Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርያልተገባ ነቀፌታ ይታሰብበት

ያልተገባ ነቀፌታ ይታሰብበት

ቀን:

በአገራችን እንደሚተረተው ‹‹ስም አይቀበርም፣ የወለደ አይረሳም፤›› ሲባል እንደቀልድ ቢታይም፣ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ያለወትሮዬ በቴሌቪዥን መስኮት ፊትለፊት ተቀምጬ በኢቢኤስ ጣቢያ አንድ ታላቅ ሰው መጠይቅ ሲደረግላቸው ተመለከትኩ፡፡ ሰውየውን ስለማውቃቸው ፕሮግራሙን በአንክሮ ተከታተልኩ፡፡  

የቃለ ምልልሱ ሒደት በአመዛኙ በንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ታሪክ ላይ ያተኮረ ነበር በጥሞና ስከታተል ቆየሁ፡፡ በመሐሉ ግን የአፄ ምኒሊክ ታሪክ መጣ። አፄ ምኒሊክ አገሪቱን ለጣልያን እንደሸጡ ዓይነት የሚጠቅስ ነገር ተነሳ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ቀርቶ በዓለም ታሪክ የተደነቁና ያስደነቁት ንጉሥ፣ ፈረንጆቹ ከቶማስ ጄፈርሰንና ከፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ጋር በማነጻጸር በዕውቀታቸው፣ በአመራራቸው፣ በመግባባት ዘይቤያቸው፣ ለሥልጣኔ ቅድሚያ በመስጠታቸውና በራዕያቸው የተደነቁባቸው ታላቅ መሪ ሆነው ሳለ የሚከራከርላቸው በሌለበት ስማቸው በክፉ ሲነሳ በመስማቴ የማውቀውን ያህል፣ የተባለውን ለማስተባበልና የእነ አፄ ቴዎድሮስን የመጨረሻ ሁኔታዎችን በማስገንዘብ ትውልዱ ታሪኩን እንዲመረምር ለመጠቆም ተገደድኩ።

ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ እንዴት ልትደፈር ቻለች? ማንስ አስደፈራት? አፄ ቴዎድሮስ እንዴት ሞቱ? የሚለውን ለመመለስና በዝብዝ ካሳ በኋላ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ወደ ሥልጣን እንዴት መጡ? የእንግሊዙ የጦር አለቃ ናፒዬር የመራው የጦር ስብስብ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ገባ? ማነው መርቶ ያስገባው? የሚለውን ሳያዳሉ ለኢትዮጵያዊያን ፍርድ እንዲሰጡበት፣ ወጣቱም ባልሆነ መንገድ እንዳይነዳ ማድረግና ታሪክን መመርመርም ተገቢ ሲሆን፣ ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች ባለሙያዎች በወገንተኝነት ሳይሆን፣ ሁሉን ባካተተና በኢትዮጵያዊነት መነሻነት ታሪክን እንዲያስጨብጡ ኃላፊነት እንዳለባቸው ለማስገንዘብ እወዳለሁ።

‹‹በዝብዝ ካሳ›› ማናቸው? የዋግ ሹም ጎበዜ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው ሦስት ዓመታት ከነገሡ በኋላ እንዴት ወረዱ? የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ ሁሉም እንዲተችበት እጋብዛለሁ። በዝብዝ ካሳ ከዝነኛው ሚካኤል ሱሁል የዘውድ ሐረግ የሚሳቡ ናቸው፡፡ ባደረጉት ትግል ለዘውድ ከመብቃታቸውም በላይ ለኢትዮጵያ ታሪክ ሠርተው ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ግን እንዴት ሊነግሡ ቻሉ? በወቅቱ የነበረውን የመሳፍንት አገዛዝ በነበራቸው ጀግንነትና ቆራጥነት አፄ ቴዎድሮስ አንኮታኩተው ከጣሉ በኋላ የዘውድ ዝሪያ ባይኖራቸውም በነበራቸው ኃይልና ተሰጥዖ ነግሠው፣ ከሚደነቁበት ዋናው ነገር አንዱ ኢትዮጵያን ወደነበረችበት አንድነት ለማምጣት መሞከራቸው የጎላው ነው፡፡ በዓለም ሰፍኖ የነበረውን የባሪያ ንግድ ለማጥፋት መሞከራቸውና የተጎዱ የእሥራኤላዊያንን ነፃ ማውጣት የሚል እጅግ በጣም የተራማጅነት አካሄዳቸው በዓለም ቀደምት አድርጓቸዋል፡፡ ምኞታቸው ተፈጽሟል ወይስ በምኞት ብቻ ቀርቷል? የሚለውን ለመመለስ ታሪክን ማገላበጥ ጥሩ መልስ ሊያስገኝ ይችላል። ይኼንን ካልኩ ዘንዳ፣ ሕይወታቸው እንዴት አለፈች? ለሚለው ጥያቄ ምላሹን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢያቀውም እንዲያው ለማስታወስ ያህል መንደርደሪያ ሰጥቼ ማለፍን መረጥኩ።                                                                      

ኢትዮጵያ 3,000 ዘመናት በምታስቆጥርበት ጊዜ በራሷ ልጅ መሪነት የውጭ ኃይል ሊመራትና መሪዋ እጄን ሰጥቼ ኢትዮጵያን አላዋርድም በማለት ሕይወቱን ከመሰዋቱም በላይ ለአእላፍ ዘመናት የነበረና የቆየን ከወርቅ፣ ከከበሩ ማዕድናት የተሠሩትን የክብር ዕቃዎች፣ በሺሕ ዓመታት የሚቆጠሩትን የክብረ ንጉሥ ዓርማዎችና የአፄ ቴዎድሮስን የወርቅ ዘውድ እንዲሁም ሌሎች ውድ ንብረቶች የናፒዬር ጦር አግበስብሶ ዘርፎ ሲሄድ መርተው ያመጡት ማን ናቸው? በዝብዝ ካሳ እንዲህ ያለውን ዝርፊያ ማስቀረት ሲችሉ አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል።                                       

በአገር ልጅ ተመርቶ የመጣው ጠላት የማያልፍ ታሪክ አበላሽቶ ሄዷል። በዝብዝ ካሳ ከተክለ ጊዮርጊስ ሥልጣን እንዲነጥቁና ለንጉሠ ነገሥትነት እንዲበቁም አግዟቸዋል። የተነሳሁት አንዱን ንጉሥ ለማመሥገን ሌላውን ለማጣጣል ሳይሆን፣ የአፄ ምኒልክ ስም በሆነ ባልሆነው ሲነሳና ኢትዮጵያን ለጣሊያን አሳልፈው እንደሰጡ በተደረገው ቃለ ምልልስ ወቅት ሲነገር ስለሰማሁ፣ አፄ ዮሐንስ ቆሞ የሚከራከርላቸው ዘር ጥለው ስለሄዱ የአፄ ዮሐንስ ስም በመልካም እየተነሳ የአፄ ምኒሊክ ስም ግን አገር እንደሸጡ ተደርጎ በመነሳቱ የተሳተውን ፈር ለማስያዝ በማሰብ ነው።

አፄ ምኒልክ ከጣሊያን ጋር በዘዴ ቢስማሙም ለጣሊያን የፈለገውን ሰጥተው ሳይሆን፣ የፈለጉትን ለአገራቸው ክብርና ሞገስን አጎናፅፈው ነው ያለፉት። ምናልባትም ይኼንን የማይገነዘብ ይኖራል ተብሎም እንደሆነ የሚሰጠው የአሉባልታ ገለጻ መስመር እንዲይዝ መደረግ አለበት። ንጉሥ ወይም ገዥ የልጆቹና የቤተሰቡ ብቻ አይደለም፡፡ በጠቅላላው የኅብረተሰቡና የሕዝቡ እንጂ፡፡ አፄ ዮሐንስም ሆኑ ሌሎች ያላግባብ ስማቸው ሲነሳ የሁላችንም የኢትዮጵያዊያን ዘሮች ናቸውና ዝም ብለን አንመለከትም።

አፄ ዮሐንስ በእርግጥ ማንኛውም መሪ እንደሚያደርገው ሁሉ ለአገራቸው፣ ለሃይማኖታቸው ተከራካሪና አማኝ እንደነበሩ የታወቀ ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ወደሠለጠነው ዓለም መንገዱን የቀየሩ፣ እንደ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው ባይ ነበሩ። ይህ አቋማቸው እንደየአመለካከታቸው የሚወሰን እንጂ ጥሩም መጥፎም ብለን ነው የምንፈርጀው ጉዳይ አይደለምና አስተያየታችንን ብናስተካክለው መልካም ይመስለኛል።

 ምኒልክን አላግባብ እየወቀሱ አንዱን ለማወደስ፣ ሌላውን መንቀፍ ትዝብት ላይ እንዳይጥለን እንጠንቀቅ። ጥያቄ ያላችሁ ጠይቁኝ፤ እንነጋግገር፡፡ በዚህ አድራሻዬ  [email protected] ጻፉልኝ፡፡

(አሰፋ አደፍርስ፣ በኢሜል የላኩት)                

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...