Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የባቡሩ ዕዳ በ30 ዓመት አይጠናቀቅም

በጥላሁን ሳርካ

‹‹እልም አለ ባቡሩ›› በሚል ርዕስ እሑድ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹ሸማች›› በሚል ዓምድ ሥር በክፍል 1 ገጽ 13 በናታን ዳዊት በጋዜጣችሁ ላወጣችሁት ጽሑፍ ምላሽ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ አንጋፋውና ሚዛናዊው የሪፖርተር ጋዜጣም የአቶ ናታንን ጽሑፍ በጥሬው እንዳቀረበው ምላሻችንንም እንደ ወረደ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስነብብ ተስፋ አለን፡፡

የጽሑፉ የመጀመርያው አንቀጽ ላይ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን ይገልጻል፡፡ አዋጪነቱም ተሠልቶ የተተገበረ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ይሞግታል፡፡

ይህ በሁለቱም ሐሳቡን ስቷል፡፡ ለባቡሩ የወጣው ጠቅላላ ወጪ ከተጠቀሰው ቁጥር ይልቃል፡፡ ኦዲት የተደረገ ሒሳብ በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ስለሚገኝ ትክክለኛውን ወጪ ለሕዝብ ማሳወቁ ይጠቅማል፡፡

ሌላው የባቡሩ አዋጪነት ጥናትም ሆነ የግንባታ ጥቅል ኮንትራት ባለቀለት ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ድርድር ተካሂዶበታል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ይኼ ዕውቀት ያለው ኢትዮጵያዊ አልነበረምና ነው፡፡ አሁን ሁላችንም በባቡር ዘርፉ አሥር ዓመት የሥራ ልምድ አግኝተናል፡፡ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ግን አቶ ናታንም ቢሆኑ (የምድር ባቡር ሠራተኛ ስለመሰሉኝ ነው) የባቡር ዘርፍ ልምዳቸው ዜሮ ዓመት ነበር ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ማንኛውም አገር ባቡር የሚገነባው ለትርፍ አይደለም፡፡ የባቡር ትራንስፖርትም ሆነ ሌሎች የትራንስፖርት ዓይነቶች ወዲያውኑ አዋጪና ትርፍ የሚዛቅባቸው ናቸው ብሎ የሚያስብ ካለ እርሱ ጉም የዘገነ ምስኪን ፍጥረት ሆኗል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመርም በዚህ መልኩ መታየት ይኖርበታል፡፡ ዋናው ጥቅሙም በገፍ የወጪና የገቢ ዕቃዎችን በማንሳት ለወደብ አገልግሎት እየወጣ ያለውን ክፍያ ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡ ይ ደግሞ እየሆነ ነው፡፡ እግረ መንገዱን ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር፣ የመንገደኞች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትንም እየሰጠ ይገኛል፡፡

በሁለተኛው አንቀጻቸውም አቶ ናታን ለትንሽ ስተዋል፡፡ ዕድለኛው ባቡራችን በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ጊዜ የተመረቀ ሲሆን፣ በጂቡቲ በኩል ደግሞ አንድ ጊዜ በድምሩ ሦስት ጊዜ ተመርቋል፡፡ አቶ ናታን ይኼ ለምን እንደገረማቸውና በተሽሞነሞኑ ቃላቶች የአንባቢን ስሜት ለመቆጣጠር እንደዳዳቸው ግልጽ ቢያደርጉት ባማረባቸው ነበር፡፡ ባቡሩ አሁንም ሥራ ያልጀመሩ ውስብስብ ጣቢያዎች ስላሉት ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት በሚሆንበት ቅርብ ቀን ምናልባትም ሌላ ምረቃም ሊኖር ስለሚችል አቶ ናታን ከብዕር ስማቸው ወጥተው ራሳቸውን የሚገልጹ ከሆነ እንጋብዛቸዋለን፡፡

የአቶ ናታን ጽሑፍ ባቡሩ ሠርቶ የዕዳውን ሩብ እንኳን መመለስ አለመቻሉንም እርግጠኛ በሆነ ሁኔታ አቅርበዋል፡፡ የትኛውን የኢኮኖሚክስ ወይም የሒሳብ አያያዝ ዕውቀት መሠረት አድርገውና በምን ደረጃ ላይ ተመሥርተው እንዲህ እንዳቀረቡ ወደፊት እንዲያሳዩን እንጠብቃለን፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን መንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶችን የሚሠራው በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ ሕዝብን ይጠቅማል ብሎ ካሰበ ነው፡፡ ህዳሴ ግድብን፣ ስኳርና ሌሎች የመብራት ኃይል ፕሮጀክቶችን ማየት ተገቢ ነው፡፡

ሌላው የተነሳው ጉዳይ ለማኔጅመንት ኮንትራክተሩ የሚከፈለው ክፍያ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቁጭቱ ትክክል ነው፡፡ ግን አማራጭ ማቅረብም ተገቢ ነው፡፡ ጎረቤታችን ኬንያ 472 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውንና ከናይሮቢ – ሞምባሳ የሚዘልቀውንና በዲዚል የሚነዳውን ባቡር መስመር 140 ሚሊዮን ዶላር በዓመት በሚከፈል የማኔጅመንት ኮንትራት ታሠራለች፡፡ በቀጥታ በዚህ ሥሌት ብቻ ብንወስድ የእኛ 756 ኪሎ ሜትር ያህል ስለሚረዝም በዓመት 224 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅብን ነበር፡፡ ጉዳዩን ከራሳችን የመክፈል አቅም ውስንነት አንፃር ብቻ ካየነው ሚዛናዊ አይሆንም፡፡

ስለብድር አመላለሱም ቢሆን በኮሜርሺያል ብድር በአሥር ዓመት ይመለስ የነበረው ብድር አሁን በኮንሴሽናል ብድር ዘይቤ 30 ዓመት በመሆኑ፣ ነገር ዓለሙ ሁሉ አልጋ በአልጋ የሆነ አድርጎ መውሰዱም ትክክል አይመስለንም፡፡ በአሥር ዓመት ዕዳውን ለመመለስ በየዓመቱ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር መክፈል የሚጠበቅብን ሲሆን፣ በ30 ዓመት ሲሆን ደግሞ 100 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅብናል፡፡ ከወለድ ውጪ ማለት ነው፡፡ ባቡሩ የቱንም ያህል ተንጠራርቶ ቢመላለስ በሁለቱም መንገዶች ዕዳውን መመለስ አይችልምም፣ አይታሰብምም፡፡ መንግሥት ይኼ ይጠፋዋል ብለን አንወስድም፡፡ ብዙ የብድር አመላለስ ሥልቶች ይኖሩታል፡፡ እኛም የራሳችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን ማለት ነው፡፡   

አቶ ናታን ስለነዳጅ ማመላለሱም አንስተው ግራ በሚያጋባ ሁኔታ መሥሪያ ቤታችንን ወንጅለዋል፡፡ መሥሪያ ቤታችን የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፣ እሳቸውም እንደጠቀሱት በሁለቱ መንግሥታት በአክሲዮን መዋጮ የተቋቋመና በተረከበው መሠረት ልማትና ተንቀሳቃሽ ባቡሮች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ መሥሪያ ቤት እንጂ የግንባታ መሥሪያ ቤት እንዳልሆነና ማናቸውንም የመስመር ግንባታ እንደማይሠራ ግንዛቤ ያጥራቸዋል ብለን አንወስድም፡፡ ስለዚህ የነዳጅ ዴፓዎችን ከባቡር መስመሩ ጋር የማገናኘቱ ጉዳይ የግንባታ ሥራ ስለሆነ በኢትዮጵያ በኩል ከአዋሽም ሆነ ከዱከም ዴፓዎች ጋር ማገናኘት (ገንዘብ ካለ) የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኃላፊነት ሲሆን፣ በጂቡቲ ወገን ደግሞ የሆራይዘን ተርሚናል ኃላፊነት ነው፡፡ እስከዚያው የባቡር ቦቴዎቹ በአግባቡ ቆመው ይጠብቃሉ ማለት ነው፡፡ ለምን ተገዙም ከሆነ ጥያቄው ቅድም ካነሱት የአዋጪነት ጥናቱ ጋር ይያያዛል ማለት ነው፡፡ አቶ ናታን ያለቀለት የአዋጪነት ጥናት ያሉት ማለት ነው፡፡

አቶ ናታን በመጨረሻም ለአዲሱ ትራንስፖርት ሚኒስትር የኢትዮ ጂቡቲ ትራንስፖርት አገልግሎትን መፈተሽ የመጀመርያ ሥራቸው እንደሚሆንም ትዕዛዝ የሚመስል ማሳሰቢም ሰጥተዋል፡፡ እኛም ይኼን ማሳሰቢያቸውን እንደግፈዋለን፡፡ ፍተሻው ግን ከግንባታው ቢጀምር ብዙ ርቀትም ሳንሄድ ችግሩ ሁሉ ይገለጻልና አቶ ናታን ምንም እንኳን መሥሪያ ቤትዎን መከላከል ጥሩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንም በዚህ ፍተሻ ውስጥ በቅድሚያ እንዲካተት ለምን አልፈለጉም የሚል ጥያቄ በማንሳት ምላሻችንን እናጠቃልላለን፡፡

በነገራችን ላይ አቶ ናታን በብዕር ስም መጡ እንጂ፣ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሠራተኛ መሆናቸውን የጠረጠርነው ከዚህ ቀደም በዚሁ ዓምድ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈ ባቡር፣ ጎርባጣው ባቡር በማለት በተከታታይ ከጻፏቸው ጽሑፎች በመነሳት ነው፡፡ ካልሆኑም ውስጥ አዋቂ በሚል ተረዱልን፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- አቶ ጥላሁን ሳርካ (ኢንጂነር) የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ጄኔራል ዳይሬክተር ናቸው፡፡      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት