Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሕፃናት ላይ የበረታው የአየር ብክለት

በሕፃናት ላይ የበረታው የአየር ብክለት

ቀን:

በዓለም 90 በመቶ ሕፃናት በየቀኑ የተመረዘ አየር ይስባሉ

በቀድሞው ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ነበር፡፡ ባልና ሚስቱ በወቅቱ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ወረድ ብሎ በሚገኘው በዛብህ ሆቴል አልጋ ይዘዋል፡፡ ወቅቱ ክረምት ነበርና ክፍላቸው የተቀጣጠለ ከሰል እንዲገባ ጠይቀው ከሰሉ ይገባል፡፡ ጠዋት ከሆቴሉ የተሰማው ግን መርዶ ነበር፡፡ ባልና ሚስቱ በከሰሉ ጭስ ታፍነው ሞተዋል፡፡ ይህ በወቅቱ በነበሩ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን በወቅቱ ጋዜጠኛ የሆኑ ግለሰብ አጫውተውናል፡፡ ጉዳዩ መነጋገሪያ የሆነውም እንዲህ ዓይነቱ ገጠመኝ እምብዛም ተሰምቶ ስለማይታወቅ ነበር፡፡

እኚህ ሰው ሌላም ገጠመኝ አላቸው፡፡ ባለቤታቸው ወልዳ ቤተሰብ ተሰብስቧል፡፡ ከመጡት እንግዶች መሀል አንዷ የባለቤታቸው ጓደኛ ነበረች፡፡ እሷም ቡና ማፍላት ትፈልግና ከአራሷ ክፍል አጠገብ ከሚገኝ ሌላ ክፍል ከሰል አያይዛ ጉድ ጉድ ማለት ትጀምራለች፡፡ ድንገት የመውደቅ ድምፅ የሰሙት የአራሷ ቤተሰቦች ድምፅ ወደሰሙበት ይሮጣሉ፡፡ ይች እንግዳ ራሷን ስታ ወድቃ ነበር፡፡ አንስተው ሆስፒታል እስኪያደርሷት በተከታታይ ያስመልሳት እንደነበር፣ ሐኪም ቤት ደርሰው በተሰጣት ሕክምና መዳኗንና ራሷን የሳተችው በጭሱ ታፍና እንደሆነ ከሆስፒታሉ እንደተነገራቸው ያስታውሳሉ፡፡

አየር በተለያዩ ምክንያቶች በቤት ውስጥ አሊያም በውጭ በመበከሉ ብዙዎች ሲታመሙ ወይም ሲሞቱ ይስተዋላል፡፡ የተበከለ አየር በመሳባቸው በትምህርት ቤት ስለወደቁ፣ በጭስ ታፍነው ቤት ውስጥ ስለሞቱ ሰዎችም ይሰማል፡፡ የአየር ብክለቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መምጣቱ ደግሞ በሰው ልጆች የመኖር ህልውና ላይ ጋሬጣ ሆኗል፡፡ በተለይ ሕፃናት የአየር ብክለቱ ዋነኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡

በኢትዮጵያም ካለው የአኗኗር ዘይቤ ማለትም ማገዶንና ከሰልን በቤት ውስጥ ለማብሰያነት ከመጠቀም አንፃር ውጭ ከሚገጥማቸው በተጨማሪ ሕፃናትም ሆኑ አዋቂዎች ቤት ውስጥ ለተበከለ አየር የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ በአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ሳራ ቴሪ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ በአዲስ አበባ በርካታ ከሰል መሸጫዎች መኖራቸውና ከሰል ለማገዶ መዋሉ፣ ከየቤቱ የሚወጣ ቆሻሻ፣ በየመንገዱ የሚቃጠሉ ቁሶች፣ የመኪና ጭስና ኢንዱስትሪዎች የሚያመነጩት በካይ ጋዝ አየሩን ለመበከል መንስዔ እንደሆኑ ገልጸው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ስትነፃፀር ለአየር ብክለት ያላት አስተዋጽኦ ኢምንት ቢሆንም፣ የተፅዕኖው ተቋዳሽ ናት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥር እየሰደደ የሚገኘው የአየር ብክለት ደግሞ በጤናው ዘርፍ ላይ ሥጋት ሆኗል ሲል ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ገልጿል፡፡

የአየር ብክለት የሰውን ልጆች ከሚፈትኑ እክሎች አንዱ ሲሆን፣ ጡንቻው ደግሞ በሕፃናት ላይ ይበረታል፡፡ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትና ታዳጊ ሕፃናት በተበከለ አየር ምክንያት የሚደርስባቸው የዕድገት መስተጓጎል የጤናው ዘርፍ ሌላው ፈተና ሆኖም ብቅ ብሏል፡፡

ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በተያዘው ሳምንት ባወጣው መረጃ ከ15 ዓመት በታች የሚገኙ 93 በመቶ ያህል ሕፃናት በየቀኑ የተበከለ አየር ይተነፍሳሉ፡፡ በዓለም 93 በመቶ ማለትም 1.8 ቢሊዮን ሕፃናት የተበከለ አየር የሚተነፍሱ መሆኑ ደግሞ ጤናቸውንና ዕድገታቸውን አደጋ ውስጥ ጥሎታል፡፡ ብዙዎችም ይሞታሉ፡፡ በ2016 ብቻ 600 ሺሕ ያህል ሕፃናት በተበከለ አየር ምክንያት በመተንፈሻ አካላቸው ላይ በደረሰ ኢንፌክሽን መሞታቸውን ገልጿል፡፡

ድርጅቱ የአየር ብክለት በሕፃናት ጤና ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት በቤት ውስጥና ከቤት ውጭ ያለው የአየር ብክለት በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሕፃናትን እየጎዳ ነው፡፡ ተፅዕኖው ደግሞ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ይጎላል፡፡

ነፍሰ ጡር እናቶች ለተበከለ አየር ሲጋለጡ ደግሞ ችግሩ የከፋ ነው፡፡ ጊዜው ያልደረሰ፣ ትንሽና ኪሎውም ከመጠን ያነሰ እንዲወልዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ብክለቱ የአዕምሮ ዕድገትን ይገታል፣ አስምንም ያባብሳል፡፡ በሕፃንነት ለሚከሰት ካንሰርም መንስዔ ነው፡፡ ለተበከለ አየር በጣም የሚጋለጡ ልጆች ደግሞ ለከፋ የልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ የተበከለ አየር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን እየመረዘና ሕይወታቸውን እያበላሸ ነው፡፡

ሕፃናት ከአዋቂዎች በተለየ የአየር ብክለት የሚጎዳቸው ከአዋቂ በፈጠነ ቶሎ ቶሎ ስለሚተነፍሱና ለመሬት ባላቸው ቅርበት ለታመቀው አየር ስለሚጋለጡ ነው፡፡ ይህም አጠቃላይ ዕድገታቸውን ይጎዳዋል፡፡

አዲስ የተወለዱና ቤት ውስጥ የሚውሉ ሕፃናት ደግሞ በተለይ በቤት ውስጥ ለሚፈጠር የተበከለ አየር ተጋላጭ ናቸው፡፡ በየቀኑም ከምግብ ማብስያ፣ ከኤሌክትሪክ ምድጃ፣ ከከሰልና ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች ለሚመነጨው ሙቀትና የአየር ብክለት የተጋለጡ ናቸው፡፡

ያልተመጣጠነ ምግብ ሰውነትን እንደሚያቀነጭረው ሁሉ የተበከለ አየር የአዕምሮ ዕድገትን ያቀነጭራል፣ ሕይወት እስከመንጠቅም ይደርሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...