Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሠራተኛው መቃብር ላይ አበባ ለማኖር አይደለም የተመረጥነው›› አቶ ዳዊ ኢብራሒም፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የቀድሞ ፕሬዚዳንት

በኢትዮጵያ የሠራተኞች ትግል ውስጥ ስማቸው ከሚጠቀስ የሠራተኛ መሪዎች መካከል አንዱ አቶ ዳዊ ኢብራሂም ናቸው፡፡ አቶ ዳዊ ከሠራተኞች ትግል ጋር ተያይዞ ስማቸው መነሳት የጀመረው በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር (ኢሠማኮ) ይባል የነበረው፣ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ተብሎ እንደገና ከተዋቀረበት 1986 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ኢሠማኮ ሲመሠረት ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት አቶ ዳዊ ናቸው፡፡ ከተመረጡበት ዕለት ጀምሮ በኃላፊነታቸው ላይ ተደላድለው ግን አልተቀመጡም፡፡ በኢሠማኮ የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት የአንድ ፕሬዚዳንት የምርጫ ዘመን አራት ዓመታት ሲሆን፣ ይህንን የምርጫ ዘመን እሳቸውና አብረዋቸው የተመረጡት የኢሠማኮ አመራሮች ከመንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ለማጠናቀቅ ብዙ ፈተና እንደ ገጠማቸው ያስታውሳሉ፡፡ በአቶ ዳዊ የሚመራው ኢሠማኮ የተመሠረተው አገሪቱ ለውጥ ውስጥ በነበረችበትና ሠራተኞችን የሚነካኩ በርካታ ጉዳዮች ጎልተው በወጡበት ወቅት ስለነበር፣ አቶ ዳዊም ሠራተኛው ሳይመክርበት ሊፈጸም የሚገባ ነገር ሊኖር አይችልም የሚሉ መጠይቆችን ይዘው በመቅረብ ከመንግሥት ጋር የተፋጠጡበት ጊዜ ነበር፡፡  በኢሠማኮ ምሥረታ ማግሥት ለሠራተኛ ማኅበሩ ዕውቅና እንዲሰጥና በሠራተኛው ጉዳይ ከመንግሥት ጋር መምከር አለብን ብለው ያቀረቡት ጥያቄ በመንግሥት ያለመወደዱ የፈጠረው ክፍተት፣ በኢሠማኮና በመንግሥት መካከል በይፋ ግጭት ውስጥ እስከመግባት አድርሶታል፡፡ የተፈጠረው አለመግባባት ደግሞ በተለይ አቶ ዳዊ ላይ እንዳነጣጠረ በወቅቱ በሰፊው ሲዘገብ ነበር፡፡ የአቶ ዳዊ ኢሠማኮ የሚሰጣቸው መግለጫዎችና መንግሥትም በኢሠማኮ ላይ እያሳደረ ነበር የሚባለው ተፅዕኖ እየከረረ በመምጣቱ የኢሠማኮ ጽሕፈት ቤት እንዲታሸግ የተደረገበትን አጋጣሚ የፈጠረ ሲሆን፣ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ ኢሠማኮ እንዲፈርስ ተደርጎም ነበር፡፡ ያለመግባባቱ እየከረረ ሲሄድ ግን አቶ ዳዊ ከአገር በመውጣት፣ ባለፉት 21 ዓመታት በኔዘርላንድ በስደት ቆይተዋል፡፡ አቶ ዳዊ በቅርቡ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ አገር እንዲገቡ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዳዊ የተወለዱት ባሌ ውስጥ አሊ በምትባል ከተማ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሊ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሮቤና በጎባ ተከታትለዋል፡፡ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በወቅቱ በነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የኢሕአፓ አባል በመሆን በአሲምባና በጎንደር ሲታገሉ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ኢሕአፓ ከተመታ በኋላ ወደ መሀል አገር በመመ ለስ ተፈሪ መኮንን ትምህር ቤትና የንግድ ሥራ ኮሌጅ፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በዚህ ወቅት ነው የሠራተኛ ማኅበራት ትግል ውስጥ የገቡት፡፡ ኢሠማኮን በማደራጀትና በፕሬዚዳንትነት እስከ 1989 ዓ.ም. ሠርተዋል፡፡  የቀድሞ የትግል እንቅስቃሴያቸውን በማስታወስ የነበረውን ሁኔታ ከአገር ከወጡ በኋላ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ ኢሠማኮ እንዴት እንደተደራጀና ከዚያም ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ የገጠማችሁን፣ እንዲሁም በመጨረሻ እንዴት ከአገር ሊወጡ እንደቻሉ ያስታወሱኝ? ከአገር ለመውጣት ውሳኔ ላይ የደረሱበትን ምክንያትም ይግለጹልኝ?

አቶ ዳዊ፡- በደርግ ጊዜ የነበረው የሠራተኛ ማኅበር ከደርግ ኢሠፓ ጋር ፈረሰ፡፡ ከግንቦት 1983 ዓ.ም. ወዲህ ለተወሰኑ ወራት ብሔራዊ የሠራተኛ ማኅበርም ሆነ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራትና መሠረታዊ ማኅበራት አልነበሩም፡፡ በዚያን ጊዜ የሠራተኛ ማኅበሩ በቦታው እንዲመለስ የተወሰነ እንቅስቃሴ ይደረግ ስለነበር፣ ሥልጣኑን ይዞ የነበረው የአዲሱ መንግሥት ኃይሎች የሠራተኛውን መደብ የሥልጣን መሠረት ለማድረግ ይጥሩ ነበር፡፡ ኢሠማን ሲያፈርሱ የባለአደራ ኮሚቴ አቋቁመው ነበር፡፡ ይህንን ኮሚቴ ይመሩ የነበሩት አቶ ዳዊት ዮሐንስ (የመጀመርያው አፈ ጉባዔ) ነበሩ፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ሊወከሉ ይችላሉ የተባሉ የሦስት ተቋማት ሠራተኛ ማኅበራት ተካተቱ፡፡ እነዚህ የአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ማኅበራት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሦስት ሦስት ሰዎች ተወከሉ፡፡ ጥያቄዎች ለዚህ ኮሚቴ ይቀርብና አንድ ጉባዔ ይጠራል፡፡ ይህም የኢሠማኮ አደራጅ ኮሚሽን እንዲቋቋም ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲወሰን በወቅቱ በሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የነበሩ ሦስት ሰዎችና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች በነበሩበት፣ በዚህ ስብሰባ ላይ እኛም ተገኝተን ነበር፡፡ በዚህ ጉባዔ 151 የሚሆኑ የሠራተኛ ማኅበራት ተሳትፈዋል፡፡ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀና ማኅበሩን እንደገና ለማደራጀት በመንግሥት በኩል የተነደፉ ዕቅዶች ቀረቡ፡፡ ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን ሠራተኞች የገጠሙዋቸው በርካታ ችግሮች ስለነበሩ አሁን መደገም የሌለበትና ወቅቱም ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩበት ነው ስለተባለ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መዳራጀት አለብን ብለው ሠራተኞች ይነሳሉ፡፡ ስለዚህ እናንተ የመንግሥት ተወካዮች ስለሆናችሁ መድረኩን ለእኛ ስጡንና እኛው በምንመርጣቸው ሰዎች ተወያይተን እንዴት መደራጀት እንዳለብን እንወስናለን የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡

ሪፖርተር፡- ለጥያቄው ምን ዓይነት መልስ ተሰጠ?

አቶ ዳዊ፡- አዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ብዙ ክርክር ተደረገ፡፡ በወቅቱ ከሦስቱ የመንግሥት ተወካዮች ነን ከሚሉት ጋር ጭቅጭቅ ተፈጠረ፡፡ ሠራተኛው ስብሰባውን የመንግሥት ተወካዮች የተባሉት ሰዎች እንዲመሩት አልፈለገም፡፡ በዚያ ሁኔታ ከግማሽ ቀን ጭቅጭቅ በኋላ አቶ ዳዊት ዮሐንስ ከበላዮቹ ጋር ተደዋውሎ ከተመለሰ በኋላ መድረኩን አስረክቡና ሠራተኞች ተመራርጠው ይምጡ የሚል መመርያ ተሰጠ መሰለኝ፣ አንድ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰው ሲቀር ሌሎቹ የመንግሥት ተወካዮች ተሰናበቱ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መንግሥት የራሱን ሰዎች አደራጅቶ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኞቻችን የተሰባሰብን ነው በነፃ የመደራጀት መብት ሊኖረን ይገባል የምንል ሰዎች ነበርን፡፡ ከሰዓት በኋላ ውይይቱ ቀጠለ፡፡ 28 የአደራጅ ኮሚሽን አባላት ተመረጡ፡፡ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የአደራጅ ኮሚሽኑ ውጣ ውረድ ቢኖረውም አደራጀነው፡፡ የተደራጁ ካሉ እንዲጠናከሩ፣ ያልተደራጁትን ደግሞ በማደራጀት 506 የሠራተኛ መሠረታዊ ማኅበራት ተደራጁ፡፡ እነዚህ ማኅበራት መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ አደረግን፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ምን ዓይነት ውሳኔ?

አቶ ዳዊ፡- ለምሳሌ የአደረጃጀቱ መዋቅር ምን መሆን አለበት? አደረጃጀቱ በክልል መሆን አለበት? ወይስ በኢንዱስትሪ? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ እያንዳንዱ መሠረታዊ ማኅበር እንዲወስን አደረግን፡፡ በዚያ ጊዜ ሠራተኛው የኢንዱስትሪ ግንኙነቱ ላይ በሙያ መመሳሰል በተሰማራበት መስኮች መደራጀቱ ይጠቅመዋል ብለን ገምተን ስለነበር ይህ እንዲወሰን ተደረገ፡፡ ከ506 ማኅበራት 505 የሚሆኑት በኢንዱስትሪ መመሳሰል ላይ ተመሥርተው መደራጀት እንደሚገባቸው ተወሰነ፡፡ ሁለተኛ በዚያን ጊዜ ተቀራራቢ ናቸው የተባሉ የኢንዱስትሪ ምድቦች በዘጠኝ ፌዴሬሽኖች ተደራጁ፡፡ ፌዴሬሽኖቹም የየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነትና የራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ ኖሯቸው እንዲደራጁ የሚያደርግ፣ ከዚያም ፌዴሬሽኖቹ በአንድነት ሆነው ኮንፌዴሬሽን መመሥረት እንዲችሉ ተወሰነ፡፡ ስለዚህ በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ተላለፈ፡፡ በኅዳር 1986 ዓ.ም. 1,500 የሚሆኑ ተወካዮች ዘጠኝ ቦታ ተከፋፍለው በሚያመሳስላቸው ሙያ የየራሳቸውን ፌዴሬሽኖች መሠረቱ፡፡ ሕገ ደንብ ማፅደቅ፣ መሪዎቸቸውን መመረጥ፣  ወደ ኮንፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ የሚወከሉ ተወካዮቻቸውን በነፃነት እንዲመርጡ ተደረገ፡፡ እዚህ ውስጥ ድርጅታዊ አሠራር አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ሠራተኛው ግን ይህንን ጉዳይ ተገንዝቦ ከታች ጀምሮ ትንቅንቅ አድርጎ፣ በአብዛኛው በራሱ ምርጫ የቀረፃቸውን ፌዴሬሽኖች ዕውን አደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ባለው እንቅስቃሴያቸው ውስጥ የመንግሥት ድርሻ ምን ነበር?

አቶ ዳዊ፡- በወቅቱ የሠራተኛውን ስሜት የሚገልጽ አንድ መፈክር ቀርፀን ነበር፡፡ ‹‹ነፃ ራሱን የቻለና ዴሞክራቲክ የሠራተኛ ማኅበር›› የሚል ነው፡፡ ይህም ከማንም ነፃ የሆነና ራሱን ችሎ በራሱ አቅም የሚንቀሳቀስ፣ በውስጡ ዲሞክራቲክ አሠራር የሚኖረው ደንቦችን በማርቀቅም ሆነ በማፅደቅ፣ መሪዎቹን በመምረጥና በማንኛውም እንቅስቃሴዎቹን አቅዶና አልሞ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ያስከብራል በሚል የቀረፅነው ነው፡፡ ይህንን መፈክር መሠረት አድርጎ በሚከናወነው ሥራ በየመድረኩ ይደረግ የነበረው ትንቅንቅ ቀላል አልነበረም፡፡ ከሞላ ጎደል በፌዴሬሽኖች በተደራጀ መንገድ ሰርገው የገቡ አንዳንድ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን የያዙበት፣ ነፃም የሆኑ ፌዴሬሽኖች የተቋቋሙበት ነበር፡፡ ነገር ግን በተወሰኑ አካባቢዎች በድርጅታዊ አሠራር የወቅቱ ገዥ ፓርቲ አባላት የያዙባቸው ነበሩ፡፡ ለማንኛውም ፌዴሬሽኖቹ ተቋቋሙ፣ ኮንፌዴሬሽኑም ተደራጀ፡፡ ኢሠማኮም ተመሠረተ፡፡

ሪፖርተር፡- ምሥረታው መቼ ነበር?

አቶ ዳዊ፡- 1986 ዓ.ም. ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የተመረጡት በዚህ የኢሠማኮ ምሥረታ ላይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላስ ምን ሆነ? እንዴት ሥራችሁን ጀመራችሁ?

አቶ ዳዊ፡- በወቅቱ በከፍተኛ ድምፅ ነበር የተመረጥኩት፡፡ እኔና የተመረጥነው አመራሮች በተመረጥን ማግሥት የተለያዩ ችግሮች ገጠሙን፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን በኮንፌዴሬሽኑ ምርጫ ላይ እርስዎ ይመረጣሉ ተብሎ እንዳልተጠበቀ ይነገር ነበር፡፡ የሠራተኛው ወኪሎች እርስዎን በመምረጣቸው የተፈጠሩ ነገሮች ነበሩ?

አቶ ዳዊ፡- አዎ! በዚያን ወቅት በኢሕአዴግ አመራሮች ዘንድ ይመረጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ሌላ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ያዘጋጃቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው ብዙ ትግል አድርጎ የሚፈልጋቸውን አመራሮች መረጠ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ቢሮ በተረከብን ማግሥት ግን የተለያዩ ማነቆዎች ተፈጠሩብን፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ማነቆዎች?

አቶ ዳዊ፡- ከእነዚህ ማነቆዎች አንዱ ኮንፌዴሬሽኑን ለማስመዝገብና ዕውቅና ለማግኘት የገጠመን ችግር ነው፡፡ ለምዝገባ ወደ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስንሄድ፣ በሕገ ደንባችን ውስጥ ያካተትናቸውን አንድ ሁለት አንቀጾች ቀይሩ ተባልን፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ አንቀጾች ምን ይዘት ነበራቸው? ቀይሩ የተባላችሁበት ምክንያትስ ምን ነበር?

አቶ ዳዊ፡- ቃላት ናቸው፡፡ አንዱ ‹‹ብሔራዊ ማኅበር ነው›› የሚለውን ‹‹አገራዊ›› በሉት የሚል ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ ያለውን ነገር መቀየር አንችልም፡፡ ምክንያቱም ጠቅላላ ጉባዔው የወሰነው ነው፡፡ በእኔ ብቻ ሊወሰን አይችልም፡፡ ምክር ቤቱም መቀየር አይችልም፡፡ የግድ ጠቅላላ ጉባዔው ነው መወሰን ያለበት፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን ለመጥራት ደግሞ አራት ዓመት መጠበቅ አለብን፡፡ ወይም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት ይኖርብናል፡፡ ይህንን ካልቀየራችሁ አይሆንም ተባለ፡፡ ጉዳዩን የኢሠማኮ አመራሮች ከፌዴሬሽኖች ጋር ተማከርንበት፡፡ ለውጡ የተባልነው ቃል ተቀራራቢ ስለሆነ ብንጠየቅበትም፣ ብንከሰስበትም እንቀበል የሚል አቋም ነበረን፡፡ አንዱ የገጠመን ይኼ ነው፡፡  ሌላው የማይፈልጉት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ስለነበር እሱ ካልወጣ ምዝገባ አይደረግም ተባለ፡፡ አንመዘግብም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ተመራጭ ማነው? በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውስጥ መግባት የለበትም ለምን ተባለ?

አቶ ዳዊ፡- ሰውዬውን ኮሚቴ ውስጥ መግባት የለበትም ያለው መንግሥት ነው፡፡ ሰውዬው ክስ ነበረበት፡፡ ዓላማው ግን የእኛ እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል ለመፍጠር ነው፡፡ የኢሠማኮ ጠቅላላ ጉባዔ ግን በከፍተኛ ድምፅ የመረጠው ሦስተኛ ሰው ነው፡፡ ዓቃቤ ንዋይ ሆኖ እንዲሠራ የተመደበ ነው፡፡ ይሠራበት በነበረ መሥሪያ ቤት ውስጥ የተከሰሰ ስለሆነ መመረጥ አልነበረበትም የሚል ነገር  ተነስቶ ነው ክርክር የገጠመው፡፡ ስለዚህ ፈቃዱን አንሰጥም አሉ፡፡ ሠራተኛው በከፍተኛ ድምፅ የመረጠውንና እምነት የጣለበትን ሰው አንመዘግብም ማለት አግባብ አይደለም ብለን ተሟገትን፣ ተከራከርን፡፡ እነሱ  ደግሞ ዕውቅና ያልተሰጠውን ሰው ያሠራሉ እየተባለ ይሸነቁጡን ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ማነቆዎች ቢሮ በከፈትን ማግሥት የገጠሙን ነበሩ፡፡ ሌላው የገጠመን ችግር ደግሞ ከመንግሥት ጋር ሊኖረን ይገባ የነበረን ግንኙነት ያመለክታል፡፡ በሌሎች አገሮች የሠራተኞች ማኅበራት ሲመረጡ ከመንግሥት ጋር ትውውቅ ማድረግ አለባቸው፡፡ አዳዲሶቹ የሠራተኛ መሪዎች ከመንግሥት ጋር ትውውቅ ያደርጋሉ፡፡ ይህ በመላው ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ የሠራተኛው ማኅበሩም አለኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች ያቀርባል፡፡ ማኅበሩ ለሠራተኞች መብት የቆመ ነውና ከመንግሥት የሚጠየቀውን ያስረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ጥያቄ የሚቀርበው የተለመደ ነው ባሉት በትውውቁ ፕሮግራም ላይ ነው?

አቶ ዳዊ፡- አዎ! ማኅበሩ አሉኝ የሚላቸውን በፖሊሲና በሕግ ደረጃ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ነውና የሚደራጀው፣ በዚህ ረገድ ከመንግሥት የሚጠበቀውን ያስረዳል፡፡ መንግሥትም የኢንዱስትሪ ዘርፉን፣ የኢንዱስትሪ ግንኙነቱንና የሠራተኛውን  የሥራ ደኅንነትም ሆነ የጫናና የደኅንነት ሁኔታ በሚመለከት የሚያስረዳበት ነው፡፡ ከዚያ መነሻነት ግንኙነት እንዲፈጠር ይደረጋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር ቀጥታ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ይህ ግንኙነት በ45 ቀናትም በሁለት ወራትም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በጋራ ነው የሚወሰነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ስንሞክር ግን በወቅቱ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን በተመለከተ ግንዛቤ አልነበራቸውም፡፡ እኛ ግን ደብዳቤ ጻፍን፡፡ በአቶ አሰፋ ብሩ በኩልም አንድ ማኅበር ሲመረጥ እንዲህ ዓይነት ትውውቅና ምክክር ይደረጋልና ይህ መሆን እንዳለበት ገልጸንላቸው ነበር፡፡ እሳቸውም የሠራተኞቹን መሪዎች ጠርታችሁ አነጋግሯቸው፣ ግንኙነቱንም ፍጠሩላቸው፣ ቀላል የሆነ አሠራር የሚኖረው በዚህ መልክ ነው ብለው እንዲነግሯቸው አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ለመቀበል እንቢ ይላሉ፡፡ በአሠራሩ ግን በዘጠና ቀናት ውስጥ መፈጸም የነበረበት ነገር ነው፡፡ ሆኖም ምንም ዓይነት ግንኙነት ከመንግሥት ጋር ሳይደረግ ስድስት ወራት ወሰደ፡፡ የኮንፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ምክር ቤት በየስድስት ወራት የሚሰበሰብ ስለነበር፣ ከመንግሥት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ሳይኖረን ይህ የጠቅላይ ምክር ቤት ስብሰባ ደረሰ፡፡ ይህ የኮንፌዴሬሽኑ የመጀመርያው ስብሰባ ነበርና በዚህ ስብሰባ ላይ አጀንዳ ሆኖ ውይይት እንዲደረግበት የተወሰነው፣ መንግሥት ሊያነጋግረን አለመፈለጉን የሚመለከት ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር የመተዋወቂያና የመነጋገሪያ ፕሮግራም እንዲዘጋጅልን ሦስት ደብዳቤዎች ጽፌያለሁ፡፡ ለሦስቱም መልስ አልሰጡም፡፡ ስለዚህ ይህንኑ ጉዳይ ለፌዴሬሽኖቻችን አሳውቀን ነበር፡፡ ልክ አጀንዳ ማስያዛችን ሲታወቅ በውስጣችን ኮንፌዴሬሽኑን ጠልፎ ለመጣል የሚሠሩ ስለነበሩ ይህንን መረጃ ለመንግሥት አቀበሉ፡፡ አቶ ዳዊ መንግሥት ኮንፌዴሬሽኑን ለማነጋገር አልፈለገም የሚል አጀንዳ ሊያቀርብ ነው ብለው ያቀበሉትን መረጃ ተከትሎ፣ በተደጋጋሚ አናግሩን ብለን እንዳልጠየቅን በአጀንዳው ላይ እንደምንነጋገር ውሳኔ ለማስተላለፍ መዘጋጀታችንን ሲያውቁ በፍጥነት እንዲመጡ ተባልን፡፡ የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት በቀናት ልዩነት ጠሩን፡፡ ሄድን፡፡ በወቅቱ 18 የምክር ቤት አባላት ይዤ ነበር የሄድኩት፡፡ እዚያ ስንደርስ መጀመርያ የገለጹልን ‹‹ኢሕአዴግ ከምንም በላይ ጊዜን ያውቃልና አሁን በሰዓቱ ጠርተናችኋል፤›› አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- እነማን ናቸው እንዲህ ያሉት? ከማን ጋር ነበር የተገናኛችሁት?

አቶ ዳዊ፡- አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ታምራት ላይኔ ናቸው፡፡ ‹የመጣችሁበት ሰዓት አልዘገየም፣ አልፈጠነም፡፡ በስድስት ወራት መጠራታችሁ ተገቢ ነው› አሉን፡፡ ስለዚህ ‹እንነጋገርበታለን ያልከውን አጀንዳ ተወው› አሉኝ፡፡ ይህንን በዚህ መንገድ ተውንና አሉን የምንላቸውን ጥያቄዎች አቀረብን፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ መቅረብ አለባቸው የተባሉት ጥያቄዎች ይዘት ምን ይመስል ነበር?

አቶ ዳዊ፡- ዝርዝሩ ሰፊ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ መንግሥት ‹ስትራክቸራል አጀስትመንት ፕሮግራም› (የመዋቅሩ ማስተካከያ) እየጀመረ ነበርና አንዱ ጥያቄያችን ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለመተግበር ታቅዶም ነበር፡፡ ከሴፍቲኔትና ከፕራይቬታይዜሽን ጉዳይም ጋር የተያያዙ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ነገሮች በቀጥታ ሠራተኛው የቆመበትን መሬት የሚንዱ ናቸው፡፡ ይህ በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በወቅቱ ንቁ የሆነ የሠራተኛ ማኅበር ነበር፡፡ ሰዎች ንቁ ናቸው፡፡ ከሥር እሳት ይነዳል፣ ከላይ እሳት ይነዳል፡፡ ከአራት ኪሎ የሚዘረጋው መስመር ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ ውስጥ ሆነን ሄደን ያነሳነው አንዱ እየመጣ ያለው የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም በአፍሪካና በእስያ ከፍተኛ ችግር የፈጠረ፣ በሠራተኛው ከፍተኛ ጫና የሚያመጣ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባሉ ሠራተኛውን በሚነኩ ጉዳዮች ላይና ፕራይቬታይዜሽንን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሁሉ መሳተፍ አለብን ብለን ጠየቅን፡፡ ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ለሴፍቲኔት ተብሎ ወደ 94 ሚሊዮን ዶላር የተሰጣቸው ገንዘብ ስለነበር፣ ይህንን ገንዘብ ቢያንስ ሠራተኛው ከፎቅ ተወርውሮ ከመፈጥፈጡ በፊት የሆነ መረብ ዘርግቶ ለመቀበል እንዲያስችል በዚህ ውስጥ የመሳተፍ ዕድል እንዲኖረንም አሳወቅን፡፡

ሌላው ጥያቄያችን ያጠነጠነው ደግሞ በዓለም የሥራ ድርጅት (IOL) የሦስትዮሽ ግንኙነት መሠረት ከአሠሪዎች፣ ከሠራተኞችና ከመንግሥት የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን፣ የአሠሪና የሠራተኛ ሕግንና ፕሮግራሞችን በተመለከተ በጥምረት  መሥራት እንደሚገባቸውና ጥምረቱ እንዲቋቋም ጠየቅን፡፡ ይህ ጥምረት ለካቢኔውም ሆነ ለሌላው አካል ሐሳብ የሚቀርብበት ስለሆነ፣ ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያ ስለተቀበለችው የሦስትዮሽ መድረኩ እንዲቋቋምልን ጠይቀናል፡፡ በእንዲህ ያለው መድረክ ሠራተኛውን የሚጎዱ ነገሮችን ለመከላከል ይረዳናል በሚል ያቀረብነው ነው፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲወጣ የተዘረፉ የሠራተኞች ንብረቶች ነበሩ፡፡ ወደ 2.4 ሚሊዮን ብር የተወሰደ ነበር፡፡ ተሽከርካሪዎች ተወስደው ነበር፡፡ እንደ ገቢ ማስገኛ ይጠቀምባቸው የነበሩ በመቀሌ፣ በአስመራና በሌሎች ከተሞች የነበሩ ንብረቶች ለሠራተኛው እንዲመለሱ የሚል ጥያቄም ነበረን፡፡ አዲስ መንግሥት እየተመሠረተ ስለሆነና ከሶሻሊት መንግሥት ወደ አዲስ መንግሥት የተገባ በመሆኑ የገበያ ኢኮኖሚ ይሆናል፣ ሊበራላይዝ እናደርጋለን፣ የገንዘብ የምንዛሪ ምጣኔ ማስተካከያ ሊደረግ ነው እየተባለ ስለነበር፣ መድረክ ተከፍቶ በቅርበት ከመንግሥት ጋር መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ይህም እንዲደረግ ጥያቄ አቀረብን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ በግንባር ቀርባችሁ ላነሳችኋቸው ጥያቄያች ምን ምላሽ ተሰጠ ታዲያ?

አቶ ዳዊ፡- በወቅቱ የቀረቡትን ጥያቄዎች በሙሉ በቀናነት ተቀበሏቸው፡፡ በተለይ ንብረትን በተመለከተ ተጨባጭ ዝርዝር አቅርቡልን ተባልን፡፡ ከመንግሥት ጋር የቀጥታ ግንኙነት ይኑረን በሚለው ላይ ደግሞ በወቅቱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን ለምን አላቋቋማችሁም ብለው ጠየቁ፡፡ ሚኒስትሩም የአሠሪዎች ማኅበር ስላልተመሠረተ ነው ብለው አስረዱ፡፡ በአቶ መለስ ‹‹ለማንኛውም ከሠራተኛው ማኅበር ጋር እየተነጋገራችሁ መድረኩን አቋቁሙ፤›› ተብሎ እዚያው መመርያ ተሰጠ፡፡ እንደ ፕራይቬታይዜሽንና ሴፍቲኔት መሰል ጉዳዮች ላይ እናሳትፋታለን አሉን፡፡ ስለእውነት  ቃል በቃል ያሉን በእምነት እናሳትፋችኋለን የሚል ነበር፡፡ እሺ ብለን ወጣን፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ምንም የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡ እዚያ ስብሰባ ላይ ይህንን ሁሉ ስንነጋገር ግን አንድ ሌላም የተወሰነ ነገር ነበር፡፡ ይህም ከበደ ታደሰ (ዶ/ር) እና ሁለት የመንግሥት ተወካዮች ከእኛ ጋር የሚገናኙ እንዲሆኑ ተወስኖ ተነገረን፡፡ ከእነሱ ጋር እየተገናኛችሁ ከመንግሥት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት አመቻቹ ተባለ፡፡ በዚህ መሠረት ለዶ/ር ከበደ ደወልኩ፡፡ ከመንግሥት ጋር የምንገናኝበት ቀን መቆረጥ አለበት አልኳቸው፡፡ በግንባር ሄደንም አነጋግረናቸው በሦስት ወራት እንገናኛለን አሉ፡፡ እኛ ደግሞ በየዕለቱ ሠራተኛው ላይ አደጋ እየደረሰ ነው፣ በ45 ቀናት እንገናኝ አልን፡፡ ለጊዜው በ45 ቀናት እንዲሆን አደረግን፡፡ ከዚያ በኋላ በሁለት ወራትም ልንገናኝ እንችላለን ተባብለን የመጀመርያውን ቀን ቆርጠን በሳምንቱ ስንሄድ ሁኔታዎች ተቀያይረው ጠበቁን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ዳዊ፡- ዶ/ር ከበደ ቢሮ ስንሄድ አሁን እናንተን እያወያየን መቀጠል አንችልም አሉን፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም ትሳተፋላችሁ ተብሎ ቃል በተገቡላችሁ ጉዳዮች ውስጥ መሳተፍ አትችሉም ብለው ነገሩን፡፡ ይኼ ሊሆን አይችልም፣ ሠራተኛውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ተሳታፊ እንድንሆንና የመነጋገሪያ መድረክ እንደሚመቻች የተነገረን በአገሪቱ መሪዎች ነውና እርስዎ ይህንን ውሳኔ ሊቀይሩ አይችሉም ብለን ለዶ/ር ከበደ ገለጽንላቸው፡፡ በእግርጥ ሐሳባቸውን ቀይረው ከሆነ ሊነግሩን የሚገባቸው እነሱ ናቸው ብለን ሞገትን፡፡ አያይዘንም ለእርስዎ የተሰጠዎት ኃላፊነት ግን ግንኙነት ፈጥራችሁ እንዲህ፣ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግራችሁ ሥሩ የሚል ነው ብለን ነገርናቸው፡፡ እነሱን ብትጠይቁም የምታገኙት መልስ ይህንን ነው አሉን፡፡ ይህንን ለማመን አልችልም አልኩ፡፡ አቶ መለስና አቶ ታምራትን ሄጄ  አነጋግራለሁ ብያቸው፣ እስከዚያው ድረስ ግን ሠራተኛውን ይመለከተዋል ያልናቸውን እንድንነጋገርበት የቀረፅናቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች እነዚህ ናቸው በማለት ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያስተላልፉልን ሰጠናቸው፡፡ በማንኛውም ሁኔታ የሠራተኛው ማኅበር ሳያውቅ የሠራተኛ ቅነሳ እንዳይካሄድ፣ ፕራይቬታይሽንም ቢሆን በደንብ የተጠናና የሠራተኛውን ዕጣ ፈንታ የሚወስን እንደሚገባ ቢታወቅም የገቡትን ቃል አጠፉ፡፡ እናንተን የምናነጋግርበት ጊዜ የለም ተባልን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን እንዳወቃችሁ የእናንተ ዕርምጃ ምን ሆነ?

አቶ ዳዊ፡- ይኼ ችግር ሲገጥመኝ እኔ የሆነውን ሁሉ ወጥቼ ለሠራተኛው አሳውቃለሁ አልኩ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ በሠራተኛው መቃብር ላይ አበባ ለማስቀመጥ አይደለም የተመረጥነው፡፡ ሠራተኛውም አያስቀምጠንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሊያሳትፈን እንደማይፈልግና እንዳገለለ ለሠራተኛው እናገራለሁ አልኳቸው፡፡ እናያለን አሉኝ፡፡ ዋና ዋናዎቹን ለማነጋገር ሞከርኩ፣ ነገሩን ለዶ/ር ከበደ ነግረው አዘጉ፡፡ እነሱ ዘንድ ተመልሼ ስጠይቅ በወቅቱ የግንዛቤ እጥረት ነበረን፣ አሁን አናደርግም አሉ፡፡ እና ሠራተኛው ሲረግፍ ዝም ብሎ ማየት ነው የምትሉት? ሠራተኛው ዕድል አለው ሥራ ይፈጠራል ኢኮኖማውን ለማጠናከር ነው የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ይህን መልስ ይዤ ከኮንፌዴሬሽኑ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተነጋገርን፡፡ የምክር ቤት አባላትንም አማከርን፡፡ ስለዚህ ምንም ነገር ማድረግ ስላልቻልን እየሆነ ስላለው ሁኔታ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አለብን ብዬ ጋዜጣዊ መግለጫው ተሰጠ፡፡ ከዚያ በኋላ ነገሩ ሁሉ ተደበላለቀ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ጊዜ ደግሞ አቶ መለስ አሜሪካ ነበሩ፡፡ አሜሪካ በነበሩበት ወቅት ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበርና ሲመለሱ እሳት ሆነው ይታገሉን አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ፀረ ሠራተኛ ነው ካሉን ይታገሉን ብለው አወጁ፡፡ ይታገሉን ማለት እንዲህ ቀላል አልነበረም፡፡ የላባደር ዘርፍ አቋቁመው ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የመንግሥትን ቢሮክራሲ ተከትሎ ታች ድረስ፣ በተለይም የሠራተኛ ማኅበራት ባሉባቸው አካባቢዎች ቀበሌ ድረስ ኔትወርክ ዘረጉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ምን ለማድረግ ማለት ነው?

አቶ ዳዊ፡- የሠራተኛ ማኅበሩን አወላልቆና አመራሩን ቀምቶ ሠራተኛ ማኅበሩን ለመቆጣጠር ነው፡፡ ይህንንም ለመተግበር 23 ገጽ ያለው የፖሊሲ አቅጣጫ አወጡ፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ይመሩ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ተስፋ ማርያም ፋሪስና አቶ አለምሰገድ ገብረ አምላክ ነበሩ፡፡ ሁሉም ሪፖርት የሚያደርጉት ለአቶ መለስ ነበር፡፡ በሠራተኞች ማኅበራት ላይ ጦርነት ታወጀ ማለት ይቻላል፡፡ መግለጫችን ትልቅ እንቅስቃሴ አስከተለ፡፡ ከዚያ በኋላ ማኅበር ስረዛ መጣ፡፡ የኮንፌዴሬሽኑን ዋና ጽሕፈት ቤት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስከ ማሸግ ተደረሰ፡፡ ፍርድ ቤት ራሱ ጽሕፈት ቤቱን ማሸግ ሕገወጥ ስለሆነ ማሸግ አትችሉም ብሎ ወስኖ እንኳን አንከፍትም አሉ፡፡ እኛ ጉዳያችንን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ስንሟገት ጉዳዩን የያዙ ዳኞች ላይ የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወሰዱ፡፡ በዚህ ምክንያት ዳኞችን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወርና ማባረር ሁሉ ተፈጸመ፡፡ የእነሱን ሐሳብ የሚደግፉ ዳኞች በመተካት የተፈለገው ተወሰነ፡፡ የኮንፌዴሬሽኑን ተሽከርካሪዎች ማገድ፣ የባንክ አካውንት መዝጋት ሁሉ ተደረሰ፡፡ ከዚያ በኋላ ሠራተኛው ተቃውሞው እየጨመረ መጣ፡፡ ኮንፌዴሬሽኑን ለመቆጣጠር በየአቅጣጫው ማስፈራራት ውስጥ ተገባ፡፡ ከሥራ ማባረር ተጠናከረ፡፡ በደርግም በኃይለ ሥላሴም ያልተደረገ በደል በሠራተኛው ላይ ደረሰ፡፡ የሠራተኞች መብቶች ተጣሱ፡፡ እንዲህም ሆኖ ኮንፌዴሬሽኑን ማፍረስ አቃታቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ረዥም ጊዜ ወስዶ ከአራት ዓመት በኋላ የራሳቸው ካድሬዎች ተሰባስበው ኮንፌዴሬሽኑን ያዙት፡፡ እስከዛሬ ድረስ በዚያ ዓይነት መንገድ የሠራተኛው እንቅስቃሴና ድምፅ እንዲታፈን ተደርጓል፡፡ በ27 ዓመታት ውስጥ ትልቅ በደል የተሠራው በሠራተኛውና በሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ላይ ነው፡፡ አሁን ያለው መንግሥት የተቋሙ ንብረቶች እንዲመለሱለት ማድረግ አለበት፡፡ ለዴሞክራሲ ግንባታ፣ ለመጪው ዕድገትና ልማትም የሠራተኛው ጉዳይን ሳያነሱ ማለፍ ተገቢ አይሆንም፡፡  ስለዚህ የተቋሙን ንብረቶች መመለስ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነው እንዴት ቆዩ? እንዴትስ ከአገር ወጡ? ከአገር የመውጣትዎ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዳዊ፡- እንደነገርኩህ ለአራት ዓመታት የሠራተኛው ማኅበራት መዋቅሮች እንዳይፈራርሱ ሠራተኛው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንዳይወድቅ፣ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትና ጠንካራ የሠራተኛ መሪዎች የተቻላቸውን ሁሉ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ በአራት ዓመታት በርካታ በደሎች ተፈጸሙ፡፡ ግፊቱ እየጨመረ ሄደ፡፡ በተለይ እኔን በግልጽ የገጠሙኝ በፈጠራ ወንጀሎች መክሰስ፣ ማዋከብ፣ ከአደባባይ እስከ ቤቴ ጓዳ ድረስ ሦስት አራት የደኅንነት መኪኖች መድቦ ጠዋት ከቤት እስከምሄድበት ድረስ መከታተል፣ እንደገና ወደ ቤት መመለስ፡፡ እንዲህ እያደረጉ ቀጠሉ፡፡ በነገርህ ላይ ሦስት ጊዜያት የግድያ ሙከራዎችን ዓይቻለሁ፡፡ የገዳይ ቡድን አባላት የሚመስሉ ሰዎች ሁለት ሦስት ጊዜ ይከታተሉኝ ነበር፡፡ የመጨረሻ ቀኔ ይሆናል ያልኩበት አጋጣሚ ደግሞ ከኡራኤል ወደ ለም ሆቴል ስሄድ ደኅንነቶች ከኡራኤል ጀምሮ ይከታተሉኛል፡፡ ታክሲ ውስጥ ነበርኩና ለሾፌሩና ከጎኔ ላለ ተሳፋሪ ይህንን ነገር እዩ በእኔ ላይ የሚፈጸም ነው፣ የሠራተኛ ማኅበር መሪ ነኝ፣ ምናልባት ሌላ ነገር ሊከተለኝ ስለሚችል የሚሆነውን እዩ፣ ዛሬ ላትናገሩ ትችላላችሁ፣ አንድ ቀን ብርሃን ሲወጣ ምስክር ትሆናላችሁ ብያቸው ነበር፡፡ መኪናቸውን አስጠግተው ከኋላና ከፊት ዘግተው ክትትላቸውን እያደረጉብኝ ያሉ ደኅንነቶች ለም ሆቴል አካባቢ ወርጄ ሆቴሉ ስገባ በተራ በተራ እየመጡ እያዩኝ ይወጣሉ፡፡ የሚፈልጉትን ማድረግ አልተመቻቸውም መሰለኝ ሄዱ፡፡ ለማንኛውም እንዲህ ያለው ነገር ለሦስት ጊዜያት ሆነ፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ግን ተለጣፊ ኢሠማኮ ለመፍጠር የራሳቸውን ጉባዔ እየጠሩ ነበር፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በኢሠማኮ ጉዳይ የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡  ፍርድ ቤት በኮንፌዴሬሽኑ ስረዛ ጉዳይ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜም ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ስንመለከት አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረብን፡፡ ስለዚህ በፈጠራ ወንጀል ተከስሼ ለረዥም ጊዜ ልታሰር እንደምችል ወይም ሊያስወግዱኝ ይችሉ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ነገሩ ከጥርጣሬ በላይ ነው፡፡ ምን እናድርግ ብለን ከተማከርን በኋላ ከአገር ለመውጣት ወሰንን፡፡ በነገራችን ላይ አቶ አሰፋ ማሩ እኔ በወጣሁ በቀናት ልዩነት ነው የተገደለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ውሳኔዎ በኋላ ነው ከአገር የወጡት? ሁኔታው እንዴት ነበር?

አቶ ዳዊ፡- አወጣጤን ሙሉ ለሙሉ ያደራጁት የሠራተኞች ማኅበራት ናቸው፡፡ በተለየ መንገድ ለማደራጀት ሞከርን፡፡ ከዚህ እስከ ሞያሌ ሁለት ሦስቴ ተመላልሰው ያጠኑ የራሳችን የማኅበር ሰዎች ነበሩ፡፡ የእኔ መውጣት ሌላም ዓላማ ነበረው፡፡ ይህም ከተቻለ ከወጣሁ በኋላ በዓለም የሥራ ድርጅትም ሆነ በመሳሰሉት ድምፅ በማሰማት መቀጠል ይሻላል ተብሎ እኔ እንድወጣ ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ እንዴት መሄድ እንዳለብኝ፣ የትኛው ቦታ ማን እንደሚያሻግረኝና እንደሚረዳኝ ካደራጀን በኋላ በሞያሌ በኩል በቀላሉ ወጣሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ብቻዎትን ነበሩ?

አቶ ዳዊ፡- ሌሎች ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- የኬንያ ቆይታዎ እንዴት ነበር? ከኬንያስ ወዴት አመሩ? ከየት ሄደው ነው እስካሁን ኔዘርላንድ የተቀመጡት?

አቶ ዳዊ፡- ናይሮቢ 17 ቀናት ነው የቆየሁት፡፡ ናይሮቢ ከገባሁ በኋላም የሚከተሉኝ ነበሩ፡፡ እዚያ የተቀበለን የዓለም አቀፍ ሠራተኞች ተወካዮች ይህንኑ ያዩ ስለነበር፣ ይይዙታል ወይም ይገሉታል የሚል ሥጋት ነበራቸው፡፡ ስለዚህ እዚህም ከተማ ይወራ የነበረው ደግሞ ተይዞ ይመጣል የሚል ነው፡፡ ናይሮቢ ውስጥ በየዕለቱ ክትትል ይደረግብን ነበር፡፡ ይህ በግልጽ ሲታወቅ የውጭ የሠራተኛ ማኅበራት ተባብራችሁ አውጡት ተባለ፡፡ ከዚያ የአውስትራሊያ ሠራተኛ ማኅበር ፎርም አስሞላን፡፡ ሊፈጥን አልቻለም፡፡ ነገር ግን የኔዘርላንድ ሠራተኞች ማኅበር የጀመረው ፈጥኖ አለቀ፡፡ በ17ኛ ቀኔ ከናይሮቢ ወጣሁ፡፡ በናይሮቢ ቆይታዬ የካናዳም ዕድል ነበር፣ ግን ለጄኔቭ ለመቅረብ ኔዘርላንድ መሄድ ነበረብኝና ሄድኩ፡፡ ኔዘርላንድ ስደርስ ካምፕ ነበር መሆን የነበረብኝ፡፡ የኔዘርላንድ ሠራተኛ ማኅበር ከካምፕ አውጥቶ ሆቴል እየከፈለ አስቀመጠኝ፡፡ ከዚያም ጄኔቭ መመላለስ ጀመርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ለጄኔቭ መቅረብ የተፈለገበትና ከዚያም በኋላ ጄኔቭ መመላለስ የጀመሩት ከአይኤልኦ ጋር ለመገናኘት ነው?

አቶ ዳዊ፡- አዎ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቁ አቤቱታውን አቀረብኩ፡፡ ጉዳዩ ተደራጅቶ እየታየና ክርክር እየተካሄደ ውሳኔ ተሰጠ፡፡ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ተወሰነ፡፡ በማኅበሩ ላይ የተሠራው አግባብ አለመሆኑ፣ ኢሠማኮ መሠረዙ፣ ጽሕፈት ቤቱ መዘጋቱ አግባብ እንዳልሆነ ሁሉ ተወሰነ፡፡ የመብት ረገጣ በመካሄዱ የሠራተኛው ማኅበሩ መሪ ወደ አገሩ ተመልሶ ዓላማውን ማራመድ እንዲችል፣ ዋስትና ተሰጥቶትና ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲመለስ ተብሎ ተወሰነ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ውሳኔ መሠረት ወደ አገር መመለስ ቻሉ?

አቶ ዳዊ፡- ውሳኔው የደረሰው መንግሥት መግባት ይችላል አለ፡፡ ነገር ግን በሕግ የሚፈለግ ከሆነ ይጠየቃል የሚል ምላሽ ስለሰጠ ውሳኔው ተፈጻሚ ሳይሆን ቀረ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ወደ አገርዎ እንዴት መጡ? ምን ለማድረግ አስበዋል?

አቶ ዳዊ፡- አሁን የመጣሁት በጊዜያዊነት ነው፡፡ ለሦስት ሳምንት ነው፡፡ አሁን በአገሪቱ ለመተንፈስ የሚያስችል ዕድል እየተፈጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የታገቱና የተሰደዱ ሰዎች እየመጡ ነው፡፡ የአፈና ሕጎች እንዲሻሻሉ ስለሚደረግ ከሞላ ጎደል ያለው ሁኔታ መልካም በመሆኑ መጥቻለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከተሰደድኩ በኋላ የሞቱትን አባቴን አልቀበርኩም፡፡ መካነ መቃብራቸውን ለማየት እመኝ ነበር፡፡ ሁለተኛ እናቴ አዛውንት ናቸው፡፡ እሳቸውንስ ለማየት ዕድል ይኖረኝ ይሆን? የሚል ጭንቀት ነበረብኝ፡፡ እሳቸውን ማየት ቻልኩ፣ የቤተሰብ ጉዳይም አንዱ ነበር፡፡ ሌላው ያለውን ሁኔታ መልከት ለማድረግ ነው፡፡ ወደ አገሬ ለመመለስ የፖለቲካ ስደተኝነት ደረጃዬ ‹‹A›› ያለኝ ስለሆነ፣ በዓለም አቀፉ የጀኔቫ ኮንቬሽን መሠረት አደጋ ይገጥመዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ይኼ መንግሥት ለሌላው ባደረገው ጥሪ መሠረት ለመመለስ ተቀባይነት እንዳለኝ ለሆላንድ መንግሥት ማረጋገጫ ማቅረብ አለብኝ፡፡ ኔዘርላንድ ከተመለስኩ በኋላ ወደ አገሬ ለአንዴና ለሁሌም እመለሳለሁ ለሚለው አደጋ የለብህም ወይ ስባል የኢትዮጵያን ፓስፖርት ማሳየት አለብኝ፡፡ እሱን ለማድረግ ነው፡፡ እዚያ ስጠየቅ በአዲሱ መንግሥት ደኅንነቴ የተጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ነገር ይዤ ለመመለስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ጉዳይ ምን ደረሰልዎ ታዲያ?

አቶ ዳዊ፡- ጀምሬያለሁ፡፡ ፓስፖርት ተሰጥቶኛል፡፡ ያለምንም ችግር አውጥቻለሁ፡፡ አሁን ይህን አቅርቤ በሁለት ወር ውስጥ ወደዚህ ለመመለስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በስደት በነበሩበት ጊዜ እዚህ ያለውን የሠራተኞች ማኅበራት እንቅስቃሴ እንዴት ያዩት ነበር? ከሠራተኛ መሪዎች ጋር ይገናኙ ነበር?

አቶ ዳዊ፡- ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የለኝም፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ የሠራተኛ መሪዎች አሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ዋጋ የከፈሉ፣ የተባረሩ፣ የታሰሩና ብዙ ፍዳ የደረሰባቸው አሉ፡፡ የበለጠ መከራ ያዩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያለማቋረጥ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ከመጣሁም በኋላ ተሰባስበን ቡና እየጠጣን አውርተናል፡፡ የሠራተኛውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ያለ የሌለ የመንግሥት ኃይል ተረባርቦ ወደ ተለጣፊ ማኅበር የተቀየረበት፣ ካድሬዎች የተሰየሙበት፣ ሌላው ቀርቶ የሠራተኛ ማኅበር አባል ሳይሆኑ እዚያ እንዲቀመጡ የተደረጉበት ጭምር ስለሆነ፣ እውነተኛ የሠራተኛ ማኅበራት እንቅስቃሴ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሁሉም የማይክደው ነው፡፡ ይህንን እንዴት እንደያዙት ያውቃሉ፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጸሙ ነገሮች ይታወቃሉ፡፡ ስለዚህ የሠራተኛውንም ጉዳይ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ መልሶ መቋቋም ይኖርበታል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ሌላው ቦታ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንመልከት፡፡ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው መንግሥትና ጠቅላይ ሚኒስትር በቀጥታ ጣልቃ ገብተው የተወሰነ ዕርማት ተደርጓል፡፡ በከፍተኛ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም እንዲህ ተደርጓል፡፡ ሠራተኞች አካባቢ ግን ይህ አልሆነም፡፡ የሲቪል ማኅበራትም የኅብረተሰቡ አባል ናቸው፡፡ የሠራተኞች ማኅበራት፣ የመምህራን ማኅበርና ሌሎች የሙያ ማኅበራት ጉዳይን በተመለከተ ግን ሲነገር አይሰማም፡፡ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ የሆነ ነገር ይታያል፡፡ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ሲደርስ መቆም የለበትም፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡንም ማካተት አለበት፡፡ የሠራተኛው የታፈነ ድምፅ ሊሰማ ይገባል፡፡ የመደራጀት መብቱ ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ይኼ መታረም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ዳዊ፡- እውነተኛ የሠራተኛ ማኅበራት እንቅስቃሴ መጀመር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ሊተኮርበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱን ለውጥ እንዴት አዩት?

አቶ ዳዊ፡- እዚህ ላይ ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከተው ነው፡፡ አገሪቱ በሽግግር ሒደት ጅማሮ ላይ ናት፡፡ እናም ለውጥ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ዳዊ፡- ምክንያቱም በሽግግር ንድፈ ሐሳቦች የተለያዩ አገሮችን ልምደች ካየህ የሚያመለክትህ ነገር አለ፡፡ እስካሁን ድረስ የሚካሄደው ነገር ጅማሮ ነው፡፡ እስረኞችን መፍታት፣ ስደተኞች እንዲመለሱ ማድረግ፣ የታገዱ ድርጅቶች ነፃ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግና አፋኝ ሕጎች እንዲሻሻሉ ማድረግ የመሳሰሉት በሽግግር ወቅት የሚታዩ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች ሁሉ የፖለቲካ ለውጥ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሲቪልና የቡድን መብት ማራመድ ነው፡፡ ነፃ እንቅስቃሴ የሚያስችሉ የመፈተሻ መስኮቶችን የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች እጅግ የሚደገፉ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲውን መንገድ ለመጀመር በቂ ሒደቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን የሽግግር ሒደቱ ግልጽ ባለ መንገድ እየተካሄደ ነው ለማለት የሚቀረው ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ዳዊ፡- ከተቃዋሚዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የግድ ቀድሞ መጀመር ነበረበት፡፡ በዚህ ድርድር የአገሪቱን ችግር የማወቅ፣ የኃይል አሠላለፎችን በግልጽ የማወቅ፣ የትኛው ድርጅት ለምን ይቆማል የሚለውንና የድርጅቶቹን ባህሪ የማወቅ ጉዳይ አለ፡፡ ጽንፈኛ የሆኑ ድርጅቶች አሉ፡፡ ሥር ነቀል የሆኑ አሉ፡፡ የለውጥ ኃይሎች አሉ፡፡ ለዘብተኛና የመሳሰሉት ዓይነት ባህሪ ያላቸው አሉ፡፡ በዚህ ሽግግር ወቅት እነዚህ ሁሉ ተዋንያን ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር በአግባቡ ተንትኖ መቀመጥ አለበት፡፡ እንዲህ ያለው ሥራ በአንድ መንግሥት ብቻ የሚሆን ሳይሆን ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ መፈጸም፣ በተለይ ከዚህ በኋላ የሚቀጥለው ድባብ የዴሞክራታይዜሽን ሸንጎ ነገር እንዲኖር ማድረግ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ‹ዴሞክራቲክ ኮንቬሽን› የሚባል ነበር የተቋቋመው፡፡ ይህንን ኮንቬንሽን የተቋቋመው በኤንኤንሲና በሌሎችም ድርጅቶች ነበር፡፡ ሁሉም የተሳተፉበት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ብታይ ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ በመዋቅር ደረጃ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ በጥቅሉ በአሉወታዊ የምታየው አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በዚህ በሽግግር ወቅት ውስጥ የባለድርሻ አካላትና የፖለቲካ ተዋንያን፣ የሲቪል ማኅበራት ተዋንያን ቁጭ ብለው አጀንዳ ቀርፀው ለውይይት በሚበቁ ጉዳዮችና ለአገሪቱ ይጠቅማሉ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ መነጋገር አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አገር ቤት ጠቅልዬ እመለሳለሁ ብለዋልና ጉዳይዎን ጨርሰው ሲመጡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ለመሥራት አስበዋል?

አቶ ዳዊ፡- በነገራችን ላይ በሠራተኛው ውስጥ ግዙፍ የሆነ ኃይል አለን፡፡ ኃይል ብቻ ሳይሆን ምክንያት አለው፡፡ ለስደት ያበቃን ምክንያት አሁንም አለ፡፡ አልተመለሰም፡፡ ብዙ ደሃዎች ያሉባት አገር ነች፡፡ የተከፋፈሉ ሐሳቦችም የሚንፀባረቅባት አገር ነች፡፡ ብዙ ጥያቄዎች የሚቀርቡባትም ነች፡፡ ይህንን ሁሉ የሚያስተናግድ አካሄድና ሲስተም  ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማኅበራዊ ፍትጊያና ማኅበረሰብ የማደራጀት ሥራ መከናወን አለበት፡፡ በየትኛውም ጥግ ላይ ያሉ ዜጎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ በተለይም የሠራተኛው ክፍል የማኅበራዊ ፍትሕ ጥያቄዎች ዛሬም ነገም የማይቆሙ ይመስለኛል፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ሁሌም መታገል አለብን፡፡ በዚህ ላይ በሲቪል አደረጃጀት የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ስለዚህ እኔንም ጨምሮ ብዙ አስተዋጽኦ ልናደርግ እንችላለን፡፡ ሕዝባችን መረጃ ኖሮት የተሻለ ውሳኔ እንዲወስን ለማድረግ የሚከናወኑ ሥራዎች አሉ፡፡ የእኔም ሐሳብ ይኸው ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...