Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ምክር ቤት አባላትን ሹመት አፀደቀ

ፓርላማው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ምክር ቤት አባላትን ሹመት አፀደቀ

ቀን:

– ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢ ሆነዋል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ምክር ቤት አባልነት ያቀረቧቸውን 23 ዕጩዎች ሹመት አፀደቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ንዑስ አንቀጽ ሁለት እንዲሁም በሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 449/97 መሠረት ዕጩ የማቅረብ ሥልጠናቸውን ተጠቅመው ነው ለምክር ቤቱ ዕጩ ተሿሚዎችን ያቀረቡት፡፡

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 449 አንቀጽ ስድስት መሠረት የኮሚሽኑ አባላት ለሕዝብ ቆጠራ ጉዳይ አግባብነት ካላቸው የፌዴራል ሚኒስቴር ሚኒስትሮች፣ ከምርጫ ቦርድ፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ከዘጠኙ ክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮች የተውጣጡ ይሆናሉ፡፡

በዚህ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሐረር ክልል ርዕሰ መስተዳድር በስተቀር  ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች በምክትል ርዕሰ መስተዳድሮችና በምክትል ከንቲባዎቻቸው የኮሚሽኑ አባል እንዲሆኑ በዕጩነት አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብና ቤት ቆጣራ ጉዳይ አግባብነት ካላቸው የፌዴራል ሚኒስቴር ሚኒስትሮች፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከምርጫ ቦርድ በሚለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ሰብሳቢነት አጭተዋል፡፡

የተቀሩት የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው፣ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አቶ ይናገር ደሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ (ብአዴን) ሲሆኑ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ (ኦሕዴድ)፣ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ (ደኢሕዴን)፣ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ (ሕወሓት) በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳና የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ (በጸሐፊነት) በአባልነት ቀርበዋል፡፡

በቀረቡ ዕጩዎች ዙሪያ የመከሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የባለፈው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ላይ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የሕዝብ ብዛት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ከፍተኛ ስህተት እንዳይደገም አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቱ ሴት ተወካዮች በበኩላቸው ከቀረቡት የኮሚሽኑ ዕጩዎች ውስጥ አንድ ሴት ብቻ በዕጩነት መቅረባቸው አስቆጥቷቸዋል፡፡

‹‹የሴቶች ስብጥር በዚህ ሹመት ላይ መታየት አለበት፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ሲገባው የታየው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ይህ የድርጅታችን ባህል አይደለም፤›› ሲሉ አንድ ሴት ተወካይ ተከራክረዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥት ከስህተቱ የመማር ልምድ ስላለው በባለፈው ቆጠራ የተከሰተው ችግር እንደማይደገም፣ የሴቶች ስብጥርን በተመለከተ የመንግሥት ቁርጠኝነት እንደሚታወቅና በዚህኛው ላይ አንድ ብቻ መወከላቸው ዕጩ ምልመላው የተካሄደው አዋጁን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የአቶ አስመላሽ መልስ ለምክር ቤቱ ሴት አባላት አጥጋቢ አልነበረም፡፡ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ‹‹ሴት ብሆንም በዚህ መድረክ ላይ አቋም መያዝ አልችልም፡፡ በተጨማሪም አዋጁን ማሻሻል የሚጠይቅ በመሆኑ ወደ ድምፅ ብንሄድ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት የኮሚሽን አባላቱ ሹመት በአንድ ተቃውሞ፣ በዘጠኝ ድምፅ ተአቅቦ ፀድቋል፡፡

ሦስተኛው ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...