ከሁለት ቢሊዮን ዶላር የድጋፍ ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሏል
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተገኙት፣ የዓለም ባንክ አባል ድርጅት የሆነው የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ሰርጂዮ ፒሜንታ፣ በኢትዮጵያ 500 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታወቁ፡፡
ሚስተር ፒሜንታ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በአፍሪካ ልማት መስኮች ድጋፍ ከሚሰጣቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት፡፡ በተለይም በፀሐይ ኃይል የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከማልማት እስከ ሥርጭት ባለው ሒደት ውስጥ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላትን የቴክኒክና የቁጥጥር አቅም ከመገንባት ጀምሮ፣ እስከ ድርድር አቅማቸው ባለው ደረጃ ኮርፖሬሽኑ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
በአይኤፍሲ ድጋፍ በአፍሪካ ትልቁ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል በማለት የገለጹት ይህ ዘርፍ፣ በመጀመርያው ምዕራፍ 250 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚፈልጉ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ የሚያስችል ዝግጅት ተካሂዶ፣ ለማልማት የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጨረታ እንዲሳተፉ የሚደረግበት ደረጃ ላይ ኮርፖሬሽኑ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በሚያቀርቡት ተወዳዳሪ ዋጋ መሠረት ጨረታው እንደሚካሄድና ለተጠቃሚዎች ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ከፀሐይ ምንጭ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመንገድና በሌሎችም መሠረተ ልማቶች ኮርፖሬሽኑ እንደሚሳተፍና እስካሁን በአገልግሎት፣ በጤና፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉት መስኮች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
‹‹የዓለም ባንክ የልማት ቀኝ እጅ ከሆነው የዓለም የልማት ማኅበር ባለፈው ዓመት የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝተናል፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳጊ አገሮች ተርታ የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላትን ቅድመ ሁኔታ ስለምታሟላ ድጋፍ ታገኛለች፤›› ቢሉም፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ ለኢትዮጵያ ይደርሳታል የሚለው በሒደት እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለአገሮች ድጋፍ ይውላል ብለዋል፡፡ ይሁንና ከፍተኛ የሥጋት ተጋላጭነት የሚታይባቸውንና የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍባቸውን ፕሮጀክቶች ለማገዝ የሚውል ድጋፍ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ እንደ አግሪ ቢዝነስና ማኑፋክቸሪንግ ያሉት ዘርፎች ከዚህ የድጋፍ መስኮት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡
በቅርቡ የ6.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ 17 ሜጋ ፕሮጀክቶች ይፋ መደረጉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክተር ጄነራል ተሾመ ታፈሰ (ዶ/ር) ጋር በተደረገ ቆይታ ወቅት መንግሥት በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲለሙ ከለያቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ ከውኃና ከፀሐይ ኃይል የሚለሙ 13 የኃይል ማመንጫዎችና 18 ሌሎች የኃይል ማስተላለፊያና የሰብስቴሽን ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ሦስት የፍጥነት መንገዶች ይፋ ተደርገዋል፡፡
ምንም እንኳ እስካሁን ባለው ሁኔታ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ ባያደርግም፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ግን በመንግሥት ይፋ ከተደረጉ ፕሮጀክቶች መካከል በተለይ በፀሐይ ኃይል መስክ ‹‹ስኬሊንግ ሶላር›› የተባሉት ፕሮጀክቶች ላይ ኮርፖሬሽኑ ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡
በመንግሥት ይፋ ከተደረጉት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች እንዲገነቡ የታቀዱትና እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ሁለት የ‹‹ስኬሊንግ ሶላር›› ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በአፋር ክልል በግል አልሚዎች ተገንብተው ለመንግሥት በመሸጥ የፀሐይ ኃይል እንዲያቀርቡ የታቀዱት፣ በአፋር ክልል ዲቼቶ ስኬሊንግ ሶላር የተሰኘውና በሶማሌ ክልል ጋድ ስኬሊንግ ሶላር ፕሮጀክት ይጠቀሳሉ፡፡ እያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠይቁ የተጠቀሱት እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ፣ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡