ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰበሰበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ፣ 288 ባለሀብቶች ለፋብሪካ ግንባታ ያቀረቡት የመሬት ጥያቄ እንዳይስተናገድ አገደ፡፡
ባለሀብቶች በተናጠል ለሚያካሂዷቸው የማኑፋክቸሪንግ ግንባታ በአጠቃላይ 133.65 ሔክታር መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው፣ አስተዳደሩ የጠየቁትን መሬት እንደሚሰጣቸው በማመን ሲጠባበቁ ነበር፡፡
የተፋለሱ አሠራሮችን በማስተካከል ሥራ ላይ የተጠመደው በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው ካቢኔ፣ የባለሀብቶቹን የመሬት ጥያቄ ባህሪያት ከመረመረ በኋላ ጥያቄያቸው እንዳይስተናገድ ዕግድ አስተላልፏል፡፡
መረጃዎች እንደጠቆሙት ካቢኔው ያሳለፈው እግድ በሁለት ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከዚህ ቀደም ለአልሚዎች መሬት ሲተላለፍ የቆየው ግልጽነት በጎደለው መንገድ ነው፡፡
‹‹የከተማውን የወደፊት ራዕይ ከግምት ያላስገባ፣ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የወጣውን መመርያ ቁጥር 16/2005 ያልተከተለ ብሎም ያፋለሰ ነው፤›› በማለት ካቢኔው፣ ቀደም ሲል መሬት የተሰጠበት አሠራር በጥልቀት እንዲታይና አዲስ የቀረቡት ጥያቄዎችም እንዳይስተናገዱ ዕግድ ጥሏል፡፡
ሁለተኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተናጠል የኢንዱስትሪ ልማት መሬት ጥያቄ መቀበል በማቆም፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት የባለሀብቶችን ጥያቄ ለማስተናገድ ውሳኔ በማሳለፉ ነው፡፡
በዚህ መሠረት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ፣ የአነስተኛና የመካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን የተሰኘ ተቋም አቋቁሟል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ጊዜ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 93.9 ሔክታር መሬት ተረክቦ የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት የተለያዩ ጥናቶችን እያካሄደ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢንዱስትሪ በከለላቸው ቦታዎች በርካታ ባለሀብቶች መሬት ወስደዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ 495.3 ሔክታር መሬት ለባለሀብቶች መተላለፉ ተገልጿል፡፡
ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ጥናቶች እነዚህ ቦታዎች ለታለመላቸው ግንባታዎች አልዋሉም፡፡ አብዛኞቹ ከውል ውጪ ለሆኑ ግንባታዎች ከመዋላቸው በተጨማሪ፣ ግንባታ ሳይካሄድባቸው የሚገኙ ሰፋፊ ቦታዎች መኖራቸውም ተመልክቷል፡፡