Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ…?!››

በዓለማችን በጉጉት ከሚጠበቁ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ውድድር ሊጀመር     44 ቀናት የቀሩት ሲሆን፣ አዘጋጇ አገር ብራዚልም ከመላው ዓለም የሚመጡትን እንግዶቿን ለማስተናገድ የመጨረሻ ሥራዎቿን እያጠናቀቀች ትገኛለች፡፡ ይህ ግዙፍ ስፖርታዊ ውድድር በጠራ የፉክክር መንፈስ ሲካሄድ ወንድማማችነትንና አንድነትን የሚያጠናክር ነው፡፡ ይህ ውድድር አገሮች ሰንደቅ ዓላማቸው የሚውለበለብበትና ብሔራዊ መዝሙራቸው የሚዘመርበት እንዲሁም ባህላቸው የሚንፀባረቅበት በመሆኑ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦችን ቀልብ የሚስብ ነው፡፡

በበፊት ጊዜያት ዘር፣ የቆዳ ቀለምና ፖለቲካዊ አመለካከት በዚህ ውድድር ላይ እያጠሉበት በተደጋጋሚ አሉታዊ የሆኑ ችግሮች ሲታዩበት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው፣ ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት አትሌቶች በዘር፣ በቆዳ ቀለምና በፖለቲካ አመለካከት ሳይከፋፈሉ፣ በስፖርታዊ ጨዋነት ውድድሩን ያከናውናሉ፡፡ ሆኖም ግን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ፍጹም የጠሩና የነፁ ናቸው እያልን አይደለም፡፡ እንደውም ከምንጊዜውም በላይ በጣም የከፋ አደጋ በስፖርቱ ላይ እያጠላ ይገኛል፡፡ ይህም ማለት ስፖርታዊ ጨዋነትን ችላ በማለት አትሌቶች ከሥነ ምግባር ውጪ በመሆን፣ ኃይል ሰጪ አበረታች መድኃኒቶችን በመጠቀም ስፖርቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ይህንን ኢ ሥነ ምግባራዊ ተግባር በአንድ ድምፅ አውግዞታል፡፡ ለዚህ ማሳያም የሚሆነው በቅርቡ በሩሲያ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ ማኅበሩ የሩሲያ የሩጫ፣ የውርወራና የዝላይ አትሌቶችን በቅርቡ ከሚጀመረው የሪዮ ኦሊምፒክ አግዷዋል፡፡ ይህንንም ዕገዳ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ለአንድ አገር ትልቅ ቅሌት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ አገሪቱም ሆነ አትሌቶቹን ክፉኛ ይጎዳቸዋል፡፡ በሩሲያ ላይ እንደተካሄደው ዓይነት ምርመራ በሌሎች አገሮች ላይ ሲካሄድ እንደነበርም ተሰምቷል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ስማቸው ሲነሳ ከነበሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያና ኬንያ ይገኙበታል፡፡ በዚህም ምርመራ ከኢትዮጵያ ስድስት ያህል አትሌቶች ኃይል ሰጪና አበረታች መድኃኒቶችን ወስደዋል ተብለው ጊዜያዊ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ በእርግጥ ለአገሪቱና ለሕዝቡ በጣም የሚያሳዝንና አንገት የሚያስደፋ ክስተት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜልቦርን ኦሊምፒክ ከተሳፈችበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ የገነኑና ስመ ጥር አትሌቶችን ማፍራት ችላለች፡፡ ለምሳሌ ያህል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ የማራቶን ወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈ ሲሆን፣ ይህ ድሉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘ ነው፡፡ ይህም ድል ዓለምን አፍ ያስያዘ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በባርሴሎናው ኦሊምፒክ ደራርቱ ቱሉ ወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘች የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ሆና በታሪክ ማኅደር ላይ ተመዝግባለች፡፡ ከዚህም ባለፈ በአትላንታው ኦሊምፒክ ፋጡማ ሮባ የመጀመሪያዋ የማራቶን ወርቅ ያመጣች አፍሪካዊት ሴት በመሆን አገሯንም አኅጉሯንም አኩርታለች፡፡

የኢትዮጵያ የኦሊምፒክና ሌሎች የዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ድል በዚህ የሚገደብ አይደለም፡፡ እነምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርና ሌሎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ በቡድን ሥራ ለዓለም ትልቅ ትምህርት ሰጥታለች፡፡ ዓለምም በዚህ ድንቅ የቡድን ሥራ ተገርሞና ተደምሞ አረንጓዴው ጐርፍ የሚል ቅፅል ስም አውጥቶላታል፡፡ ይህ ታሪክ የሚያኮራ ሆኖ ሳለ በቅርቡ ግን ከአትሌቶቻችን ጋር ተያይዞ እየተሰማ ያለው ዜና ከአስደንጋጭነቱ ባለፈ አሳፋሪ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህም ረገድ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጀምሮ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ከውግዘት ባለፈ፣ በእንደዚህ ዓይነት አስነዋሪ ተግባር ተሳትፈው የተገኙ አትሌቶችን መቅጣት አለባቸው፡፡ እንደሚታወቀው ሩጫ ለኢትዮጵያ ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ለዓመታት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለዚህም ጀግኖች አትሌቶቻችንን ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዘመናት በጦርነትና በረሃብ የምትታወቀ ሲሆን፣ በሩጫው ዘርፍ እየተገኘ ያለው ድል ይህንን የጐደፈ ስም በማጥራት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ ባለፉት ዓመታት አትሌቶቻችን ባስመዘገቡት ድል በመሳብ፣ ከተለያዩ አገሮች ዓለም አቀፍ ታዋቂ አትሌቶች ኢትዮጵያ በመምጣት ሥልጠና ይወስዳሉ፡፡ ይህም ለቱሪዝም ዘርፉ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ከዚህም ባለፈ የአትሌቶቻችን ድል የአንድነትንና የአሸናፊነትን መንፈስ በዜጐች መካከል ያጠነክራል፡፡ በተጨማሪም አትሌቶቻችን የሚያስመዘግቡት ድል ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በማነቃቃት መልካም አርዓያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

አትሌቲክሱ ከላይ እንደተገለጸው ከባድ የሆኑ ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል አበረታችና ኃይል ሰጪ መድኃኒት መጠቀም፣ ሙስና እንዲሁም በአመራሩና በአትሌቶች መካከል ያለው ሽኩቻ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም እንላለን፡፡ ለዚህም አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ለዚህ ችግር በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት አደጋው ከፍተኛ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይባስ ብሎም በተተኪ አትሌቶች ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ቀውስ አገርን የሚጐዳ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማን ይዘውና አገርን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ከእንደዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ድርጊት መቆጠብ አለባቸው፡፡ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ? እንደሚል ተረቱ ይህ የአበረታች መድኃኒት ችግር በአፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አገርን ብሎም ሕዝብን እንዲሁም አትሌቶችን ይጐዳል፡፡       

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...