Wednesday, July 24, 2024

የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነትና ገለልተኝነት መፈተን አለበት!

በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ላይ በዋነኛነት ከሚነሱ ችግሮች መካከል ተጠቃሹ የሕዝብ አመኔታ ማጣት ነው፡፡ የሕዝብ አመኔታ ያጣ ተቋምን እንደገና እንዲያንሰራራ ለማድረግ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ለውጥ ግን ማዕበል መፍጠር አለበት፡፡ በሕዝብ ዘንድ የነበረውን የተበላሸ ገጽታ መለወጥ የሚፈልግ የፍትሕ ሥርዓት፣ ከማዕበሉ በኋላ ራሱን ችሎ መቆም መቻልም ይኖርበታል፡፡ ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሷን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊንና ምክትላቸውን አቶ ሰለሞን አረዳን ለማሾም ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ተሿሚዎቹ ፍትሕ ፍትሕ የሚሸት ተቋም እንደሚያደርጉት እተማመናለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በፍትሕ ሥርዓቱ እጅግ በጣም ከመመረሩ የተነሳ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መተማመኛ ይፈልጋል፡፡ ይህ መተማመኛ የሚገኘው ግን የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነትና ገለልተኝነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ መቀለጃ እንዲሆን የመንግሥት ሚና ከፍተኛ ስለነበር፣ ወደ ክብሩ ለመመለስ ሕዝብ የሚያሳምን ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱ ተሿሚዎች ከዚህ ቀደም ከሚታወቀው የፓርቲ ፖለቲካ ልማዳዊ አሠራር ውጪ የተሾሙ በመሆናቸው ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ ይህ ተስፋ እንዳይመክን ግን የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በሚገባ መፈተን አለበት፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ጉዳይ ሲነሳ የፍርድ ቤቶች ነፃነትና ገለልተኝነት የብዙዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ነው፡፡ ብዙዎች ፍርድ ቤቶች ነፃነት እንደሌላቸውና ገለልተኝነታቸውም ፋይዳ ቢስ መሆን በድፍረት ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ መድረኮች ከተሰሙ ድምፆች መገንዘብ እንደተቻለው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በተለያዩ ምክንያቶች በሕዝብ ዘንድ ያለው አመኔታ ደብዛው ጠፍቷል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሕጉ መሠረትና በህሊናቸው እየተመሩ የሚወስኑ ዳኞች ነፃነትና ገለልተኝነት መዳፈን ነው፡፡ ብዙዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ሳቢያ ፍትሕ ማጣታቸውን በምሬት ሲገልጹ፣ የግድ ሆኖባቸው እንጂ ፍርድ ቤት ደጃፍ ባይደርሱ ይመርጣሉ፡፡ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ እየተቸበቸበ ንፁኃን ለእስር ሲዳረጉ፣ ለፍተው ያፈሩትን ሀብት በጠራራ ፀሐይ ሲቀሙ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ሕይወታቸውን ሲያጡ የታደጋቸው የለም፡፡ በሐሰተኛ ክስ ለእስር ተዳርገው ቁም ስቅላቸውን ያዩ ብዙ ናቸው፡፡ በፖለቲካ ምክንያት በተጭበረበረ ክስ አሳራቸውን ያዩትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን እንደ ግል ንብረታቸው የተቆጣጠሩት ኃይሎች አገሪቱን ወህኒ አድርገዋታል፡፡ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ምክንያት በርካታ በደሎች ደርሰዋል፡፡ ይህንን የተበለሻሸ የፍትሕ ሥርዓት ለማፅዳት ፈተናው ከባድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ፍትሕ ፍትሕ የሚሸት ተቋም ለመፍጠር፣ ለዘመናት ያልተጠረገ በረት የሚመስለውን ተቋም ማፅዳት ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከላይ እስከ ታች ያሉትን መዋቅሮች ፈትሾ ለፍትሕና ለርትዕ የሚቆሙ ባለሙያዎችን ማፈላለግ ይኖርበታል፡፡ በትምህርት ዝግጅት፣ በብቃትና በልምድ ከፍተኛ ተሞክሮ ያላቸውን የመስኩ ባለሙያዎችን ከአገር ውስጥም ከውጭም ከያሉበት አፈላልጎ የፅዳቱን ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ አገራቸውን በነፃ ጭምር ለማገልገል ዝግጁ የሆኑ በርካታ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ በስፋት የሚታዩት አስተዳደራዊና የፍትሕ ችግሮች ተቋሙን አሽመድምደውታል፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79 በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤት ብቻ መሆኑን፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካልና ከማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ሌላ ተፅዕኖ ነፃ እንደሆነ፣ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት እንደሚያከናውኑ፣ ከሕግ በስተቀር በሌላ እንደማይመሩ፣ ወዘተ. ደንግጓል፡፡ ይህ ከወረቀት ጌጥነት ያላለፈ ድንጋጌ ለኢትዮጵያውያን ፍትሕ ፈላጊዎች ሰቆቃ ነበር፣ አሁንም ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የጉልበተኞችና የሕገወጦች መጫወቻ በመደረጋቸው ፍትሕ ሸቀጥ ሆኗል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሥርዓት ለመለወጥ ከባድ ትግል ያስፈልጋል፡፡ በዘመናችን ለአንድ አገር ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነዳጅ፣ ወርቅ ወይም አልማዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም መተማመን እንጂ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ተገርስሶ ፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት ካጡ የአገር ውድቀት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአግባቡ ሥራውን ካልሠራ፣ ፖሊስ የሚፈለግበትን ኃላፊነት ካልተወጣ፣ ማረሚያ ቤቶች በሕጉ መሠረት ታራሚዎችን ካላስተናገዱና ፍርድ ቤቶች የጉልበተኞች መፈንጫ ከሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱ ጤንነት ይቃወሳል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን ይጠፋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከሚተችባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግን የልብ ትርታ እያዳመጠ መንቀሳቀሱ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሥራቸውን በነፃነት ማከናወን ሲገባቸው፣ አላስፈላጊ ሥምሪት ውስጥ ገብተው ፍትሕ እንዲደረመስ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጉቦና ምልጃ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከመጀመርያው ምርመራ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ድረስ ሕዝብን የሚያማርሩ አስከፊ ድርጊቶች ይፈጽማሉ፡፡ በተበላሸው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ መከሰስ ያለባቸው ተጠርጣሪዎች ማንም ዝንባቸውን እሽ ለማለት አይፈቅድለትም፡፡ መከሰስ የማይገባቸው ንፁኃን ደግሞ ያለ ኃጢያታቸው ፍዳቸውን ያያሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነቱን ተነጥቆ ራቁቱን የቆመ ስለሆነ፣ ሕዝብ ፍትሕ የት ነው እያለ ቢፈልግ ማግኘት አይቻለውም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ላሽቋል፡፡ ይህንን የላሸቀ ሥርዓት ከመሠረቱ መለወጥ ይገባል፡፡ ሕዝብ የሚያምንበት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በአገልጋይነት መንፈስ የተጣለባቸውን አደራ የሚወጡ በርካቶች ቢኖሩም፣ የእነዚህን ሀቀኞች ልፋትና ጥረት በዜሮ የሚያባዙ የዚያኑ ያህል አሉ፡፡ በፍትሕ ዕጦት የሚማረረው ሕዝብ የሕግ የበላይነት የለም ብሎ ደምድሟል፡፡ ሕግ እየተጣመመ የሚፈረድበት ምስኪን ለምን ንፁህ ሆንኩ ብሎ እየተንገበገበ ራሱን ለወንጀል እንዲያዘጋጅ የሚገደደው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ሥራውን በሕጉ መሠረት ማከወናወን ሲሳነው ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳይሰፍን በማድረግና ፍትሕ በማዛባት አገርን የሰቆቃ ምድር ማድረግ፣ ታይቶ የማይታወቅ ሕዝባዊ ነውጥ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ የተጠራቀመ ብሶት የወለደው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ፍትሕ ፍትሕ በሚሸት ተቋማዊ ግንባታ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ ሕግን ለሕገወጥ ተግባር በሚጠቀሙ ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ተቋማዊ ግንባታ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ተግባር ሊሳካ የሚችለው ደግሞ ብቃት ያላቸው፣ ደፋሮችና ለፍትሕ የቆሙ ባለሙያዎች ሲሰባሰቡ ነው፡፡ በፍትሕ ቀልድ የለም መባል አለበት፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል ሲባል ለሕግ የበላይነት መከበር ከሕግ አውጪው፣ ከሕግ ተርጓሚውና ከአስፈጻሚው መንግሥታዊ አካል ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቃል፡፡ በሕግ የበላይነት አገር ማስተዳደርና በሕግ መግዛት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ተቋማዊ ጥንካሬ ሲረጋገጥ ሕጎች ጥራታቸውንና ደረጃቸውን ጠብቀው ይወጣሉ፡፡ በሕግ ክፍተቶች የሚጠቀሙ ቀበኞች አደብ ይገዛሉ፡፡ በተለይ ሦስቱ የመንግሥት አካላት በአግባቡ እየተናበቡና አንዱ በሌላው ላይ ቁጥጥር እያደረገ ሥራቸውን ሲያከናወኑ፣ ፍትሕ የተጠማው ሕዝብ መልስ ያገኛል፡፡ ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› ዓይነት አሠራር በተንሰራፋበት የፍትሕ ሥርዓት ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸው ግፍና በደል በዚህ ጊዜ መደገም የለበትም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የተንሰራፉ ነውረኛ ድርጊቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለባቸው፡፡ በፍትሕ መቀለድ መብቃት አለበት፡፡ ፍትሕ የሕዝብ መተማመኛ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ‹ፖሊስ በምርምራ ወቅት ዜጎችን ያሰቃያል፣ ዓቃቤ ሕግ በሐሰተኛ ክስ ዜጎችን ያንገላታል፣ ዳኛ በጉቦ ወይም በባለሥልጣን ትዕዛዝ ይፈርዳል፣ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል. . .› የሚባሉ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊቶች በፍጥነት መወገድ አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የተበላሸና የዘቀጠ አሠራር በፍጥነት አስወግዶ ፍትሕ ማንገሥ ያዋጣል፡፡ ከዚህ በኋላ ፍትሕ የማንም መጫወቻና መቀለጃ እንዳይሆን፣ ተጠሪነቱ የሕዝብ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ የመንግሥትም ሆነ የጉልበተኞች ጣልቃ ገብነት ማክተም ይኖርበታል፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነትና ገለልተኛነት መፈተን አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...

የአገሪቱን የፖለቲካ ዕብደት ለማርገብ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሚና ምን ይሁን?

በያሲን ባህሩ   የኦሮሚያ ብልፅግና      በአገር ደረጃ የብሔር ፖለቲካ በሥራ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...