ተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል አሉ
ከመስከረም 2 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማና አካባቢው፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በበርካታ ሰዎች ሞት፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ የተጠረጠሩ 89 ግለሰቦች ምርመራ ወደ ፌዴራል የሕግ ተቋማት ተዛወረ፡፡
የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች እየቀረቡና ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው ከአንድ ወር በላይ በእስር የቆዩት ተጠርጣሪዎች የምርመራ መዝገብ፣ ወደ ፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮና ፍርድ ቤቶች የተቀየረው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝ መሆኑ ታውቋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት እየቀረበ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በተያዙባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ቀርበው በተጠረጠሩበት ‹‹ሁከት፣ ረብሻና ግድያ›› ወንጀሎች ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅባቸው ቆይተዋል፡፡ የምርመራ ሒደቱም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የምርመራው አካል የሆነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የምርመራ ሒደቱና እየተገኙ ያሉ ማስረጃዎች በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (3) ሥር የሚሸኑ በመሆናቸው፣ የምርመራ ሒደቱ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተዛውሮ መቀጠል እንዳለበት ውሳኔ መስጠቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የምርመራ ቡድኑን ሐሳብና የዓቃቤ ሕግ ውሳኔ ሰነድን ተቀብሎ፣ የምርመራ ሒደቱን አስቀጥሏል፡፡ በመሆኑም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሶቄ ማርያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ መስከረም 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አቶ ዳኜ ፈዬራና አቶ አዱፋ ደሜ የተባሉ ግለሰቦችን 13 ተጠርጣሪዎች በመኖሪያ ሥፍራቸው ‹‹ማን ተገድሎ ማን ይቀራል?›› በማለት በገጀራ፣ በዱላ፣ በድንጋይና በአካፋ ቀጥቅጠው መግደላቸውን አስረድቷል፡፡ በስድስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን፣ ግምታቸው ከ300 ሺሕ ብር በላይ የሆነ ንብረትና ሁለት ተሽከርካሪዎችን ማውደማቸውንም አክሏል፡፡
ሌሎች አሥር ተጠርጣሪዎች ደግሞ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው አስኮ ጨረታ፣ ቃሌ ሠፈርና ፖሊስ ጣቢያ፣ ካኦጄጄ ዱቄት ፋብሪካ፣ ብርጭቆ አካባቢና በሌሎች ቦታዎች የኦነግ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ምክንያት በማድረግ፣ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን መፈጸማቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እስካሁን በውል ካልታወቁ አካላት ትዕዛዝ በመቀበል በሕዝቡ ዘንድ ‹‹መንግሥት የለም›› የሚል ግንዛቤ እንዲኖር፣ የሕዝብ መጠቀሚያ ቦታዎችን የተለያዩ ቀለማት ከመቀባትና ሁከት ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ አቶ አዲሱ ደጀኔ፣ አቶ ባህረዲን ሐሰን፣ አቶ ቦንቃ ቦንቼ፣ አቶ መሐመድ አክመል፣ አቶ ሰለሞን ካሳሁንና አንድ ስሙ ያልታወቀ ግለሰብ በድምሩ ስድስት ግለሰቦች በገጀራ፣ በዱላ፣ በድንጋይና በተለያዩ መሣሪያዎች ጨፍጭፈው መግደላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ተሽከርካሪዎችን ማቃጠላቸውን፣ አስኮ አዲስ ሠፈር የሚገኙትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥበቃ ሠራተኞችን ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ በመንጠቅና በማስፈራራት ለሁከቱ መጠቀሚያ ማድረጋቸውን፣ ከአቢሲኒያ ባንክ ጥበቃዎችም መሣሪያ በመንጠቅና የባንኩን መስታወቶች በመሰባበር ከ900 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ማድረሳቸውን፣ በዳሸን ባንክ 13 ሺሕ ብር ግምት ያለው ንብረት ማውደማቸውንና በአዋሽ ባንክ 5,000 ብር የሚገመት ንብረት ማውደማቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ የብሔር ግጭት እንዲፈጠር የተለያዩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙና ሲቀሰቅሱ እንደነበርም አክሏል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከተው፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ግድያ በተፈጸመባቸው 28 ግለሰቦች የተጠረጠሩ 32 ግለሰቦችንም አቅርቧል፡፡ በአጠቃላይ ምርመራቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ ተይዞ የነበሩ 89 ተጠርጣሪዎች የምርመራ ሒደትና የወንጀሉ አፈጻጸም በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሥር የሚወድቅ በመሆኑ፣ ለተጨማሪ ምርመራ በአዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (20) መሠረት 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸውና በራሳቸው ባቀረቡት አቤቱታ የተጠየቀባቸውን ተጨማሪ ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች ከታሰሩ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው፣ ከስድስት ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ መክረማቸውንና ምርመራው ተጣርቶ ያለቀ በመሆኑ ሊለቀቁ እንጂ ወደ ሌላ የምርመራ አካል ተሸጋግረው ተጨማሪ ጊዜ ሊጠየቅባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶቸ እየቀረቡና ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው ሲመረመሩ በመክረማቸው፣ ተጨማሪ ጊዜ ለምን እንዳስፈለገ እንዳልገባቸውም አክለዋል፡፡
በሕጉ መሠረት የተገኘባቸው የወንጀል ድርጊት ካለ ክስ ሊቀርብባቸው እንደሚገባ ወይም በነፃ መሰናበት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ ያመለከቱት ተጠርጣሪዎቹ ከታሰሩ ጊዜ ጀምሮ በጨለማ ቤት ውስጥ መታሰራቸውን፣ ለፍርድ ቤቱ ክብር ሲሉ ባይገልጹትም በመርማሪዎች የሚሰደቡት አፀያፊ ስድብ እንዳለ፣ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም. የሰጡትን ቃል ጥቅምት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሰጡ ተደርገው በግዳጅ እንዲፈርሙ መደረጋቸውን፣ ከቤተሰቦቻቸው ተገናኝተው እንደማያውቁ፣ ሌሊት እየተወሰዱ እንደሚደበደቡ፣ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መባላቸው ሳይረጋገጥ መርማሪ ‹‹ወንጀለኞች›› በማለት እንደሚፈርድባቸው ገልጸዋል፡፡ መቀጣት ካለባቸው በሕግ እንጂ በጉልበት መሆን እንደሌለበትም አክለዋል፡፡ በተለይ ድብደባ የሚፈጸምባቸው ሌሊት ሌሊት መሆኑንና ጠጥተው በሚመጡ መርማሪዎች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሕክምና እንደማይፈቀድላቸው፣ ከታሰሩ ጀምሮ ልብስ መቀየርና ሰውነታቸውን መታጠብ እንዳልቻሉም ተናግረዋል፡፡ ከስድስት ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደገና በፌዴራል ፖሊስ አንድ ተብሎ መጀመሩ አግባብ አለመሆኑን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አንድ ተጠርጣሪ ማስረጃ ሳይገኝበት ወይም ሳይሰበሰብ እንደማይታሰር የተናገሩት ቃል ዓመት ሳይሆነው እየተጣሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቢያንስ ቢያንስ እሳቸው ከተናገሩት ጋር የሚናበብ ሥራ ሊያከናውን እንደሚገባም አክለዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ ተጠርጣሪዎቹ ያሉበት እስር ቤት ዘመናዊና ማንኛውም ተጠርጣሪ የሚታሰርበት መሆኑን አስረድቷል፡፡ በሲሲቲቪ የሚጠበቅ በመሆኑ ማንም ማየት እንደሚችልና ጨለማ የሚባል ነገር እንደሌለም ገልጿል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ቤተሰብም ሆነ የሕግ ባለሙያ እየጠየቃቸው መሆኑንም አክሏል፡፡ የፖሊስን ስም ለማጥፋት ካልሆነ በስተቀር፣ ሌሊት የሚደረግ ምርመራ እንደሌለና መጠጥ በጠጣ መርማሪ እንደሚመረመሩ መናገራቸው የተቋሙንም ስም ማጥፋት መሆኑን አስረድቷል፡፡ በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ወደ ሽብርተኝነት የሚያመራ በመሆኑ ገና በርካታ ምርመራዎች የሚቀሩት መሆኑን ጠቁሞ፣ የጠየቀው 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ፣ የተወሰኑ የምርመራ መዝገቦች ላይ የ28 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ‹‹ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?›› በሚለው ላይ ተወያይቶ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 26 እና 27 ቀን ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፣ በሦስት የምርመራ መዝገቦች ላይ ግን የተጠርጣሪዎችን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ 28 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡