Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናከሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ግብረ አበሮቻቸው ጋር ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች...

  ከሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ግብረ አበሮቻቸው ጋር ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ

  ቀን:

  በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና ዙሪያው ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች በተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) እና ሌሎች ጋር ተሳትፈዋል የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

  በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላለፉት 64 ቀናት (እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ፣ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ራሂማ መሐመድ፣ የፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ፈሪሃን ጣሂርና የዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ መሐመድ አደራጅተውታል የተባለው ‹‹ሄጎ›› የወጣቶች ቡድን አባላት መሆናቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

  በቅርቡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ወጣት ጎሌድ አበልጎዳና ወጣት ወርሳቤ ሼክ አብዲ ሻሂ የሚባሉ ናቸው፡፡ በክልሉ ለአራት ቀናት በተፈጸመው ማፈናቀል፣ ተቋማትን ማቃጠል፣ የጅምላ ግድያ፣ ዘረፋና ሴቶችን በመድፈር ወንጀል ተሳታፊ እንደነበሩ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

  ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት የተቃውሞ አቤቱታ፣ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመበት ዞንና እነሱ የሚኖሩበት ዞን የተለያየ መሆኑን በማስረዳት፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ተማሪ መሆናቸውንና በወቅቱም ትምህርት ላይ እንደነበሩ አክለዋል፡፡ ወርሳቤ የሚባለው ተጠርጣሪ ዕድሜውን ሲያስመዘግብ 14 ዓመትና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን በመግለጹ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ዕድሜው በሕክምና ባለሙያ መረጋገጥ ስላለበት ወደ ጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ሆስፒታል መላኩንም መርማሪ ቡድኑ አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዕድሜን በሚመለከት ምርመራ ማቆሙን በመግለጹ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ምርመራው ተደርጎ፣ የወጣቱ ዕድሜ ‹‹ከ18 እስከ 20 ዓመት ይሆናል›› መባሉን ለፍርድ ቤቱ በሰነድ አረጋግጧል፡፡

  ተጠርጣሪው ግን የሆስፒሉታን የምርመራ ውጤት በመቃወም፣ በሌላ የሕክምና እስከሚረጋገጥ ድረስ ከጎልማሶች ጋር መታሰር እንደሌለበት አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ የሁለቱን ወገኖች ክርክር የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ግን፣ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን መቃወሚያ ውደቅ አድርጎታል፡፡

  በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩትን አቶ አብዲ መሐመድ፣ ወ/ሮ ፈሪሃ መሐመድ፣ አቶ አብዱራዛቅ ሳኒና አቶ ፈሪሃን ጣሂር የምርመራ መዝገብን በሚመለከትም፣ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ የሠራውንና ይቀረኛል ያለውን የምርመራ ሒደት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተፈቀደለት አሥር ቀናት ውስጥ የ11 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ በጅምላ ተቀብረው የነበሩ ሰዎች አስከሬን ምርመራ ሰነድ ለትርጉም መስጠቱን፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የምርመራ ውጤት ለትርጉም መስጠቱን፣ ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለሄጎ ቡድን ወጪ የተደረገን ገንዘብ የሚያሳይ ከ105 ገጽ በላይ የሰነድ ማስረጃ ለትርጉም መስጠቱንና በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ 53 ገጽ የሰነድ ማስረጃ ለትርጉም መስጠቱን አስረድቷል፡፡

  የሚቀረው የምርመራ ሒደት ደግሞ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን መያዝ፣ የወንጀል ድርጊቱን ከጥንስሱ እስከ ፍፃሜው ያለውን ሒደት የሚያውቁ የተለያዩ ምስክሮች ቃል መቀበል፣ በጅምላ ተቀብረው የነበሩ ግለሰቦችን ማንነት መለየት፣ በተለያዩ ቦታዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ቃል መቀበል፣ በሆስፒታል የታከሙ አካል ጉዳተኞችን ቃል መቀበል፣ ለትርጉም የተላኩ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰብ፣ የተደፈሩ ሴቶችን ቃል መቀበልና የተደበቁ በርካታ የጦር መሣሪያዎችንና ገንዘብ ፈልጎ መያዝ እንደሚፈቀረው አስረድቶ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

  ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት ተቃውሞ፣ መርማሪ ቡድኑ ለ64 ቀናት ደንበኞቻቸውን አስሮ ለፍርድ ቤት እያቀረበው ያለው የምርመራ ሪፖርት ተመሳሳይና አንድ ዓይነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተመሳሳይ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበው የምርመራ ሒደት፣ ምስክር መስማት፣ ሰነድ መሰብሰብና ማስተርጎም፣ ግብረ አበሮች መያዝ በማለት ከመቀጠሉ በስተቀር በአግባቡ ለሥራው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ባለመሆኑ፣ ‹‹የጠየቀው ተጨማሪ 14 ቀናት በፍፁም ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ የሕግ መሠረትም የለውም፡፡ እንዲያውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) ላይ የተሰጠን መሠረታዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ሊፈቀድ አይገባም፤›› ብለዋል፡፡

  ተጠርጣሪዎቹ ጠበቆቻቸው ያላነሷቸው ነጥቦች እንዳላቸው በመግለጽ እንዲናገሩ ችሎቱን ሲጠይቁ፣ በዕለቱ ሰብሳቢ ዳኛ ሆነው የተሰየሙት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው አንሺሶ ‹‹የቀራቸው ሐሳብ ካለ ለጠበቆቻችሁ ተናገሩና እነሱ ያስረዱ፡፡ አካሄዱ ስለማይፈቅድ እናንተ መናገር አትችሉም፤›› በማለታቸው፣ እነሱም ለጠበቆቻቸው ሳያስረዱ በዝምታ አልፈውታል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ የሠራውን ሲመለከት፣ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን መገንዘቡን ጠቁሞ፣ ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው ቢከበርላቸው ከአገር ሊወጡ እንደሚችሉ፣ ምስክር ሊያባብሉና ሊያስጠፉ፣ እንዲሁም ሰነዶቹን ሊያስጠፉ እንደሚችሉ፣ መርማሪ ቡድኑ የገለጸው ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 59(2) እና ከሕገ መንግሥቱ 19(5) አኳያ አሳማኝ መሆኑን መገንዘቡን በመግለጽ፣ የተጠርጣሪዎቹን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ቡድኑ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡           

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img