የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ከተሻሻለው የፌዴራል ሥራ አስፈጻሚ ተቋማት አደራጃጀት ጋር የሚስማማ ማሻሻያ፣ ተቋማቱን በሚቆጣጠሩ ቋሚ ኮሚቴዎቹ አደረጃጀት ላይ በመጪው ሳምንት እንደሚያካሂድ ታወቀ።
በአሁኑ ወቅት በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ላይ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉ 20 ቋሚ ኮሚቴዎች ይገኛሉ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በካቢኔያቸው ላይ ባደረጉት ማሻሻያ 30 የነበሩትን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በማጠፍ ወደ 20 ዝቅ በማድረጋቸው፣ ምክር ቤቱም የቋሚ ኮሚቴዎቹን ብዛት በዚሁ መጠን እንደሚቀንስ ምንጮች ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ከማድረግ በተጨማሪ፣ አዲስ የቋሚ ኮሚቴ ሊቃነ መናብርት ሹመትና ድልድል እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደ አዲስ በሚያቋቁመው የራሱ ቋሚ ኮሚቴዎች መካከል፣ ቅንጅት የሚፈጥር ሕጋዊ አሠራር በማሻሻያው እንደሚዘረጋም ምንጮቹ ገልጸዋል።
በሚደረገው ማሻሻያ በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ አደረጃጀት እንደማይኖር፣ ነገር ግን የገዥው ፓርቲ ተጠሪ ወይም በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች ተጠሪ አደረጃጀት እንደሚበልጥ ምንጮች ገልጸዋል።
የመንግሥት ተጠሪ አደረጃጀት ላለፉት አምስት ዓመታት በላይ በምክር ቤቱ ሲሠራበት የቆየና በምክር ቤቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደነበረውም ምንጮቹ ይገልጻሉ። የመንግሥት ተጠሪ ሆኖ የሚመደበው ገዥው ፓርቲን የሚወክሉ የምክር ቤት አባላትን በበላይነት የሚመራ ብቻ ሳይሆን፣ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆኑ ተፅዕኖው የጎላ እንዲሆን ማድረጉን፣ ይህም የምክር ቤት አባላት መንግሥትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሚናቸውን እንደጎዳ ይገልጻሉ።
ለዚህ የሚሰጡት ምክንያትም የመንግሥት ተጠሪው በምክር ቤቱ የኢሕአዴግ አባላትን በበላይነት የመምራት ኃላፊነትን ደርቦ በመያዙ፣ በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ሐሳብ የሚያቀርቡ አባላትን የመለየት ሕጋዊ ሥልጣን የነበረው መሆኑን ነው።
በምክር ቤቱ በሚደረጉ ውይይቶችም ሆኑ በፓርቲ መድረኮች የመንግሥት ተጠሪው አስተያየት እንደ መጨረሻ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር፣ ይህም ምክንያታዊ ሙግት ባህል እንዳይሆን ማድረጉን ያመለክታሉ።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ በመሆን ባለፉት ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ሲሆኑ፣ ከዚያ በፊት በምክር ቤቱ የኢሕአዴግ ተጠሪ በመሆን አቶ ሽፈራው ጃርሶ በመቀጠልም አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይታወሳሉ።