በቅርቡ ይፋ የተደረገው የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት መሠረት ተከትሎ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተነጥሎ፣ እንደ አዲስ ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀውን የጉምሩክ ኮሚሽን እንዲመሩ አቶ ደበሌ ቀበታ መሾማቸው ታወቀ፡፡
በአዲሱ አደረጃጀት የአገር ውስጥ ገቢ ሚኒስቴር ሲመሠረት፣ የጉምሩክ ዘርፍ ደግሞ በኮሚሽንነት እንደሚደራጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት የጉምሩክ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከ ሲሆን፣ በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ነገር ግን ረቂቅ አዋጁ ገና ባይፀድቅም የቀድሞው የአቃቂ ጉምሩክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደበሌ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሾማቸውን፣ ሹመቱም ለገቢዎች ሚኒስቴር ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ መገለጹን ከፍተኛ ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ የማቋቋሚያ አዋጁ እንደፀደቀ በሳምንት ውስጥ ኮሚሽኑ በቀጥታ ሥራ እንደሚጀመር፣ ለዚህም የአገር ውስጥ ገቢ ሚኒስቴር ኮሚሽኑን በፍጥነት አቋቁሞ ወደ ሥራ ለማስባት እየሠራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በተመሳሳይ መንገድ ከቀድሞው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ወደ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የተለወጠውን ተቋም በኮሚሽነርነት እንዲመሩ፣ አቶ በየነ ገብረ መስቀል መሾማቸውን ከኤጀንሲው ከተገኘ መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንዲሁም አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል የኤጀንሲው ምክትል ኮሚሽነር ሆነው እንደተሾሙ የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲሷ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሪት ዳግማዊ ሞገስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠሪነት ከሚኒስቴሩ ወደ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግሥት ውሳኔ መዛወሩን አስታውቀዋል፡፡
በአዲሱ መዋቅር መሠረት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ከ11 ወደ 10 ዝቅ ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የኢትዮጵያ መንገዶች በባለሥልጣን፣ የትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ የክፍያና መንገዶች ኢንተርፕራይዝ፣ የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት፣ የመድን ፈንድ አስተዳደር፣ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን፣ የምድር ባቡር አክሲዮን ማኅበርና የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ናቸው፡፡