በዚህ ሳምንት አንኳር ከነበሩ የኢትዮጵያ ክንዋኔዎች መካከል ከአራት ኪሎው ፓርላማ የተሰማው ዜና ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የፕሬዚዳንትነት መንበራቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በማስመልከት ያደረጉት የመሰናበቻ ንግግራቸውም ከሰሞኑ አገራዊ ክስተቶች ጆሮ የተሰጠው ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን በሰፊው የዘገቡበት ጉዳይ ነበር፡፡ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ (ዶ/ር) በላይ መነጋገሪያውና ዓለም የተቀባበለው ዓብይ ወሬ፣ ጉምቱዋ ዲፕሎማት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአገሪቱም ለአፍሪካም ተምሳሌት የተደረጉበትን ሹመት ተቀብለው በፕሬዚዳንትነት የመሰየማቸው ዜና ነው፡፡
ከአራት ኪሎ አጀብ ያሰኘው ወሬ ሲበሰር፣ ከካዛንችሱ ኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴልም የአገሪቱን አንጋፋ የንግድ ምክር ቤት ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት እንዲመሩ አንዲት የንግዱ ዘርፍ ጉምቱ ሴት ተመርጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ለመምራት ይችላሉ የተባሉ ሁለት ዕጩዎች በምክር ቤቱ አካላት ለመመረጥ ራሳቸውን በማስተዋወቅ ከተፎካከሩ በኋላ በመጨረሻም፣ የንግድ ምክር ቤቱ በ70 ዓመታት ታሪኩ የመጀመርያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ለመሰየም በቅቷል፡፡ እስከ ምርጫው ዕለት ማለትም እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ዕጩዎችን ሳያሳውቅ የሰነበተው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ በምርጫ አመቻች ኮሚቴው አማካይነት ለፕሬዚዳንትነት በዕጩነት ያቀረባቸው ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ አንዷ ተወዳዳሪ ነበሩ፡፡
ለንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትነት ከታጩት ከወ/ሮ መሰንበት ጋር የተወዳደሩትና በንግዱ ዓለም የዳበረ ልምድ ያላቸው አቶ ሰለሃዲን ከሊፋ ነበሩ፡፡ አቶ ሳላዲን ሳማትራ የተባለው የመርከብና የሎጂስቲክስ ወኪል ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በቤተሰብ የሚተዳደሩ እንደ ካዲስኮ ቀለምና ሆስፒታል ያሉ በርካታ የንግድ ተቋማትን ያፈሩት አባታቸው አቶ ከሊፋ አብዱልቃድርና ቤተቦቻቸው በሚያስተዳድሯቸው ትልልቅ ኩባንያዎች ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ የንግድ ሰው ናቸው፡፡
በንግዱ ዓለም 30 ዓመታት ልምድ ካላቸው ከአቶ ሰላሃዲን ጋር ለውድድር የቀረቡት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በብቸኝነት የባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ካገለገሉት ሁለት እንስቶች መካከል አንዱ በመሆን ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ወ/ሮ መሰንበት የዓባይ ባንክን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡ ባንኩን ከለቀቁ በኋላም ኒው ዳይሜንሽን የንግድ ሥራ አመራር አማካሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚል መጠሪያ ያለውን ድርጅት በማቋቋምና በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ቀድሞውንም የንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት ያገለገሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ ከቦርድ አባልነታቸው የለቀቁት ከዓባይ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው በመነሳታቸው ምክንያት ነበር፡፡ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው የቀረቡትም በአዲሱ ኩባንያቸው በኩል ነበር፡፡ በቢዝነስ አስተዳደር መስክ የተመረቁት ወ/ሮ መሰንበት፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በማገልገል የ35 ዓመታት የሥራ ልምድ አካብተዋል፡፡
በፓርላማው የአዲሷ ፕሬዚዳንት የወ/ሮ ሳህለወርቅ ሹመት እንደተጠናቀቀ ከተፎካካሪ ዕጩዎቹ ለመምረጥ ድምፅ ወደ መስጠቱ የገቡት የንግድ ምክር ቤቱ አባላት፣ ድምፃቸውን የሰጡት ከወደ ፓርላማው የተሰማውን ወሬ እያጣጣሙ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በምርጫው ወቅት ድምፅ የሚሰጡ አባላት ስለአዲሷ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሲያወጉ ተደምጠዋል፡፡
ለዕጩ ፕሬዚዳንቶችና ለቦርድ አባላት ምርጫ የተሰጠው ድምፅ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ውጤቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ እንደሚገለጽ የተነገረለት የምርጫ ሒደት ሲንቀረፈፍ በመቆየቱ ውጤቱን ለማወቅ እስከ አመሻሹ 11፡30 ሰዓት ድረስ ለመጠበቅ አስገድዷል፡፡ አሰልቺው የድምፅ ቆጠራ ከተጠናቀቀ በኋላ የተገኘው ውጤት፣ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ አዲስ ክስተት የሆኑትን ዕጩ ወደ ላይ ያወጣ ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት በመምራት የመጀመርያዋ የንግድ ምክር ቤቱ ሴት ኃላፊ ለመሆን ችለው ነበር፡፡ ለአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ደግሞ ወ/ሮ መሰንበት በ419 ድምፅ አሸንፈው ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል፡፡ አቶ ሰለሃዲን 227 ድምፅ እንዳገኙ ተጠቅሷል፡፡
በዕለቱ ምርጫ ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ ዕጩዎችም ድምፅ ያገኙበት ነበር፡፡ በምርጫው ሒደት አነጋጋሪ የነበረ ጉዳይም ታይቷል፡፡ ይህም ምክትል ፕሬዚዳንቱን የሚመለከት ነበር፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አበባው መኮንን በድጋሚ የምክትልነት ቦታውን እንደያዙ የሚቆዩበትን ዕድል ያገኙበት መንገድ ነበር ያነጋገረው፡፡ እኚህ ኃላፊ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶችን የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታን ለረዥም ዓመታት በማፈራረቅ የቆዩ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ የኃላፊነት ቦታውን የመያዛቸው ጉዳይ በጉባዔተኛው ዘንድ ጥያቄዎች ተነስተው አወያይተዋል፡፡ ሆኖም ቦታው ለዘርፍ ምክር ቤቶች ውክልና ሲባል የተሰኘ በመሆኑ ድጋሚ መመረጥ እንደሚችሉ በመገለጹ ያለ ተፎካካሪ የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡
አቶ አበባው እንደሌሎቹ በካርድ ድምፅ አግኝተው ሳይሆን፣ ከዘርፍ ማኅበራት ተወክለው በመምጣታቸው ቢሳተፉም፣ ዘርፍ ምክር ቤቱ ያለ እርሳቸው የሚሰየመው ሌላ ሰው የለውም ወይ? የሚል ጥያቄ ማስነሳታቸው አልቀረም፡፡ ይህም ሆኖ ድጋሚ መመረጥ ይችላሉ በመባሉ በቦታቸው ረግተዋል፡፡ ለምርጫ አመቻችነት የተሰየመው ኮሚቴም በዕለቱ እንደ አስመራጭ ኮሚቴነተም እንዲቀጥል መደረጉ ለምን የሚል ጥያቄ አስነስቶም ነበር፡፡ የምርጫው ውጤትም በአንዳንዶች ዘንድ ያልተጠበቀ ተብሏል፡፡
አዲሷ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ከአቶ ኤልያስ ገነቲ የኃላፊነት ቦታውን ተረክበዋል፡፡