Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየንግግር መድረኮች ለዴሞክራሲ ግንባታ ያስፈልጉናል!

የንግግር መድረኮች ለዴሞክራሲ ግንባታ ያስፈልጉናል!

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ሪፖርተር መስከረም 13 ቀን 2011 .. “የሕዝብን ቀልብ የሚገዛው የላቀ ሐሳብ ነው!” በሚል ርዕስ በጻፈው ርዕሰ አንቀጹ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ይጠብቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን እያመነዠኩ በሌላ መንገድ እነሱን ለመድገም መሞከር ትርፉ ውድቀት ነው፡፡ በሠለጠነ መንገድ መቀራረብ፣ መነጋገርና መደራደር የሚጠቅመው የተሻሉ ሐሳቦች እንዳይባክኑ ነው፡፡ የላቀ ሐሳብ ተጨምቆ የሚወጣውና አሸናፊ የሚሆነውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የሐሳብ እጥረት ያለበት ሌላውን አደናቅፎ አገርን ከሚያተራምስ ወደ ውስጡ ቢመለከት ይበጀዋል፡፡ በተለይ ጽንፈኝነት ከውስጣቸው ተንጠፍጥፎ አልወጣ ያላቸው ወገኖች መልካም አጋጣሚን ከሚያመክኑ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብን ይማሩ፡፡ ዴሞክራሲ ስላነበነቡት ሳይሆን፣ በሚገባ አውቀውት ተግባራዊ ሲያደርጉት ነው ማንነትን የሚመሰክረው፡፡ ለማነብነብማ አምባገነኖች ጣዕሙ እንዳለቀ ማስቲካ ሲያመነዥጉት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች ጽንፈኛ አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አደብ አስገዝተው ለሐሳብ ነፃነት ይታገሉ፡፡ የሐሳብ ልዕልና ይቅደም ይበሉ፡፡ የሕዝብን ቀልብ የሚገዛው የላቀ ሐሳብ ብቻ ነው!›› በማለት ያስነብበናል። ዳሩ ግን የሕዝብን ቀልብ የሚገዛው ሐሳብ እንደምን ወደ ሕዝብ ሊደርስና በሕዝብ ሊሰርፅ ይችላል?

ምንም እንኳን መድረሻዎቹና መሠራጫዎቹ በርካታ ቢሆኑም ጸሐፊው እንደ አንድ ጉድለት የማያየውና ክፍተቱ መሟላት አለበት ብሎ የሚያምነው አንደኛው መንገድ የንግግር መድረክ ዕጦት ብቻ ሳይሆን፣ የንግግር ጥበብም ጭምር ነው። ይኼንንም እንደሚከተለው ለማቅረብ ይሞክራል። 

- Advertisement -

የሕዝብን መንፈስ የሚማርክ ለጆሮ የሚጥም ንግግር የማድረግ አስፈላጊነት 

ዛሬ በአገራችን በርካታ የፖለቲካ ንቅናቄዎችና ፖርቲዎች በየጊዜው እየተፈጠሩና እያደጉ ናቸው። አንዳንዶቹም የመልካም አዝመራ ውጤታቸውን የሚያፍሱ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ፈጥነው አድገው ፈጥነው ይከስማሉ፡፡ አንዳንዱ ራሳቸውን ችለው ሲቆሙ፣ ሌሎች ደግሞ እንደ ሐረግ የሌላ ድጋፍ የሚሹ ይሆናሉ። በዚህ የዴሞክራሲ ሀሁ እየቆጠርን ባለንበት ወቅት ግን የልዩ ልዩ ድርጅቶች መሪዎች በየአጋጣሚው የሕዝቡን መንፈስ የሚማርክ ለጆሮ የሚጥም ንግግር የማድረግ አስፈላጊነት ጎን ለጎን እየጎላ መምጣቱ አልቀረም፡፡ ይህም ከንግግር ጥበብና ጥበቡን ለማዳበር ጥረት ከማድረግ ጋር ይያያዛል፡፡ ታዲያ የንግግር ጥበብ ምንድነው? ብሎ ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

ኒውማንና ጀኔቨየቭ ቢ ብሬክ ‹‹አንደርስታንዲንግ ኤንድ ዩዚንግ ኢንግሊሽ» በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን (1951)፣ የንግግር ችሎታን በተመለከተ ከጥንት ግሪካውያን ፈላስፎች አንስቶ በሕይወት እስካሉት ሊቃውንት ድረስ በርካታ ትንታኔ ተሰጥቷል፡፡ ሲሰሮ የንግግር ችሎታ በከፍተኛ የጥበብ ሥራ ውስጥ እንደሚካተት ሲገልጽ፣ ደሞስቴንም በሕዝብ መካከል ውብ የሆነ ንግግር ለማድረግ ከፍተኛ ድምፅ ካለው ፏፏቴ ጋር በማወዳደር ልምምድ ያደርግ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን። እንደ ቶማስ ጀፈርሰን፣ አብርሃም ሊንከን፣ ዊንስተን ቸርችል፣ ማህታማ ጋንዲ፣ ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ ሌኒን፣ ስታሊን፣ ሂትለር፣ ሞሶሊኒ፣ ፍራንከሊን ዴላኖ ሩዝቬልት፣ ማኦ ዜዱንግ፣ ፊደል ካስትሮ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግና የመሳሰሉት የሕዝባቸውን ስሜት በንግግራቸው ይማርኩና ሐሳባቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርጉ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ጆርጅ ካምፕቤል የተባሉ ሊቅም የንግግር ጥበብን ከሕንፃ ጥበብ ጋር አነፃፅረው ሲገልጹት፣ «ሁለቱም የጥበብ መስህቦች ውበትና ጠቀሜታ አላቸው፤» በማለት አስቀምጠውታል፡፡
       በሕዝብ ፊት ያማረ ንግግር ማድረግ ብዙ ሰዎች እንደሚገምቱት ከለፍላፊነት ጋር በጭራሽ የተያያዘ አይደለም። አንድን አገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ለመለወጥ የሚያበቃ ልሳነ ቅንነት ወይም አንደበተ ርቱዕነት ጥበብ ነው። ይህም ጥበብ የተሞላበት ንግግር ለማድረግ ከሁሉ አስቀድሞ ስለሚናገሩት ጉዳይ መምረጥ፣ በመረጡት ጉዳይ ላይ በቂ ትንታኔ ለመስጠት መቻል፣ ለመተንተንም በቂ ጥናት ማካሄድ ይጠይቃል። ይህም ከተናጋሪው የመፍጠር፣ የመፈላሰፍና የነገር ብልት አወጣጥ ጋር ሲዳመር የበለጠ ይሆናል፡፡ ንግግር አድራጊዎች ጥበብ በተሞላበት ዘይቤ ቃላቱን ከአንደበታቸው ሲያንቆረቁሩት አድማጭ ደግሞ ውኃ የተጠማ ያህል አፉን ከፍቶ ያዳምጣል፡፡ ይህም ማለት ንግግራቸውን ብቻ ሳይሆን አድማጫቸውንም አሳምረው መያዝ፣ ስለእነሱም በጥንቃቄ ማሰብ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እጅግ ያማረ ንግግር የሚመነጨው ተናጋሪው ስለሚናገርበት ጉዳይ ከፍተኛና ጥልቀት ያለው ሐሳብ ሲኖረውና በሚማርክ ስሜት ተሞልቶ ለማቅረብ አቅም ሲኖረው ነው። የተናጋሪውን ጥልቅ ፍላጎት ካንፀባረቀ ደግሞ የደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን፣ የተቃዋሚዎቹን ልብ ሊማርክ ይችላል፡፡ 

እስካሁን ድረስ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጥሩ የአነጋገር ችሎታ የተናጋሪውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚረዳ ቢሆንም፣ እንዴት ጥሩ ንግግር ለማድረግ እንደሚቻል ግን ዘዴውን በጥብቅ መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ሔንሪ ኑማን የተባሉ ሊቅ ምሁር ስለሚባል ሰው ፀባይ አስመልክተው ሲናገሩ፣ «ጨዋ ሰው ማንኛውም የሚያንቀጠቅጥና የሚያንዘፈዝፍ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን በትዕግሥት የሚያስተናግድ፣ የሚያፋጭና የሚያነታርክ ሐሳብ በውይይት ወቅት ቢነሳም፣ ውዝግብና ውጥረት እንዲሁም መጠራጠርንና ወደ አንድ አቅጣጫ የማይወስደውን የደበዘዘ ሁኔታ አስለውጦ ሰዎችን የሚያረጋጋና አስማምቶ ወደየቤታቸው የሚሸኝ ነው፡፡ እንደዚህ ያለው ሰው ጓደኞቹን ሁሉ የሚመለከታቸው በአንድ ዓይን ነው። ለዓይነ አፋሮችም ሆነ ባዕድነት ለሚሰማቸው ደግ፣ ባለማወቅ ለተሠራ ስህተት ፈጥኖ ይቅር ባይ፣ የሚናገረውን አስተዋይ፣ የሰውን ንግግር ሳይሰለች የሚያዳምጥ ነው። ጨዋ ሰው ካልተጠየቀ በስተቀር ስለራሱ አይናገርም፡፡ ለሰዎች ውለታ ሲሠራ የተሠራ ያህል አይሰማውም፡፡ ለሐሜትና ለአሉባልታ ጆሮ የለውም፡፡ በሚሰጠው አስተያየት ትክክልም፣ ስህተትም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስህተቱ የሚፈጥረው ትክክል እንደሚሠራው ሁሉ ከቅንነት ነው፤» በማለት ያስቀመጡት የመልካም ተናጋሪ ምሳሌ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ በሕዝብ ፊት ጥሩ ንግግር ለማድረግ ደግሞ የተፈጥሮ ችሎታ ብቻ አይበቃም፡፡ በነገረ ጥበብ መጠበብ ያስፈልጋል። ጠቢብ ለመሆን ደግሞ ጠበብት በዚህ ሐሳብ ላይ ተመርኩዘው ስለሰጡት አስተያየት ማወቅ፣ በርካታ ለሆኑ ጊዜያት የታላላቅ የሰዎችን ንግግር ማዳመጥና ለብዙ ጊዜ የመናገር ልምምድ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ንግግር አድራጊ የሰመረ መልዕክት በራስ የመተማመን ስሜት ማስተላለፍ የሚችለው፣ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ የቀረበ እንደሆነ ነው። በግሉ የሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ፣ የተከበረና ተመራጭ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም። ይህም ለሕዝብ ንግግር በማድረግ ለማሳወቅ፣ ለመሳብና ወደሚፈለገው አቅጣጫ ለመውሰድ ችግርን አልፎ አርኪ ውጤት ማግኘት የሚቻል መሆኑን የሚያሳምን ነው።

 በአገራችን በዚህ በኩል የሚሰጥ ትምህርት የለም እንጂ፣ በሌሎች አገሮች ግን ስላለ ዕድሉና ፍላጎቱ ካለ መማርም እንደ አንድ መፍትሔ ይቆጠራል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን በሕዝብ ፊት ለመናገር ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች፣ ነገር ግን ደግሞ ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር ያልቻሉትን ለመረዳት ነው፡፡ ስለዚህም ንግግር አድራጊ አድማጮቹ እንቅስቃሴውን፣ የአገላለጽ ስሜቱንና የድምፁን አወራረድ ተመልክተው አስተያየት የሚሰጡት ለነገሩ ብቻ ሳይሆን፣ ለተናጋሪው ዕውቀት ጭምር መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ስለዚህም ተናጋሪው አስደሳች ንግግር ለማድረግ ከፈለገ ከተመልካች ጋር አስደሳች ግንኙነት ለመፍጠር አስቀድሞ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት ንግግር ከሚያደርግላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነትንና በእነሱ የመተማመን ስሜትን ማሳደር ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥሩ የንግግር ችሎታ አለው የሚባል ሰው ስሜታቸውን የሚነካና በሐሳብም ተካፋይ የሚያደርግ ነጥቦችን እያነሳ፣ ተካፋይ የሚሆኑበትን መንገድ ማግኘቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። የሚያቀርባቸው መረጃዎችና ልምዶች ለሕዝቡ ያለውን ታማኝነት ማረጋገጫዎች፣ ፍላጎታቸውን ተረድቶ ወደ እነርሱ ማዘንበሉን የሚፈነጥቁ ምልክቶች መሆናቸውንና አለመሆናቸውን አስቀድሞ ማስተንተን ይጠበቅበታል። ከባህላቸው፣ ከወጋቸውና ከሰብዓዊ ክብራቸው ጋር የተያያዘ መሆኑንም ማጤን ይኖርበታል፡፡

በመሠረቱ ልሳነ ቅንነትን ወይም አንደበተ ርቱዕነትን ተላብሶ የሚስብ ንግግር ለማድረግ መወሰድ ስላለበት፣ ለቅድሚያ ጥንቃቄና ጥበብ በቂ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሕዝብ ፊት ንግግር ለማድረግ የተፈጥሮ ችሎታ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ጠበብት በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት አድርገዋል፡፡ በዚህም ጥናት ዓለምን የቀየሩ ሰዎች አደርገዋለሁ፣ ይሳካልኛል፣ ይሆንልኛል ብለው ወስነው የሚነሱ ናቸው። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ቢወድቁ እንደሚነሱ አሳምረው ያውቃሉ። ሆኖም ጀርመናዊው ደራሲና ፈላስፋ ወልፍ ጋንግ ፈንገተ እንደገለጸው፣ ‹‹ማወቅ ብቻ አይበቃም፣ የሚያውቁትን በተግባር ማዋል ያስፈልጋል። ምኞት ብቻ አይበቃም፣ ማድረግን ይጠይቃል፡፡›› 

የዓለማችን ምርጥ ንግግሮችና ውጤቶቻቸው

 እንግሊዛዊው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ለምሳሌ ካደረጉት ሰፊ ንግግር የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀጾች ያዋሉት፣ የአድማጮቻቸው ስሜት በመማረክ መሆኑን ከሚከተለው ንግግር እንመልከት፡፡ ‹‹ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንድገባና የሁለቱም ጉባዔዎች ተወካዮች በሚገኙበት ሥፍራ ተገኝቼ ንግግር ለማድረግ በመቻሌ ታላቅ ክብር ይሰማኛል፡፡ የጥንት አባቶች ለዩናይትድ ስቴትስ ህልውና ለብዙ ዓመታት ጥረት እንዳደረጉት ሁሉ እኔም አንዱ እንግሊዛዊ በመካከላችሁ ተገኝቼ ስስተናገድ በሕይወቴ ከተከናወኑት አስደናቂ ነገሮች ሁሉ የላቀ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ይኼንንም አስደናቂ ሁኔታ ትዝታዋ በአዕምሮዬ የማይጠፋው እናቴ ብትመለከተው ኖሮ ምንኛ ወሰን የሌለው ደስታ ይሰማኝ እንደነበር ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ነገሩ የተገላበጠ እንጂ፣ አባቴ አሜሪካዊ እናቴ ደግሞ እንግሊዛዊ ቢሆኑ ኖሮ ሳልጋበዝ ከመካከላችሁ በተገኘሁ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ድምፄን የምትሰሙት ለመጀመሪያ ጊዜ ባልሆነ፣ በዚህም ምክንያት ተጋባዥ እንግዳችሁ ለመሆን ባልፈለግሁም ነበር፡፡ ብፈልግ ኖሮ ደግሞ በስምምነት የሚፈጸም ነገር በሆነ ነበር፡፡ ይሁንና ነገሮች እንዳሉ ቢሆኑ ደግሞ የተሻሉ ናቸው ብዬ እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ ግን ምንም እንኳን ተጋባዥ እንግዳችሁ ሆኜ ብመጣም፣ እንግሊዝኛ በሚናገሩ ጉባዔተኞች መካከል ስለምገኝ ከባህር የወጣ ዓሳ እንደሆንኩ ልናዘዝላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ የሃውስ ኦፍ ኮመንስ ልጅ በመሆኔም፣ በዴሞክራሲና በሕዝብ እንዳምን በአባቴ ቤት ተኮትኩቼ ያደግሁ ነኝ። በመሠረቱ ያኔ ዘመኑ የአርስቶክራቶችና የቪክቶሪያውያን እንዲሁም ዓለም የጥቂቶች ለዚያውም በጣም ጥቂት የሆኑ ሰዎች ናት በሚልባት ጊዜ አባቴ ከሠራተኛው መደብ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረው፡፡ ስለዚህም በአትላንቲክ ውቅያኖስ ሁለት ዳርቻዎች የሞኖፖሊ ማዕከል በሚነፍስበትና በጌትስበርግ የመንግሥት ሐሳብ ከሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ የሚል በነበረበት ጊዜ በመልካም ሁኔታ ላይ ነበርኩ፤›› በማለት የአሜሪካውያንን ልብ ማርከዋል።

‹‹ነገ ማድረግ የሚገባንን እንዳናከናውን የሚያደርገን ዛሬ ያለን ጥርጣሬ ነው፤›› በማለት በመግለጻቸው የሚጠቀሱት ፍራንክሊን ሩዝቬልት የተባሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም፣ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 2 ቀን 1933 በአርበኞች መሀል ተገኝተው ያደረጉት ንግግር በእሳቸውና በአድማጮቻቸው መካከል ከፍተኛ ግንኙነት ወይም ልብን የማሸነፍ ሚና ተጫውቷል የሚል ግንዛቤ አለ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያደረጉት ንግግር፣ ‹‹ወደዚህ ሥፍራ የእናንተ ጓድ ሆኜ ዳግመኛ ስመጣ ደስ ይለኛል። የመጣሁትም በአሜሪካ ጦርነቶች ውስጥ በተካፈሉ አርበኞች እምነት ስላለኝ ነው፡፡ እንዲሁም እናንተ ወደ ኋይት ሃውስ መጥታችሁ ልታዩኝ እንደምትችሉት ሁሉ እኔም እናንተ ወደምትገኙበት ሥፍራ መጥቼ ለማየት ስለምችል ነው፡፡ የእኔና የእናንተ ግንኙነት ባሳለፍናቸው የጦርነት ጊዜያት ላይ ሁሉ እንጂ በስድስት ወራት የተመሠረተ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። ይህም ብቻ አይደለም፣ እናንተ እኔ ችግራችሁን እንድፈታላችሁ እንደምትሹት ሁሉ፣ እኔም ከእናንተ ዘንድ የመፍትሔ ሐሳብ ለመፈለግ ነው፡፡ የጦር ሠራዊት ማኀበር እስካሁን ድረስ በፈታኞቹ ወቅቶች ያሳየውን ትዕግሥትና ታማኝነት እኔም ሆንኩ አገሬ ታደንቀዋለች፡፡ በዚህም ምክንያት አመርቂ ውጤት ልናስገኝ ችለናል፡፡ የሆነ ሆኖ ዛሬም ስለብሔራዊ አንድነት ላነጋግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ይኼንንም ሁኔታ በመጽሐፍ ላይ እንዳለው ጽንሰ ሐሳብ ወይም የንግድ ሰዎች በገበያ ውስጥ እንደሚያደርጉት መደራደር ሳይሆን፣ እንደ አንድ ሕይወት እንዳለው ነገር የሚታይ ነው፡፡ ይህም ማለት እርስ በርሳችን በጋራ ገበያ የምንኖርበት የጋራ መንግሥት፣ የጋራ ታክስ የምንከፍልበት ከመካከላችንም ብዙዎቹ ከፍተኛ ታክስ የሚከፍሉበት ማለት ነው፡፡ በዚህ ገበያ እኛ ለሌሎች እንደምንሰጠው ሁሉ ከሌሎችም እንቀበላለንና፡፡ ስለዚህም የአገሪቱን አንድነት ማወቅ ማለት፣ ከሌላው ነገር ሁሉ ተቀዳሚ ማድረግ ማለት፣ የጋራ የሆነ በጎ ነገር ሁሉ በእርሷ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ማጤን ማለት ነው። ይህ ሲሆን በሌላ አነጋገር በውስጣችን ጀግንነት አለን ማለት ነው፡፡››

ከዚህ ንግግር የምንረዳው ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረው ከአድማጮቻቸው ጋር በአካልም በመንፈስም አንድ ለመሆን ያልተቆጠበ ጥረት ለማድረግ መቻላቸውን ነው፡፡ «አባት አርበኛ ጓዶች፣ አሁንም አገር መልሶ የመገንባት ቀጣይ ተግባም የበለጠ ጥረትን የሚጠይቅ ነው። እስካሁን ለአገራችን ህልውና ሕይወታችሁን ለመለገስ ዝግጁ መሆናችሁን ያረጋገጣችሁ፣ በሁሉም ግንባር ትብብራችሁን በግንባር ቀደምነት በማሳየት ያገለገላችሁ፣ ለአሜሪካ ሕዝብ አንድነት ቃለ መሃላ ያደረጋችሁ፣ የአሜሪካዊ ዜጋ ታላቅነትን ሐሳብ የደገፋችሁ፣ ዛሬም እንደገና ለአሸብራቂ ሥራ ተመርጣችኋልና እንደ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትና እንደ ጓዳችሁ ከእናንተ የአዎንታ ምላሽ እጠብቃለሁ፤» በማለት ወኔ የሚቀሰቅስ ንግግርም አድርገዋል፡፡ ሁለቱም ንግግሮች ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችሉ ስለነበሩ፣ በተናጋሪውና በአድማጩ መካከል የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር የተደረገውን ጥረት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህም ንግግር በቂ ምላሽ ያስገኘ በመሆኑ ሐሳቡን የተቀበሉት አድማጮች ምን ያህል ተናጋሪው ለእነሱ ታማኝና ትሁት እንደነበሩ አረጋግጦላቸዋል፡፡

ቀደም ሲል በፖለቲካው ረገድ የሚደረገው ንግግር ምን መምሰል እንዳለበት ለመግለጽ የተሞከረ ሲሆን፣ በሌሎች ማኀበራዊ ግንኙነቶችም ሆነ የመዝናኛ ፕሮግራሞች የሚደረግ ንግግርም ቢሆን ለአድማጭ ጆሮ የሚጥም እንዲሆን በቃላት አመራረጥም ሆነ በድምፅ ቅላፄ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ንግግር ያማረ የሚሆነው ግን ኮምጠጥ ብሎ በመናገር ሳይሆን ሰውነትን ፈታ አድርጎ ነው፡፡ ኮስታራ ተናጋሪ እንኳን ቢሆን አልፎ አልፎ የአነጋገር ለዛዎች ጣል ማድረግ ተገቢ እንደሆነ፣ በዚህ ረገድ የበሰለ ሙያ ያላቸው ሊቃውንት አስተያየታቸውን ይለግሳሉ፡፡ ጥሩ ንግግር ለማሰማት መደረግ ያለበት ዝግጅት በሕዝብ ፊት ጥሩ ንግግር ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች፣ አብዛኛዎቹ ምን መናገር እንዳለባቸው በብጣሽ ወረቀት ወይም በሐሳባቸው ቅደም ተከተል አውጥተው መቅረብ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ንግግር በሚጀምሩበት ጊዜ  ይዞርባቸውና ምን እንደተናገሩ እንኳን ሳያውቁ የሚቀሩ፣ ያደረጉት ንግግር የሕዝቡን ስሜት ይቀስቅስ አይቀስቅስ ከሁኔታው የማይረዱ ይኖራሉ፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? መልሱ በጣም አጭር ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ሰዎች ለመናገር እንጂ፣ እንዴት እንደሚናገ ምን እንደሚናገሩ፣ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ አያውቁም፡፡ በሌላ አጭር መግለጫ አልተዘጋጁበትም፡፡ ራሳቸውንም አላዘጋጁም፡፡ ስለዚህም አንድ ንግግር አድራጊ በመጀመሪያ ስለሚናገረው ርዕሰ ጉዳይ ጠንቅቆ ማወቅ፣ ቀጥሎም የሚናገረውን ሐሳብ በቅደም ተከተል መንደፍ፣ በሦስተኛ ደረጀ ንግግሩን ብቻውን ሆኖ መለማመድና በመጨረሻም ንግግሩን በተግባር መግለጽ ናቸው፡፡ ስለርዕሰ ጉዳዩ ጠንቅቆ ማወቅ ሲባል የተናጋሪውና የአድማጩን፣ እንዲሁም የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘብ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በረሃብ በተጎዳ ሕዝብ መሀል ባልተራቡ ሰዎች ንግግር ቢደረግ ምፀት ከመሆን ሊዘል አይችልም፡፡ ይህም ማለት በረሃብ የተጎዳ ሕዝብ ስለጥጋብ እንኳን ቢነሳለት፣ ከእሱ ፍላጎትና ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተዛመደ መሆን አለበት፡፡ ስለረሃቡ ማንሳት ሲፈልግም ስለዚህ ጉዳይ ውስጠ ሚስጥሩን ፈልፍሎ መረዳት ይጠቅማል፡፡ እንኳን ከምንም ተነስቶ፣ ትንሽ ዕውቀት ይዞ መነሳት በተናጋሪው ላይ እምነት የሚያሳጣ ከመሆኑ በላይ ያስንቀዋል፡፡ የሌላውን አካባቢ ምሳሌ ይዞ መነሳት እንኳን በቂ የማይሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን እንመልከት፡፡
    «ጓዶች በአሁኑ ጊዜ አገራችን ከፍተኛ የሆነ አብዮት እያካሄደች ነው፡፡ በአንፃሩም ደግሞ ፀረ አብዮታዊና ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ስለሚፈታተኑን ወዳለምነው ግብ በቀላሉ ለማምራት አልቻልንም፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ ደግሞ በብዙ አብዮት ባካሄዱ አገሮች ተከስቷል፡፡ የቻይና አብዮት ለምሳሌ የወሰድን እንደሆነ ለድል አድራጊነት የበቁት የጫማቸውን ቆዳ እየበሉ ነው። ስለዚህ እኛም አብዮታዊ ትግሉን ከዳር ለማድረስ የእነሱን አርዓያ መከተል ይጠበቅብናል፤» የሚል ንግግር አንድ ጥራዝ ነጠቅ ካድሬ ለደሃ ገበሬዎች ያቀርባል፡፡ ከገበሬዎች አንዱ፣ «ነገሩ እንዳሉት ሊሆን ይችላል። እነሱስ ጫማቸውን በሉ፣ እኛ ጫማ የሌለንስ ምን እንብላ?» ብሎ ይጠይቃል። ተናጋሪው መባሉን እንጂ አባባሉ የሚያስከትልበትን ችግር ድሮውንም አስቦ ያደረገው ስላልነበረ፣ «ጥፍርህን ብላ ጥፍራም!» አለና ጩኸቱን አንቧረቀበት ይባላል። ይህ ቀላል ምሳሌ የሚያመለክተን በመጀመሪያ ንግግር ከማድረግ በፊት የሚናገሩትን ርዕሰ ጉዳይ ማወቅ፣ ከተናጋሪውና ከአድማጩ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ወይም የማይጣጣም መሆኑን ማጤን፣ ከዚህም በተጨማሪ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር አብሮ ይሄዳል ወይስ አይሄድም? ብሎ ለአፍታ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡
በመሠረቱ ተናጋሪው የሚናገረውን ርዕሰ ጉዳይ ጠንቅቆ ማወቅ ብቻ በቂ የማይሆንበት ጊዜም እንዳለ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ተደጋግሞ ለመግለጽ እንደተሞከረውም፣
‹‹ለሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት እታገላለሁ፣ ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በግንባር ቀደምነት እሠለፋለሁ፣ በሕዝቦች መካከል እኩልነት፣ ወንድማማችነት፣ ፍቅርና አንድነት ዕውን ሆኖ ማየት እፈልጋለሁ፤›› የሚልም የሌሎችን መብቶች መጠበቅ የሚኖርበት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ካለው ፅኑ እምነት የመነጨ ቢሆን ይመረጣል፡፡       ቮልቴር «የተናገርከው ሙሉ በሙሉ ስህተት መሆኑን አውቃለሁ፣ ነገር ግን የፈለግኸውን እንድትናገር እስከ መጨረሻው ከጎንህ እቆማለሁ፤» በማለት ያስገነዘበውን ብዙ ዴሞክራቶች እየጠቀሱት የሚኖሩትም፣ «እኛ ትክክል ነን፣ ነገር ግን ሌሎቹ ስህተታችንን፣ ድክመታችንንና የተሳሳተ አቅጣጫችንን ሲነግሩን መብታቸው መሆኑን መቀበል አለብን፤›› ለማለት ነው፡፡ ይህም ከሆነ ወደፊት በቀበሌም ሆነ በወረዳ የሚካሄደው ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ይከናወናል፡፡

በዚህች ዴሞክራሲን ለማስፈን ጥረት በሚደረግባት አገር የዓለም ፖለቲከኞች፣  «እውነት እነዚህ ሰዎች ዴሞክራሲያዊ ሆነ መንገድ ምርጫ ያካሂዱ ይሆን?» ብለው በታላቅ ጉጉት በመጠበቅ ላይ ባሉበት ወቅት፣ አስመራጭ አካላት ኢ ዴሞክራሲ የሰፈነበት ተልዕኮ እንዳይከናወን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ አስመራጮች እነሱ ተናጋሪዎች ሕዝቡ ደግሞ አድማጭ፣ እነሱ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሕዝቡ ደግሞ ፈጻሚ፣ እነሱ የምርጫው አቅጣጫና ማንነት ጠቋሚ፣ ሕዝቡ ደግሞ ተጠቋሚ ከሆነ ዴሞክሪሲያዊ እውነትነት ይቀራል፡፡ በሕዝብ የልብ ትርታ መመራቱ ቀርቶ በሸፍጥ መጓዝ ይመጣል። ውጤቱም የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በቀጣዩ ምርጫ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለውን ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ለመዘርጋት መሆኑን በማረጋገጥ መራጮችም፣ አስመራጮችም፣ ተመራጮችም፣ ኃላፊነታቸውን በትክክል እንዲወጡ የሚያስችል ሁኔታ ያመቻቻል ብለው፣ የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝቦች እንዲሁም ታሪክ ይጠብቃሉ፡፡

ንግግር የማድረጊያ ሥፍራ

አንዲት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቆርጣ የምትነሳ አገር ሕዝብ በአስተሳሰብ እንዲመራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅባታል። ከእነዚህ አንዱም የንግግር አደባባይ ማዘጋጀት ይጠበቅባታል። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በአዲስ አበባ ውስጥ ምሁራን ሐሳባቸውን የሚሰጡባቸው ሥፍራዎች ከእነዚህም ውስጥ የወወክማ አዳራሾች ይጠቀሳሉ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ጉድ የሚያሰኝ ንግግር የማድረግ ልማድ መሥርተው ነበር። የደሴ ተማሪዎች አራዳ ላይ ያደረጉት የነበረው ንግግር አይረሴ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሕዝብ ንግግር ሊያደርግ የሚችልባቸው አደባባዮች አሉ። በእነዚህ አደባባዮች ሰላማዊ የሆነ የንግግር ገበያ መፍጠር ይቻላል። ይህም ሲሆን ሰዎች ስለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሒደት ግንዛቤ ይኖራቸዋል። የታፈኑ አፎችና ስሜቶች መተንፈሻ ያገኛሉ። ‹‹እነገሌ ምን አሉ? ሌሎቹስ? የትኛው አመለካከት ይሻላል?›› ወደሚል ይኬዳል። ይህ በመገናኛ ብዝኃን ሲስተጋባ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው አሉባልታ ቦታ ያጣል። በዚች አገር ወደፊት ሥልጣን የሚይዙ ወጣቶች የዴሞክራሲ ልምድ ያገኛሉ። የከተማና የጫካ ሽፍትነት ይቀራል።

ማጠቃለያ

ሪፖርተር በዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያ ላይ እንዳቀረበውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ይጠብቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን እያመነዠኩ በሌላ መንገድ እነሱን ለመድገም መሞከር ትርፉ ውድቀት ነው፡፡ በሠለጠነ መንገድ መቀራረብ፣ መነጋገርና መደራደር የሚጠቅመው የተሻሉ ሐሳቦች እንዳይባክኑ ነው፡፡ የላቀ ሐሳብ ተጨምቆ የሚወጣውና አሸናፊ የሚሆነውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አዎን መሪዎቻችን የሚመኙትን ለማድረግ የሚቸገሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ሆኖም ከ1901-1909 (እ.ኤ.አ.) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቴዎዶር ሩዝቬልት፣ ‹‹የትም ብትሆን ባለህ ነገር ሁሉ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤›› እንዳሉት የሚቻላቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በመጨረሻም አንዳንድ ነጥብ “የሺ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንዲሉ የተሳካለት ተናጋሪ ለመሆን አንባቢ መሆንን ይጠይቃል። ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ማርከስ ታሊየስ ሲሰሮ እንዳለው፣ ‹‹መጽሐፍ የሌለበት ክፍል ነፍስ እንደሌለው አካል ነው፡፡››

መልካም የምርጫ ዝግጅት!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...