ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በቅርቡ ሊያከናውን ስላቀደው ጠቅላላ ጉባዔውና በአገሪቱ እየተከናወነ ስላለው የለውጥ ሒደት መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ማብራሪያ ሰጠ፡፡
የፓርቲው አመራሮች ይህን ማብራሪያ የሰጡት ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ባዘጋጁት መድረክ ላይ ሲሆን የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የፈረንሣይ፣ የጣሊያን፣ የሆላንድ፣ የቤልጂየም፣ የአውስትራሊያ፣ የኦስትሪያ ኤምባሲዎች፣ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮችን ጨምሮ የ28 አገሮች ተወካዮች በሥፍራው በመገኘት ማብራሪያውን ተከታትለዋል፡፡
በዚህም መሠረት በአገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ያለው የለውጥ አየር ላለፉት ሦስት ዓመት የአገሪቱ ወጣቶች ባካሄዱት ትግል የተገኘው ውጤት እንደሆነ የፓርቲው አመራሮች ገልጸው፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ለውጥና በአጠቃላይ ደግሞ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠሩትን የለውጥ ኃይሎች ፓርቲው እንደሚያመሠግንና እንደሚያደንቅ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አሁን የተፈጠረው የለውጥ አየር እንዲመጣ መስዋዕት የሆኑና አስተዋፅኦ ያበረከቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችንና አባላትን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችንና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን አስተዋፅኦ እንደሚያደንቁ አክለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ወደ አገር እንዲገቡ ጥሪ ማድረጉና በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከሽብርተኝነት ዝርዝር መሰረዙ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትን ማሻሻሉ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት መፍታቱ፣ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ ኃላፊነት ማምጣቱ መልካምና የሚበረታታ ዕርምጃ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲውን አጠቃላይ አደረጃጀትና ዕቅድ በተመለከተ ደግሞ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና ማኒፌስቶ የወቅቱ ፖለቲካ በሚጠይቀው ደረጃ ለማሻሻል እየሠሩ እንደሆነ፣ በዚህም መሠረት በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ አማራጭ ሆኖ የፖለቲካ ኃይል ለመቅረብ እንዲያስችለው ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና ከግለሰቦች ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሆነ በመግለጽ፣ ይኼንንም የተሳካ ለማድረግ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚደረግ አመራሮቹ አስገንዝበዋል፡፡
ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና ግለሰቦች ጋር ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት ከቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራር አባል አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ከሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ እንዲሁም ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ጋር ውጤታማ ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውን እንዲሁ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አስታውቀዋል፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማት እንደ አዲስ እንዲዋቀሩ ሰማያዊ ፓርቲ የጠየቀ ሲሆን፣ እንደ አዲስ የማዋቀሩን ሒደት መንግሥት ብቻውን የሚመራው ሳይሆን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና የአገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ ሊሳተፉበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡