Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉአንዳንድ ጥያቄዎች

አንዳንድ ጥያቄዎች

ቀን:

በአንዳርጋቸው አሰግድ

ለ2012 ዓ.ም. ፌዴራል ምክር ቤት ምርጫ የቀሩት 21 ወራት ናቸው፡፡ ለምረጡኝ ዘመቻ የሚውሉት ወራት ሲቀነሱ፣ የሚቀሩት ወራት ወደ አሥር ይወርዳሉ፡፡ “ይከፋፈላል”፣ “እንዲያውም ሳይፈርስና ሳይበተን አይቀርም” ሲባልለት የነበረው ኢሕአዴግ፣ የዜና ማሠራጫዎችን ሲያጨናንቅ ከረመ፡፡ የአባል ድርጅቶቹ ጉባዔዎች “መታደሳቸውን” እያወጁ ተጠናቀቁ፡፡ ወጣቶችንና የተማሩ ግለሰቦችን አካተው ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ እየተሠለፉ መሆናቸው ግልጽ ሆኗል፡፡ ወጣቶችና የተማሩ ግለሰቦች መካተታቸው መልካም ነው፡፡ አንዱን ወይም ሌላውን የኢሕአዴግ ድርጅት የተቀላቀሉት የተማሩ ግለሰቦች የፓርቲ ምሁራን ሆነው ያበቁ እንዲሆን፣ ወይም ምሁር ከሚባለው ጎራ ይቆዩ እንደሆነ ወደፊት ይታያል፡፡

ምሁር የአንዱ ወይም የሌላው የብሔር ድርጅት ንብረት አይደለም፡፡ የአደባባይ ንብረት (ወይም የአደባባይ ብሔር) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የምሁር ቤቱ (ወይም ብሔሩ) ነፃ ሐሳቢነቱ ነው፡፡ ለሐሳብ ነፃነቱ ያለው ቀናዊነቱ ነው፡፡ ለመሠረተ ጭብጥ (Fact Based) ሂሳዊ ትንተና ያለው ፅኑ አቋምና ፍቅር ነው፡፡ የአደባባይ ምሁር (Public Intellectual) ይባላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምሁራን ናቸው የአገዛዝ ሥርዓቶችን ጉድፎች በሒሳዊ ትንተና እየለቀሙ የኅብረተሰቦች ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ሲያግዙ የኖሩት፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር ጋዜጣ ኢሕአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚባለውን የድርጅቱን ርዕዮተ ዓለም የሚተካ ርዕዮተ ዓለም ተጠንቶ በመጪው ጉባዔ እንዲቀርብ (በ11ኛ ጉባዔው) ወስኗል በማለት ቢዘግብም (ሪፖርተር መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም)፣ በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የተሠራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር አስተባብለዋል (አይጋ ፎረም፣ ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡፡ ወ/ሮ ፈትለወርቅ አክለውም፣ ‹‹አንዳንድ የግንባሩ ብሔራዊ ድርጅቶች አባላት ግንባሩ የሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራም መለወጥ አለበት የሚል ሐሳብ አንስተው ነበር። ውይይት ከተደረገበት በኋላ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራምን ይዞ ለመቀጠል ከስምምነት ተደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

ለጥናቱ ሁለት ዓመት ሙሉ የሚያስፈልግበት ምክንያት ከበፊቱም ግልጽ አልነበረም፡፡ የርዕዮተ ዓለም መለወጥ ጥያቄ ይኼንን ያህል የሚያግደረድርበት ምክንያትም የዚያኑ ያህል ግልጽ አይደለም፡፡ ስለሂሳዊ ግምገማ ባህሉ ብዙ የሚናገረው ኢሕአዴግ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ላይ ሲደርስ የሚተችበት ምክንያት የለም፡፡ ስንትና ስንት ከማርክሲዝም ቤት የመጡ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም መደባቸውን ስንት ጊዜ ቀይረዋልና የሚያሳፍር ነገር የለበትም፡፡

ለማንኛውም በአንድ ድርጅት ውስጥ አንዴ የተነሳ ሐሳብ በአንድ ዙር አይሞትም፡፡ ስለዚህም ውይይቱ በኢሕአዴግ ውስጥ እንደሚቀጥል ለመገመት ይቻላል፡፡ ኢሕአዴግ ከድርጅቱ ውጪ ያሉትንም አመለካከቶች እንደሚያዳምጥ ተስፋ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶቹን አክሎ እንደሚስፋፋ ዶ/ር ዓብይ በመክፈቻ ንግግራቸው አሳውቀዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይ አያይዘው ኢሕአዴግ ከእንግዲህ ‹‹የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርጅት እንዲሆን›› ሲሉ ለኢሕአዴግ የተለየ ምኞትና ዕቅድ ያላቸው መስሏል፡፡

ይህ ‹‹የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርጅት›› የተባለ ነገር አሳሳቢ ነው፡፡ ከፖለቲካ አንፃር ሲታይ እንዲያውም ያስፈራል፡፡ የታሪክ ምሳሌዎችን በማቅረብ ለማስረዳት መሞከር መቸኮል ይሆናል፡፡ ይሁንና የፖለቲካ ታሪክ ተማሪው አሁን ደግሞ “የዜጎች ፓርቲ” ስለሚባል አስፈሪ ነገር የሚመላለስበት ሌላ ምዕራፍ እንዳይከፈት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምን?

የአዴፓ ሊቀመንበር፣ የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በሰጡት አንድ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ፣ ኢሕአዴግ ስምንት ሚሊዮን አባላት እንዳሉት በእርካታ ገልጸው ነበር፡፡ በዚህ ብዛት፣ ኢሕአዴግ ከ100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስምንት በመቶውን አባሉ አድርጓል ማለት ነው፡፡ ለማነፃፀር ያህል ለ11ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ተጋብዘው ከነበሩት የኢሕአዴግ ወዳጅ ፓርቲዎች መካከል 86.3 ሚሊዮን አባላት አሉት የሚባልለት የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ከቻይና ሕዝብ 6.3 በመቶ ነው፡፡ 3.6 ሚሊዮን አባላት ያሉት የቪየትናም ኮሙዩኒስት ፓርቲ ከቪየትናም ሕዝብ አራት በመቶ ነው፡፡ 769,000 አባላት ያሉት የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ ከደቡብ አፍሪካ ሕዝብ አንድ በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከ457 እስከ 700 ሺሕ አባላት ያሉት የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲም ከጀርመን ሕዘብ አንድ በመቶ ብቻ ነው፡፡

የኢሕአዴግ አባላት ብዛት በኢትዮጵያ ለሚገኙት 20 ሚሊዮን የአባና የእማ ወራ ቤት ቢካፈል፣ አንድ የኢሕአዴግ አባል ለየሁለቱ አባና እማ ወራ ቤት ይደርሳል፡፡ የአባላቱ ቁጥር ለኢሕአዴግ ሩብ ዘመን ሲካፈል፣ ወደ 300 ሺሕ አባላት በየዓመቱ ለኢሕአዴግ ተመልምለዋል፣ ወይም ወደ ኢሕአዴግ ጎርፈዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ መረጠ በተባለው 20 ሚሊዮን ሕዝብ ሲካፈል ደግሞ፣ ከመራጩ ሕዝብ 40 በመቶው የኢሕአዴግ አባል ነበር ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ “የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርጅት” ከሆነ፣ መዳረሻው ምን ሊሆን ነው?

ኢትዮጵያ የምርትና የትምህርት ጥራት እንደሚያስፈልጋት ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ በእኔ አረዳድ ኢሕአዴግም የአባላት ጥራት በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ የኢሕአዴግ “ጥልቅ ተሃድሶ” በእውነትና የምር ጥልቅ የሚሆነው፣ ኢሕአዴግ በብዛት መሥፈርት ራሱን በራሱ ሲያረካ አይደለም፡፡ “ኪራይ ሰብሳቢዎች” እና “ጥገኞች” ከሚላቸው ራሱን አፅድቶ የላቀ የአባላት ጥራት ሲኖረው ነው፡፡ የላቀ ውስጣዊ ዴሞክራሲ ሲኖረውና የዳበረ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል ሲኖረው ነው፡፡ በሌላ በኩል ጉባዔያቸውን ስላደረጉና ለ2012 ምርጫ መዘጋጀት ስለጀመሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አልተሰማም፡፡ አካሂደውም ከሆነ ሒደትና ውጤታቸው ከኢሕአዴጎቹ እኩል ስለማይዘገብ አይታወቅም፡፡ የዴሞክራሲያዊ መድረክ መስፋት የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉባዔዎችና ሌላም ሌላም ሥራቸው በእኩልና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መዘገብን ይጠይቃል፡፡

በመሀል አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች መዳረሻቸው የማይታወቅ የተለያዩ ሐሳቦችን በተለያዩ መድረኮች ላይ እየሰነዘሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ማገልገል የለባቸውም፤›› (ዶ/ር ዓብይ)፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ እንዲፈርስ እንፈልጋለን፤›› (የሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋ)፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሪፎርም ባያደርግ ይመረጣል፤›› የኦፌኮ አቶ በቀለ ገርባ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ይጥፋ የሚል አቋም የለንም፤›› (የአረና አቶ ገብሩ አሥራት)፡፡ ‹‹አማራ በአማራነቱ ከቆመ፣ ኅብረ ብሔር ድርጅቶች በአማራ ክልል መቆሚያ አይኖራቸውም፤›› (የአብን ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፡፡  ‹‹ለፕሬዚዳንታዊ ዴሞክራሲ እንታገላለን፤›› የግንቦት 7 ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)፡፡ ‹‹ከውጭ ከገቡ ድርጅቶች ጋራ መንግሥት ያደረገው ስምምነት በይፋ ይገለጽ፤›› (ኢዴፓ). . . የሚሉት ናቸው፡፡

በሌላው ወገን አንዳንዶቹ የገቡበትን “ኅብረት” እያፈረሱ ናቸው፡፡ ሌሎቹ “ምናልባት ሌላ ኅብረት እንደሚገቡ” እያስታወቁ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዓብይና የአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች በየበኩላቸው ደግሞ፣ ‹‹ሁለት፣ ከበዛም ሦስት ወይም አምስት ብሔራዊ ፓርቲዎች ይበቃሉ፤›› እያሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ መሀል አንዳንድ አክቲቪስት፣ አርቲስት፣ ብሎገር. . . የሚባሉ ግለሰቦች የመጣላቸውን እንደ ወረደ ሲያወራርዱ ይደመጣሉ፡፡ ‹‹ሁለት፣ ከበዛም ሦስት ወይም አምስት ብሔራዊ ፓርቲዎች ይበቃሉ›› የሚለው ሐሳብ ኢትዮጵያ ከ27 ዓመታት የብሔር ተኮር ፖለቲካ ታላቃ፣ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ብሔራዊና አገራዊ ፖለቲካ ስለሚጠራ የሚደገፍ ነው፡፡ ይሁንና ነባራዊው ሁኔታ ምንድነው?

የአቶ ሰለሞን ገብረ የሱስ ጥናት ለምሳሌ “በ2006 ከነበሩት 80 ድርጅቶች መካከል 70 በመቶው (56) የብሔር እንደሆኑና 30 በመቶ (24) አገር አቀፍ እንደሆኑ ያስረዳል (ሰለሞን ገበረ የሱስ ገብሩ፣ Political Parties, Party Programmacity and Party System in Post 1991 Ethiopia, June 2014፣ገጽ 427)፡፡ በተመዘገቡት 80 አገር አቀፍና የብሔር ድርጅቶች ላይ ከውጭ የገቡት ሲታከሉ ብዛታቸው ከ100 በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ከውጭ የገቡት የፖለቲካ ድርጅቶች ምዝገባ እስካሁን የተጓተተው በአንዳንድ የአመራር አባሎቻቸው የዜግነት ጥያቄ ምክንያት እንደሆነ ይሰማል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅም ‹‹የውጭ አገር ዜጎች አባል የሆኑበት የፖለቲካ ድርጅት መመዝገብ አይችልም፤›› በማለት በማያሻማ ቋንቋ ይደነግጋል (አዋጅ ቁጥር 573/2008፣ አንቀጽ 10/4)፡፡ ይህ የማንኛውም አገር ቋሚ የዜግነት መብት ሕግ ለፓርቲ ምዝገባ ሲባል ሊለወጥ የሚችል አይደለም፡፡ አሁን እንደሚጠየቀው ድርብ ዜግነት (Dual Citizenship) ቢደነገግ አንኳን፣ የሚለወጥ ሕግ አይደለም፡፡ የዜግነት ምርጫ የግለሰብ ፖለቲከኛ የግል ምርጫና ውሳኔ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእርግጥም የውጭ ምንዛሪ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እጥረት የለባትም፡፡ ከ100 በላይ የሚሆኑት ድርጅቶች ለምርጫው በቀሩት አሥራ ወራት ውስጥ በምንና እንዴት ወደ ሁለት፣ ሦስትና አምስት ፓርቲዎች ሊሰባሰቡ እንደሚችሉ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህም እንግዲህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲጀመር ከሁሉም በፊት በሲቪክ ባህልና በሰጥቶ መቀበል የፖለቲካ ጥበብ የታነፁና የዳበሩ ናቸው ወይ? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ሳይነሳ ነው፡፡ የድርጅታቸው ውስጣዊ ዴሞክራሲ ጉዳይ ሳይመዘንና ዴሞክራሲያዊ ባህልን ለማጎልበት የሚጠይቃቸው ሥራና ጊዜ ሳይታሰብ ነው፡፡ ከእስከ ዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ትብብር፣ ኅብረት፣ ቅንጅት፣ ጥምረት፣ ወዘተ. ክሽፈቶች የተቀሰመው ትምህርትና ተመክሮ ምንና ምን እንደሆነ ሳይጠየቅ ነው፡፡ የሁለት፣ የሦስትና የአምስት ፓርቲዎች መኖር በቅድሚያና ከሁሉም ነገር በፊት፣ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ የጋራ ስትራቴጂያዊ ጥቅሞች ላይ የተስማሙና ፅኑ የጋራ አቋም የያዙ የኢትዮጵያ ፓርቲዎችን መኖር ይጠይቃል፡፡ ከዚህ የፖለቲካ ሰገነት ላይ ሲደረስ ብቻ ነው፣ ስለብሔራዊ/አገራዊ መግባባትና ውል መናገር የሚቻለው፡፡ ብሔራዊ/አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች በማንኛውም ገዥና ተቃዋሚ ፓርቲ የማይጣሱ ብሔራዊ/አገራዊ ዓምድ ሆነው የሚፀኑት፡፡

የፓርቲዎች የምረጡኝ ውድድር/ፉክክር ብሔራዊ/አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን አስበልጬ እጠብቃለሁ/አጎለብታለሁ በሚሉ ተወዳዳሪዎች/ተፎካካሪዎች መካከል የሚካሄድ የሚሆነው፡፡ የመጨረሻ መጨረሻም፣ ማን? ማንን? የሚለው የሥልጣን ጥያቄ ብሔራዊ/አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ማን አስበልጦ ይጠብቃል/ያጎለብታል? በሚለው ቋሚ መሥፈርት የሚመዘነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ/አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ የተስማሙ ፓርቲዎች ባለቤት ናት ወይ?

ያም ሆነ ይህ ለሁለት፣ ለሦስትና ለአምስት ፓርቲዎች መኖር ያለው አንድ ብቸኛ መንገድ በርዕዮተ ዓለምና በፖለቲካ ፕሮግራም ዙሪያ መደራጀት ነው፡፡ ይህም፣ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ አገሮች እንደሚፈጸመው ሁሉ፣ ፓርቲዎቹ እንቆምለታለን/እንወክላለን በሚሉት ማኅበራዊ ክፍል (መደብ) አንፃር (ከበርቴ፣ ዝቅተኛ አምራችና ነጋዴ፣ ሠራተኛ፣ ገበሬና ከብት አርቢ. . . ) ተደራጅተው ረድፋቸውን ይይዛሉ ማለት ነው፡፡ እንቆምለታለን/እንወክላለን በሚሉት በእያንዳንዱ ማኅበራዊ ክፍል (መደብ) ዘንድ ተለይተው ለመታወቅና ተቀባይነትን ለማግኘት በቅተዋል ማለት ነው፡፡

ይህ ዕውን ሊሆን የሚችለው ቢያንስ ሦስት የማይታለፉ ጉዳዮች ከወዲሁ ግልጽ መልሶችን ያገኙ ከሆነ ነው፡፡ አንደኛ፣ “ሊበራል” ፣ “ሶሻል ዴሞክራቲክ”፣ “የሠራተኛ”. . . ነን የሚሉትን ድርጅቶች በዛሬይቱ የኢትዮጵያና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሊበራል፣ ሶሻል ዴሞክራት፣ የሠራተኛ. . . የሚያሰኟቸው የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራሞችም ምንድን ናቸው? እያንዳንዳቸው የፖለቲካ ቤተሰባቸውን በሚመለከት ቢያንስ ስለአገሪቱ ነባራዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሁኔታና የውጭ ፖለቲካ ተቀራራቢ ሊባል የሚችል ትንተና፣ አመለካከትና አረዳድ አላቸው ወይ?

አባሎቻቸውና በመጠኑም ቢሆን ወዳጆቻቸው በየፖለቲካ ቤተሰቡ የርዕዮተዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራሞች ታሪክና የ21’ኛው ክፍለ ዘመን አመለካከት ላይ በበቂ የሠለጠኑና የታነፁ ናቸው ወይ? እንቆምለታለን/እንወክላለን ስለሚሉት ማኅበራዊ ክፍል (መደብ) የጥቅምና የመብት ጥያቄዎች ያላቸው መረጃ፣ ያከናወኑት ጥናትና የጨበጡት ነባራዊ ዕውቀት እሰከምን ድረስ ነው? ከማኅበራዊ ክፍሉ (መደብ) ጋራ ያበጁት፣ የገነቡትና ያደራጁት ድርጅታዊና ወዳጃዊ ግንኙነቶችና ትስስሮች እስከምን የደረጁ ናቸው?

ማኅበራዊ ሳይንስ እንደዚሁም፣ የኅብረተሰብ ክፍልን (መደብን) “መደብ በራሱና መደብ ለራሱ” በሚል ከፍሎ ይመለከታል፡፡ መደብ በራሱ፣ አንድ መደብ በምርት ክንዋኔና ግንኙነት ውስጥ ያለውን ብዛትና ሥፍራ ማለት ነው፡፡ መደብ ለራሱ፣ አንድ መደብ ለጥቅሙና ለመብቱ ፀንቶ ለመቆምና ለመታገል ያለውን የንቃተ ህሊና ደረጃና የድርጅታዊ ጥንካሬ ጉልበት ማለት ነው፡፡ ሊበራል፣ “ሶሻል ዴሞክራቲክ”፣ “የሠራተኛ”. . . ነን የሚሉት የኢትጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ አንፃር በየፖለቲካ ቤተሰባቸው ዘንድ ያደረጉት ግምገማና ጥናት ምንድነው? በመጨረሻና በአጭር ጊዜ ሲታሰብ ደግሞ፣ እንቆምለታለን/እንወክላለን ለሚሉት ማኅበራዊ ክፍል (መደብ) በአንድ የምርጫ ዘመን (አምስት ዓመታት ውስጥ) ለማስገኘት የሚታገሉላቸው የጥቅሞችና የመብቶች አማራጮች የትኞቹ ናቸው? ሁለተኛ ሕገ መንግሥቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ‹‹በፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚልኳቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው፤›› (አንቀጽ 61/1) ይላል፡፡ የሁለት፣ ሦስትና አምስት ፓርቲዎች መኖር ሐሳብ በዚህም ደረጃ አንፃራዊ የምክር ቤቶች አወቃቀር ለውጥ እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡ የተያዘው/የሚያዘው አስተሳሰብ ምንድነው? ሦስተኛ በርዕዮተ ዓለም መስመር መደራጀት በግዴታ (የብሔር ድርጅቶች በሲቪክ መብት ተሟጋች ማኅበር መደራጀት ስለሚችሉ) የማይጠበቅባቸው የብሔር ድርጅቶች ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል?

አዋጅ 573/2000 አንቀጽ 5/1 ሀ መ በተጨማሪ፣ ‹‹አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሠረተው 1,500 መሥራች አባላት ሲኖሩት፣ ከእነዚህ መሥራች አባላት ውስጥ ከአርባ በመቶ የማይበልጡት የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ የተቀሩት መሥራች አባላት ነዋሪነታቸው በኢትዮጵያ ከሚገኙት ክልሎች ውስጥ ቢያንስ በአራቱ ክልሎች መደበኛ ነዋሪዎች ሲሆኑና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (ሐ) መሠረት ከየክልሉ ለአገር አቀፍ ፓርቲ መሥራችነት ከሚመዘገቡት አባላት በእያንዳንዱ ክልል አሥራ አምስት በመቶ ሲሆኑ ነው፤›› ይላል፡፡ የክልል ፓርቲዎች ስለሚመሠረቱበት መሥፈርት ደግሞ፣ ‹‹650 መሥራች አባላት ሲኖሩትና ከመሥራች አባላቱ ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሆኑት የክልሉ መደበኛ ነዋሪዎች ሲሆኑ ነው፤›› ይላል (አንቀጽ 6/1 ሀ እና ለ)፡፤ የሁለት፣ ሦስትና አምስት ፓርቲዎች ሐሳብ እነዚህ አንቀጾች እንዲፈተሹም ይጠይቃል፡፡

ለተመለከቱትና ለተመሳሳይ ጥያቄዎች ከወዲሁ ተገቢና ዘላቂ መልሶችን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ተቃራኒው ብሔራዊ መግባባት የሚባለውን በአሸዋ ላይ ለማቆም የመወሰን ያህል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት “ታላቁ ሙከራ” ተብሎ በተጠራው በቋንቋ መሥፈርት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ አስተዳደር አወቃቀር ብዙ ዓይታለች፡፡ አሁን ከ27 ዓመታት በኋላ ለሌላ ላልተጠና፣ በውል ላልተሞከረበትና በሕዝብ ይሁንታ ላልተባረከ የፓርቲዎች አወቃቀር “ታላቅ ሙከራ መዳረግ የለባትም፡፡ የተነሱት አንዳንድ ጥየቄዎች ለምርጫው በቀሩት አሥራ ወራት ውስጥ ተሟልተው ለመመለስ እንደማይችሉ አስተውላለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የጊዜ ገደብ ከተቀመጠለት ስተራቴጂካዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ኢትዮጵያ በዚህም አኳያ ለጋራ ስትራቴጂያዊ ትብብር የበቁ ፓርቲዎች ባለቤት ናት ወይ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...