Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየመንጋ ፍርድ በመንጋ ህሊና

የመንጋ ፍርድ በመንጋ ህሊና

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም

ኢሕአዴግ ቤተ መንግሥት ሲገባ ሚዛን ተፈሪ ነበርኩ፡፡ በሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. በሚዛን ንግድ ባንክ ፊት ለፊት ባለው ቦታ አንድ ታጋይ አንድ ሕፃን ልጅ የያዘች ነፍሰ ጡር እናትን፣ ቤቷ በረንዳ ላይ አንድ ሰው ሞቶ በመገኘቱ ለመንጋ ፍርድ (Mob Justice) ያቀርባል፡፡ ዙሪያውን የከበቡት ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፡፡

ታጋዩ ‹‹ሴትዮዋ በረንዳ ላይ ሰው ሞቶ መገኘቱን›› ገልጾ ለመንጋ ፍርድ የተሰበሰቡትን ዳኝነት እንዲሰጡ ይጠይቃል፡፡ በታዳጊ ወጣቶቹ መሀል ጥቂት ትልልቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ የተሰበሰቡትም ‹‹ሟቹ ቤቷ በረንዳ ላይ ሞቶ ከተገኘ፣ የገደለችው እሷ ነችና ትገደል!›› ብለው ይጮሃሉ፡፡ ‹‹ነፍሰ ጡር ነኝ! የልጅ እናት ነኝ!›› ብላ ብትጮህ ሰሚ አላገኘችም፡፡ ታጋዩ ለደቂቃ እንኳ ማሰብ አልፈቀደም፡፡ ወዲያው ሕፃን ልጇን ከእጇ መንጭቆ ያላቅቅና እዚያው በጥይት ተደብድባ ትገደላለች፡፡

ኢሕአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ ከመንግሥትነት ባህሪ ወርዶ በመንጋ ፍርድ የሚመራ የሠፈር ጎበዝ አለቃ እስከ መሆን ደርሶ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ተወው እንጂ አገር ለማረጋጋት በሚል ሰበብ ቦርሳ መንጭቆ የሚሮጠውን ጭምር ገድሏል፡፡ የሚዛን ተፈሪው አሰቃቂ ድርጊት ከሌሎች መንጋ ፍርዶች የሚለየው በመንግሥት መፈጸሙ ነበር፡፡ ከ27 ዓመታት በኋላም ትናንት የተፈጸመ ያህል በህሊናዬ ግዘፍ ነስቶ ይታየኛል፡፡

‹‹ታሪክ ራሱን ይድግማል›› እንዲሉ፣ ይህ አሰቃቂ ድርጊት አሁን በአገራችን የሚታየውን የመንጋ ፍርድ ያስታውሰኛል፡፡ ‹‹አንድ ወሬኛ አገር ይፈታል፣ አንድ ቅማል ሱሪ ያስፈታል›› እንዲሉ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2011 .ም. በምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ለምርምር የሄዱ ተመራማሪዎች በተፈጸመባቸው መንጋ ፍርድ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ቢቢሲ የአማርኛው ድረ ገጽ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪን ጠቅሶ እንዳቀረበው ግለሰቦቹ ጥቃቱ ተፈጸመባቸው ገበያ ቀን ሲሆን፣ በአዲስ ዓለም የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተማሪዎች መረጃ ሰጥተው፣ ከተመረጡ ልጆች ለጥናት የሚያስፈልግ የሽንትና የዓይነ ምድር ናሙና በመውሰድ ላይ ነበሩ።

እንደ ቋያ እሳት በቅጽበት የተዛመተው የተሳሳተ መረጃ በርካታ ሰዎች እንዲሰባሰቡ አደረገ፡፡ ‹‹ልጆቻችን የጤና ክትባት እየተሰጣቸው ነው፣ እየተመረዙብን ነው፣ ሊገደሉብን ነው፤›› በማለት ወደ ትምህርት ቤት አቀኑ፡፡ የትምህርት ቤቱ ጥበቃዎችም በአካባቢው በነበሩ ጥቂት ፖሊሶች ታግዘው ተመራማሪዎቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመወሰድ ላይ ሳሉ፣ ተመራማሪዎቹ በድንጋይና በዱላ አሰቃቂ ጥቃት ደርሶባቸው ሕይወታቸው አልፏል። አንዱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ጥናት ወደ ቦታው ያመራ ሲሆን፣ ሌላው በሜጫ ወረዳ በሚገኝ ጤና ጣቢያ የሚሠራ የጤና መኮንን ነው፡፡ ሌላ የጤና ባለሙያም ጉዳት ደርሶበት በሕክምና ላይ ይገኛል

ህሊና ማድረግ ያለብንና የሌለብንን እንድንገነዘብና እንድናመዛዝን የሚረዳን የውስጥ ዳኛ ነው፡፡ ማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት ለህሊና (Conscience) የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ህሊና የሰው ልጅ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሲኖር ስለአካባቢው የሚኖረው ግንዛቤና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ኃላፊነት የሚያውቅበት፣ ግለሰቡም ስለራሱ ድርጊትና ፀባይ የሚያጤንበት ልዩ ልዩ መልክ ያለው ስሜታዊ ክስተት ነው፡፡ ህሊና በተፈጥሮ የሚገኝ ሳይሆን የሰው ልጅ በኅብረተሰቡ ውስጥ ባለው ሥፍራ ሊጫወተው ከሚገባው ሚና ጋር አብሮ የሚፈጠርና የሚያድግ ነው. . .፡፡ ግለሰቡ በኅብረተሰቡ የሚፈለግበትን ግዴታ እንዲያሟላ ህሊና የግፊት ኃይል ሆኖ ይሠራል፡፡

‹‹Urban Dictionary›› ለ‹‹መንጋ ፍርድ›› (Mob Justice) የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ‹‹When a large angry mob takes justice into their own hands. Usually ends with somebody getting hanged, torched or pitchfork’d. A common method of dispensing justice in the more rural areas of a country.›› በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንጋ ፍርድ ተበራክቷል፡፡ በየቦታው የምንሰማው በመንጋ ህሊና የሚሰጠውን የመንጋ ፍርድ ነው፡፡ ሰው በመንጋ ህሊና መመራት ሲጀምር የራሱን ህሊና አውጥቶ ይጥላል፡፡ ቢቢሲ ድረ ገጽ ሶሲዮሎጂ ምሁሩን የራስ ወርቅ አድማሴን (ዶ/ር) ጠቅሶ እንዳቀረበው፣ የመንጋ ፍርድ (Mob Justice) ታፍኖ የነበረ ወይም ታፍኜ ነበር ብሎ የሚያስብ ማኅበረሰብ፣ አሁን ነፃ ነኝ ምንም የምሠራው ነገር አያስጠይቀኝም ብሎ ሲያስብ የሚገባበት ሁኔታ ነው

እንደ የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶ/ር) ‹‹አንድ ሰውሞብሲሳፈር የሚመራው በራሱ ህሊና ሳይሆን በመንጋ ነው። መንጋው የራሱን ህሊና ይፈጥራል›› የሚሉት የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ በመንጋ ህሊና ከፍተኛ ጥፋት ካደረሱ በኋላ ከመንጋው ተነጥለው ወደ ህሊናቸው ሲመለሱ ያደረጉትን ማመን እንደሚከብዳቸውና እንደሚፀፀቱ በጥናት መመልከቱን ተናግረዋልመንጋ ህሊና በባህሪው ስክነት ስለሌለው ነገሮችን ለማስተዋልና ለመመርመር ዳተኛ ነው፡፡

በሻሸመኔ ከተማ ጃዋርን ለመቀበል ስታዲየም በወጣው ሕዝብ መሀል ‹‹ቦምብ ይዟል›› ተብሎ በተነዛ ውዥንብር አንድ ወጣት ወጣቶች ተደብዶቦ ይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ ልብሱ ተገፎና ተዘቅዝቆ ተገድሏል፡፡ ይህን አሰቃቂ ድርጊት ከንፈር ከመምጠጥ ውጪ ወደ ፊት እንዳይደገም (ለመማርያ) አልተጠቀምንበትም፡፡ አንድን ሰው በአንድ ወንጀል ከሶ፣ ራስ ምስክር፣ ራስ ፈራጅ፣ ቀጪም ራስ የሆነበት የመንጋ ፍርድ በየአካባቢው እየተፈጸመ ነው፡፡ የአንዱን ጉድ ሰምተን ሳንጨርስ ሌሎች ንፁኃን ሰዎች በመንጋ ፍርድ በድንጋይ ተወግረው፣ በዱላና በብረት ተቀጥቅጠው በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና መፈናቀሎችን እንሰማለን፡፡

ለመንጋ ህሊናና መንጋ ፍርድ መበራከት በርካታ መንስዔዎች ይኖራሉ፡፡ የመንግሥት በተለይም በታችኛው እርከን ያሉ መዋቅሮች መዳከምና ኅብረተሰቡን ለዘመናት አስተሳስረው ያኖሩ ማኅበራዊ ድሮች (Social Fabrics) መበጣጠስ ይጠቀሳሉ፡፡ ለዚህም የእምነት የማኅበረሰብ አቀፍ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣት ዓብይ ምክንያቶች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት ብዙ ዘመን ታውሮ ዓይኑ ድንገት እንደ በራ ሰው ልቡናን የሚያጥበረብር ነው፡፡ እዚህም እዚያም የምንሰማው ወሬ ጆሮን የሚያሳክክና የሰው ልጅን ጭካኔ የሚያመለክት ነው፡፡ በውጭ ሰዎች ሳይቀር የተወደስንበት መልካም እሴቶች በጭካኔና በክፋት እየተለወጡ ነው፡፡ ‹‹ፍቅርና መደመር››ን የመንጋ ፍርድና የመንጋ ህሊና ጥላቸውን እያጠሉባቸውና በላዔሰብ ሊደመስሳቸው ነው፡፡ በላዔሰብ እንዲጠፋ ካልተደረገ በላዔሰቡ ‹‹ፍቅርና መደመር››ን ያጠፋሉ፡፡  

መንግሥት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም መንጋ ፍርድና መንጋ ህሊናን ለማስቆም ትኩረት ሰጥቶ ዘርፈ ብዙ ሥራ መሥራት ይገባዋል፡፡ በታችኛው እርከን የተጀመረው ሥርዓተ አልበኝነት ወደ ማዕከላዊ መንግሥት መምጣቱ አይቀርም፡፡ የእምነትና የማኅበረሰብ አቀፍ ተቋማትም በእግዚአብሔርና በህሊናቸው ፊት መንጋ ህሊና ወደ ግለ ህሊና እንዲቀየር በትጋት ሊሠሩ ይገባል፡፡ እኛም፣ ‹‹አዳኝም የለም፣ ጠመንጃም የለም፤›› ብላ ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ እንደቀበረችው ሰጎን፣ ሁሉንም ለመርሳትና የሆነውን ነገር ሁሉ እንዳልሆነ ለመቁጠር ከኤሊ ቅርፊት የጠጠረ ምሽግ ሠርተን ዝምታን ማብዛት አደጋው ከባድ ነው፡፡ ነገ የእያንዳንዳችንን በር ያንኳኳልና፡፡

በመጨረሻም የንብና የወባ ትንኝን ተቃራኒ ሥራ ላቅርብ፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ነፍሳት አበባን ይቀስማሉ፡፡ ንብ ከአበባ ባገኘችው ንጥር ማር ትሠራለች፡፡ ከራሷ አልፋ ለሰው መድኃኒትን ታመርታለች፡፡ የወባ ትንኝ ደግሞ ከዚያው ከአበባ በተገኘው ንጥር መርዟን ትሠራለች፡፡ በመርዟም የወባ በሽታን ታስተላልፋለች፡፡ እንግዲህ አንደኛው ለመድኃኒት ሌላው ለመርዝ አውለውታል፡፡ ‹‹ፍቅርን፣ ይቅርታንና መደመርን›› የምትቀስመውን በወባ ትንኝ እንዳትጠፋ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ መንጋ ህሊናን ወደ ግለ ህሊና መቀየር ለነገ አይባልምና፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...