ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው የፀደቀላቸው አዲሷ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ አዲሱ ቢሮአቸውን በመጎብኘት ሥራ ጀምረዋል፡፡ የሕዝብ አመኔታን ለመፍጠር ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ ፍርድ ቤቶችንና ቢሮአቸውን ለሕዝብ ምቹ ማድረግ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕዝብን የምናገለግልበት ተቋም የግድ ምቹ መሆን አለበት፤›› ብለው፣ ‹‹የምንፈልገውን የፍትሕ ሥርዓት ለማምጣት አይቸግረንም ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉም ተስፋቸውን አክለዋል፡፡
‹‹ከሁሉም በላይ ግን የሕግ የበላይነትን ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ እንደ ቀድሞው ጊዜ ፍትሕ የምናገኝበት ተቋም አለ ብሎ የሚያምንበት ደረጃ ለመድረስ የምንሠራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹የፍትሕ ተቋማትን ወደምንፈልገው ደረጃ ለማድረስና መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስተካከል በመንግሥት በኩል ያለው ቁርጠኝነት ሥራችንን በነፃነት ለመሥራት የሚያስችለን መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ስለዚህ ከፍትሕ አካላት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን በሙሉ ደረጃ በደረጃ እያስተካከልን እንሠራለን፡፡ በቅድሚያ መሠራት የሚገባቸውን ለይተን እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡
የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ስለሚኖር በዚህ መሠረት ሕዝብ አመኔታ የሚጥልበት ተቋም ለመፍጠር አይቸግርም ብለው፣ ‹‹ከሹመታችን በኋላ ከሕዝብ ያገኘነው ድጋፍ ደግሞ የምንፈልገውን ለማሳካት ትልቅ አቅም ይሆነናል፤› ብለዋል፡፡
‹‹ነፃ የፍትሕ ተቋም እንዲኖረን የሁሉም ፍላጎት ነው፡፡ ለውጥ ፈላጊው ሕዝብ በሙሉ ይህንን ይሻል፡፡ ነፃ የሆነ ፍርድ ቤት እንዳይኖር የሚፈልግ የለም፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነትን ማስፈን አልተቻለም የሚለውን አመለካከት ሊቀይር የሚችል አሠራር ይኖረናል፡፡ በጥቅሉ ግን የምንፈልገውን የፍትሕ ሥርዓት ለማምጣት አይቸግረንም ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
‹‹የሕግ የበላይነት ብዙ ጽንሰ ሐሳብ ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ሕግን በጠበቀ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ዳኞችን ብቻ ሳይሆን ጠበቆችንም ሕጉን ጠብቀው በአግባቡ መሥራትን የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ሁሉም የበኩሉን በሕግ አግባብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያሉትን ሥራዎች በማከናወን ጭምር ነው አመኔታ ሊፈጠር የሚችለው፤›› ብለዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ ሹመታቸው የፀደቀላቸው አዲሶቹ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ፣ ተቋሙን የሚጠበቅበት ኃላፊነት እንዲወጣ ከፍተኛ አደራና እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ተቋሙን ፍትሕ ፍትሕ የሚሸት ለማድረግ በተሿሚዎቹ እተማመናለሁ፤›› ማለታቸው በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ ተችሮታል፡፡
ሁለቱም ተሿሚዎች የሕግ ባለሙያነታቸው በከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና በዳበረ ልምድ የተመሠከረለት በመሆኑም፣ የዳኝነት አካሉ በሕዝብ የተነፈገውን አመኔታ ለማስመለስ ይጠቅማል እየተባለ ነው፡፡ የዳኝነት አካሉን ነፃነትና ገለልተኝነት በተግባር በማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ተሿሚዎቹ፣ ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት ከመመደባቸው በፊት ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመሠረተው 13 አካላት ያሉት የሕግና የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት አባላት ሆነው መመደባቸው አይዘነጋም፡፡ አማካሪ ምክር ቤቱ የሚዲያ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራትና የፀረ ሽብርተኝነት ሕጎችን ለማሻሻል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማገዝ ነው የተመሠረተው፡፡
ወ/ሮ መዓዛ ከተሾሙ በኋላ በሰጡት አጭር መግለጫ፣ ‹‹ሕግ በተገቢው ሁኔታ በፍርድ ቤቶች ካልተተረጎመና ተገቢው ውሳኔ ካልተሰጠ ወረቀት ላይ ነው የሚቀረው፤›› ብለው፣ ‹‹የሕግ አምላክ ስንል የሕግ አምላክ ፍርድ ቤት ነው ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በማከልም በእርግጠኝነት መናገር የሚፈልጉት ሕዝብ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው አመኔታ መመለስ እንዳለበት ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያ ሥራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቡም ሕግ ለማስከበር ኃላፊነት አለበት ብለው፣ ‹‹መብታችንን የሚያስከብርልን ፍርድ ቤት ነው ብለን መጠበቅ የለብንም፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ መብቱ እንዲከበርና ሕግ እንዲከበር የራሱንም የሌሎችንም መብት ማክበር ግዴታው እንደሆነ ማወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡