Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክስለሕፃናቱ ፍትሕ “አንድ መዝገብ” እንደ ማሳያ

ስለሕፃናቱ ፍትሕ “አንድ መዝገብ” እንደ ማሳያ

ቀን:

በሪያድ አብዱል ወኪል

ለነው “ሦስተኛው ዓለም” እየተባለ በሚጠራውና ይልቁንም ምዕራባውያኑ በጨለማ አኅጉርነት በሚመስሉት የዓለም ከባቢ ውስጥ ቢሆንም፣ ከዓለም ተነጥለን ልንኖር የምንችልበት አጋጣሚ የለም፡፡ የሰሜን ኮሪያ ሪፐብሊክ መሥራችና “ዘለዓለማዊው መሪ!” በሚል ቅጽላቸው የሚታወቁት ኪም ኢል ሱንግ “በዚች ሰፊ ዓለም ውስጥ አንድ ቤተሰብ ከአንዲት ትንሽ የውኃ ጠብታ የበለጠ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዲት ጠብታ ውኃም የዓለም አንደኛዋ ክፍል ስለሆነች ከዓለም ተነጥላ ልትኖር አትችልም፤” ስለማለታቸው የሕይወት ታሪካቸውን ከሚተርከው መጽሐፍ አንብቤያለሁ፡፡

ዓለማችን በየጊዜውና በየዘርፉ ለውጦችን እያስተናገደች ሲሆን፣ ከለውጦቹ ጋር ደግሞ የአኅጉርና የአገራችን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችም አብረው መለወጣቸው አይቀርም፡፡ እነሆ ኢትዮጵያችን ውስጥም መሠረታዊ የሚባል ፖለቲካዊ ለውጥ መጥቷል፡፡ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃቱም አለ፡፡ ይህ ጽሑፍ ትኩረቱን በሕፃናት የፍትሕ አስተዳደር እንዲሁም ሕፃናቱን ከአዋቂ ተጠርጣሪና ፍርደኞች ጋር ቀላቅሎ በማሰር ላይ ያደረገ ነው፡፡

በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩትና በየመገናኛ ብዙኃኑ ይፋ የወጡት የማሰቃየት መረጃዎች፣ እኔም በሥራ አጋጣሚ በማረፊያና በማረሚያ ቤቶች ጉብኝቴ ወቅት ያስተዋልኳቸው ጉዳዮች ለነገሩ ትኩረት ሰጥቼ እንድጽፍበት ምክንያት ሆነውኛል፡፡ የሚዲያው ትኩረት የተነፈገው ቢሆንና ምን ያህሎቻችንም ጉዳዩን እንዳስተዋልነው ባላውቅም፣ ሰቀቀኖቹ የተሰሙት ከአዋቂዎቹ ታራሚዎች ብቻ አልነበረም፡፡

በደቡቧ ማዕከል ሐዋሳ የማዕከሉ ግንባታ ቢጀመርም፣ አንድ ለአገሪቱ በሆነውና በመዲናችን ከሚገኘው ተቋምም ይህ ድምፅ ተሰምቶ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም “የጠባይ ማረሚያ” ተብሎ ይታወቅ የነበረውና በአሁን አጠራሩ “በወንጀል ነገር ውስጥ የገቡ ሕፃናት ፀባይ ማረሚያና የተሃድሶ ማዕከል” በሚባለው ተቋምም በሕፃናቱ ላይ የተለያዩ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች ሲደርሱባቸው ማንም ሊከላከልላቸው እንዳልቻለ የሚገልጽ መረጃ ከዚያን ሰሞን የሰቆቃ ዜናዎች ጋር አብሮ ተዘግቧል፡፡

ችግሩ የተቋሙ መኮንኖች ብቻ አልነበረም፡፡ ሕፃናቱ እነዚህን ሰቆቃዎች በተለያዩ ወቅቶች የሕፃናቱን ጉዳይ ከምርመራ እስከ ክስ ሒደት ድረስ ያለውን ሥነ ሥርዓት በበላይ ተቆጣጣሪነት ለሚመራው ፍርድ ቤት በችሎት ቢያሰሙም፣ ዳኞች ምንም የፈየዱላቸው ነገር እንደሌለና ሲታመሙ እንኳን በቂ ሕክምና እንደማያገኙ በሕፃናቱ አንደበት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ባልደረቦች የተናገሩትን በሐዘን ውስጥ ሆኜ አዳምጫለሁ፡፡

የወንጀል ሕጋችን ዓላማና ግብ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግን ገልጠን ማንበብ ስንጀምር የመጀመሪያው አንቀጽ ድንጋጌ፣ “የወንጀል ሕግ ዓላማ፣ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦቹን ሰላም፣ ደኅንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ግብ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጽሙ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው፤” በማለት የወንጀል ሕጉ ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ ተተልሞ እናገኛለን፡፡

የግማሽ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው የወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን በ1996 ዓ.ም. እንዲሻሻል ምክንያት የሆነውና በተሻሻለው ሕግ ውስጥም ከተካተቱ አበይት ጉዳዮች ቀዳሚው ነገር የቅጣት ዓላማና ግብን የሚመለከተው ክፍል ነው፡፡ በለውጡም ቅጣት እንደ አንድ ራሱን እንደቻለ ግብ ሆኖ አልተወሰደም ይልቁንም ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ እንደ አንድ የማረሚያ መንገድ ሆኖ እንጂ፡፡ ስለዚህም ከሰብዓዊ መብቶችና ከዓለም ዓቀፍ ሕግጋት አንፃር አገናዝቦ የቅጣት ዓላማው ምን መሆን እንዳለበት መግለጹ አስፈላጊ ነበር፡፡

በወንጀል ሕጋችን ሦስት ዋነኛ የቅጣት ዓይነቶች ሲኖሩ፣ ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በተቀመጡት ሥነ ሥርዓቶች ውስጥ አልፎ ጥፋተኛ ስለመሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከእነዚሁ የቅጣት ዓይነቶች አንዱ፣ ሁለቱ አልያም እንደ ነገሩ ሁኔታ ሦስቱንም ሊቀጣባቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህ ዋነኛ ቅጣቶች ቀዳሚው ነፃነትን የሚያሳጣው የእስራት ቅጣት ሲሆን፣ በዚሁ ምድብ ውስጥም የማረፊያ ቤት እስራት ይካተታል፡፡

ሕፃናቱና “የማረፊያ ቤት” እስራት

የወንጀል ሕጋችን ልዩ ክፍል አካል ሆኖ የደንብ መተላለፍ ሕጎችን ባካተተበት የመጽሐፉ ሦስተኛ ክፍል ውስጥ (ከአንቀጽ 734 እስከ 865) የደንብ መተላለፍን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ስለቅጣት ሲያትቱ “. . . በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል፤” በሚል አገላለጽ ነው የሚጨርሱት፡፡ ይህም ሆኖ ማረፊያ ቤቶቹ ውስጥ ከቀላሎቹ የደንብ መተላለፍ ድርጊቶች ባሻገር ከስርቆት እስከ ግድያ ድረስ በወንጀል የተጠረጠሩትንም ሆነ በጊዜ ቀጠሮ የሚቆዩትን እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ወደ ማረሚያ ቤት ያልተላኩ ፍርደኞችን ላልተወሰነ የእስራት ጊዜ በውስጣቸው ያቆያሉ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ የማረፊያ ቤት እስራት ከመዲናችን በመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት እንኳ ሕፃናቱን ከግድያ ፍርደኛ ጋር በአንድ ጣራ ሥር ያኖራል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሕፃናትንና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወጣት ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ ሦስት ደረጃዎችን አውጥቷል፡፡ ይኸውም ዕድሜያቸው ዘጠኝ ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት የወንጀል ተጠያቂነት የሌለባቸው ፍጹም ኢኃላፊ ናቸውና በእነዚህ ሕፃናት ላይ የወንጀል ሕጉ ተፈጻሚነት አይኖረውም በማለት ይልቁንም የቅርብ ሰዎቻቸው ተገቢ የሆኑትን ጥንቃቄዎች እንዲያደርጉላቸው ይመከራል ይላል፡፡

ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት ያሉ ወጣት ታዳጊዎችን በተመለከተ ደግሞ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 53 ታዳጊዎቹ ወንጀል ፈጽመውና ጥፋተኛ ሆነውም በተገኙ ጊዜ የሚወሰኑባቸው ቅጣቶችና የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 157 እስከ 168 በተደነገገው መሠረት ሲሆን፣ እነዚህ ሕፃናት ያሉበት የዕድሜ ክልል የአንዲት አገር የተስፋ መስኮቶች (Windows of Hope) ያሰኛቸዋልና ብርቱ ጥንቃቄ እንደሚያሻ በመጠቆም “ለአዋቂ ጥፋተኞች የተደነገጉት መደበኛ ቅጣቶች ለወጣት ወንጀል አድራጊዎች ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፤ ከአዋቂዎችም ጋር አይታሰሩም፤” በማለት ያስጠነቅቃል፡፡

የወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 110 (1) “እስረኞችን መለያየት” በሚል ርዕስ ሥር ጾታቸው የተለያዩ እስረኞች በተለያዩ እስር ቤቶች ቅጣታቸውን እንደሚፈጽሙ በመግለጽ በአቅም ምክንያት ይህ መሆን ባይችል እንኳን ባለው ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የተለያዩ ክፍሎች ሊዘጋጁ እንደሚገባ ተገልጾ እናነባለን፡፡ ተዘዋውሬ ካየሁት፣ ካነበብኩትና ከሰማሁት አንፃር በመላው ኢትዮጵያ ይህ መርህ እየተተገበረ ስለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡

ግን ደግሞ በዚያው ድንጋጌ ንዑስ ሁለትና ሦስት ሥር ተከታዩ መርህ በማያሻማ ቃል ሰፍሮ እናነባለን፡፡ “በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወይም በልዩ ክፍል ተለይተው እንዲታሰሩ የተፈረደባቸው ጥፋተኞች በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ለአካለ መጠን ካልደረሱ እስረኞች ጋር በፍጹም እንዳይገናኙ ይደረጋል፡፡” እስረኞች በዕድሜና ሁኔታ ማለትም በዕዳ ምክንያት የሚታሰሩትም ሆኑ የቀላልና የጽኑ እስራት ፍርደኞች ተለያይተው መያዝ እንዳለባቸው በጥብቅ ተደንግጓል፡፡ የቅጣቶቹ አፈጻጸምም ሆነ የቅጣቶቹ ዓላማ የተለያዩ ናቸውና፡፡

በገጠር የወረዳ “ማረፊያ ቤቶች” በማዳበሪያ ዕዳ ምክንያት ያለሕግ አግባብ በፍትሐ ብሔር የሚታሰሩ ገበሬዎችን ካነሳሁ አይቀር አንድ መፈታት ያለበትን ችግር ጠቁሜ ማለፉን እመርጣለሁ፡፡ በሕግ ዕይታ መንግሥት ራሱን የቻለ አንድ ተከራካሪ ተቋም (Entity) ነው፡፡ የመንግሥትን ብድር ያልከፈሉ ወይም የማይከፍሉ ሰዎች በፍትሐ ብሔር ሊከሰሱ ካልሆነ በቀር በፖሊስ የሚደበደቡበት፣ ከዓቃቤ ሕግና ከፀጥታው አካልም “የተለየ ውግንና” እየተጠየቀ ጉዳዩ ላይ የሚመቻቹበት ብሎም ሰዎቹ የሚታሰሩበት ምክንያት መቀጠል አይኖርበትም፡፡ የየወረዳው የፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች የሕግ ባለሙያ ባልሆኑበት የሹመት ሒደት ውስጥ ደግሞ ይህ ችግር ሊፈታ አይችልምና ሊስተካከል ይገባል፡፡

ምንም እንኳን መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ በቂ ሀብት ባይኖረንም በሰብዓዊ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዙሪያ አስገዳጅ ነገር ሊኖረንና “በጀት የለንም” በሚል ምክንያት መንግሥት የቆዩትን ያህል ቢቆዩም፣ በማረፊያ ቤት ለሚያስራቸው ሰዎች ሕፃናቱን ጨምሮ የሚቀርበው ምግብ የተቆላ ወይም የተቀቀለ አተር ብቻና ብቻ መሆኑ አስሮ የማስራብ ሰቆቃ አንድ ገጽታ ነውና ይህም ሊታሰብበት የግድ ይሆናል፡፡ በማረሚያ ቤቶች የምግብ በጀት ላይ እንኳን ስሞታ በሚቀርብበት ሁኔታ የማረፊያ ቤቶቹን ማሰብ ከባድ አይሆንም፡፡

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በማረፊያ ቤቶች ብቻ አይደለም ይህ ድብልቅልቁ የወጣ አያያዝ የሚታየው፡፡ ከአዲስ አበባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ብቻ ተጉዛችሁ የአንዱን ክልል ወይም የዞን አስተዳደር ማረሚያ ቤቶችን ብትጎበኙ በምታዩት የዕድሜም ሆነ የሁኔታ እስረኞች መቀላቀል ደንግጣችሁ መመለሳችሁና በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለመታረም ሳይሆን ለአዲስ ወንጀል ድፍረት መቅሰምን ታዝባችሁ መመለሳችሁ አይቀርም፡፡

በሦስተኝነት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 18 ወይም ከ15 በላይና ከ18 በታች ያሉ ወጣት ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ ጉዳያቸው የሚታየው በወንጀል ሕጉ መደበኛ ድንጋጌዎች መሠረት እንደሆነና ፍርድ ቤቱ ግን ቅጣቱን የሚወስነው የነገሩን ሁኔታ በማመዛዘን እንደሆነ ቢገልጽም፣ ፍርድ ቤቱ ካመነበት ለአካለ መጠን ላልደረሱት ወንጀል አድራጊዎች የተመደበውን የልዩ ቅጣት አወሳሰን ደንብ በመከተል ቅጣቱን ሊወስን እንደሚችልም አስፍሯል፡፡

ስለዚህም በአንቀጽ 176 መሠረት ሕፃኑ ከሞት ቅጣት በመለስ ያሉ ቅጣቶችም ሊጣሉበት ይችላሉና የእስራት ቅጣት በሚፈጸምበት ጊዜ “ለአካለ መጠን ከደረሱ ወንጀለኞች ተለይቶ የመታሰር ደንብ ለአካለ መጠን እስከሚደርስ ድረስ በጥብቅ መፈጸም አለበት፤” የሚለውን መርህ አትኩሮት ይሰጥበታል፡፡

መሠረታዊው “የሕግ” ስህተት

ዕድሜው 11 ዓመት የሆነው ሕፃን ዕድሜዋ አራት ዓመት በሆናት ሕፃን ላይ የግበረ ሥጋ ድፍረት በደል ፈጽሟል፣ ድንግልናዋንም ገርስሷል በማለት ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 627 (1) ሥር ከሰሰውና በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ ፍርድ ቤት መዝገቡን ለሕፃናቱ በተቀመጠው ሥነ ሥርዓት ሳይሆን በመደበኛው የወንጀል አሰማም ሥነ ሥርዓት ሲያስኬድና ሲመረምር ቆይቶ ሕፃኑን በተከሰሰበት የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ሥር ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት የአሥር ዓመት ጽኑ እስራት ይፈርድበታል፡፡

ጉዳዩ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢባልበትም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ይጸናል፡፡ በሰበር ይግባኝ ሲኬድም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጥፋተኝነቱን በተመለከተ የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አፅድቆ ቅጣቱን ግን ወደ አምስት ዓመት ዝቅ ያደርግለትና በድምፅ ብልጫ የወልዲያ ማረሚያ ቤት የእስራት ቅጣቱን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ለዚህም ምክንያቴ ያለው በክልሉ የሕፃናት ፀባይ ማረሚያና የተሃድሶ ማዕከል አለመኖሩን ነበር፡፡

መዝገቡ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተብሎበትና ይግባኝ ባይ አመልካችም “ጥፋተኛ ብባል እንኳን ከአዋቂዎች ጋር መታሰር የለብኝም፤” በማለቱ መዝገቡ “ያስቀርባል!” ተብሎና በሰበር ችሎቱ ታይቶ ተከሳሽ ዕድሜው 11 ዓመት ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጦ ሳለ፣ የሥር ፍርድ ቤትም ጉዳዩ ለሕፃናቱ በተቀመጠው የወንጀል ሕግ አንቀጽ ከ157 እስከ 168 ለምን መታየት እንደማይኖርበት ሳይገልጹ በመደበኛው ማየታቸው አግባብ ስላይደለ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት አዝዟል፡፡ በተጠሪነት የቀረበው የክልሉ ዓቃቤ ሕግም ስህተቱን አውቋልና ተቃውሞ እንደማይኖረው ለችሎቱ አሳውቋል፡፡

የወረዳው ፍርድ ቤት የፍርድ ሒደት ሥነ ሥርዓት ዓለም አቀፎቹን ሕግጋትና የታወቁ መርሆዎች እንዲሁም አገራዊዎቹን ከመጣሱ ባሻገርም ቅጣቱን ከአዋቂ ታራሚዎች ጋር እንዲፈጽም “የወልዲያ ማረሚያ ቤት ፍርዱን ያስፈጽም” ማለታቸው መሠረታዊ የመብትና የሥነ ሥርዓት የሕግ ጥሰት ስለመኖሩ በቂ ማሳያ ነው በማለት በመዝገብ ቁጥር 118130 የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አግዶ በማቆየት ለወልድያ ማረሚያ ቤት የመፍቻ ዋራንት እንዲጻፍ የፌዴራሉ ሰበር አዟል፡፡

ስህተቱ ለምን ተፈጠረ መፍትሔውስ ምንድን ነው?

ለጥቃት የቅርብ ተጋላጭ በመሆናቸው ሳቢያ የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸውና ጥበቃም እንዲደረግላቸው ከሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ሕፃናት በሁሉም መስፈርት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አገራችን የሕፃናትን ጉዳይ የሚመለከት መርሆም አላት፡፡ የሕፃናት መብት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ በርካታ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችን በፊርማቸው ይሁነኝ ካሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥም ቀዳሚዋ ነች፡፡ ሕገ መንግሥቷም በድንጋጌዎቹ የሚታማ አይደለም፡፡ ሆኖም በፍትሕ አካሉ ላይ እንደሚሰማሩ የሚጠበቁት የሕግ ተማሪዎች ስለሰብዓዊ መብቶች፣ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የህዳጣን መብት ትምህርቶች በዩኒቨርሲቲ መምህራኑ በይድረስ ይድረስ እንጂ እንደሌሎች የሕግ ትምህርቶች በቁምነገር አይሰጧቸውም፡፡

ይህንን በየዘርፉ የሚስተዋለውን የሥርዓተ ትምህርቱን ችግር ይፈታሉ፣ ለፍትሕ አካላቱም የተሻለ ግንዛቤ ይፈጥራሉ ተብለው በተቋቋሙት የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከላትም አንደኛ ነገር ሠልጣኞቹ አብጠርጥረው ሊያውቋቸው የሚገቧቸውን ፖሊሲዎች ያለማሳወቅ ሰፍኖባቸዋል፡፡ እኔ በራሴ ባጋጠመኝም ሆነ በየክልሎቹ የማሠልጠኛ ማዕከላት ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ያጣራሁት መረጃም ያረጋገጠልኝ ይህንኑ እውነታ ነው፡፡

በመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዙሪያ የተለያዩ ሥልጠናዎች ላይ የመሳተፉን ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ቦታዎች ጥያቄዬን የማቀርበው የፍትሕ አካላቱን በቀዳሚነትና በቀጥታ የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ላይ ሥልጠናውን ስጡን እያልኩ ነበር፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምጽፍላችሁ ጎብዘው ለማንበብ ከበረቱት ባለሙያዎች በስተቀር በርካታ ዳኞችና ዓቃብያነ ሕግ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲያችንን አብጠርጥረው አያውቁትም፡፡ በሁለት ቅጽ የተጠቃለለውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብርንም እንዲሁ አናውቀውም፡፡ ይህ መራር እውነት ደግሞ ወደ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ባለሙያዎች ሲወረድ አስደንጋጭ መልክ ይይዛል፡፡

ሁለተኛው ነገር በመንግሥትና መንግሥትን በሚመራው ኢሕአዴግ በኩል የሚታየው ችግር የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ሲሆን፣ ይኸውም ሥልጠና ሲባል ባለሙያውን እንደየሙያው በቀጥታ በሚመለከተው፣ ክፍተትም አለበት ተብሎ በሚታመነው ጉዳይ ላይ ከማብቃት ይልቅ የፖለቲካዊ የጠመቃ ሥልጠናዎች መብዛት ለችግሩ የራሱን አበርክቷል፡፡ ይህ ችግር ባለሙያዎችን ሁሉ በየስምሪታቸው ዘርፍ የሚመለከታቸውን ፖሊሲ በማሳወቅ መፍታት የሚቻል ሲሆን፣ በተለይ የፍትሕ አካላቱ ደግሞ አብዛኞቹን የአገሪቱን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የመንግሥት ዕቅዶችን አብላልተው እንዲያውቁ ይጠበቃል፡፡

በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር የተቋቋመውና “The African Child Policy Forum” በተባለው አኅጉራዊ ተቋም የሚደገፈው የሕፃናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕፃናት የሕግ ከለላ ማዕከልን በማቋቋም ባለፉት ዓመታት በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን የሕፃናት ፍትሕ አስተዳደር ለማሻሻል የሚገባውን ያህል ባይሆንም የሚችለውንና የአቅሙን ያህል ተግቷል፡፡ እንደማሳያ ያነሳሁትን የፌዴራሉ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔም የሕግና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በመመደብ ከእልባት ያደረሰው ይኸው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ነው፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ለሚያልፉ ሕፃናት የሕግ ከለላ፣ የሥነ ልቦናና የሕግ ምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችንም ያሰናዳል፡፡ ከሚስተዋሉት ችግሮች ስፋት አንፃር ግን የጽሕፈት ቤቱ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ የተገደበና እጀ ሰባራ ያደረገውም ይመስላልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቢያንስ በክልል ደረጃ ለሕፃናቱ የሚሆን የተሃድሶ ተቋምን ዕውን ለማድረግ መጣር ይኖርበታል እላለሁ፡፡

ሌላው እንደ ችግር መነሳትና በቶሎ መታረምም የሚኖርበት ጉዳይ ፍርድ ቤቶቻችን በተለይም ከክልል በመለስ ያሉቱ ፍርድ ቤቶች የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች የሏቸውም፡፡ የሕፃናት ችሎቶች ዛሬም እንደ መሠረታዊ ነገር ሳይሆን እንደ ቅንጦት ይቆጠራሉ፡፡ የሕፃናት መብቶችን ከሚመለከቱ ዓለም አቀፍ መርሆችና ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ውስጥ ለሕፃናቱ ደኅንነትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠት አንዱና ቀዳሚው ቢሆንም፣ የእነዚህ ሁለት ነገሮች አለመሟላት እጅግ በጣም ችግር እያስከተለ ያለ ነገር ነው፡፡

የማኅበራዊ ጉዳይ ባለሙያዎች በፍርድ ቤት ችሎቶች ውስጥ በሕፃናቱና በዳኞች መካከል በመሆን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ሲሆን በወንጀል ተጠቂነት፣ በምስክርነት እንዲሁም በፈጻሚነት ተጠርጥረውም ሆነ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ሕፃናትን በተመለከተ በሚያቀርቡት ጥናትና ባህሪ ላይ የተመሠረተ መረጃ መሠረት ፍርድ ቤቶች የሕፃናቱን ደኅንነት ያስቀደመ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ሙያዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ከሕፃናቱ ጋር የተናበቡ ችሎቶችን የማደራጀቱ ሥራም ለነገ የምናሳድረው መሆን ስለማይኖርበትም የፍርድ ቤቶቻችን ከሪፎርማቸው ጋር ሊያስኬዱት ተገቢ ይሆናል፡፡

ምንም እንኳን አመልካቹ ከእርሱ ዕድሜ በታች ያለች ሕፃን ላይ የግብረ ሥጋ ድፍረት ወንጀልን የፈጸመና ይህም ከከባድ ወንጀሎች ውስጥ የሚካተት ቢሆንም፣ የመብትና የሥነ ሥርዓታዊ ስህተቱ እንዲታረም ሆኗል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ስለት በአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ወገን ነውና የተበዳይዋን ሕፃን ጉዳይም ጽሕፈት ቤቱና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ችላ እንዳላሉት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አገራችን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በተለይም የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረሙና ለተፈጻሚነታቸው ቃል በመግባቱ በኩል የምታሳየውን ግንባር ቀደምነት እነዚህኑ ስምምነቶች በቆራጥነት በማሳወቁና በመተግበሩ በኩልም ብትበረታበት መልካም ይሆናል፡፡ በግዞት እስር ሳቢያ ሕይወቱ በብዙ የተቀየረችው ዕውቁ ደራሲ ፊዩዶር ሚካሎቪች ዶስቶቭስኪ “በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን የሥልጣኔ ደረጃ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ ገብቶ ማወቅ ይቻላል፤” ይለናል፡፡ ለሕፃናቱ ደኅንነት በምንሰጠው ትኩረት በሰሞንኛው የዓለም የሕፃናት ቀንና በዓለም መለኪያ ብንመዘን ደረጃችን ስንተኛ ላይ ያርፍ ይሆን?

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጉራጌ ዞን የወለኔ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...