)

1

የቢዝነስ ማካሄድ ቅለት

47.77

161

50.43

2

የቢዝነስ ሥራን መጀመር

68.43

174

76.82

3

የግንባታ ፈቃድ ማግኘት

50.55

169

56.91

4

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ማግኘት

59.29

125

45.91

5

ንብረትን ማስመዝገብ

51.32

139

51.71

6

ብድር ማግኘት

15.00

173

40.73

7

አነስተኛ የኢንቨስትመንት ድርሻ ላላቸው ከለላ መኖር

28.33

176

43.72

8

የታክስ ክፍያ መፈጸም

62.14

133

57.49

9

ጠረፍ ማዶ ንግድ ማካሄድ

45.34

167

52.56

10

የውል ስምምነትን ማስፈጸም

59.99

68

48.14

11

ለብድርና ዕዳ ያለመክፈል መፍትሔ መኖር

37.31

122

30.28

Source: World Bank, 2018: Doing Business 2018 – Reforming to Create Jobs.

      ከላይ ከተጠቀሰው ዝቅተኛ አማካይ አፈጻጸም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቢዝነስን ለማካሄድ አስፈላጊ ከሆኑ ዝርዝር የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት መለኪያ ፈርጆች መሀል፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አማካይ የተሻለ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ እነዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ማግኘት፣ የታክስ ክፍያ መፈጸም፣ የውል ስምምነትን ማስፈጸም፣ እንዲሁም ለብድርና ዕዳ ያለመክፈል መፍትሔ መኖር ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በቀሩት ስድስት መለኪያ ፈርጆች ማለትም የቢዝነስ ሥራን መጀመር፣ የግንባታ ፈቃድ ማግኘት፣ ንብረትን ማስመዝገብ፣ ብድር ማግኘት፣ አነስተኛ የኢንቨስትመንት ድርሻ ላላቸው ከለላ መኖር፣ እንዲሁም የጠረፍ ማዶ ንግድ ማካሄድ በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳየች መሆኑን ሠንጠረዡ መግለጹን ያመለክታል፡፡

ቢዝነስን በቀላል ለማካሄድ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች

      ይህ ምዕራፍ በቅድሚያ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ ተግባር ላይ የዋሉ የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት ማሻሻያዎችን በአጭር ይዳስሳል፡፡ እነዚህም ቢዝነስን በቀላሉ ለማካሄድ የሚያስችሉና በተቃራኒ ቢዝነስን ለማካሄድ አዳጋች የሆኑ በሚል ይመደባሉ፡፡ በመቀጠል ከእዚህ መንደርደሪያ በመነሳት የቢዝነስ አሠራር ቁጥጥር ሥርዓትን ቀለል በማድረግ፣ በአሁኑ ጊዜ እየተጠናከረ በመጣው ዓለም አቀፍ ትስስር አገራችን የተሻለ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ይጠቁማል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ በኢትዮጵያ የቢዝነስ አሠራርና ቁጥጥር ሥርዓትን ለማቅለል ከተወሰዱ ማሻሻያዎች መሀከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም፣

 • እ.ኤ.አ. በ2010 የቢዝነስ ሥራን መጀመር ቀላል ለማድረግ የተቀናጀ የንግድ ምዝገባ አሠራር ሒደት መከተል፣ የንብረት ማስተላለፍ ምዝገባን በቀላል ለማካሄድ አስተዳደራዊ ተግባራትን ባልተማከለ ሥርዓት ወደ በታች ዕርከን በማዛወር፣ እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት የቦታ ምዝገባ ሒደቶችን በተቀናጀ መልኩ በማከናወን፣ የተከማቹ ጉዳዮችን በመቀነስ፣ የጉዳዮች ሥራ አመራርን በማሻሻልና የውስጥ ሥልጠና በመስጠትና የፍርድ አስፈጻሚውን ሚና በማሻሻል በፍርድ ቤቶች ያለውን መዘግየት በመቀነስ የውል ስምምነትን በቀላል ማስፈጸም፣
 • እ.ኤ.አ. በ2011 የጠረፍ ማዶ ንግድን በቀላል ለማካሄድ ብቃት የጎደለው የውስጥ ቢሮክራሲ አሠራር ማሻሻያ ማድረግ፣
 • እ.ኤ.አ. በ2013 የብድር መረጃዎችን በኢንተርኔት መረብ አማካይነት በቀጥታ ለመለዋወጥና የግል መረጃዎችን በመከታተል ተበዳሪዎች ለሚኖራቸው መብት ዋስትና በመስጠት በቀላሉ ብድር ማግኘት እንዲቻል መደረጉ፣
 • እ.ኤ.አ. በ2016 የንግድ ድርጅት ስያሜን ለማፅደቅ የሚያስችል ግልጽ የአሠራር መመሪያ በማዘጋጀት የቢዝነስ ሥራን በቀላል መጀመር እንዲቻል መደረጉ፣
 • እ.ኤ.አ. በ2018 ለንግድ ድርጅት ምዝገባ የሚያስፈልግ የባንክ ሒሳብ መክፈትና ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀረት የቢዝነስ ሥራን በቀላል መጀመር እንዲቻል፣ እንዲሁም የጠረፍ ማዶ ንግድን በቀላል ለማካሄድ በሥጋት መጠን ላይ የተመሠረት የክትትል ሥርዓት መዘርጋት፣ የውጭ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስመጡ (አስመጪ) ድርጅቶች ሰነዶችን በማቀናጀትና የጉምሩክ ባለሥልጣን በማጠናከር የተወሰዱ ዕርምጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡

      ከእዚህ ተቃራኒ በአገራችን ከተወሰዱና ቢዝነስን ለማካሄድ አዳጋች ከሆኑ ዕርምጃዎች መሀል የሚከተሉት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም፣

 • እ.ኤ.አ. በ2012 የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የነበረው መዘግየት ይበልጥ አስቸጋሪ መሆኑ፣
 • እ.ኤ.አ. በ2013 የተጀመረው የማኅበራዊ ዋስትና ክፍያ የታክስ ክፍያን ለመፈጸም አስቸጋሪ መሆኑ ይጠቀሳሉ፡፡

      ከእዚህ በላይ ከቀረበው ማብራሪያ በመነሳት በመጪው ጊዜ በኢትዮጵያ የቢዝነስ አሠራር ቁጥጥር ሥርዓትን ቀለል ለማድረግ፣ በቅድሚያ ከእዚህ በታች የተዘረዘሩ ስድስት ዓብይ የቢዝነስ ዑደት ፈርጆች አግባብነት ያላቸው ማሻሻያዎችን በተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም፣

 • ብድር ማግኘት ተንቀሳቃሽ የብድር ዋስትና መያዣና የብድር መረጃ ሥርዓትን የሚመለከቱ የሕግ መብቶች ጥንካሬ መለኪያ (ከ0 እስከ 12 ሚዛን) 3፣ የብድር መረጃ ሥርዓት ጥልቀት መለኪያ (ከ0 እስከ 8 ሚዛን) 0፣ የብድር መረጃ ቢሮ ሽፋን (ከጠቅላላ ጎልማሶች ያለው ድርሻ) 0፣ እና የብድር ምዝገባ ሽፋን (ከጠቅላላ ጎልማሶች ያለው ድርሻ) 0.3 በመቶ መሆን፣
 • አነስተኛ የኢንቨስትመንት ድርሻ ላላቸው ከለላ መኖር አነስተኛ ባለድርሻዎች በድርሻ ልውውጥና በኮርፖሬት አመራር ያላቸው መብቶችን የሚመለከቱ በይፋ የመግለጽ መጠን መለኪያ (ከ0 እስከ 10 ሚዛን) 3፣ በዳይሬክተር ለሚኖር ዕዳ ዋስትና መጠን መለኪያ (ከ0 እስከ 10 ሚዛን) 0፣ በባለድርሻዎች ክስን በቀላል የማቅረብ መጠን መለኪያ (ከ0 እስከ 10 ሚዛን) 2፣ የባለድርሻዎች መብቶች መጠን መለኪያ (ከ0 እስከ 10 ሚዛን) 5፣ የባለቤትነትና ቁጥጥር መጠን መለኪያ (ከ0 እስከ 10 ሚዛን) 3፣ እና የኮርፖሬት ግልጽ አሠራር መጠን መለኪያ (ከ0 እስከ 10 ሚዛን) 4፣
 • የጠረፍ ማዶ ንግድ ማከናወን ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አስፈላጊ ሰነዶችን ለማሟላት 76 ሰዓት የሚወስድና 175 ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ የጠረፍ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት 51 ሰዓት የሚወስድና 172 ዶላር የሚፈልግ መሆኑ፣ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት አስፈላጊ ሰነዶችን ለማሟላት 194 ሰዓት የሚወስድና 750 ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ የጠረፍ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት 166 ሰዓት የሚወስድና 738 ዶላር የሚፈልግ መሆኑ፣
 • የግንባታ ፈቃድ ማግኘት የማከማቻ መጋዘን ሕንፃ ግንባታ ለማጠናቀቅ 13 ሒደቶች የሚያስፈልጉ፣ 130 ቀናት የሚወስድ፣ እንዲሁም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት የሚጠይቀው ወጪ መጠን ከግንባታው ጠቅላላ ወጪ 16.5 በመቶ ሲሆን የግንባታ ጥራት ቁጥጥር መለኪያ (ከ0 እስከ 15 ሚዛን) 7.0 መሆኑን ያመለክታል፣
 • ንብረትን ማስመዝገብ ንብረትን ለማስተላለፍ 7 ሒደቶች የሚያስፈልጉ፣ 52 ቀናት የሚወስድና ከንብረቱ ዋጋ 6 በመቶ ያህል ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ የቦታ አስተዳደር ሥርዓት ጥራት መለኪያ (ከ0 እስከ 30 ሚዛን) 6.0 መሆኑ፣
 • የቢዝነስ ሥራ መጀመር 12 የአሠራር ሒደቶች የሚከተል፣ 33 ቀናት የሚወስድ፣ እንዲሁም ከነፍስ ወከፍ ገቢ 57.8 በመቶ ያህል ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል እንደሚፈልግ ያመለክታል፡፡

      ከእዚህ በመቀጠል ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በተቀሩትና ከእዚህ በታች በተመለከቱ አራት ዓብይ የቢዝነስ ዑደት ፈርጆች ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ጋር በንፅፅር የተሻለ አፈጻጸም ያሳየች ቢሆንም፣ እየተጠናከረ በመጣው ዓለም አቀፍ ትስስር ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን አስፈላጊ ማሻሻያዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም፣

 • የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ማግኘት ከኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመር አገልግሎት ለማግኘት አራት የአሠራር ሒደቶች የሚያስፈልጉ፣ 95 ቀናት የሚወስድ ከነፍስ ወከፍ ገቢ 1027.9 በመቶ ያህል ወጪ የሚያስከትል ሲሆን፣ የአቅርቦት አስተማማኝነትና የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ግልጽ መሆን መለኪያ (ከ0 እስከ 8 ሚዛን) 0 መሆኑ፣
 • ታክስ ክፍያ መፈጸም በንግድ ሥራ ድርጅት ሁሉንም የታክስ መመሪያዎችና ድኅረ ማሳወቂያ የአሠራር ሒደቶችን በዓመት ለማሟላት 30 ክፍያዎች የሚያስፈልጉ፣ 306 ቀናት የሚወስድና በአጠቃላይ ታክስና ሌሎች ክፍያዎች ከትርፍ 38.6 በመቶ ድርሻ እንደሚይዙ እንዲሁም ለታክስ ክፍያ ገቢን የማስመዝገብ መለኪያ (ከ0 እስከ 100 ሚዛን) 50.89 መሆኑ፣
 • የውል ስምምነትን ማስፈጸም የንግድ ፍትሕ ብሔር ክስ ውሳኔ ለመድረስ 530 ቀናት የሚወስድና በክስ የተጠየቀውን ዋጋ 15.2 በመቶ ያህል ወጪ የሚያስከትል እንዲሁም የፍትሕ ሒደት ጥራት መለኪያ (ከ0 እስከ 18 ሚዛን) 5.5 መሆኑ፣
 • ለብድርና ዕዳ ያለመክፈል መፍትሔ መኖር የንግድ ብድርና ዕዳ ማስከፈል ሦስት ዓመት እንደሚወስድና የንብረቱን ዋጋ 14.5 በመቶ ያህል ወጪ እንደሚያስከትል፣ እንዲሁም ለብድርና ዕዳ ማስከፈል ያለው የሕግ ማዕቀፍ ጥንካሬ መለኪያ (ከ0 እስከ 16 ሚዛን) 7.0 መሆኑ፣

      ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለመድረስ በሰነቀችው ራዕይ መንግሥት በልዩ ልዩ መስኮች ከሚያደርገው የልማት ጥረት ጎን ለጎን፣ የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴና የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲጠናከር የቢዝነስ ሥራን በቀላሉ ለማካሄድ የሚያስችሉ የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን፣ ይኼም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ መጠን እንደሚያሳድግ ይታወቃል፡፡

      በእዚህ ረገድ ሊወሰዱ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያንፀባርቁ፣ የኢትዮጵያን አፈጻጸም በአሥር ዓብይ ፈርጆች በተካተቱ የአሠራርና ቁጥጥር ሥርዓት መለኪያዎች ከሌሎች የአኅጉራችን አገሮች ጋር በንፅፅር በማሳየት በመጪው ጊዜ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚያስፈልግ ማሻሻያዎችን በመጠቆም ጽሑፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል የተነጣጠሉ ማሻሻያዎችን በአዝጋሚ ሒደት ለመተግበር ከመወጠን ይልቅ፣ ከአጠቃላይ የማሻሻያ ማዕቀፍ በመነሳት ሁሉን አቀፍ ተያያዥና ተዛማጅ ዕርምጃዎችን ማቀድ አመርቂ ውጤት ለማሳየት እንደሚያግዝ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻም በመስኩ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን የአንድ ወቅት ተግባር እንደሆኑ ከመገንዘብ ይልቅ፣ በየጊዜው አገራችን ያላትን አፈጻጸም ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር በመፈተሽ አግባብነት ያላቸው ማሻሻያዎችን በተከታታይ ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት እንዲሰጥ ጽሑፉ አበክሮ ያስገነዝባል፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...