– የክልል መንግሥታት ድጐማን ከክልሎች ጋር በትብብር ኦዲት እንዲያደርግ ይፈቅዳል
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መንግሥት የሚበደራቸው ብድሮች በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን እንዲሁም ከፍተኛ በጀት እየተመደበላቸው የሚገኙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን ኦዲት እንዲያደርግ የሚፈቅድ ማሻሻያ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 669/2002 ላይ የተወሰኑ ተጨማሪ የኦዲት ኃላፊነቶችን የሚሰጥ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ኦዲተሩ ከዚህ ቀደም ከለጋሾች በሚገኝ ገንዘብ ላይ ሲያከናውን የቆየውን ኦዲት በማስፋት የለጋሾችና አበዳሪዎች ሒሳብ በሚል ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ በጀት እየተመደበለትና እያደገ የመጣውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሥርዓት ተጠያቂነት ትኩረት ሰጥቶ መገምገምና ኦዲት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት በማሻሻያው ላይ እንዲካተት መደረጉን የረቂቁ ማሻሻያ ሠነድ መግለጫ ያስረዳል፡፡
ከዚህ ቀደም አከራካሪ የነበረው የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው ድጐማ ሒሳብ ኦዲት ጉዳይን በተመለከተ በክልሎች ጣልቃ በመግባት ትዕዛዝ የመስጠትን ትርጉም እንዳይዝ ትብብርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን አስፈላጊውን ቁጥጥር ‹‹በመተባበር›› ያደርጋል በሚል እንዲሻሻል በረቂቁ ተካቷል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጐማ ኦዲት ማድረግ እንዳልቻሉ የቀድሞው ዋና ኦዲተር ለማ አርጋው በተደጋጋሚ ሪፖርት ማድረጋቸው የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ማስቆጣቱና ክልሎች የሚያገኙትን ድጐማ ‹‹ከፈለጉ ሊያቃጥሉት ይችላሉ፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ውዝግብ በኋላ ዋና ኦዲተር በክልሎች ድጐማ ሒሳብ ላይ ኦዲት ለማድረግም ሞክሮ እንደማያውቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ከፀደቀ ዋና ኦዲተር በዚህ የድጐማ ሒሳብ ላይ ኦዲት ማድረግ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡
ረቂቁ ማሻሻያ ለዝርዝር ዕይታ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ደግሞ ለሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡