Monday, March 20, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ከ13 ዓመታት በኋላ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ አገኘ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓለም ባንክ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሏል

የዓለም ባንክ ከግንቦት 1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በአገሪቱ በተፈጠረው  የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት አቋርጦ የነበረውን ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ፣ በከፍተኛ የገንዘብ መጠን ዳግም ጀመረ፡፡

የዓለም ባንክ ግሩፕ ዓርብ ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መንግሥት በሁለት የገንዘብ አቅርቦት ስምምነት ሰነዶች 1.35 ቢሊዮን ብር ለመስጠት ስምምነት ፈርሟል፡፡

የመጀመርያው ስምምነት 1.2 ቢሊዮን ዶላር (33.3 ቢሊዮን ብር) ሲሆን፣ ሁለተኛው 150 ሚሊዮን ዶላር (4.4 ቢሊዮን ብር) ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፣ ተቋርጦ የነበረው ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በከፍተኛ የገንዘብ መጠን ተጀምሯል፡፡

‹‹ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ተቋርጦ ነበር፣ በአንፃሩ የዓለም ባንክ ድጋፍ ሲሰጥ የቆየው በመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ (PBS) አሠራር ነው፤›› በማለት የገለጹት አቶ አህመድ፣ ‹‹የዓለም ባንክ በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን ሪፎርም ለመደገፍ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ አህመድ ይህ የገንዘብ መጠን ከፍተኛ የሚባል ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ከባንኩ ይገኛል ብለዋል፡፡

የዓለም ባንክ ከሰጠው ገንዘብ ውስጥ 600 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ሲሆን፣ 600 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ አነስተኛ ወለድ የሚከፍልበት ብድር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአነስተኛ ወለድ የሚታሰብ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለሚደግፉ ለቴክኒክና ሙያ ማስፋፊያ ይውላል ተብሏል፡፡

አቶ አህመድ እንደገለጹት፣ ብድሩ እጅግ አነስተኛ ወለድ የሚታሰብበት በመሆኑ ድጋፍ ሊባል ይቻላል፡፡ የአሥር ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለውና በ40 ዓመታት ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በቀጥታ በጀት ድጋፍ ሊገኝ የቻለው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን ለመደገፍ ነው ተብሏል፡፡

በተለይም በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፍን፣ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና መንግሥት የሚያካሂዳቸውን የልማት ሥራዎች ለመደገፍ የሚውል መሆኑ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአገሪቱ የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ከመቅረፍ፣ የልማት ፋይናንስ የገጠመውን ችግር በማቃለል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ድህነትን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሙያና ክህሎትን በማሳደግ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላት በማስፋት በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በትራንስፖርትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ ሙያ ያላቸውን ወጣቶች ማፍራት ላይ ያለመ ነውም ተብሏል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን ተርክ እንደገለጹት፣ ከወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተጀመረው መሠረታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራንን፣ የንግዱን ማኅበረሰብ በማወያየትና በማሳተፍ ጉዞውን ቀጥሏል ብለዋል፡፡  በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቆየውን ያለመግባባት በሰላም ለመፍታት ብዙ ዕርምጃ መሄዱን፣ ይህንን የዓለም ባንክ እንደሚደግፍ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ባንክ መንግሥት የጀመረውን የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ጅማሮና የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የጀመራቸውን ሥራዎች በበጎ ይመለከታቸዋል ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች