Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምትክ መሬት ሳያገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች ምትክ እንዲሰጣቸው ውሳኔ ተሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተቃውሞ አቅርቧል

የቻይናው ግዙፍ የጫማ አምራች ኩባንያ ኋጂዬን ግሩፕ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እየገነባ ባለው የኢንዱስትሪ ዞን፣ ምትክ መሬት ሳይሰጣቸው ለተነሱ ዜጎች ምትክ መሬት እንዲሰጥ መታዘዙን ምንጮች ገለጹ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የተገኘው መረጃ፣ ኋጂዬን ግሩፕ የሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ አርሶ አደሮች እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ምትክ ቦታ ሳይሰጥ እንዲነሱ ነው የተደረገው፡፡  

ይህ አሠራር ተቀባይነት የለውም በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ለተነሱ ዜጎች፣ በአስቸኳይ ምትክ ቦታ እንዲሰጥ ትዕዛዝ መስጠቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለኋጂዬን ግሩፕ በተሰጠው ቦታ ላይ የነበሩ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ነው የሰፈሩት የሚል አቋም መያዙን ምንጮች ያመለክታሉ፡፡

ክፍለ ከተማው እነዚህ ዜጎች ሕገወጥ ናቸው በማለት ተገቢውን ክፍያ ማግኘት እንደሌለባቸው መከራከሪያውን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

በዚህ ሒደት ወደ ሕግ የሄዱ የተወሰኑ ዜጎች በመኖራቸው፣ ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት አላገኘም፡፡ በዚህ ሒደት የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ነዋሪዎች ተጠቃለው ባለመነሳታቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ እየተጓተተበት መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡

ኋጂዬን ግሩፕ በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አካባቢ 138 ሔክታር መሬት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መሬት ላይ በተለይ በምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ግንባታ ሳይት ላይ፣ በርካታ ዜጎች ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ነበሩ፡፡

በኦሮሚያ ልዩ ዞን ዱከም ከተማ በተገነባው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ጫማ በማምረት ላይ የሚገኘው ኋጂዬን ግሩፕ፣ በአዲስ አበባ የራሱን የኢንዱስትሪ ዞን በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ለመገንባት አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው የሚያካሂደው የኢንዱስትሪ ዞን ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

‹‹ኋጂዬን እስካሁን ስድስት ሼዶች ገንብቷል፡፡ በምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት የታቀደ ግንባታዎችን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ግን በቦታው ላይ ያሉ ሰዎች መነሳት የግድ ይላል፡፡ እስካሁን ባለመነሳታቸውም ፕሮጀክቱ እየጓተተ ነው፤›› በማለት አቶ ወንዱ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ አብዮት ያመጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ኋጂዬን ግሩፕና የታይዋን ኩባንያ ጆርጂ ሹ ናቸው፡፡

ኋጂዬን ግሩፕ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ዞን ሲጠናቀቅ በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገባ ሲሆን፣ ጆርጂ ሹ በሞጆ ከተማ የሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን ሲጠናቀቅ፣ በዓመት 250 ሚሊዮን ዶላር ያስገባል ተብሏል፡፡

አቶ ወንዱ እንደገለጹት፣ በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በሚጠናቀቅበት ዓመት፣ ኢትዮጵያ ከጫማና ከቆዳ ውጤቶች 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎ ታቅዷል፡፡ ይህ ዕቅድ የተዘጋጀው ሁለቱን ግዙፍ ኩባንያዎች መሠረት በማድረግ መሆኑን አቶ ወንዱ ገልጸው፣ ከሁለቱ ኩባንያዎች ብቻ በድምሩ 550 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች