በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በሳምንቱ በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደረሰባቸው፡፡
ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የተወሰኑ ወጣቶች በከተማው ቀበሌ 04 በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ በቅርቡ ከተማዋ ላይ ብጥብጥ ለማስነሳት አስባችኋል በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ጓደኞቻቸውን በኃይል ለማስፈታት ሞክረው እንደነበር፣ በዚህም ፖሊስ ስድስት ወጣቶችን በማሰር ችግሩን ለማረጋጋት እንደቻለ የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉሌድ አውሎ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ሌላ ብጥብጥ በማገርሸቱ፣ አቶ ወንድወሰን ደስታና ሼክ አህመድ አብዱል የተባሉ ግለሰቦች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም አንድ የፖሊስ ባልደረባ በደረሰበት ድብደባ ሕክምና ሲደረግለት ቆይቶ፣ ሆስፒታል ውስጥ መሞቱን አቶ ጉሌድ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ አራት ግለሰቦች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. የተወሰኑ የከተማው ነዋሪዎች መጠነኛ ሠልፍ አድርገው እንደነበር፣ በአካባቢው ከነበሩ ነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ በግጭቱ ምክንያት ሱቆች፣ ባንኮችና የመንግሥት ተቋማት ተዘግተው ነበር፡፡
አሁንም በጅግጅጋ ያለው ውጥረት እንዳልረገበ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከሪፖርተር ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ዑመር፣ በክልሉ መጠነኛ የሆነ ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ነገር ግን በተለይ በጅግጅጋ ባለፈው ሳምንት አለመረጋጋት ማገርሸቱንና ውጥረትም አለመርገቡን ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማው ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች እየተደረጉ ነው ሲሉ አቶ ጉሌድ ገልጸዋል፡፡
በጅግጅጋ ከተማ ከወራት በፊት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች መሞታቸውና ንብረታቸው ከመውደሙ በተጨማሪ፣ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው ይታወሳል፡፡
የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድና ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት በዚህ ምክንያት በሕግ ጥላ ሥር መዋላቸው አይዘነጋም፡፡