Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት ለከፍተኛ የሞት ቁጥር መመዝገብ መንስዔ ሆኗል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአገሪቱ ለሚከሰተው 53 ከመቶ ሞት ምክንያት እንደሆነ ማይክሮ ኒውትረንት ኢኒሺዬቲቭ የተባለ ተቋም ያደረገው ጥናት አመለከተ፡፡ አደገኛ  የምግብ እጥረት፣ የአይረን ዕጥረት (አኔሚያ) የቫይታሚን ኤ እንዲሁም የአዮዲን እጥረት በአገሪቱ በስፋት የሚታዩ ችግሮች መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ 32 በመቶ ለሚሆነው የሕፃናት ሞትም የቫይታሚን ኤ እጥረት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ቫይታሚንና ሌሎች ንጥረ ነገሮች እጥረት ተጋላጭ ሆኗል፤›› ያሉት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና የሥነ ምግብ ባለሙያ አቶ ድልነሳው ዘርፉ፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ድልነሳው ገላጻ፣ የምግብ ስብጥሩን ለማስፋት እየተሠራ ነው፡፡ የኅብረተሰቡን የእንስሳት ተዋፅኦ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ተጠቃሚነት ለመጨመር ልዩ ልዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የምግቦችን የንጥረ ነገር ይዘት የዳበረ ለማድረግ ሰው ሠራሽ የምግብ ማበልፀጊያ (ፉድ ፎርቲፊኬሽን) በስፋት እንዲሠራበት ለማድረግ የሚረዱ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፡፡

መንግሥት ከዓመታት በፊት ባወጣው የብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ውስጥ ፉድ ፎርቲፊኬሽን አንዱ ነው፡፡ ‹‹ፉድ ፎርቲፊኬሽን ማለት በተፈጥሯቸው ንጥረ ነገር ያልያዙ ምግቦችን በአርቲፊሻል መንገድ በንጥረ ነገር እንዲበለጽጉ ማድረግና በፋብሪካ በሚቀነባበሩበት ጊዜ የንጥረ ነገር ይዘታቸውን የሚያጡ ምርቶች፣ በሰው ሠራሽ መንገድ በጥንረ ነገር እንዲዳብሩ የሚደረግበት ሒደት ነው፤›› የሚሉት አቶ ድልነሳው፣ አሠራሩ በጨው ላይ ተሞክሮ ውጤታማ እንደነበር፣ ነገር ግን በርካታ የጨው አምራች ኩባንያዎች በተገቢው ደረጃ እንዳልተገበሩት ተናግረዋል፡፡  

ለዘመናት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ምግቦች በተለያዩ አጋጣሚዎች የአዮዲን ንጥረ ነገር  ይዘታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል፡፡ ይህም ብዙዎችን በአዮዲን እጥረት ምክንያት ለሚከሰቱ የተለያዩ የጤና ቀውሶች ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ከዓመታት በፊት በፉድ ፎርቲፊኬሽን መንገድ የአዮዲን ንጥረ ነገር የያዘ ጨው ለኅረተሰቡ እንዲቀርብ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ለውጦችም እየታዩ ነው፡፡ የንጥረ ነገር ችግሮችን በስፋት ሊቀንስ እንደሚችልም ታምኖበት ነበር፡፡ ይሁንና  በ2006 እና 2007 ዓ.ም. በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ ለኅብረተሰቡ እየቀረበ ያለው ተገቢው ንጥረ ነገር የያዘ ጨው መጠን  ከ25 በመቶ ሊበልጥ አልቻለም፡፡

ይህም በእንቅርት የሚጠቁ እናቶች ቁጥር 39.9 ከመቶ እንዲደርስ፣ ከስድስት እስከ 12 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ልጆች 35.8 ከመቶ በእንቅርት በሽታ እንዲጠቁ በሽታውም እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡ የሌሎቹ ንጥረ ነገሮች እጥረትም ማኅበረሰቡን ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየዳረገ ይገኛል፡፡  የአዮዲን እጥረት ብዙዎች በቀላሉ ሊድን በሚችል የጤና ችግር ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን እንዲያጡ፣ 17 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች ለደም ማነስ በሽታ እንዲጋለጡ ሰበብ ሆኗል፡፡

‹‹ችግሩን ለመከላከል ኩባንያዎችን ተቆጣጥሮ ማሠራት ብዙ የሚፈጥረው ለውጥ የለም፡፡ አምነውበት እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ያሉት አቶ ድልነሳው፣ የግንዛቤ ማሻሻያ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

አቶ ድልነሳው ይኼንን የጠቀሱት፣ ማይክሮ ኒውትረንት ኢንሺኤቲብ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ማክሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በደሳለኝ ሆቴል ለምግብ አቀነባባሪ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅት ላይ ነው፡፡

በዕለቱ ስለ ማይክሮ ኒውትረንትና የቫይታሚኖች ጠቀሜታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ለምግብነት እየቀረቡ ያሉ በፋብሪካ የተቀነባባሩ ምርቶች በምርት ሒደት የያዙትን ንጥረ ነገር ምን ያህል እንደሚያጡ፣ በዚህም በጤና ላይ የሚያደርሱት ቀውስ እንዲሁም ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ስለታሰበው የፉድ ፎርቲፊኬሽን አተገባበር ላይ  ለተሳታፊዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

‹‹በግንዛቤ ማጣትና በሌሎች ምክንያቶች አብዛኛው ኅብረተሰብ ከሚመገበው ነገር አስፈላጊዎችን ንጥረ ነገር እያገኘ አይደለም፤›› ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሽብሩ ተመስገን ኮሌጁ በልዩ ልዩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራሞች እንደሚያካሂድ፣ ከፕሮግራሞቹ መካከልም ከንጥረ ምግብ ጋር በተያያዘ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡ ልዩ ልዩ ጥናቶችን በማውጣትም ለሕዝቡ እንዲደረስ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የተመጣጠነ የምግብ ችግር በተለይ በሕፃናት እናቶች ጤና ላይ የከፋ ችግር እያደረሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም የያዙት ንጥረ ነገር በፋብሪካ በዝግጅት ሒደት (ፕሮሰሲንግ) የሚያጡና ንጥረ ነገር የሌላቸው ምግቦችን በፉድ ፎርቲፊኬሽን የተሟላ ንጥረ ነገር እንዲኖራቸው የግድ ይላል፡፡ ይህም ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነውን የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት ለመቋቋም እንደሚያስችል በጥናቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች