ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዳኜ መላኩ በፈቃዳቸው የሥራ መልቀቂያ በማቅረባቸው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን በዕጩ ፕሬዚዳንትነት አቅርበው አሹመዋል፡፡
ወ/ሮ መአዛ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፤ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ በሕግ ትምህርት አግኝተዋል፡፡ በአሜሪካ ኬንታኪ ዩንቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ግለ ታሪካቸው ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ መዓዛ በንግድ ሚኒስቴር የሕግ ባለሙያነት፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት እንዳገለገሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን በመመሥረትና በመምራት ለሴቶችና ለሕፃናት መብትና ፍትሕ መታገላቸውንም ገልጸዋል፡፡ በንግድ ዓለምም ውጤታማ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ዕጩ ፕሬዚዳንቷን በሙሉ ድምፅ የተቀበለ ሲሆን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የቀረቡለትን አቶ ሰሎሞን አረዳንም በተመሳሳይ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
አቶ ሰሎሞን አረዳ በአሁኑ ወቅት የስመ ጥር ዓለም አቀፍ ተቋማት የሕግ አማካሪ እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት የተሿሚው የግል ታሪክ ተመልክቷል፡፡
አቶ ሰለሞን በኩዩ ገብረ ጉራቻ የተወለዱ ሲሆን፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዳገኙ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሕግ ከአምስተረዳም ዩኒቨርሲቲ እንዳገኙ ተገልጿል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሕዝብ አስተዳደር እንዲሁም በሕግ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ሄግ) በግልግል ዳኝነትም አገልግለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ እንደተናገሩት ተሿሚዎቹ ‹‹ፍትሕ ፍትሕ የሚሸት ተቋም እንደሚያደርጉት እተማመናለሁ፤›› ብለዋል፡፡