Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕብረት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ከፍ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሕብረት ባንክ ባለአክሲዮኖች የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን ወሰኑ፡፡ የ2010 ዓ.ም. የትርፍ ምጣኔውን በ42 በመቶ በማሳደግ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠኑን ወደ 34 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰናቸውም ተገልጿል፡፡

የሕብረት ባንክ ባለአክሲዮኖች ሐሙስ፣ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ፣ ባንኩ በ2010 ዓ.ም. ያስመዘገበው ውጤት ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሕብረት ባንክን አቅም ለማጠናከር እስካሁን ያስመዘገበውን የሦስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ተወስኗል፡፡ ይህም የባንኩን የማበደር አቅም ለማሳደግ ያስችለዋል፡፡ ባንኩ የካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ መወሰኑ ካሉት የግል ባንኮች ሁለተኛው ከፍተኛ ካፒታል የያዘ ባንክ ያደርገዋል፡፡ የባንኩ የ2010 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ከዚህ ቀደም ከነበረው እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት ያየበት ዓመት ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የባንኩ የ2010 ዓ.ም. ሪፖርት ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ ውጤት ታይቶባቸዋል የተባሉ አፈጻጸሞቹ በ2010 ዓ.ም. ግን የተሻለ አፈጻጸም እንዳሳዩ ከባንኩ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ባንኩ የሚጠበቅበትን ያህል መልካም አፈጻጸም ላለማሳየቱ በባለአክሲዮኖቹ ጭምር ቅሬታ ያስነሳው የባንኩ የትርፍ ምጣኔ ከአቻ ባንኮች አንፃር አነስተኛ መሆኑ ነበር፡፡ በወቅቱ ሕብረት ባንክ ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ ምጣኔ ካቻምናው ካገኘው አኳያ የ14 በመቶ ብልጫ ብቻ ማሳየቱ ዝቅተኛ ውጤት እንደሆነ ተቆጥሮ ነበር፡፡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉም በዚያን ወቅት የባንኩ ትርፋማነት ከአገሪቱ ባንኮች ሲነፃፀር ዝቅ ማለቱን አምነው ነበር፡፡

በ2010 ዓ.ም. ግን የባንኩ ትርፍ ዓምና የቀረበበትን ቅሬታ አላስነሳም፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ በሪፖርታቸው እንዳቀረቡትም፣ የባንኩ የትርፍ ምጣኔ ጨምሯል፡፡  ‹‹በ2010 የሒሳብ ዓመት ባንካችን ከግብር በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ዓምና ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር የ42.81 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፤›› በማለት ዕድገቱን በአኀዝ አስደግፈው ገልጸውታል፡፡

በ2009 ዓ.ም. የነበረው የትርፍ ዕድገት 14 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 706.98 ሚሊዮን ብር ማትረፍ እንደቻለ አቶ ኢየሱስ ወርቅ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሒሳብ ዓመቱ የትርፍ መጠን በ211.94 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ በመሆኑ ዓምና ያስመዘገበው የትርፍ ዕድገት ‹‹በኢንዱስትሪው ካሉ አቻ ባንኮች የዕድገት ምጣኔ ጋር ሲወዳደር በሦስተኝነት ትልቅ ደረጃን አስገኝቶለታል፤›› በሚል የሚገለጽ ውጤት ለማስመዝገብ አስችሎታል፡፡ የባንኩ የትርፍ ድርሻ ክፍፍሉም ዓምና ከነበረበት 27 በመቶ በ2010 ዓ.ም. ወደ 35 በመቶ አድጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር ባንኩ የሰጠው የብድር መጠንም በ2010 ዓ.ም. የሰመረ ውጤት ካያሰባቸው መካከል ተመድቧል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት እንዲሁም ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ተመዝግቦ ከነበረው መጠን ጋር ሲወዳደር የ24.53 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 15.07 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዚህ ረገድ የተመዘገበው ውጤት ባንኩ ከተፎካካሪ የግል ባንኮች ረገድ በአራተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ስለማስቻሉም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ይህ መጠን ከ2009 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ2.97 ቢሊዮን ብር ወይም የ24.53 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ባንኩ ለተለያዩ የንግድ ዘርፎች ያዋለውን ብድር በተመለከተ የቀረበው ማብራሪያ፣ ከአጠቃላይ ብድር ውስጥ ለወጪ ንግድ የተሰጠው በ23.75 በመቶ  ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዘ ያሳያል፡፡ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ብድር የ15.10 በመቶ፣ የአገር ውስጥ የገቢ ንግድ የ13 በመቶ እንዲሁም የግንባታ ዘርፍ የ11.6 በመቶ  ድርሻ እንደነበራቸው ታውቋል፡፡

ባንኩ የሰጠው ብድር ጤናማ ስለመሆኑ ለማሳየት በቀረበው ሪፖርት፣ የተበላሸ የብድር መጠን በ1.98 በመቶ የተወሰነ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ‹‹በብድር አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥሙ ሥጋቶችን ከመቅረፍ አንፃር አወንታዊ የሚባል እንቅስቃሴ መደረጉን የሚያሳይና ለተለያዩ ዘርፎች በተሰጠው የብድር ዓይነትም ሆነ የተሰጡ ብድሮችን በአግባቡ ከማስተዳደር አንፃር ባንካችን ጥሩ ውጤት እንዳስመዘገበ አመላካች ነው፤›› ተብሏል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 23.08 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ይህ መጠን ዓምና ከተመዘገበው የ17.80 ቢሊዮን ብር አኳያ ሲታይ፣ የ29.63 በመቶ ጭማሪ ወይም የ5.28 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህም በኢንዱስትሪው  ያለውን የገበያ ድርሻ ወደ 14 በመቶ አሳድጎታል፡፡ ሕብረት ባንክ በሒሳብ ዓመቱ የደንበኞቹን ቁጥርም ለማሳደግ ችሏል፡፡ ይህንን ተከትሎም በባንኩ ገንዘብ ያስቀመጡ ደንበኞች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 644.12 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም ዓምና ከተመዘገበው ጋር ሲወዳደር የ297.24 ሚሊዮን ብር ወይም የ85.69 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም. 198.08 ሚሊዮን ብር ለወለድ አልባ የብድር አገልግሎት (የሙራባሃ የፋይናንስ አገልግሎት) መሰጠቱ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ረገድ የተመዘገበው ውጤት በቀደመው ዓመት ከተመዘገበው ውጤት አንፃር ሲመዘን፣ የ108.12 ሚሊዮን ብር ወይም የ120.20 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በዓለም  አቀፍ  የባንክ አገልግሎት ረገድም ባንኩ ያገኘው የገቢ መጠን 530.4 ሚሊዮን ብር ሆኖ እንደነበር የሚገልጸው የባንኩ ሪፖርት፣ በሌሎች የባንክ አገልግሎቶችም ዕድገት የታየበት አፈጻጸም እንዳስመዘገበ አስታውቋል፡፡  

የሕብር ወኪል የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ወኪሎቹን ወደ 463 ከማሳደጉም በተጨማሪ፣ ሕብር የሞባይል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹን ቁጥርም ወደ 144,154 ከፍ ለማድረግ እንደቻለ የባንኩ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በ2009 ዓ.ም. ካስመዘገበው የሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ አኳያ፣ በ2010 ዓ.ም. የ889.49 ሚሊዮን ብር ወይም የ44.5 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ገቢውን ወደ 2.89 ቢሊዮን ብር አሳድጎታል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ወጪም ወደ 2.18 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ከ2009 ዓ.ም. አንፃር የ677.55 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡

የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ በተለይ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮኖቻቸው እንዲሸጡ መደረጉ አግባብ ባለመሆኑ ወደነበረበት ሊመለስ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዳያስፖራው በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲሳተፍ መደረግ አለበት የሚል እምነት ያላቸው አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ድርጊት ተቃውመዋል፡፡

ሕብረት ባንክ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የፋይናንስ ተቋማት ጎዳና የሚል መጠሪያ እያተረፈ በመጣው ሰንጋ ተራ አካባቢ እያስገነባ የሚገኘው ባለ 34 ወለል ሕንፃን ወደ ማጠናቀቁ እንደተቃረበ ተገልጿል፡፡ በ2030 (እ.ኤ.አ) በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አምስት ምርጥ ባንኮች  አንዱ ለመሆን እንደወጠነ የገለጹት የባንኩ ኃላፊዎች፣  በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት መሠረት የሒሳብ ሪፖርቱ የቀረበበት ነበር፡፡

አቶ ታዬ እንደገለጹት፣ ባንኩ የ2010 የሒሳብ ሪፖርቱን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ስታንዳርድ (IFRS) በተኘው የሒሳብ አያያዝና አቀራረብ መሠረት ሪፖርት አድርጓል፡፡ ሕብረት ባንክ እንዲህ ባለው ደረጃ ሪፖርት በማቅረቡ ቀዳሚው ባንክ ያደረገዋል ብለዋል፡፡

በ2010 መጨረሻ የተመዘገበው የሕብረት ባንክ ጠቅላላ ሀብት 28.03 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በ2009 ዓ.ም. ከተመዘገበው የ22.0 ቢሊዮን ብር አኳያ በንፅፅር ሲታይ የ6.02 ቢሊዮን ብር ወይም የ27.37 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታልም በ2009 ዓ.ም. ከተመዘገበው የ2.48 ቢሊዮን ብር አኳያ የ471.39 ሚሊዮን ብር ወይም የ18.99 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 2.95 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ሕብረት ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ3700 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች