ትግል ኑሮ እኮ ነው!
ትግል ኑሮ እኮ ነው ÷ ሰዉን ሰው ያሰኘው።
በ‘ንስሳ ዓራዊቱ ÷ እንዳሠለጠነው
በጽሕፈተ ምድሩ ÷ አምላክ ገዥ ያረገው
የሰው ልጅ ዕድያ ÷ ትግል ኑሮ እኮ ነው።
ጥሮ ግሮ ለፍቶ ÷ ሠርቶ ከተረፈው
ተካፍሎ እበላ ያለው
ትግል ኑሮ እንጂ
የሰው ልጅማ ያው ÷ ጥጋብ በገደለው።
ከጽሕፈተ ምድሩ ÷ ምኅዳሩ ቢጠበው
በባለብርቱ እጁ ÷ ተራራ የናደው
ትግል ኑሮ እንጂ ÷ ኧረ ማንስ ሰው ነው?
በአዕዋፍ ዝማሬ ÷ ነጋ ‘ሚታጀበው
ሁሉን በየፊናው የሚቀሰቅሰው
ትግል ኑሮ ባይሆን ÷ ተቆጡ ማን አየው?
ጫካው ጥራኝ ካለው ÷ ዱሩ ጥራኝ ካለው
ባገር ፍቅር ስሜት ÷ በሰላም እሳቤው
የዕድገት ብልፅግና ÷ ዝናር የታጠቀው
ትግል ኑሮ እኮ ነው! ሁሉም ያገሬ ሰው።
ካህኑ ‘ሚሰብከው ÷ ኢማሙ የሚጣራው
አዛኑም ቅዳሴው ÷ ወዝና ጣዕም ያለው
መሠማሪያ ሜዳው ÷ ትግል ኑሮ እኮ ነው።
ኃይለ ልዑል ካሣ
ግንቦት 20/2008 ዓ.ም.
****************
ኖርዌይ ለፊንላንድ በስጦታ መልክ ተራራ ልትሰጥ ነው
ፊንላንድ እ.ኤ.አ. በ1917 ከሩሲያ ነፃ የወጣችበትን 100ኛ ዓመት የነፃነት በዓል ቀን በማሰብ ኖርዌይ ካሏት በርካታ ተራሮች መካከል አንዱን በስጦታ ታበርክትላት የሚል እንቅስቃሴ ከተጀመረ መቆየቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ ኖርዌይ ለፊንላንድ እንድትሰጣት የታሰበው ተራራ የተወሰነ ክፍል የሚገኘው በፊንላንድ ቢሆንም የተራራው 20 ሜትር የሚሆነው ክፍል የሚገኘው በኖርዌይ ነው፡፡ ይህው ተራራ ለፊንላንድ ካሏት ከፍታማ ቦታዎች በከፍታው ቀዳሚው ነው፡፡ ይህንን ተራራ ለፊንላንድ በስጦታ መልክ ኖርዌይ ታበርክት የሚለው ኦንላየን ዘመቻ ዘመቻ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የሁለቱ አገሮች ድንበር ዳግም እንዲካለልም ሐሳብ ይሰነዝራል፡፡ ፊንላንድ እ.ኤ.አ. በ1917 ነፃነቷን ያወጀችው በዚያው ዓመት በሩሲያ የሕዝቦች መብት እስከመገንጠል ድረስ መታወጅን ተከትሎ ነው፡፡
****************
በጃፓን 12,000 ሰዎች በተመሳሳይ ምክንያት በአንድ ዓመት ውስጥ ጠፉ
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 12,000 ሺሕ ሰዎች በአንድ ዓይነት ምክንያት መጥፋታቸውና የደረሱበት አለመታወቁን የጃፓን መንግሥት አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ የፖሊስ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው እ.ኤ.አ. በ2015 12,208 ሰዎች ጠፍተዋል፡፡ ይህ ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 13 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ እነዚህ የጠፉ ሰዎች በዕድሜ የገፉና የመጥፋታቸው ምክንያት የመርሳት በሽታ ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡ ከእነዚህ የጠፉ ሰዎች ብዙዎቹ ከሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ሲንከራተቱ የሚገኙ ሲሆን፣ የሚሞቱና በዚያው ጠፍተው የቀሩም አሉ፡፡ የጃፓን መንግሥት የመርሳት ችግር ስላለባቸውና ስለሚጠፉ ሰዎች መረጃ መሰብሰብ የጀመረው እ.ኤ.አ. 2012 ላይ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት 4.62 ሚሊዮን ሰዎች በችግሩ ተጠቂ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስተወቀው እ.ኤ.አ. በ2025 ይህ ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን ሊያድግ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡